Monday, 13 August 2018 00:00

የኢትዮጵያ ሱማሌ ፖለቲካ - ትናንትና ዛሬ!

Written by  ይነገር ጌታቸው
Rate this item
(3 votes)

  በኢትዮጵያ ፖለቲካ ሰማይ ስር ያልተለመዱ ሁነቶች የየዕለት ዜና ማሞቂያ ከሆኑ ውለው አድረዋል፡፡ ከእነዚህ ጉዳዮች መካከል ከፊሎቹ ትናንት ያልነበሩና የሰርክ ህይወታችንን የሚፈታተኑ ሲሆኑ ቀሪዎቹ ተዳፍነው ኖረው እንደ አዲስ ማቆጥቆጥ የጀመሩ ናቸው፡፡ ለዚህ ማሳያ ከሚሆኑት መካከል ወቅታዊው የኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል (ሕገ መንግሥቱ ሱማሌ ክልል ነው የሚለው) ፖለቲካ አንዱ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል የሀገሪቱን አንድ ሦስተኛ  የቆዳ ስፋት የሚሸፍን  ሲሆን ከኦሮሞና አማራ በመቀጠልም ሦስተኛው በርካታ ቁጥር  ያለው የፌደራላዊት ኢትዮጵያ አካል መሆኑ ይታወቃል፡፡
ይህ እውነት የክልሉ ፖለቲካ በግዛት አንድነት አራማጆችም ይሁን በፌደራሊስት አስተሳሰብ ኃይሎች ትልቅ ቦታ እንዲሰጠው ያስገድዳል። ይህ ብቻም አይደለም፡፡ በክልሉ በኩል ኢትዮጵያ የምትጎራበተው አካባቢ የዓለማቀፍ ሽብር ቡድኖች መፈንጫ መሆኑም ስጋቱን ይጨምረዋል። እንዲህ ያለው ስጋት ግን ድንገት ትናንት ያቆጠቆጠ ሳይሆን ስርዓት ወርዶ ስርዓት ሲተካም ያልደበዘዘ ነው፡፡ ምናልባት አዲሱ ነገር የራስን ዕድል በራስ መወሰን እስከ መገንጠል መብትን ጥያቄው አድርጎ ዘመናትን የተሻገረው  የክልሉ ፖለቲካ ልሂቅ፣ ለምን በድህረ ኢህአዴግ ፖለቲካ ውስጥ መረጋጋት ተሳነው የሚለው ይመስላል፡፡ የዚህ ጽሁፍ መነሻና መድረሻም ይኼው ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሱማሌ ፖለቲካን በወፍ በረር ማሳየት፡፡
የምኒልክ ቤተ-መንግስት ቡራኬ!
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፣ በአንድ ወቅት፣በፖለቲካ ሕይወታቸው ሁሌም የሚገርማቸው ጉዳይ የሱማሌ ፖለቲከኞች፣ በነሐሴው ጉባዔ ላይ መሳተፋቸው እንደሆነ ተናግረው ነበር፡፡ ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አግራሞት ከሁለት ነገሮች የተቀዳ ይመስላል፡፡ የመጀመሪያው የሱማሌ ፖለቲከኞች ከኢትዮጵያ በመንፈስ ከራቁ በርካታ አመታት ያስቆጠሩ በመሆናቸው ነው፡፡
የምዕራብ ሶማሊያ ነጻነት ግንባርን መስርተው ለኦጋዴን ነጻነት ሲፋለሙ የኖሩት ኃይሎች በርግጥም ህገ-መንግስት በማጽደቅ ሂደት ውስጥ ተሳታፊ ለመሆን ተወካይ መላካቸው ሊያስገርም ይችላል፡፡ ሁለተኛው የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አግራሞት፣ በሱዳን አደራዳሪነት የሱማሌ ፖለቲካ ኃይሎች በሽግግር መንግስቱ ውስጥ ተሳታፊ እንዲሆኑ ሲደረግ የነበረው ሂደት ተስፋ አስቆራጭ ከመሆኑ የሚመነጭ ነው፡፡
በርግጥም የወቅቱ የኦብነግ ሊቀ መንበር ሼክ ኢብራሂም አብዱላሂ ማህ፣ የሽግግር ቻርተሩን እንዲቀበል ለቀረበለት ጥያቄ፣ ቻርተሩ ለኢትዮጵያውያን እንጂ ለኦጋዴን ህዝብ ምኑ ነው ማለቱ ለእንዲህ ያለው አግራሞት ጉልበት እንደሚሆን የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ሳኡዲ አረቢያ መቀመጫውን ያደረገው አብዱላሂ ማህ፣ በሱዳን በኩል ቢለመንም አሻፈረኝ ብሎ ወደመጣበት ተመልሷል፡፡
