Saturday, 11 August 2018 11:01

“አየር ወደ ዶላር ተመነዘረ!”

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(2 votes)

 “ሁለቴ ካርቦን ሸጠን 71 ሺ ዶላር አግኝተናል”
                  በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወላይታ ዞን ዳሞት ተራራ፣ ኮካቴ ማራጨሬ ቀበሌ ውስጥ እገኛለሁ። ሥፍራው ከ10 ዓመት በፊት ከፍተኛ ረሃብና ድርቅ ያጠቃው በአየር ንብረት ለውጡ በእጅጉ የተጎዳ ነበር፡፡
ዳሞት ተራራውን ዙሪያውን ከበው የከተሙትና ኑሮአቸውን የመሰረቱት የአካባቢው አርሶ አደሮች፤ ከበላያቸው ቆሞ ለም መሬታቸውን እያጠበ ወስዶ፣ እነሱን ለድርቅና ረሃብ በመዳረግ፣ እጃቸውን ለእርዳታ እንዲዘረጉ ማድረጉ ሳያንስ ለጎርፍና ለንፋስ አደጋ አጋልጦአቸው የኖረውን ተራራ ሽቅብ እያዩ ዓመታትን አሳልፈዋል። ነዋሪዎቹ በየጊዜው ከሚከሰተው የጎርፍና የናዳ አደጋ እንዲጠብቃቸው ፈጣሪያቸውን ከመለማመን ውጪ ምንም ነገር ማድረግ ሳይችሉ ዓመታት ነጉደዋል፡፡
የዛሬ 10 ዓመት ግድም እንዲህ በክረምቱ ወራት ላይ በስፍራው የተከሰተው የጎርፍና የናዳ አደጋ ግን ለአካባቢው ነዋሪዎች ትልቅ የማንቂያ ደወል ነበር፡፡ በወቅቱ ምሽት ላይ መጣል የጀመረው ዝናብ ሃይልና መጠኑን ጨምሮ፣ ሌሊቱንም ሲዘንብ አደረ፡፡ ከምሽት እስከ ንጋት ያወረደው ዝናብ ያስከተለው ጎርፍና ናዳ፣ ተራራውን ተገን አድርገው የሚኖሩትን ስድስትና ሰባት የቤተሰብ አባላት ያሏቸው የሶስት አባወራ ቤቶች ከእነሙሉ ንብረቶቻቸው ጠራርጎ ወሰደ፡፡ ይህ አስከፊ አደጋ የአካባቢን ነዋሪ ህዝብ በእጅጉ አስቆጣ፡፡ በተራራው መራቆት ሣቢያ በየጊዜው የሚያጋጥማቸውን የተፈጥሮ አደጋዎች እያማረሩ ለዓመታት በዝምታ የኖሩት የኮካቴ መንደር ነዋሪዎች፣ ልጅ አዋቂ ሳይሉ ለስራ በእልህ ተነሱ። ህብረተሰቡ አካባቢን ለመለወጥ የሚያደርገውን ትግል ለማገዝ ደግሞ “ወርልድቪዥን” የተባለ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ግንባር ቀደም ሆኖ ተሰለፈ፡፡
በ1992 ዓ.ም በአካባቢው ተከስቶ በነበው የድርቅና የረሃብ አደጋ ሣቢያ ለከፍተኛ ችግር የተጋለጡ የአካባቢውን ነዋሪዎች ለመታደግ ወደ ስፍራው ገብቶ የነበረው ይኸው ድርጅት፤ በአስቸኳይ የምግብ እርዳታ፣ በጤና፣ በንፁህ ውሃና በትምህርት ላይ ትኩረቱን አድርጎ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፡፡
