Print this page
Sunday, 12 August 2018 00:00

አቶ ልደቱ አያሌው ራሳቸውን ከፖለቲካ ማግለላቸውን አስታወቁ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(8 votes)

 “የግድያ ዛቻና ማስፈራሪያ ደርሶኛል”

     ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ በተቃዋሚ ፖለቲከኛነት የሚታወቁት አቶ ልደቱ አያሌው፤ “የግድያ ዛቻ ተሰንዝሮብኛል” በማለት ራሳቸውን ከማንኛውም የፖለቲካ እንቅስቃሴ ማግለላቸውን ለአዲስ አድማስ አስታወቁ፡፡
“እኔ በድርጅት መታገል እንጂ በግል መታገል ለሃገሪቱ ፖለቲካ ያን ያህል ጠቃሚ ነው ብዬ አላምንም” ያሉት አቶ ልደቱ፤ “ፓርቲያችንን ኢዴፓን ያፈረሰው የምርጫ ቦርድ ፈርሶ አዲስ ካልተመሠረተ በስተቀር የፖለቲካ ድርጅት ማቋቋም አስፈላጊ አይደለም” ብለዋል፡፡  
የኢዴፓ መሥራችና  አመራር የነበሩት አንጋፋው ፖለቲከኛ አቶ ልደቱ፤ ራሳቸውን ከፖለቲካ ለማግለል የተገደዱት በፓርቲያቸው መፍረስ ብቻ አይደለም፡፡ ሌላም ምክንያት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ በቅርቡ በመቐሌ አንድ ስብሰባ ላይ በመሣተፋቸውና ንግግር በማድረጋቸው የግድያ ዛቻና “ንብረትህን እናወድማለን” የሚሉ ማስፈራሪያዎች እንደደረሳቸው የገለጹት አቶ ልደቱ፤ “ከፖለቲካ ራሴን ለማግለሌ አንደኛው ምክንያት ራሴንና ቤተሰቦቼን ከአላስፈላጊ መስዋዕትነት ለመከላከል ነው” ብለዋል፡፡
“ዛሬም አማራጭ ሃሳብ ለመስማት ያልተዘጋጁ ሰዎች አሉ” የሚሉት ፖለቲከኛው፤ ንብረቴን ለማውደም ቀጠሮ ጭምር ተይዟል፤ “አንተንም ገድለንህ አደባባይ እንጥልሃለን” የሚል ዛቻ ከተለያዩ አካላት ደርሶኛል ብለዋል፡፡ በሃገሪቱ የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴም በጭፍን አስተሳሰብ ወደ ኋላ እንዳይመለስ ስጋት እንዳላቸው አልሸሸጉም፡፡  
ከዚህ በኋላ ማንኛውም አይነት የፖለቲካ ተሣትፎ አይኖረኝም ያሉት አቶ ልደቱ፤ ፖለቲካዊ አስተያየቶችንና ሃሳቦችንም ከመስጠት እቆጠባለሁ ብለዋል፡፡

Read 10550 times