ሀገር ከመረከቡ የኢትዮጵያን አንድ ሶስተኛ የቆዳ ስፋት እንደሚያጣ የገባው ኢህአዴግ፤ በጊዜው ወደ ሁለተኛው አማራጭ ፊቱን ማዞሩ የማይቀር ነበር። በዚህም በሱማሌ ህዝብ አነስተኛ ቅቡልነት ያለውን የምዕራብ ሶማሊያ ነጻነት ግንባርን ወደ ማግባባት አዘነበለ፡፡ የወቅቱ ፕሬዚዳንት አቶ መለስ ዜናዊ ባደረጉት ያላሰለሰ ጥረትም፣ የፖለቲካ ድርጅቱ ከነጻ አውጭነት ስያሜው ወጥቶ፣ የምዕራብ ሶማሊያ  ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ በሚል መጠራት ጀመረ፡፡
ምሶዴፓ በነሀሴው ኮንፈረንስ ላይ ሁለት ወንበር ያገኘ ሲሆን የኢሳና የጉረጉኸ ፖለቲካ ድርጅቶችም ሱማሌን በመወከል ተጨማሪ መቀመጫን አግኝተዋል። ይህ ተሳትፎ ግን አስራ ሦስት ያህል ጎሳዎች ላሉት የሱማሌ ክልል በቂ የሚባል አልነበረም፡፡ ይሁን እንጂ የሱማሌ ህዝብ የክልልነት ጥያቄው ዕውን ሆኖ በ1985 ዓ.ም የወሰን ማካለል ስራ ሲጀመር፣ ኦብነግ ሀገር ውስጥ ገብቶ ለመሳተፍ ፍላጎት እንዳለው አሳወቀ። በወቅቱ የድርጅቱ ቃል አቀባይ የነበረው አብዱላሂ ሞሐመድ ሰዒድ፣ ወደ አዲስ አበባ መምጣትም በኢህአዴግና በሱማሌ ፖለቲካ ልሂቃን መካከል ያለውን ልዩነት ለማርገብ ትልቅ አስተዋጽኦ ነበረው። ኦብነግ በፌደራሊዝሙ ሐሳብ ላይ እንደሚስማማና በተግባር አይቶት ከመዘነ በኋላ ከኢህአዴግ ጋር ለመስራት እንደሚወስንም አስታወቀ፡፡ በኢህአዴግ ሰፊ ድጋፍም፣ በጥር ወር 1985 ዓ.ም ጋርቦ ላይ ብሄራዊ ኮንፈረንስ አካሂዶ በይፋ ስራ ጀመረ፡፡
ኦብነግ ኮንፈረንስ በማካሄድ በሀገራዊ ፓርቲነት ለመንቀሳቀስ ዝግጁ መሆኑን ቢገልጽም፣ የድርጅቱ መሪ የነበረው ሸክ ኢብራሂም ግን ከኢህአዴግ ሰዎች ጋር መገናኘት አልፈለግም የሚል አቋም ያዘ፡፡ እንዲህ ያለው ተቃርኖ ያሳሰበው የሽግግር መንግስቱም፣ ኦብነግን በዓይነ ቁራኛ እየተከታተለ ጉዞውን ቀጠለ። መንግስት አልባ በሆነችው ሶማሊያ በኩል መውጫ መግቢያውን ያደረገው የሪያድ ዩኒቨርሲቲ መምህሩ ሸክ ኢብራሂም፣ በጊዜ ሂደት አላማው ግልጽ እየሆነ መጣ፡፡
የሽግግር መንግስቱን አለሁ እያለ ለነገ ትግሉ የሚረዳውን ወታደራዊ ኃይል ማደራጀት ጀመረ። እንዲህ ያለው የኦብነግ ሀሳብ በመሀል ሀገሩ ፖለቲከኛ መደናገርን ቢፈጥርም፣ የምርጫ ወቅት በመቃረቡ ለውሳኔ አዳጋች ነበረ፡፡ በሁለት ቢላዋ የሚበላው የኦብነግ አመራር ግን በ1987 ዓ.ም በተካሄደው ምርጫ፣ ተሳትፎ  በማድረግ ከፍተኛ ድምጽን አገኘ፡፡ ኦጋዴን በሚል የሚጠራውን አካባቢም ሱማሌ ክልል ብሎ ለመጥራት መወሰኑን አስታወቀ፡፡
የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ታምራት ላይኔ፣ በድሉ ማግስት ወደ ድሬደዋ አቅንተውም፣ ከዚህ በኋላ ሱማሌ ኢትዮጵያዊ ዜግነት አግኝቷል ሲሉ ተደመጡ። የክልል መንግስት ምስረታ ውስጥ የገባው ኦብነግ፤ ድሬደዋን ዋና መቀመጫው አድርጎ መረጠ፡፡ ይሁን እንጂ ድሬደዋ ላይ የኦሮሚያ የይገባኛል ጥያቄ በመነሳቱ ለጊዜው ጎዴን ምርጫው አደረገ፡፡ ክልሉን የሚመራ ምክር ቤት ሲቋቋም ግን አካሄዱ አላስደሰተኝም ያለው ሸክ ኢብራሂም፤ ክልሉን ከመምራት አፈገፈገ። በዚህ የተነሳም አብዱላሂ መሐመድ ሰዒድ፣ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ሆኖ ተመረጠ፡፡ በነገሩ የተደሰቱት አቶ መለስም፤ አብዱላሂ መሐመድን አዲስ አበባ አስጠርተው፣ በሁሉም ነገር ከጎኑ እንደሚሆኑ፣ ነገር ግን የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻ አውጭ ግንባር የሚለው ስያሜ ወደ ፓርቲነት እንዲቀየር አሳሰቡ፡፡
