Saturday, 11 August 2018 11:12

በ‘ዛገ መነጽር’ ያዩት ነገር…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(11 votes)


    እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ዓይኑን በእጅጉ የሚያመው አንድ ሀብታም ሰው ነበር፡፡ አገሩ ውስጥ ያሉ የዓይን ሀኪሞች ዘንድ ሁሉ ያዳርሳል፡፡ የታዘዙለት ብዙ አይነት መድሀኒቶችንም ተጠቀመ፡፡ ሆኖም፣ ምንም ሊሻለው አልቻለም፡፡
በመጨረሻ እንዲህ አይነት የጤና ችግር ያለባቸውን ሰዎች ማዳን ይችላሉ የተባሉ ባህታዊ ተጠሩ፡፡ ባህታዊውም ችግሩ በአንድ ጊዜ ገባቸው፡፡ ሀብታሙ ሰውዬም ለተወሰነ ጊዜ አረንጓዴ  ቀለም ብቻ እንዲያይና ሌሎች ቀለማትን ችላ እንዲላቸው መከሩት፡፡ ነገሩ ያልተለመደ ቢሆንም ሀብታሙ ሰው ግን ለመዳን ባለው ጉጉት ሊሞክረው ወሰነ፡፡
ቀለም ቀቢዎችን ሰበሰበናም፣ በርካታ ቆርቆሮ አረንጓዴ ቀለም አስገዛ፡፡ እሱ ሊያያቸው የሚችላቸውን ነገሮች በሙሉ አንድም ሳይቀር አረንጓዴ ቀለም እንዲቀቡ አደረገ፡፡ ከጥቂት ቀናት በኋላም ባህታዊው ሊጠይቀው መጡ። እሳቸውም ለብሰው የነበሩት ሙሉ ቀይ ልብስ ስለነበር ቀለም ቀቢዎቹ አረንጓዴ ቀለም ቸለሱባቸው፡፡ ባህታዊውም ምክንያቱን ሲሰሙ ሳቁ፡፡ ሀብታሙንም እንዲህ አሉት፤ “በጥቂት ዶላር አረንጓዴ መስታወት ያለው የዓይን መነጽር ብትገዛ ኖሮ ግድዳዎቹን፣ዛፎቹን፣ የቤት እቃዎቹንና ሌሎችን ሁሉ ቀለም ከመቀባት ድነህ በርካታ ገንዘብ ታተርፍ ነበር፡፡ ዓለምን በሙሉ አረንጓዴ ቀለም ልትቀባት አትችልም፡፡”
እናም… ነገሩ አመለካከታችንን ከለወጥን ዓለምም እንደዛው ትሆናለች፡፡ ዓለምን ለመለወጥ መሞከር ሞኝነት ነው፣ ምክንያቱም መጀመሪያ መለወጥ ያለብን ራሳችንን ነውና፡፡
ስሙኝማ… አንዳንዶቻችን የያዝነው አስተሳሰብ ልክ አለመሆኑን እያወቅን እንኳን ነገራችን… “ፍንክች የአባ ቢላዋ ልጅ!” አይነት ነው፡፡ አመለካከታችንን መለወጡ ሞት ይመስለናላ! አስተሳሰብ መለወጥ ሽንፈት ይመስለናላ! ይቺ ‘ኤጎ’ የሚሏት ነገር እላያችን ላይ ሰፍራ መጫወቻ አድርጋናለች፡፡
እያንዳንዳችን ነገሮችን የምናይበት የየራሳችን ምልከታ አለን፡፡ ሰርግ ቤት “እንዴት ነሽ ገዳዎ!” ሲባል፣ ያው ምላሹ “አሀ ገዳዎ” አይነት ነው። በህይወት ግን አንድ ወገን “እንዴት ነሽ ገዳዎ!” ስላለ ብቻ  ሌላኛው ወገን የግድ… “አሀ ገዳዎ!” ማለት የለበትም፡፡ ከ“እንዴት ነሽ ገዳዎ” የተሻለ ዜማ ሊኖረው ይችላላ!  “እንዴት ነሽ ገዳዎ!”… አለ አይደል… ከዘመኑ አስተሳሰብ ጋር የማይሄድ ነው ብሎ ያስብ ይሆናላ! እናላችሁ… “ሁልህም ለምን ተመሳሳይ አቋም አልያዝክም” ልንባል አንችልም… ሊሆን አይችልማ፡፡
