Sunday, 12 August 2018 00:00

በእኛ ሐገር ወህኒ የነገስታት ቤተሰቦች ማጎሪያ ነበር

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(2 votes)

 ‹‹አሁን ወደ ስድሳው እየተጠጋሁ ነው›› አሉኝ፤ በአንድ አጋጣሚ ያገኘኋቸው አንድ አዛውንት። ፀጉራቸው ፍፁም ሸበቶ ነው፡፡ ቀይ ፊታቸውን የወረረው ያጨለጨለ ፂም፤ አረጋዊ መሆናቸውን ለመናገር ይሞክራል፡፡ ግን የዓይናቸው ፀዳል፤ ተስፋን እየረጨ ወጣት ያስመስላቸዋል፡፡ ከገፃቸው የሚነበበው ተስፋ፤ ዕድሜአቸውን ያስረሳል። አዛውንቱ ልዩ ቅኔ ሆነዋል፡፡ የዕድሜ ርዝመት ያዛላቸው ቢመስልም፤ ተስፋ ጢም አድርጎ የሞላቸው በመሆኑ የአዛውንት- ወጣት ሆነዋል፡፡ እንባና ሣቅን አንድ ላይ አዝለዋል፡፡
ምዕራባዊው የአመሻሽ ጮራ እየመታቸው ነው። ‹‹ቅጥቅጥ›› ከሚሉት መለስተኛ አውቶብስ ከጋቢና ተቀምጠዋል፡፡ በመስታወቱ ዘልቆ የሚገባው የፀሐይ ብርሐን እያተኮሳቸው፤ የመኪናው  ሞተርና የተፋፈገ ሙቀት እያላባቸው ነው፡፡ ከራሳቸው ላይ እንደ ዘበት ጣል ያደረጉት ባርኔጣ አለ፡፡ ሙቀቱ ሲጠና ባርኔጣቸውን አውልቀው ከጉልበታቸው አደረጉት፡፡ ባርኔጣቸው ሲወልቅ ከአናታቸው መሀል ካለው በራ ችርፍፍ ያለ ላብ ታየ፡፡
እኔ ከአጠገባቸው ሞተሩ ላይ ተቀምጫለሁ። ባርኔጣቸውን ከጉልበታቸው ሲያኖሩ ቀልቤ ተስቦ፤ ከጭናቸው ያደረጉትን ወረቀት ሰረቅ አድርጌ አየሁት። ወሬ ለመጀመር ብዙ አልቆዩም። እንቅስቃሴ ላይ ካለው የተሳፈርንበት መኪና ጋር እየታከኩ የሚያልፉ ሰዎችን ተመልክተው፤ ‹‹ታያለህ መኪናውን እንደ ፍየል እየታከኩ ያልፋሉ፤ ጉድ እኮ ነው፡፡ ከመኪና በግ የሚፈሩ ናቸው›› ብለው ወሬ የጀመሩት ገና ከመነሻችን ነበር፡፡
ድካምና ሙቀቱ ለወሬ የሚያዘጋጅ ባይሆንም በሚያዩት ነገር ሁሉ አስተያየት ይሰጣሉ፡፡ በሐገራችን የሚታየው ለውጥ በወጣቱ ብቻ ሣይሆን በአዛውንቱም ልብ የተስፋ ችቦ እንደ ለኮሰ የሚያስረዳ አስተያየት ያላቸው ሽማግሌ ናቸው፡፡ ጥቂት በዝምታ ቆይተው አንድ ሰሞነኛ ወሬ አነሱ።
‹‹አሁን ከትናንት ወዲያ ሰውየውን ገደሉት። መቼም ግፍ ነው›› አሉ፡፡ ስሜታቸው ክፉኛ ተነክቷል። በምሬት አከሉ፡፡ ‹‹እንደው ምን አደረግናቸው?›› አሉ። ‹‹በወቅቱ ብዙ ወጣቶች አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለም ከዓይናቸው ላይ ተቀብተው ነበር፡፡ ይህን ያዩ አንዳንድ ሰዎች ስቀው ይሆናል፡፡ ይተቹም ይሆናል። እኔ ግን አልሳቅኩም፡፡ አልነቀፍኩም፡፡ እንዲያውም የታየኝ ቅኔ ነው፡፡ ወጣቶቹ ‹ይቺ ባንዲራ የዓይናችን ብሌን ናት› ማለታቸው ነው፡፡ ትርጉሙ ይኸ ነው፤ ሌላ እንዳይመስልህ›› በማለት፤ ለኢትዮጵያውያን ባንዲራ ልዩ ስሜት እንዳለው መግለፅ ጀመሩ፡፡