ሱማሌ ክልል ከኦጋዴን በተጨማሪ ሌሎች ጎሳዎች እንዳሉበት በማሳሰብም የስሙ መቀየር ላይ ድርድር እንደሌለ ቀጭን ትዕዛዝ ሰጡ፡፡ አማርኛ መናገር የማይችለው አብዱላሂ፣ በጊዜው አጣብቂኝ ውስጥ መግባቱ እውነት ነበር፡፡ በአንድ በኩል የሼክ ኢብራሂም ረጅም ገመድ እግሩ ላይ እንደታሰረ ነው። በሌላ በኩል፤ ወታደራዊ  ኃይሉ በእጃቸው ያለው አቶ መለስ ምን እያሰቡ እንደሆነ እርግጠኛ አልነበረም። በዚህ ምክንያትም ልቡ የወደደውን ሊያደርግ ሲንደረደር አቶ መለስ ቀደሙት፡፡ ክልሉን ለመገንጠል ሲንቀሳቀስ ነበር የሚል ታፔላ ለጥፈው ዘብጥያ ወረወሩት፡፡ ሱማሌ ክልል ዳግም ከኢህአዴግ እጅ መውጣት ጀመረች፡፡ ይህ ያስደነገጣቸው የምኒልክ ቤተ-መንግስት ሰዎች፣ የዚያድ ባሬ ጦር ኃይል አብራሪ የነበረውን ሀሰን ጀርኸለን በረጅም ገመድ አስረው “ሂድ ሱማሌን ጠብቅ” ሊሉት ፈለጉ፡፡ የሀሰን ስልጣን ግን ከቀደመውም የከፋ ሆነ፡፡ ኦብነግ በህገ-መንግስቱ የተሰጠኝን የመገንጠል መብት መጠቀም እችላለሁ የሚል ተደጋጋሚ ጥያቄ  ለኢህአዴግ ማሰማት ቀጠለ፡፡ ህገ-መንግስቱ ከጸደቀ ከሦስት ወራት በኋላም ጅግጅጋ ላይ በክልሉ ምክር ቤት በኩል የመገንጠል ጥያቄን በይፋ አጸድቆ ለፌደራል መንግስቱ ላከ፡፡
በወቅቱ በተለያዩ አካባቢዎች የኦብነግን የመገንጠል ሃሳብ የሚደግፉ ሰልፎች የተካሄዱ ሲሆን በዋርዴሩ ሰልፍ ላይ የተገኙት የኦብነጉ መሪም በመከላከያ ሀይሉ ቁጥጥር ስር ዋሉ፡፡ ሸከሀሰን ለቀናት በማረሚያ ቤት ቢቆዩም ደም አፋሳሽ በሆነ የተኩስ ልውውጥ ከማረሚያ ቤት ሊያመልጡ ቻሉ፡፡ ይህ የታሪክ ወቅት ኦብነግ፣ ከኢህአዴግ ጋር በሰላማዊ መንገድ መታገል እርባና ቢስ መሆኑን የተረዳበት ጊዜ ይመስላል፡፡ በዚህ ምክንያትም ዋናው የኦብነግ አመራር ሀገር ጥሎ በመውጣት፣ በወታደራዊ ትግል ነጻነቱን ለማግኘት መንቀሳቀስ ጀመረ፡፡
የቀረው አንጃ ተስፋ ሳይቆርጥ ራስን በራስ የማስተዳደር መብቱን ለመተግበር ደፋ ቀና ማለትን ምርጫው አደረገ፡፡ የምኒልክ ቤተ-መንግስት ሰዎች በሱማሌ ክልል የፖለቲካ ልሂቃን ተስፋ ቢቆርጡም አዲስ ርዕሰ መስተዳደር ለመሾም ግን ወደ ኋላ አላሉም። እናም በሁለት አመት ጊዜ  ውስጥ ሦስተኛውን የክልሉ ፕሬዚዳንት አብዱራሐማን ኡጋስ ሞሐመድን መሾማቸው ተሰማ፡፡
አቶ መለስ በወቅቱ ወደ ሀረር በማምራት ለክልሉ ፖለቲከኞች፣ “ህገ-መንግስቱ ለህዝቡ እንጂ ለእናንተ ለፖለቲካ ነጋዴዎች አይደለም የመገንጠልን መብት የፈቀደው” የሚል ማሳሰቢያን አስተላለፉ፡፡ በዚህ ሳያበቁም የክልሉን የፖለቲካ ችግር ለመጨረሻ ጊዜ ለመፍታት ከኦብነግ የተነጠለውን አንጃ፣ ከምዕራብ ሱማሌ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ጋር እንዲዋሀድና ለክልሉ መረጋጋት እንዲሰራ ምክር አቀረቡ፡፡
ይህን ባሉ በማግስቱም የኢትዮጵያ ሶማሌ ዴሞክራሲያዊ ሊግ ሁርሶ ላይ ተመሰረተ፡፡ አህመድ ማካሂል ሀሰን አዲሱ ሊቀመንበር ተደርጎ መሰየሙን ተከትሎም ክልሉን ማስተዳደር ጀመረ፡፡ በዚህ ፊታቸውን የነጩት የቀድሞው ርዕሰ መስተዳደር አብዱራሃመን ኡጋስ ሞሃመድም፣ ስልጣናቸውን ለማስመለስ መሳሪያ ታጥቀው ደፋ ቀና ሲሉ በቁጥጥር ስር ዋሉ፡፡ ኢሶዴሊም ሶማሌን ለማረጋጋት ቢጥርም የሚሳካለት አልሆነም፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ፤ ከግለሰባዊ ለውጥ ይልቅ የፓርቲውን አደረጃጀት መቀየር አስፈላጊ ነው ብለው በማመናቸው ሱማሌ ክልል ከሌላ ፓርቲ ጋር ተዋወቀ፡፡ የሱማሌ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የትናንት ታሪክን ሊያሽር አሀዱ ብሎ ጉዞ ጀመረ፡፡ ከሀዲር ሙዓለምም የድርጅቱ መሪ ሆኖ ብቅ አለ፡፡ ጎሳ ተኮሩ የሱማሌ ፖለቲካ ግን ለዚህ ሰውም የሚበጅ አልሆነም፡፡ እናም የምኒልክ ቤተ-መንግስት ሰዎች የሚያምኑትን  እስኪያገኙ ድረስ አሰሳቸውን ቀጠሉ፡፡ የክልሉ መሪዎችም ከቤተ-መንግስት ወደ ማረሚያ ቤት ማምራትን ለምደውታል፡፡