ከ‘ፖለቲካ ነፍሴ’ እስከ ‘ፖለቲካና ኮረንቲ በሩቁ’ ብዙዎቻችን ነገረ ሥራችን… “ሁልህም ለምን የእኔን አቋም አልያዝክም!” “ለምን በእኔ የከበሮ ምት ዳንኪራ አልረገጥክም!” “ለምን በእኔ ዜማ እስክስታ አልወረድክም!” አይነት ሆኖ ነው ስንጯጯህ የኖርነው፡፡
ሁላችንን ባይሆን እንኳን ብዙዎቻችንን “ሊያስማሙን ይገባሉ” የሚባሉ እውነታዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ግን እንደዚህ አይነት ነገሮች ላይም አንድ ሺህ አንድ ጽንፍ የያዙ አመለካከቶች ይኖራሉ፡፡ ‘ብስለት’ የሚመጣው ሁላችንም አመለካከታችንን አደባባይ ለማውጣት እድል ስናገኝ ነው፡፡ እንደፈለግነው ‘ብስለት’ ያልመጣውም፣ ይህንን እድል እርስ በእርስ በመነፋፈጋችን ነው፡፡ አንድ ነገር በተነገረ ቁጥር…
“ይቺንማ እናውቃታለን፣ ከጀርባ ሆነው ቁልፉን የሚያሽከረክሩት እነማን እንደሆኑማ እናውቃለን…”
“እንዲህ የሚሉት የድሮ ስርአት ናፋቂዎች ናቸው…”
“እንዲሀ የሚሉት ስልጣን የተነጠቁ ናቸው…”
ማለቱ ይቀናናል፡፡ ወደ አደባባይ የወጡ አስተሳሰቦችን፣ አመለካከቶችን፣ ፖለቲካዊም ሆኑ ምንም አይነት እምነቶችን ዘርዝረን ከማየቱ በፊት ችሎት አስችለን፣ተከሳሽ መከላከያውን ለማሰማት እድል ሳያገኝ፣ እኛው ከሳሽ፣ እኛው ፍርድ ሸንጎ፣ እኛው ዳኛ እንሆናለን፡፡ ይሄ የትም አላስኬደንም፣ የትምም አያስኬደንም! የማስደንበሪያ ቅጽላ በመደርደር ጫፍ የደረሰ ህብረተሰብ አናውቅም፡፡
እናላችሁ…ወደፊት ልንሄድበት በምንፈልገው ጎዳና ላይ ለመቀጠል የሰዎችን አስተሳሰቦች፣ አማራጭ ሃሳቦችንና የመሳሰሉትን የምንመዝንበት ጠባያችን ላይ ለውጥ ያስፈልገናል፣ ከአሉታዊ ድምዳሜ ተነስተን ነገሮች ላይ ውሳኔ የምናሳልፍበት አካሄድን መለወጥ ይኖርብናል፡፡ መመልከቻ መነጽራችን ጥራት ያለው ምስል የሚያሳየን ሊሆን ይገባል፡፡ ‘አንጋረ ፈላስፋ’ መጽሐፍ ላይ …‘አንዲት ሴት ደርሳ ሶቅራጥስን “ኸረግ መልክህ ምንኛ ክፉ ነው” ብትለው፣ “በዛገው መነጽርሽ አይተሽኝ ነው” አላት’ የሚል ነገር አለ፡፡ ዘንድሮ ችግራችን ይኸው ነው…ነገሮችን በዛገ መነጽር ማየቱ፣ በተበላሸ መነጽር ማየቱ!
የመበላሸት ነገር ካነሳን አይቀር…እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል፣ የዘንድሮውንስ እሺ እንደምንም እዚህ ደርሰናል፣  …ለከርሞው ክረምት ግን በየወረዳው እየተቧደንን፣ ጀልባ በሊዝ እንዲሰጠን እንፈልጋለን፡፡ ዝናቡ ጠብ ሲል መንቀሳቀስ ከባድ እየሆነ ነዋ! ከበድ ያለ ዝናብ ሲዘንብ፣ አንድ ሺህ አንድ ሀይቆች የሚፈጠሩባት ከተማ እየሆነች ነዋ! የምር …ወጣቶች ለጉልበታቸው እያስከፈሉ ሰዎችን ተሸክመው ከዚህኛው እዛኛው ጫፍ የሚያሻግሩባት ከተማ ሆናለቻ! ብዙ ባለ መኪኖች በየአስፋልቱ መሀል የተጠራቀመ ውሀ እያዩ ሁሉ በመጡበት ፍጥነት እየከነፉ፣ የቆሸሸ ውሀ ቸልሰውብን የሚሄዱባት ከተማ ሆናለቻ! እኔ የምለው…መንገዶቻችን ሲሠሩ እንደ ልብ የሚተጣጠፉ ሆነው ነው እንዴ!