‹‹የባንዲራችን ቀዩ ቀለም፤ከዚህ ከደማችን ተቀድቶ (የእጃቸውን ቆዳ ቆንጥጠው) የተቀለመ ይመስለኛል›› ካሉ በኋላ፤ አክለው፤‹‹ድሃ ልንሆን እንችላለን፡፡ ግን ኩሩ ህዝብ ነን፡፡ ወትሮም ጅብ ለሆዱ፤ ነብር ለክብሩ ነው፡፡››
‹‹እኔ ወጣቱን ትውልድ አልንቅም፡፡ የማያውቅ እንዳይመስልህ፡፡ አዋቂ ነው፡፡ እኔ በወጣቱ ትውልድ ተስፋ አለኝ፡፡ ልማቱን እያሳየን ነው። አባይን እየገደበ ነው፡፡ እኔ በአባይ ውሃ ጎመን ተክዬ አልበላሁም፡፡ እኛ ድሃ ብንሆንም አባይን እንገድባለን ብሎ ተነሳ፡፡ እኔ ዕድሜዬ አልቋል። ግን የያዝኩት ተስፋ አለኝ፡፡ አንድ ቀን ልጆቼ ከልመና ይወጣሉ የሚል ተስፋ እየታየኝ፤ የሰው ሃገር ከማየትና ከመሰደድ ይድናሉ እያልኩኝ በግድቡ እጅግ ደስ ይለኛል፤ ዘላለም ከሚጸየፉንና በድህነታችን ከሚስቁብን አሁን እየራበን እንገድበዋለን። ክብራችንን ማስጠበቂያ ነው፡፡ ተጀምሯል፡፡ እንጨርሰዋለን፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ እንደዚህ ነው፡፡››
አዛውንቱ ጆሮና ስሜቴን ማርከዋቸዋል፡፡ ወጋቸውን ቀጠሉ፡፡ ስለ ህዝቡ አንድነት አወሩ። የጦርነት ታሪኩን ዘከሩ - የቅርብና የሩቅ ታሪክ እየጠቀሱ፤ ‹‹እኔ ሐገሬን እወዳታለሁ፡፡ እሷ ደባብሳኝ ባታውቅም እኔ እወዳታለሁ፡፡ አሁን ደግሞ እንዲህ ያለ መሪ ሰጠን፡፡ ዶ/ር ዐቢይ የኢትዮጵያ ህዝብ አባት ነው፡፡ ሞት አይቀር ሰው ለምን ይዋሻል …›› አሉ፡፡ አዛውንቱ፤ ስለ ሀገራቸው ፍቅር አውርተው፤ አይናቸው በእንባ ሲረጥብ መሐረም አውጥተው ዓይናቸውን መጠራረግ ያዙ፡፡ አሳዘኑኝ፡፡
ያለፈ ታሪካቸውን ለመገመት ጀመርኩ። ወታደር ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ከእርሳቸው ስለይ ምን ቃል ተናግሬ የአዛውንት ልባቸውን ማፅናት እንደምችል በማሰላሰል ግራ እንደ ተጋባሁ ወረድኩ፡፡ ‹‹አይዞዎት›› ማለቴን ብቻ አስታውሳለሁ፡፡ ተስፋና ሐዘን የተቀላቀለበት የአዛውንቱ ስሜት፤ የሐገራችን ታሪክ ግልባጭ ሆኖ ታሰበኝ፡፡ የአዛውንቱ በዕንባ የታጀበ የሐዘንና የቁጭት ስሜት ተሻግሬ፤ እርሳቸው ያልተናገሩትን የትናንት ታሪክ አስታወስኩ፡፡ በተስፋቸው ደግሞ የዛሬንና የነገን ብሩህ ዘመን አጉልቼ ተመለከትኩ፡፡ ተስፋ ማጣት በተስፋ ተተክቶ፤ ጨለማ በብርሐን ተለውጦ፤ መሸማቀቅ በዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ተሸንፎ፤ ጦርነት ለሰላም ቦታ ለቅቆ ታየኝ፡፡