የመጨረሻው መጀመሪያ
 የሱማሌ ክልል ፖለቲካ እጅጉን ጎሳ ተኮር ነው፡፡ በዚህ የተነሳም በክልሉ ውስጥም ይሁን  ከሌላ ክልል ጋር የሚፈጠሩ አለመግባባቶች መነሻና መድረሻቸው በጎሳ የተቀነበበ ነው፡፡ የአካባቢው ህዝብ አርብቶ አደር እንደመሆኑ መጠን ለዘመናት የተጠቀመባቸው የግጦሽ መሬቶች ለከብቶች መኖ መንፈግ ጀምረዋል። ዘወትራዊው የውኃ ችግር ተጨምሮበትም  እንዲህ ያለው የግጦሽ መሬት ፍለጋ፣ የጎሳን ድንበር ጥሶ ከሌላ መንደር ያስውላል፡፡ ይህ ደግሞ ግጭትን የአካባቢው የዕለት ተዕለት ህይወት አካል አድርጎት ቆይቷል፡፡ በተለይም ኢትዮጵያ፣ ማንነት ላይ ያተኮረ ፌደራላዊ ስርዓትን መከተል ከጀመረች በኋላ እነዚህ ግጭቶች፣ ከጎሳ አልፈው ክልላዊ አንደምታን እየተላበሱ መጥተዋል፡፡
በዚህ የተነሳም በአካባቢው የሚከሰቱ ግጭቶች እንዳለፈው ዘመን በቦረናና በኢሳ ጎሳ መካከል ተብለው የሚታለፉ ሳይሆን በኦሮሚያና በሱማሌ መካከል እየተባሉ የሚጠቀሱ ሆኑ፡፡ የፌደራል ስርዓቱ መሰረቱን መጣል በጀመረ ማግስት የድንበር ይገባኛል ጥያቄዎች፣ በየቦታው ጎሳ ዘለል መልክ የመያዛቸው  መንስዔም ይህ ይመስላል፡፡ የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻነት ግንባርን የመሰሉ በሶማሌ ክልል ሰፊ ተቀባይነት ያላቸው የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የታሪካዊ የግዛት ጥያቄን አላማቸው አድርገው፣ የተለያዩ ቦታዎችን ወደ ሱማሌ ክልል እንዲዋሰኑ የወተወቱትም በዚህ ገፊ ምክንያት ነው፡፡
የኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል ከአፋርና ኦሮሚያ ጋር እንደመጎራበቱ መጠን ዛሬም ያልተፈቱ የድንበር ጥያቄዎች እንዳሉበት እሙን ነው፡፡ በተለይም ከኦሮሚያ ጋር የተያያዘው  የወሰን ጥያቄ  በየጊዜው ለሞቀ የፖለቲካ ክርክር ሲጋብዝ ቆይቷል፡፡ ሁለቱ ክልሎች ሰፊ የጋራ ወሰን ያላቸው ከመሆን አልፎ በድንበር አካባቢ ያለው ህዝብ አርብቶ አደር መሆኑም ጥያቄያቸውን በግጭት የታጀበ እንዲሆን ሰፊ ዕድል ፈጥሯል፡፡ እንዲህ ያለው የይገባኛል ጥያቄ ግን የግጦሽ መሬትን ብቻ ማዕከል ያደረገ አይደለም፡፡ ከሀገሪቱ ሁለተኛ ከተማ  ድሬደዋ ጀምሮ ከባቢሌ እስከ ሞያሌ የተዘረጋ ነው፡፡
ድሬደዋ የሱማሌ፣ኦሮሚያና አፋር ታሪካዊ የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባት ከተማ ናት፡፡ ኢህአዴግ ስልጣነ መንበሩን ከተቆጣጠረ በኋላ ኦህዴድ ቀድሞ በአካባቢው የተገኘ የፖለቲካ ድርጀት እንደመሆኑ መጠን የድሬደዋ ጉዳይ ወደ ኦሮሚያ ያደላ ቢመስልም፣ የሱማሌ ክልልም ዋና መቀመጫውን በዚህች መዲና ለማድረግ መወሰኑ በርካታ ውዝግብ አስነስቶ ነበር፡፡ አፋሮች በሱማሌ የኢሳ ጎሳ አባላት ከአካባቢው ቢርቁም የታሪካዊ ባለቤትነት ጥያቄያቸው ግን  በፌደራላዊ ስርዓቱ ይፈታል የሚል ዕምነት ነበራቸው፡፡