ሀሳብ አለን… ከዓመት ዓመት እንዲሁ የሚቀጥል ከሆነ እቅጩ ይነገረንና በዓለም ድንቃ ድንቅ መዝገብ እንዲሰፍርልን ‘ፔቲሽን’ ተፈራርመን እንላክ፡፡ ‘ናሽናል ጂኦግራፊ ዋይልድ’… አለ አይደል… ‘አንቴምድ አዲስ አበባ’ የሚል ዘጋቢ ፊልም ሊያስተላልፍልን ይችላል! እናም እንዲሁ የሚቀጥል ከሆነ…ለቱሪዝም እንጠቀምበታለን! ልክ ነዋ…“በኒው ዮርክና በለንደን መሀል አስፋልት በዓመት ለሁለት ወር የሚፈጠር ሀይቅ አይተዋል? አላዩም፡፡  እንግዲያው፣ ጎምጅተው አይቀሩም፤ ቅልጥ ባለው የአዲስ አበባ ክፍል በህንጻዎች መሀል ዝናብን ተከትሎ የሚፈጠር ሀይቅ አለልዎት ይባልልን!
ደግሞላችሁ…አዲስ አበባ ብዙ ቦታ እግር መንገዶቿ ለዓይን የሚስቡም፣ ምቹም ናቸው፡፡ መልካም ሀሳብ ነው፡፡ ግን ደግሞ እንጠይቃለን…እነኚህ መንገዶች ሲነጠፉ ምን ያህል ዓመት ያገለግላሉ ተብለው ነው? ምክንያቱም…‘በሰው ሙያ መግባት’ አይሁንብንና ምንም አይነት ግንባታ ሲነደፍ የሚቆይበት ጊዜ ሙያዊ ግምታዊ ስሌት አለና፡፡ መነጫነጭ ልማዳችሁ ነው አትበሉንና… ብዙ ቦታ እኮ ንጣፎቹ ደርሰው የቆሙባቸው ቦታዎች…አለ አይደል…ቶሎ ለመንቀልም እንዲያመቹ ሆነው የተሰሩ ነው የሚመስለው። የአራት ዓመት ህጻን ብድግ ሊያደርጋቸው ይችላላ! በተለያዩ ቦታዎች ደግሞ ትንሽ ተንጥፎ ቀጥ፣ ትንሽ ተነጥፎ ቀጥ ሆኗል፡፡ ሲብስበት ደግሞ ይህ ጸሃፊ እንደሚኖርበት የመሀል ከተማ መንደር፣ የሾለ ኮረት ከብዙ ሳምንታት በፊት ተበተነና በቃ! እኔ የምለው ኮብልስቶን ምናምን የሚነጠፈው እንደ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ‘ሲዝን አንድ፣ ሲዝን ሁለት’ በሚል ነው እንዴ! “ለዚቹ ነው እንዴ ገና ሌሎች አስርት ዓመታት የሚያገለግለውን የኬር ንጣፍ ያነሳችሁት?» ብንል ግራ ስለሚገባን ነው። ወይንስ የሥራው ‘ሮድማፕ’ ምናምን የሚሉት ነገር አልነበራችሁም!
ይቺን ስሙኝማ…አሜሪካ ውስጥ እግር ኳስ አሁንም ቢሆን ይሄን ያህል ነው ይባላል፡፡ አሁንም ስፖርቱን ተወዳጅ ለማድረግ እየተለፋ ነው አሉ፡፡ ‘ኒው ዮርክ ኰስሞስ’ የተባለውን ቡድን ለመመስረት ስቲቭ ሮስ የተባለ ሰው ትልቅ ሚና ተጫውቷል፡፡ እናማ… ስቲቭ ሮስ ለዚህ ስኬቱ የአባቱን ምክር ይጠቅሳል፡፡ አባቱ እንዲህ ብሎት ነበር… “በህይወት ውስጥ አንደኛ… ቀኑን ሙሉ የሚሠሩ ሰዎች አሉ፣ ሁለተኛ…ቀኑን ሙሉ ህልም የሚያልሙ ሰዎች አሉ፣ ሦስተኛ ለአንድ ሰዓት ያህል ህልም ካለሙ በኋላ ህልማቸውን ለማሳካት ወደ ሥራ የሚሰማሩ አሉ፡፡ ከሦስተኞቹ ጋር ተቀላቀል፤ ምክንያቱም እዚያ ብዙ ፉክክር የለምና” ነው ያለው አባቱ፡፡
እናም ሀሳቦች ለመለዋወጥ፣ አንዳችን ከሌላኛችን ጋር በመደማመጥ…መንገድ ሆነ፣ መብራት ሆነ፣ ውሀ ሆነ በሁሉም መስኮች ሥራዎችን ለመሥራት… ለአንድ ሰዓት ያህል አልመው፣ በኋላ ህልማቸውን ለማሳካት ወደ ሥራ የሚሰማሩ ሰዎችና ተቋማት ያስፈልጉናል፡፡ ለዚህ ሁሉ…አለ አይደል… ሶቅራጥስ “በዛገው መነጽርሽ አይተሽኝ ነው” እንዳለው፣ ነገሮችን በዛገ መነጽር ማየት እስከቀጠለ ድረስ ሁሉም ነገር ‘ዘ ሴም ኦልድ ስቶሪ’ ነው የሚሆነው፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 7547 times