የአዛውንቱ ጨዋታ፤ ሐገር እንደ ሰንሰለት የተያያዙ ተከታታይ ትውልዶች ህይወት መሆኑን አመለከተኝ፡፡ ታሪክ፤ እያንዳንዱ ትውልድ ከኋላውና ከፊቱ፤ ከሌላ ትውልድ ሕይወት ጋር የሚቆራኝበት የማይበጠስ ሰንሰለት መሆኑን አስገነዘበኝ፡፡ በታሪክ ፉርጎ የተያያዙ የተረካቢና የአስረካቢ ትውልዶች ባቡር ሽው - እልም ሲል ታየኝ፡፡
አዛውንቱ፤ ስለ ኢትዮጵያ ህዝብ ህግ አዋቂነት ተረኩ፡፡ ስለ ነገስታቱ ፈሪሃ እግዚአብሔር አተቱ። ‹‹ይህን የፍትሕ ምድር ያረከሰው ደርግ ነው›› አሉ። ግን የደርግን የሽብር ዓመታት በዝርዝር ለመናገር አልፈለጉም፡፡ ምክንያቱም የምህረትና የይቅርታ ዘመን ነው፡፡
የዳኝነት ተግባር በኢትዮጵያ ረጅም ታሪክ እንዳለው ምሁራን ይናገራሉ፡፡ ቻርልስ ሻፈር የተባለ፤ በቀይ ሽብር የፍርድ ሂደት ዙሪያ ጥናት ያደረገ አንድ ምሁር፤ ‹‹በዓለም ላይ ከኢትዮጵያ የሚበልጥ ረጅም ዘመን ያስቆጠረ ብቸኛ ችሎት ቢኖር ሰማያዊው ችሎት ነው›› ሲሉ ጠ/ሚ መለስ መናገራቸውን ጠቅሷል፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ ብዙ ሺህ ዓመታትን ያስቆጠረ ችሎት ወይም የዳኝነት ታሪክ ያለው ቢሆንም፤ በሀገራችን ሁሉን የሚገዛና ከአፅናፍ እስከ አፅናፍ የሚተገበር የተፃፈ ህግ መኖሩ የሚያከራክር ቢሆንም፤ ከጥንት ጀምሮ የነበሩና ሥር የሰደደ የህግ ፅንሰ ሐሳቦች መኖራቸው የሚካድ አይደለም፡፡ ነገሥታቱ ‹‹እግዚአብሔር ያሳይዎ፤ መልዓክ ያመልክትዎ›› እየተባሉ፤ ሙግት እየተቀበሉ፤ ዳኝነት የሚሰጡበት ጥንታዊ ስርዓት ነበረ፡፡
ነገስታቱ የህግ አውጭ፣ የህግ ተርጓሚና የህግ አስፈፃሚ ሚና ሲጫወቱ የሚታዩበት ስርዓት ነው። ነገስታቱ የቀረበላቸውን ነገር ሁሉ ከማየት የሚያግዳቸው ነገር አልነበረም። ነገስታቱ የህግ ገደብ የለባቸውም፡፡ ሆኖም፤ ከ15ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ሥራ ላይ እንደዋለ የሚነገርለት ፍትሐ ነገስት ተፈጻሚነቱ እምብዛም ነበር። ስለዚህ በአብዛኛው ተፈፃሚነት የነበራቸው በብቀላ ላይ የሚያተኩሩ የየብሔረሰቡ ልማዳዊ ህጎች ነበሩ። በአንዳንድ ብሄረሰቦች፤ ሰው የገደለ እንኳን የደም ካሣ (ጉማ) ከፍሎ ከኃላፊነት ነፃ መሆን የሚችልበት ዕድል ነበር፡፡ በሌሎች ደግሞ የደም ካሳ መቀበል የሚወገዝ ነውር ስለ ነበር፤ የግል ተበዳዩም ሆነ ዘመዶቹ በወንጀለኛውና በቤተሰቡ ላይ የበቀል እርምጃ የመውሰድ ባህላዊ ግዴታ ነበረባቸው። ሁለቱን በአማራጭነት የሚጠቀሙ ብሔረሰቦችም ነበሩ፡፡