ይህ ዕምነታቸው ግን የሱማሌና ኦሮሚያ ፖለቲከኞች በድሬደዋ ይገባኛል ላይ ዙሩን ሲያከሩት እየረገበ የሄደ ይመስላል፡፡ በዚህ የተነሳም በሽግግር መንግስቱ ማግስት ድሬደዋ አምስት ግለሰቦችን  በያዘው  የጋራ ምክር ቤት እንድትመራ በፌደራሉ መንግስት ሲወሰን፣ አንድም መቀመጫ ለማግኘት አልታደሉም። ሁለት ከሶማሌ፣ ሁለት ከኦሮሚያ እንዲሁም አንድ አማራን ያካተተው የድሬደዋ የጋራ አስተዳደር፤ በጊዜ ሂደት ከተማዋን ወደ ፌደራል ከተማነት እንድትሸጋገር አድርጓል፡፡ ይህ መፍትሄ ግን ፍጹም ህገ-መንግስታዊ  ባለመሆኑ የድሬደዋ ችግር የአደጋ ጊዜ መውጫ እንኳ  የሌለው ህንጻ መሆኑ የሚያከራክር አይደለም፡፡
ሶማሌና ኦሮሚያ ግን የወሰን ይገባኛል ጥያቄያቸው ድሬደዋ ተነስቶ ድሬደዋ የሚያበቃ አይደለም፡፡ የሶማሌ ህዝብ ከባቢሌ እስከ ሞያሌ ያለው ግዛት የራሱ ስለመሆኑ ያብራራል፡፡ በተለይም ከአብዮቱ በኋላ አርብቶ አደሮቹ መንግስት በተከተለው የመሬት ላራሹ መርህ፣ ከአካባቢያቸው እየተገፉ በመሬታቸው ባይተዋር መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡ የሱማሌ አዛውንቶች፤ አሁን ያለው የፌደራል ስርዓት፣ ይህን ታሪካዊ ግፍ ተረድቶ መፍትሄ የማይሰጥ ከሆነ፣ ከደርግ በምን ይሻላል ሲሉም ይጠይቃሉ፡፡ “አርብቶ አደሮች በመሆናችን አካባቢያችንን ጥለን ወደ ሌላ ስፍራ ግጦሽ ፍለጋ ባመራንበት ወቅት ለኦሮሞ አርሶ አደር  መሬታችን ተከፋፈለብን” የሚለው ቅሬታቸውም፣ አሁንም ሳይፈታ በእንጥልጥል የሚገኝ ጉዳይ ይመስላል፡፡
በቅርቡ ተደጋጋሚ ግጭቶች የሚስተዋልባት ባቢሌም፤ የሁለቱ ክልሎች የውዝግብ ምንጭ ከሆነች ውላ አድራለች፡፡ ባቢሌ ኢህአዴግ ሀገር ማስተዳደር በጀመረ ማግስት በኦህዴድ አስተዳደር መዋቅር ውስጥ የገባች ብትሆንም ኦብነግ ግን ይህን ፈጽሞ እንደማይቀበለው በተደጋጋሚ አሳውቋል፡፡ በሱማሌ ክልል ይንቀሳቀስ የነበረው አሊ-ኢቲሀድ አል-እስላሚያም፣ ባቢሌን ከኦህዴድ አስተዳደር ለመንጠቅ ተደጋጋሚ ወታደራዊ ጥቃት ፈጽሟል፡፡ በአካባቢው የሚገኙት የሶማሌ ሀዌ ጎሳ ታጣቂዎችም ባቢሌን ለመንጠቅ የሚቦዝኑ አልሆኑም፡፡
በተለያዩ ቦታዎች የነበሩ አለመግባባቶች የቤት ስራውን ያበዛበት ኢህአዴግም፣ በጊዜው ከሀዌ ታጣቂዎች ጋር ለመላተም ፍላጎት የነበረው አይመስልም፡፡ ከዛ ይልቅ ከቁጥጥሩ ለመውጣት ጫፍ የደረሰውን የእስልምና ግንባር ለነጻነት ድርጅትን ለመውጋት፣ ሀዌዎችን ማስታጠቅን ምርጫው አድርጓል፡፡ የሀዌ ጎሳ አባላት ይህን ድርጅት ከአካባቢው ካስወጡ በኋላ ግን ወደ መሰረታዊው ጥያቄያቸው ለመመለስ አፍታም አለወሰደባቸውም፡፡ በዚህ የተነሳም ኢህአዴግ ባቢሌን በኦሮሚያና ሶማሌ የጋራ አስተዳደር ስር የምትተዳደር ከተማ እንድትሆነ ወሰነ፡፡
የኢትዮጵያ ሶማሌና የኦሮሚያ የድንበር ይገባኛል ጥያቄ ግን ባቢሌ ላይ አልተጠናቀቅም፡፡ መኢሶ ላይም ቀጠለ፡፡ የኢሳና ሀዌ ጎሳ አባላት የሚበረክቱበት ይህ አካባቢ፤ መሬቶችን ለእርሻም የሚጠቀም በመሆኑ ውዝግቡ ወቅትን ጠብቆ የግጦሽ ቦታ ለማግኘት ብቻ አልሆነም፡፡ በዚህ የተነሳም  በቅደመ ኢህአዴግ ጊዜ በወታደራዊ አማራጭ የታፈኑ የግዛት ወሰን ጥያቄዎች በየቦታው ፈነዱ፡፡ ኢሳዎች በ1978 በኦሮሞና በደርግ ወታደሮች ደርሶብናል የሚሉትን ግፍ ለመበቀል፣ በመኢሶና ዙሪያዋ  የኦሮሚያ አካባቢዎች ላይ ጥቃት መፈጸም ጀመሩ፡፡
ኢህአዴግ የድንበር ይገባኛል ጥያቄውን በጊዜያዊነት ሲፈታ ቢቆይም፣ በ1997 ግን በህዘበ ውሳኔ ወሰን የመለየት ስራ ተካሄደ፡፡ ይህ የወሰን ማካለል ውሳኔ ሁለት መሰረታዊ ቅራኔዎች የነበሩበት ነው፡፡ የመጀመሪያው የሶማሌ ክልል አርብቶ አደሮች ለእንዲህ ያለ ህዘበ ውሳኔ የሚመቹ ካለመሆናቸው ይመነጫል። የአካባቢው የፖለቲካ ልሂቃን እንደሚሉት፤ አርብቶ አደር በሆነ አካባቢ ለዛውም ጥቂቶች ተበታትነው በሚኖሩበት የሶማሌ ክልል ውስጥ ህዝበ ውሳኔ ማድረግ፣ መሬቱን ከመሸለም ያልተናነሰ ተግባር ነበር፡፡ የቅራኔው ምንጭ ግን ይህ ብቻ አልነበረም፡፡
