Print this page
Saturday, 11 August 2018 11:03

የዳያስፖራ ትረስት ፈንድ አማካሪ ም/ቤት ሥራ ጀምሯል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

 የኢትዮጵያ ዳያስፖራዎች የትረስት ፈንድ አማካሪ ምክር ቤት መቋቋሙን የጠቆመው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅ/ቤት፤ ዕውቅ ዳያስፖራ ምሁራንን ጨምሮ ተሰሚነት ያላቸው ግለሰቦችን ያካተት 15 አባላት ያሉት ኮሚቴ ተደራጅቶ ሥራ መጀመሩን አስታውቋል፡፡   
በመላው አለም 3 ሚሊዮን ያህል ዳያስፖራዎች ይኖራሉ ተብሎ እንደሚገመት የጠቆመው ፅ/ቤቱ፤ ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ቀደም ሲል እያንዳንዱ ዳያስፖራ በቀን 1 ዶላር  ቢለግስ ብለው ያቀረቡት ሃሳብ ሰፊ ተቀባይነት ማግኘቱን ተከትሎ፣ ኮሚቴ አቋቁሞ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መግባት ማስፈለጉን ይገልጻል፡፡
በዚህ መሠረት ታዋቂው የፖለቲካ ሳይንስ ምሁርና በካሊፎርኒያ ስቴት ዩኒቪርስቲ የህግ ምሁርና ጠበቃ የሆኑት ፕሮፌሰር  አለማየሁ ገ/ማርያም፣ የአማካሪ ም/ቤቱ ሊቀ መንበር ሆነው ተሾመዋል፡፡ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም የብዙሃን ትረስት ፈንድ አስተባባሪ ዶ/ር ብስራት አክሊሉ፣ የአፍሪካ ልማት ባንክ ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ገብርኤል ንጋቱ፣ የፓንቶን ካፒታል ግሩፕ መስራችና ዳይሬክተር አቶ ካሣሁን ከበደ፣ በሜሪላንድ ዩኒቨርስቲ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ምርምር ጉባኤ ዳይሬክተር  ዶ/ር ለማ ሠንበቴ፣ የአደጋ ስጋት አመራር ከፍተኛ ባለሙያ ወ/ሮ ሉሊት እጅጉ፣ ከፍተኛ የፖሊሲ ጥናት ባለሙያ ዶ/ር መና ደምሴ፣ የአፍሪካ መሠረተ ልማት ፋውንዴሽን ዳይሬክተር ወ/ሮ ሚሚ አለማየሁ፣ የሰብአዊ መብት ተከራካሪው አቶ ኦባንግ ሜቶ፣ ታዋቂው አክቲቪስት ታማኝ በየነ፣ የአሜሪካ ሜትሮፖሊታን ትራንስፖርት ኔትወርክ ፕሬዚዳንት አቶ ታሺታ ቱፋ፣ የአለም ባንክ አማካሪ አቶ ይሄነው ዋለልኝ፣ የፀሃይ አሣታሚ ኩባንያ ባለቤት አቶ ኤልያስ ወንድሙ እንዲሁም አቶ ሚኒልክ አለሙና አቶ ሮብሰን ኢታና የአማካሪ ም/ቤቱ አባላት ሆነው ተመርጠዋል፡፡ ኮሚቴው ሥራውን በይፋ መጀመሩንም የጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት አስታውቋል፡፡  

Read 4435 times