የእነዚህን የተለያዩ ልማዳዊ ህጎች ተፈጸሚነት ከሞላ ጎደል ያስቀረውና በልማዳዊ ህጎቻችን መለያየት የተነሳ ሊከሰት የሚችለውን የተዘበራረቀ የፍትሕ አስተዳደር አንድ ወጥ ለማድረግ የተቻለው፤ ወይም ከዘመናዊ የፍትሕ አስተዳደር ስርዓትጋር የተቀራረበ ስርዓት መፍጠር የተቻለው በ1923 ዓ.ም በታወጁት ህጎች ነው፡፡
ታሪክ እንደሚያስረዳን፤ የዐቃቤ ህግ መስሪያ ቤት የተቋቋመው በ1934 ዓ.ም ነበር፡፡ የዐቃቤ ህግ መስሪያ ቤት እስከ ተቋቋመበት እስከ 1934 ዓ.ም ድረስ፤ የወንጀል ጉዳት የደረሰበት ሰው ወይም ዘመዱ በደሉን ማመልከት ብቻ ሳይሆን ተከራክሮ መርታትና በወንጀለኛው ላይ የሚበየነውን ቅጣት ተግባራዊ የማድረግ ኃላፊነት ጭምር ይሸከም ነበር፡፡ በወቅቱ፤ የመንግስት ጥቅምን ይቃረናሉ ተብለው ይወሰዱ የነበሩት ድርጊቶችም፤ በአብዛኛው በቤተ ክርስቲያንና በንጉሣዊያን ቤተሰቦች ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ ጉዳዮች ብቻ ነበሩ፡፡
ይህ ሁኔታ ተቀይሮ የፍትህ አስተዳደሩን ራሱን አስችሎ ለማደራጀት ጥረት የተጀመረው፤ የመጀመሪያው ካቢኔ በተቋቋመበት በ1900 ዓ.ም ነበር፡፡ ሆኖም፤ ፍርድ ቤቶችን በተዋረድ የማዋቀሩ፤ መሠረታዊ የስነስርአት ሕጎችን የመደንገጉ፤ እንዲሁም የአቃቤ ሕግ መስሪያ ቤቶችን የማቋቋም ተግባር የተከናወነው ከ1934 እስከ 1952 ዓ.ም ባሉት ዓመታት ነው።
በሐገሪቱ ታሪክ ቋሚ መዲና አለመኖሩ፤ እስር ቤት የማቋቋምን ዕድል እንዳልፈጠረ የሚገልፁ ምሁራን አሉ፡፡ ‹‹አለመግባባትና ግጭት በካሳ፣ በምህረትና በዕርቅ እንዲፈቱ መደረጉ፤ እንደ ማረሚያ ቤት ያለ ተቋም እንዳይፈጠር አድርጓል›› የሚሉት ምሁራን፤ ‹‹ወህኒ አምባ›› በመባል የሚታወቁት እስር ቤቶች የስልጣን ተቀናቃኞች ብቻ የሚታሰሩባቸው ቦታዎች እንደ ነበሩ ያስረዳሉ። ሆኖም ቀደም ባለው ዘመን የነበረው የዳኝነት ስርዓት፤ በጣም ጠቃሚ የህግ ፅንሰ ሐሳቦች እንዲዳብሩ ያደረገ መሆኑ አይካድም፡፡ ህዝቡም ለህግ አክብሮት እንዲኖረው አድርጓል፡፡