ተራራውን ደን በማልበስ የሚመጣበትን ተፈጥሮአዊ አደጋ ለመከተር የተነሳው የኮካቴ ቀበሌ ህዝብ፤ በወርልድቪዥን በሚደረግለት እርዳታ እየታገዘ ተራራውን ደን የማልበሱን ሥራ ተያያዘው፡፡ የወገኖቹ ሞት በቁጣ ቀስቅሶት ለለውጥ የተነሳው የአካባቢው ነዋሪ፤ ተራራን በአረንጓዴ ጥቃጥቅ ደን ለመሙላት የፈጀበት ጊዜ ከባድ ችግርና መከራ ካሳለፈበት ጊዜ አንፃር በእጅጉ አነስተኛ ነበር፡፡ ደኑ በአየር ንብረቱ ለውጥ ሣቢያ ጠፍተው ከነበሩት 35 ምንጮች መካከል አሥራ ሶስቱን ወደ ህይወት መልሶ አካባቢውን እጅግ በሚያስገርም ውበት ለመሙላትና ቦታውን ዓለምን ወዳስደነቀና ምሁራንን ለምርምር ወደሚያመላልስ ልዩ ስፍራ ለመቀየር የወሰደበት ጥቂት ዓመታትን ብቻ ነበር፡፡ አገር በቀል በሆኑ ዛፎፍ፣ ለመድሃኒትነት በሚውሉ የተለያዩ የዕፅዋት አይነቶች የተጠቀጠቀው ደን፤ መኖሪያ አጥተው ከአካባቢው ሸሽተው ለነበሩ የዱር እንስሳትም መጠለያ ሆነ፡፡ ተፈጥሮም ፊቷን ወደ ስፍራው መለሰች፡፡ አካባቢውም የበርካቶችን ዓይንና ልብ መሳብ ጀመረ፡፡
ንፁህ ተፈጥሮአዊ አየሩ፣ እንደ በረዶ የቀዘቀዘው ንፁህ የምንጭ ውሃው… ሥፍራውን ይበልጥ ተወዳጅ አደረገው፡፡
ቀድሞ በወባ፣ በእንቅርትና በሌሎችም በሽታዎች አዘውትሮ ይጠቃ የነበረው የአካባቢው ነዋሪ፤ ጤናው እየተመለሰ መጣ፡፡ ከዚህ በኋላ ነበር ወርልድቪዥን በአካባቢው የሚመነጨውን ካርቦን ለገበያ በማቅረብ ለአካባቢው ህዝብ ገቢ የሚያስገኝ ተግባር ለመከወን የተነሳው። ድርጅቱ ባከናወነው የገበያ ማፈላለግ ሥራ፤ አንድ ቶን ካርቦን በአራት ዶላር ሂሳብ ለመግዛት ወርልድ ባንክ ለአስር ዓመት ውል ገብቶ ግዥውን ጀመረ። እስከ አሁን ድረስ ለሁለት ጊዜያት ያህል ግዥ የተፈፀመበትን 71 ሺ ዶላር የአካባቢው አርሶአደሮች በማህበራቸው በኩል ተቀብለዋል፡፡ የሶስተኛ ዙር ሽያጭም ተከናውኖ፣ በአሁኑ ወቅት አርሶ አደሮቹ የሽያጭን ገቢ በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ፡፡
የወላይታ ዞን ኮካቴ ዳሞት ደን ባንክ፣ አግሮ ፎረስተሪ ማህበር ስብሳቢ የሆኑት አቶ በረታ ባሣ የካርቦን ሽያጩን በተመለከተ ተጠይቀው “ራሳችንን ከጎርፍና ከንፋስ አደጋ ለመከላከል የተከልነው ደን እንኳን ደኑ አየሩ ዶላር ሆኖ፣ በየጊዜው የካርቦን ሽያጭ ገቢ እየተባለ ይሰጠናል። ደናችን ያለው በእጃችን፣ ተቆርጦ የሚወስድ የሚጠፋ ነገር የለንም፤ ግን ምኑ ተሸጦ ገንዘብ እንደሚያስገኝልን አያገባንም፡፡ አየር ወደ ዶላር ይቀየራል እንዴ?… ሳይንስና ጊዜ አያመጡት ነገር የለም፡፡” ብለዋል፡፡
