Saturday, 11 August 2018 11:02

“የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ” ታላቅ ህዝባዊ ስብሰባ እያደረገ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)


            “በአንድ ስብሰባ እስከ 15 ሺህ ህዝብ እየተሳተፈ ነው”

     ከተመሰረተ ሦስት ወራትን ብቻ ያስቆጠረው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)፤ በአማራ ክልልና በሌሎች ዋና ዋና ከተሞች ህዝባዊ ውይይቶችን እያደረገ መሆኑን ገልፆ፤ በውይይት መድረኮቹ በአማካይ ከ10 ሺህ እስከ 15 ሺህ የሚደርስ ህዝብ  እየተሳተፈ ነው ብሏል፡፡
ከቀናት በፊት በአዲስ አበባ ዋና ጽ/ቤቱን የከፈተው ንቅናቄው፤ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች 15 ያህል ጽ/ቤቶችን በ3 ወራት ጊዜ ውስጥ ከፍቶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም የአብን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ክርስቲያን ታደለ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
እስካሁን ባህርዳር፣ ጎንደር፣ ደሴ፣ ወልዲያ፣ ደብረ ማርቆስና ደብረ ብርሃን ስብሰባውን ያደረገው ንቅናቄው፤ በቀጣይ በአዲስ አበባ፣ ሃዋሳ፣ ድሬደዋ፣ ሃረር፣ ሰቆጣ፣ ኢንጂባራ፣ ፍኖተ ሰላምና አሶሳ እንደሚያካሂድ አቶ ክርስቲያን ተናገረዋል፡፡
በህዝባዊ ስብሰባዎቹ ላይ ስለ ንቅናቄው የፖለቲካ አላማና ግቦች፣ ስለ አማራ ብሄርተኝነት ፈተናዎችና እንዲሁም ስለ አገሪቱ አንድነት ውይይት እንደሚደረግ ጠቁመውም እስካሁን ባለው ሂደት ህብረተሰቡ ከተገመተው በላይ ንቁ ተሳታፊ እየሆነ ነው ብለዋል - ኃላፊው፡፡
ከህዝቡ ጋር የሚደረገው ውይይት በዋናነት ንቅናቄው የፖለቲካ አስተሳሰብ መሰረቱን ለማፅናት አጋዥ እንደሚሆነው ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡
በእያንዳንዱ የስብሰባ መድረክ ላይ በሺዎች እየተገኙና አዳራሾች እየሞሉ ስብሰባዎች ወደ አደባባይ የተቀየሩበት አጋጣሚ እንዳለ የጠቀሱት አቶ ክርስቲያን፤ ከዚህ የምንረዳው ህዝቡ ምን ያህል ተደራጅቶ ለመታገል የተዘጋጀ መሆኑን ነው ብለዋል፡፡
“ንቅናቄውንም የራሱ አድርጎ መውሰዱን ተገንዝበናል፤ ይህም በቀጣይ በትልቅ የኃላፊነት ስሜት እንድንቀሳቀስ ያሳስበናል፤ ከህዝቡ ትልቅ አደራ ነው እየተቀበልን ያለነው” ይላሉ - አቶ ክርስቲያን፡፡
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ በቀጣይ በአማራ ክልልና በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች ጽ/ቤቶችን እንደሚከፍት አስታውቋል፡፡ ንቅናቄው የአማራ ብሔርን መብትና ነፃነት ለማስከበር፣ ጭቆናና በደሉንም ለመዋጋት አልሞ የተቋቋመ መሆኑ ይታወቃል፡፡ 

Read 5730 times