ጥፋት የሰራ ሰው ቤተ ክርስቲያን በመግባት ተማጽኖ ሲያቀርብ፤ በህግ  ካልሆነ በቀር አልነካም ብሎ የማመን ዝንባሌ ይዞ እንደሆነ፤ ነገስታትም በራሳቸው እርምጃ ከመውሰድ ተቆጥበው የህግ ሊቃውንትን ጉባዔ ጠርቶ ምክር በመጠየቅ ውሳኔ የሚያሳልፉበት አጋጣሚዎች የተለመደ አሰራር እንደነበረ ምሁራን ያትታሉ፡፡ ‹‹እንኳን ሰው ዛፍ ያስጥላል›› የሚል ብሂል የሚገዛው የፍትሕ ስሜት እንደ ነበር ግልጽ ነው። እንዲህ ያሉ ጠቃሚ የፍትሕ -ርትዕ የአስተሳሰብ ዝንባሌዎችን በማጥፋት ከነባር ወግና ልማድ የራቀ ውሳኔ ሲደረግ የታየው በደርግ ዘመነ መንግስት ነው፡፡
እርግጥ ነው፤ በአፄ ቴዎድሮስ ዘመን ከነባሩ ወግ ያፈነገጠ ነገር መታየቱን የሚጠቅሱ ቢኖሩም እንደ ደርግ ዘመን ጨርሶ አውሬነት የነገሰበት ሁኔታ እንዳልነበረ ምሁራን ይገልፃሉ።  በነገስታቱ ይታይ የነበረውን የህግ ክቡርነትንና በሐይማኖታዊ ምግባሮች የመገራት ዝንባሌን፣ እንዲሁም ለተሸነፈ ሰው ርህራሄ የማሳየት ዝንባሌን፣ ምህረትንና እርቅን የመፈለግ ቀና መንፈስንና ባህልን በማጥፋት አረመኔአዊ ጭካኔ ያነገሰው የደርግ ወታደራዊ አገዛዝ መሆኑን ቻርልስ ሻፈርም ይገልጣል፡፡
አሁን እንደሚታየው፤ በኢትዮጵያ ታሪክ በርካታ የእርቅና የርህራሄ ምሣሌዎች አሉ። በኢትዮጵያ ታሪክ እርቅ የጦርነትን ያህል አንድ የችግር መፍቻ ተደርጎ ሲሰራበት የቆየ መሆኑን የነገስታቱ የዜና መዋዕል ምስክር ነው። ለተሸናፊ ኃይል ደግነት በማሳየት ግጭቶች የሚደመደሙበትን አጋጣሚም እናያለን፡፡
ቻርልስ ሻፈር፤ ስለ ቀይ ሽብር የፍርድ ሂደት ሲያትት፤ ‹‹ከእስረኞች አያያዝ ጋር በተገናኘ መታየት ያለበት የኢትዮጵያውያን ባህል ነው›› ይላል፡፡ ታዲያ ከእዚህ ጋር አያይዞ የሚጠቅሰው፤ የአድዋን ጦርነት ክስተት ነው፡፡ የአድዋው ጦርነት፤ 4ሺህ የጣሊያን 2ሺህ አስካሪሶች ያለቁበትና 2ሺህ የተማረኩበት ነበር፡፡ የጥቁር ህዝቦች ድል ተደርጎ የሚጠቀሰው አድዋ የአድናቆት ስሜት የመፍጠሩን ያህል፤ አፄ ምኒልክ ለጣሊያን ወታደሮች ያሳዩት ርህራሄ በዚሁ መጠን ግርምትን የፈጠረ ተግባር ሆኗል፡፡ ነገሩ ዛሬም እንቆቅልሽ እንደሆነ አለ፡፡
ሆኖም እንደ ቻርልስ ሻፈር አስተያየት፤ ‹‹እንቆቅልሹ ፍች የሚገኝለት ከኢትዮጵያ የቆየ ትውፊት አንፃር ሲታይ ነው፡፡ ብዙዎች ምኒልክ የተበታተነውን የጣሊያን ጦር ቀይ ባህር እስኪገባ ያላሰደዱት ለምንድን ነው? የሚለውን ጥያቄ ከምኒልክ ለስላሳ ባህርይ ጋር ሊያቆራኙት ይሞክራሉ፡፡ ሆኖም ተሸናፊን የማሳደድ ፍላጎቱ ያልታየው፤ ለተሸናፊ ገር መሆንን ከሚያበረታታው፤ ለዘመናት ከነበረው የኢትዮጵያ የድህረ ጦርነት የግጭት አፈታት ትውፊት ጋር በተያያዘ ሊሆን እንደሚችል መታሰብ አለበት፡፡››