ወርልድቪዥን በዚህ ሥፍራ የነበረውን የፕሮጀክት ጊዜ በማጠናቀቁ፣ አካባቢውን ለነዋሪው አስረክቦ የወጣ ቢሆንም የካርቦን ሽያጭ ገበያ የማፈላለጉን ሥራ ግን አሁንም በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ ምክንያቱም ገበያ የማፈላለግ ተግባር ከፍተኛ ጥረትን የሚጠይቅና በአለም አቀፍ ደረጃ የሚከናወን ነው፡፡ ይህንን ኃላፊነት የሚቀበል አካል እስከሚገኝም ድረስ በዚህ ሥራ ላይ እንደሚቆይ በድርጅቱ የሶደና ኡምቦ ካርቦን ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ተስፋሁን ኢዩኤል ነግረውናል፡፡ ይህንን በድርጅቱ የሚደረገውን ድጋፍ ለማገዝና ህብረተሰቡ ቀጣይነት ያለው ተፈጥሮን ተንከባክቦ በማቆየት ከተፈጥሮአዊ ደን የሚገኘውን ገቢ የማሣደጉን ተግባር እንዲቀጥልበት በማድረጉ ረገድ በመንግስት በኩል ምን እየተደረገ ነው ስንል የወላይታ ዞን አካባቢ ጥበቃና ደን ልማት ፅ/ቤት ተወካይ አቶ ብርሃኑ ጩማን ጠይቀን በሰጡን መልስ፤
“ሥፍራው ቀደም ሲል በድርቅና የረሃብ አደጋዎች በተደጋጋሚ ሲጠቃ የኖረ ሲሆን ከ10 ዓመታት ወዲህ አካባቢው ተቀይሮ እንኳንስ ደኑ አየሩ በዶላር የሚመነዘር መሆኑ አስደስቶናል፤ ይህንን በወርልድቪዥን የተጀመረውን ተግባር በማስቀጠል አካባቢውም ሆነ አገሪቱ ከካርቦን ሽያጭ ይበልጥ ተጠቃሚ የምትሆንበትን መንገድ ለመፈለግ እየሰራን ነው” ብለዋል፡፡ ይህንን ተሞክሮም በሌሎቹ የክልሉ አካባቢዎች ለማስፋትና ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ጥረት እናደርጋለን” ብለዋል፡፡
ወደፊትስ ዕቅዳችሁ ምንድነው ስል የአካባቢውን የህብረት ስራ ማህበር ሰብሰቢ አቶ በራታ ካሣን ጠየቅኋቸው “ሥፍራውን የቱሪዝም መዳረሻ በማድረግ፣ ቱሪስቶች ወደ አካባቢው  እየመጡ እንዲዝናኑ ለማድረግና የአካባቢው አርሶ አደርም ገቢውን ለማሳደግ፣ ክልላችንንም ይበልጥ ለማስተዋወቅ እቅድ አለን፡፡ ይህንን ዕቅዳችንን ተግባራዊ ለማድረግም የጀመርናቸው ሥራዎች አሉ፡፡
ወደ ተራራው የሚያወጣ መንገድ በበቂ ሁኔታ አለመኖሩ፣ ዕቅዳችንን ተግባራዊ ለማድረግ እንዳንችል እንቅፋት ፈጥሮብናል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የሚመለከተው መንግስታዊ አካል ትኩረት ሰጥቶ ሁኔታዎን ቢያመቻችልን ሥፍራው በቅርብ ጊዜ ውስጥ የቱሪስት መዳረሻ በመሆን ለአገሪቱም ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ ለማስገኘት የሚችል እንደሆነ እምነታችን ነው” ሲሉ አስረድተዋል፡፡

Read 2737 times