ሁለቱም ክልሎች በህዝበ ውሳኔው ወቅት ከተለያየ አካባቢ ህዝብ አምጥተው በማስፈር  አሸናፊ ለመሆን ባትለዋል፡፡ የምርጫ ቦርድም ይህን ተረድቶ ምርጫውን ውድቅ አድርጎት ነበር፡፡ በእንዲህ ያለው ውዝግብ የታጀበው ህዝበ ውሳኔ፣ በመጨረሻም ኦሮሚያን አሸናፊ አደረገ፡፡ ከ424 ህዝበ ውሳኔ ከተካሄደባቸው ቀበሌዎች  350 የኦሮሚያ ክልልን ለመቀላቀል ወሰኑ። የቀሩት ቀበሌዎች ወደ ሶማሌ ክልል ተጠቃለሉ፡፡ ሞያሌ ላይ ያለው ውዝግብ ግን በህዝበ ውሳኔ ብቻ የሚቋጭ አልነበረም፡፡
ሞያሌን ለሁለት ከፍሎ የኦሮሚያና የሶማሌ በሚል እንድትጠራ አደረጋት፡፡ የሁለቱ ክልሎች ታሪካዊ የግዛት ይገባኛል ጥያቄ በዚህ መልኩ ዕልባት ያገኘ ቢመስልም የሚረግብ ግን አልሆነም፡፡ በ1998 የሶማሊያ ታጣቂዎች መኢሶ ላይ ጥቃት ፈጽመው፣ የበርካቶችን ህይወት ነጠቁ፡፡ የታሪካዊ ግዛት ጥያቄው ከዚህ በኋላም የሚቆም አልሆነም፡፡
የመከላክያ ኃይሉ በአንድ በኩል የሱማሌ ክልልን እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ግዛት የማስቀጠል ሀላፊነት ተሰጥቶት ከኦብነግና አሊ-ኢትሀድ አል-ስላምያ ጋር በየጉራንጉሩ ይፋለማል፡፡ ወዲህ ደግሞ ጎሳ ተኮር የሆነው ጸብ የክልል ፖለቲካን ተላብሶ ውሉ የጠፋ ቋጠሮን ሆኗል፡፡ በእነዚህ አጣብቂኞች መሀል የፌደራል መንግስቱ እንደተለመደው አዲስ ሰውን ለማንገስ ወሰነ።
የመጨረሻው መጨረሻ
በክልሉ ያለውን የፖለቲካ አሰላለፍ የተረዳና የኦብነግን ተወዳጅነት የሚገዳደር የክልል ርዕስ መስተዳደር ማግኘቱ አዳጋች ቢሆንም አቶ መለስ ግን አንድ ሰው ላይ አይናቸውን ጥለዋል፡፡ ሰውየው የክልሉ የፍትህና ጸጥታ ዘርፍ ሀላፊ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ሶማሊያ ዴሞክራሲያዊ ሊግና የኦብነግ ህጋዊው አንጃ ተዳቅለው ኢሶህዴፓን ሲመሰርቱም እዛው ነበር። ህጋዊ  እንቅስቃሴን ከሚያደርገው ኦብነግ ጋር በመሆን ሲታገል የኖረው ይህ ሰው፤ የሸክ ኢብራሂምን የኦብነግ አንጃ ጠንቅቆ እንደሚያውቀው የሚያጠራጥር አይደለም፡፡
ይህ ብቻም አይደለም፤ በዛይድ ባሬ ስርአት ውስጥ የነበሩትን የፕሬዚዳንት አማካሪዎች ወዳጅ ማድረጉም የቀጠናውን ፖለቲካ ከማንም በላይ እንዲረዳ አስችሎታል፡፡ አቶ መለስ ከዚህ ሰው ላይ አይናቸውን ለመንቀል አልፈለጉም፡፡ ከአስር አንድ ያልተሳኩ ሙከራዎች በኋላ አስራ ሁለተኛው ሰው ላይ ተስፋ  የጣሉት አቶ መለስ፤ በኢሶህዴፓ በኩል  ለስልጣን እንዲበቃ አደረጉት፡፡ አብዲ መሃመድ ዑመር ከሱ በፊት ያሉት የክልል ርዕሰ መስተዳደሮች መጨረሻቸው ማረሚያ ቤት መሆኑን ቢያውቅም ወደ ኋላ ግን አላለም፡፡
ኦብነግ  የኦጋዴን ህዝብ፣ የራሱ ዕድል በራሱ መወሰን አለበት ከሚለው አቋሙ አላፈገፈገም፡፡  የአዲሱን ርዕሰ መስተዳደር ሹመትም በክልሉ ለውጥ የማያመጣ በማለት ማውገዙን ቀጠለ፡፡ የተለመዱ ጥቃቶችንም በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች መፈጸሙን አጠናከረ፡፡ በነዳጅ ፍለጋ ላይ የነበሩ ቻይናውያንና ኢትዮጵያውያን ላይ በወሰደው ጥቃትም አለማቀፋዊ መነጋገሪያ ለመሆን በቃ፡፡ የአብዲ መሀመድ ዑመር አስተዳደር በጊዜ ሂደት በሁለት እግሩ መቆም ጀምሯል፡፡