በአድዋው ጦርነት በጦር ምርኮኛነት የተያዙ፤ 49 የጣሊያን ጦር መኮንኖችና 1656 ወታደሮች የተስተናገዱበት ሁኔታ ኢትዮጵያውያንን የተሸናፊ አያያዝን ያመለክታል፡፡ በኢትዮጵያ የዘመነ መሳፍንት ታሪክ እንደምናየው ጦርነቱ በአንዱ አሸናፊነት ሲጠናቀቅ፣ ለወታደሮችና ለመኮንኖች ወዲያው ምህረት ይሰጣል፡፡ በዘመነ መሳፍንት ጦርነት ገጥሞ የተሸነፈ ዙፋን ናፋቂ መሳፍንት ነገ ተመልሶ ሲመጣ የሚታየው በዚህ የተነሳ ነው፡፡ በግንባር ተሰልፎ የተገኘ ወታደር አይገደልም፡፡ ብዙውን ጊዜ በጦርነት የተሸነፈ መስፍን እንዲያመልጥ በር ይከፈትለታል፡፡ ከተያዘ ደግሞ ስምምነት እንዲያደርግ ወይም በጦርነት ያለመፈላለግ ቃል ኪዳን እንዲገባ ይገደዳል፡፡ ከዚያም ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ወደ ግዛቱ እንዲሄድ ይደረጋል፡፡ እንዲህ ያለ ገርነት ማሳየት የመሳፍንት ወግ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ጦርነት ተካሂዶ ሲያበቃ፤ የተሸናፊና የአሸናፊ ጦር አባላት እንደሚቀላቀሉ የጠቀሰው አርኖልድ ዲ አባደይ፤‹‹የሚተዋወቁ የአሸናፊና ተሸናፊ ጦር አባላት እንደ ወዳጅ ሲነጋገሩ፤ በጠላቱ ወገን ተሰልፎ የተዋጋ አንድ የሚያውቁትን ሰው እያነሱ በመጨነቅ ሲጠያየቁ ታያላችሁ›› ሲል ፅፏል፡፡
በሁለት ወገን ተሰልፈው ጦርነት የገጠሙ ተራ ወታደሮች በጦርነቱ ፍፃሜ ሲተቃቀፉ፣ አንዱ ሌላውን ሲረዳና ስለ ጦርነቱ የየራሳቸውን ትረካ ሲያወሩ ማየት ለእነ ዲ አባደይ እንግዳ ነገር ነው፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ የአሸናፊው ጦር መሪ፤ ጥቂት የጦር መሪዎችን በጦር ምርኮኝነት ይይዙና ጭፍራውን በ24 ሰዓት ማሰናበት የተለመደ ነገር ነው፡፡ ምኒልክ በመቀሌ ጦርነት የማረኳቸውን ጣሊያኖች መልቀቃቸውም ከዚህ የተለመደ አሰራር የመነጨ ነው ይላል ቻርልስ ሻፈር፡፡
በአድዋው ጦርነት ከተማረኩ 1700 ጣሊያኖች ከአንድ መቶ የማይበልጡት በተለያየ በሽታ ህይወታቸው አልፏል፡፡ በጣም የቆሰሉት ወደ አዲስ አበባና ወደ ሐረር በሸክም ተልከው በሩሲያና በጣሊያን የህክምና ባለሙያዎች እርዳታ እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ ቀሪዎቹ በተለያዩ አካባቢዎች ለሚገዙ ራሶች ተከፋፍለው ተሰጥተዋል፡፡ በመሳፍንቱ ቤት የተቀማጠለ ኑሮ መኖር ችለዋል፡፡ ብዙዎቹ መልካም መስተንግዶ ያገኙ ሲሆን በምርኮኛ ልውውጥ ወደ ጣሊያን የመመለስ ዕድል ከተመቻቸላቸው በኋላም በመሳፍንቱ ግብዣ ወይም በገዛ ፈቃዳቸው በኢትዮጵያ ለመኖር ወስነዋል፡፡