በአንጻሩ ኦብነጎች የትናንቱን ያህል ጉልበት ቢያጡም እዚህም እዚያም ጥቃታቸውን አላቆሙም። ታሪካዊው የኦሮሚያና ሶማሌ ክልል የወሰን ጉዳይ ውዝግብም ፋታ የሚሰጥ አልነበረም፡፡ በእነዚህ ውጫዊና ውስጣዊ ችግሮች መሃል የተገኘው አዲሱ አመራር፣ በመከላከያ ሰራዊቱ ድጋፍ እየተደረገለት፣ የአቶ መለስ ምክር ታክሎበት ወደ መረጋጋት ማምራት ጀመረ፡፡ አብዲ መሀመድ ዑመር ያመጣው ሰላም በበርካቶች መደነቅ ጀመረ፡፡  የሱማሌ ዲያስፖራ ከጎኑ ሆኖ የሚችለውን ሁሉ እንደሚረዳው ቃል ገባለት። በ2006 በክልሉ የተከበረውን የብሄር ብሄረሰቦች ቀን ለተመለከተ ሰው በርግጥም የአቶ አብዲ አመራር ስኬታማ ስለመሆኑ ይመሰክራል፡፡
አዕላፍ መሰረተ ልማቶችን ከባዶ ተነስቶ ለማጠናቀቅ የበቃው ይህ አመራር የገንዘብ ድጋፉ ከዲያስፖራውም ስለመሆኑ የሚያጠራጥር አልነበረም፡፡ ርዕሰ መስተዳደሩ ከዲያስፖራው ጋር የፈጠረው ግንኙነት ለክልሉ ፖለቲካ ሁለት ጥቅሞችን እንደሚያበረክት እሙን ነበር፡፡ የመጀመሪያው ጅግጅጋን ከሌሎች ክልሎች ከተማ በተሻለ የዕድገት ጎዳና ላይ እንድትገኝ ረድቷታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በውጪው አለም ካለው የሱማሌ ዲያስፖራ ሰፊ ድጋፍ እያገኘ መምጣቱ፣ የኦብነግ የጀርባ አጥንት የሆነውን የዲያስፖራ ድጋፍ እንዲቀንስ አድርጎታል፡፡
ሁለት ድሎችን ያስመዘገበው የአቶ አብዲ አመራር፣ በመከላከያ ሰራዊት የእጅ  አዙር አገዛዝ ስር የነበረውን ክልሉን ሙሉ በሙሉ ወደ ማስተዳደር ተንደረደረ፡፡ ስልጣነ መንበሩን ከተረከበ ከአመታት በኋላም ክልሉን ወደ መረጋጋት ለመመለስ ቻለ፡፡ በዚህ ጊዜ ግን አብዲ መሀመድ ዑመር ከሌላ እውነት ጋር መጋፈጥ ጀመረ፡፡ ጎሳ ተኮሩ የሶማሊያ ፖለቲካ፣ የሱን ስልጣን ለመንጠቅ ተደራጅቷል፡፡ ከኦሮሚያ ጋር ያለው የታሪካዊ የድንበር ይገባኛል ጥያቄ  ከቁጥጥር መውጣት ጀምሯል፡፡
በሁለቱም ክልል አመራሮች መካከል ያለው የንግድ ከተሞችን በሚያስተዳደሩት ክልል ስር አድርጎ ለሙስና ለም መሬት የማድረግ አዝማሚያ ጨምሯል። የኮንትሮባንድ ንግዱ ተጠቃሚ ያደረጋቸው አካላት የሱማሌ ክልልን ትልቁ የፖለቲካ ገበያ አደረጉት። ለረጅም ጊዜ ስልጣን ላይ ለመቆየት የታደለው አብዲ መሃመድ ዑመር በአንድ ነገር እርግጠኛ የሆነ ይመስላል፡፡ ከእሱ በፊት ከነበሩ አስራ አንድ ርዕሰ መስተዳድሮች የተሻለ መሆኑንና ክልሉን የማረጋጋት ቁልፉ በእጁ እንዳለ፡፡ ከምኒልክ ቤተ-መንግስት ስልጣን ቀብተው የላኩት ሰዎችም የአብዲ መሀመድን ጥቅም ተረድተዋል፡፡ የሱማሊያ ሰንደቅ ዓላማ ሲውለበለብበት የኖረውን ክልል ኢትዮጵያዊ አድርጓልና፡፡
አቶ አብዲ ኦብነግና ሌሎች የሚፈነጩበትን ክልል፣ በልምድ ታጅበው የግላቸው አደረጉ፡፡ ኢህአዴግ፤ ኦብነግ ከሚፈነጭበት የኢሶህዴፓው ሰው ቢፈነጭበት የማጣው ነገር ብዙ አይደለም ብሎ ለቀቀው፡፡ እናም በረጅሙ ከምኒልክ ቤተ-መንግስት የታሰረበትን ገመድ በጥሶ ያሻውን ሲያደርግ ተው የሚል አልተገኘም። የመሀል ሀገሩ ፖለቲካ ይህን ላለማድረጉ ሌሎች ተጨማሪ ምክንያቶችም ነበሩት፡፡ አንዱ በአቶ መለስ ይሁንታ የተሾሙትን ሰው ለመንካት ድፍረቱን ያገኘ አልነበረም፡፡ ሌላው እሳቸውን መነካካትም ክልሉን ወደለየለት ቀውስ  እንደሚወስደው መረዳቱ አዳጋች አይደለም ፡፡
የኢትዮጵያ ፖለቲካ በመሀል ሀገር ተቃውሞ መናጥ መጀመሩም፣ የኢህአዴግ ዓይን  ከአቶ አብዲ ላይ  እንዲነቀል የራሱን አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ በዚህ መሃል ግን የኢትዮጵያ ሱማሌና የኦሮሚያ ድንበር ግጭት ዳግም አገረሸ፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ የተባለው የሀገር ውስጥ ፍልሰትም ተመዘገበ፡፡ የሁለቱ ክልል አመራሮች ችግሩን ለመፍታት ቢሞክሩም፣ እርቁ የምር ሊሆን አልቻለም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከተሾሙ በኋላ ወደ ጅግጅጋ አምርተው፣ የሁለቱን ክልል ርዕሰ መስተዳድሮች ቢያወያዩም ነገሩ የመዳፈን እንጂ የመጥፋት ምልክት አላሳየም፡፡