እንደ መዲና የሚያገለግል ከተማ በሌለበት እና እስር ቤት የሚባል ነገር ባልነበረበት በዚያ ዘመን ምርኮኛን ለየመሳፍንቱ ማደል ልማድ ነበር። የተለየ ሙያ ያላቸው ሰዎች ደግሞ በሙያቸው እያገለገሉ ኖረዋል፡፡ የአድዋ ጦርነት በተካሄደ ጊዜ አዲስ አበባ ዋና ከተማ ለመሆን ሽር ጉድ ትል የነበረበት ጊዜ ነው፡፡ ስለዚህ አዲስ አበባ ለመሰረተ ልማት ግንባታ ባለሙያዎችን ትፈልግ ስለነበር ብዙዎቹ የጣሊያን ምርኮኞች፣ ዛሬ ጣሊያን ሠፈር እየተባለ በሚጠራው የአዲስ አበባ አካባቢ ኖረዋል። በዚሁ ጊዜ ምርኮኞቹ በምህንድስና እና በግንባታ ፕሮጀክቶች ውስጥ ተቀጥረው እንዲሰሩ ተፈቅዶላቸው ነበር፡፡ የእነዚህ ፕሮጀክቶች አለቃ ሆነው የሚያዙም ነበሩ፡፡ በወቅቱ የጣሊያን ባለስልጣናት ኢትዮጵያን በጦር ምርኮኞች አያያዝ ስሟን ለማጥፋትና ለመክሰስ ሲራወጡ በነበረበት ወቅት፤ ክሳቸውን ከንቱ በማድረግ ቆሽታቸውን ለማሳረር እንዳሴሩ ሁሉ፤ ብዙዎቹ የጦር ምርኮኞች በኢትዮጵያ ለመቆየት ወሰኑ፡፡ እንዲያውም ጥቂቶቹ፤ እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ በኢትዮጵያ መኖርን መረጡ፡፡
እንግዲህ እንደ አዛውንቱ አስተያየት፤ ደርግ የሰበረው ይህን ዓይነት ሐገራዊ ወግና ባህልን ነው፡፡ ደርግ፤ የፖለቲካ አለመግባባትን በጅምላ ጭፍጨፋ ወይም በቀይ ሽብር ለመፍታት የሞከረ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይል ነው። የደርግ መንግስት፤ በፖለቲካዊና ወታደራዊ ቀውሶች አፈታትም ሆነ በእስረኞች አያያዝ ረገድ ፍፁም አረመኔያዊ ባህርይ ያሳየ መንግስት ነበር። ይህ አሰራር ወደ ኢህአዴግ ዘመን መሸጋገሩን ሲጠራጠር የቆየ ሰው፤ አሁን እርም አውጥቷል። ሁላችንም ደንግጠናል፡፡ ‹‹እንዲህም ይደረግ ነበር›› አሰኝቶናል፡፡ ከዶ/ር ዐቢይ በስተቀር ሌሎች የስርዓቱ ባለሟሎች (በግል)፤ እንዲሁም ገዢውን ፓርቲ ጨምሮ፤ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም በመግለጫ እንኳን ሲያወግዙት አላየሁም፡፡ ብዙ ሊባልበት የሚገባ ነገር ቢሆንም፤ እንደ መደበኛ ዜና ታልፏል። ይህም ነገ ሊደገም የሚችል ችግር መሆኑን እንዳስብ አድርጎኛል፡፡ ለህዝቡ ትምህርት በሚሰጥ መንገድ መያዝና በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢ ባሉ እስር ቤቶች ያለውን ነገር መፈተሽም ያስፈልጋል፡፡   


Read 3129 times