አቶ አብዲ  አጣብቂኝ ውስጥ እንደገባ እሙን ነበር። በአንድ በኩል፣ አሁን ያለው የምኒልክ ቤተ-መንግስት ሰው የሾመው አይደለም፡፡ ከላይ እንደጠቀስኩት፣ ጅግጅጋ  ቤተ-መንግስት ለመግባት ቡራኬው ያለው አዲስ አበባ ላይ ነው፡፡ በሌላ በኩል የጎሳ ፖለቲከኞች አጋጣሚውን ተጠቅመው ከስልጣን እንዲወርድ መወትወታቸውን ቀጥለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይም በፊናቸው ሌላ ፈተና እየጠበቃቸው ነበር። የመጀመሪያው የኦሮሞ ፖለቲካ ትግል ለስልጣን ያበቃቸው መሪ  ናቸውና፣ የኦሮሚያን ህዝብ ጥያቄ የመስማት ሀላፊነት አለባቸው፡፡ አብዲ ኢሌ በሚል ስሙ የሚታወቀው ይህ ሰው፤ በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ የሚወደድ አይደለም፡፡ ሁለተኛ እሳቸው ሹመት የሰጡት አመራር አለመሆኑ ነገ ክፉ ላለማሰቡ እርግጠኛ እንዲሆኑ አላስቻላቸውም፡፡
በዚህ መሀል ግን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ምቹ አጋጣሚ ያገኙ ይመስላል፡፡ የመሀል ሀገር ፖለቲካው ንረት መቀዛቀዝ ሲጀምር አይናቸውን ዳግም ወደ ሱማሌ ክልል ላኩ፡፡ አቶ አብዲ የጠቅላይ ሚኒስትሩ መንገድ ከግለሰባዊ አለመግባባት ብቻ ሳይሆን ከፖለቲካዊ ርዕዮት መለያየት የተነሳ ምቾት እንደማይሰጠው እሙን ነው፡፡ በፌደራላዊ ስርዓቱ ላይ ጥያቄ መነሳት የለበትም ለሚለው አብዲ መሀመድ ዑመር፤ የዶክተር ዐቢይ ንግግርና ተግባር የሚዋጥ አይሆንም፡፡
የመደመር ፖለቲካን ከአንገት በላይ ተቀብሎ ሰልፍ ቢወጣም፣ ፌርማታው ግን ለሱም ሆነ ለሱማሌ ህዝብ የሚሆን አይደለም፡፡ እናም ሁለቱም ወቅት መጠበቅን ምርጫቸው አደረጉ፡፡ የመሀል ሀገሩ ሰው ዕውቅና የሰጡትና ይሁንታን የቸሩት ውይይት፣ በድሬደዋ ስለ አብዲ ሊመክር ቀጠሮ ተቆረጠ፡፡ ለአቶ አብዲ አመራር የዚህ ስብሰባ  አላማ ግልጽ ነበር፡፡ በመደመር ስም ስልጣን ለመንጠቅ  የሚደረግ እንቅስቃሴ ነው። እናም ስብሰባው ህገ-ወጥ  ነው፣ መካሄድ የለበትም ሲል ለድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ደጋግሞ ተማጸነ፡፡ የሚሰማው ግን አልተገኘም፡፡
የአብዲ የመጫወቻ ካርታው ተማጽኖ ብቻ አልነበረም፡፡ ወዲያው ሌላኛውን ካርድ መዘዘው፡፡ የራስን ዕድል በራስ መወሰን እስከ መገንጠል የሚል ነው፡፡ ካርዱን በፌደራል መንግስቱ ላይ ለመምዘዝ ሲንደረደር የመከላክያ ኃይሉ ጣልቃ ገባ፡፡ አቶ አብዲ ካርዱን ወደ ኪሱ መለሰው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር  ዐቢይ አሁን  ትልቅ ሸክም ተገላግለዋል፡፡ ስልጣን የሚሹት የኢትዮጵያ ሶማሌ ጎሳዎችም፣ የኦጋዴኑ ሰው ከመንበሩ መነሳቱ ሳያስደስታቸው አይቀርም፡፡  
ሆኖም የኢትዮጵያ ሶማሌ ፖለቲካ ድርሰት ዛሬም አላለቀም፡፡ ፌርማታ አልባው ፖለቲካ ቀጥሏል!!  የኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል አሁንም አደጋ አንዣቦበታል። ነገስ? በእርግጠኛነት መናገር አዳጋች ነው፡፡ ብዙ ሥራና ጥንቃቄ ይፈልጋል፡፡


Read 4860 times