Print this page
Saturday, 11 August 2018 10:57

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(4 votes)


            “ሰው ራሱ ሃሳብ ነው፤ ሃሳብ ከሌለ ሰው የለም”
              

    አማላጅ ሁኚልኝ
በምሽቱ ሰማይ
በህዋው ወለል ላይ፣
ጨረቃ ፈርሻ
ከዋክብት ሲደምቁ፣
ሰማየ ሰማያት
በቀን ሞት ሲስቁ፣
ንገሪያት ለነፍሴ
“ጥያቄ” ነው ብለሽ
እንድትሆነኝ መልሴ!!
አንድ ወይዘሮ ባለቤታቸው በሞት ሲለዩአቸው፣ ባህሪያቸው ተቀየረ፡፡ ፀሃይ ነው፣ ዝናብ ነው ሳይሉ በየቀኑ ወደ ሰውየው መቃብር እየሄዱ፤ “እባክህ ጥራኝ፣ እባክህ ውሰደኝ፣ አምላኬ ስለምን ዝም ትለኛለህ?” እያሉ ማልቀስ ሆነ ሥራቸው፡፡ ጎረቤት ቢመክራቸው፣ ልጆቻቸው ቢያባብሏቸው አሻፈረኝ አሉ፡፡…አንድ ቀን እንደ ወትሯቸው ከሃውልቱ ላይ ተደፍተው ሲያማርሩ…
“እገሊት” የሚል ድምፅ ሰሙ፡፡ ስማቸው ነው። የሚያውቃቸው ሰው የጠራቸው መስሏቸው ቀና አሉ።…ማንም አልነበረም፡፡ ወዲያ ወዲህ ቢገላመጡም…. ኮሽ አላለም፡፡ ሁለት ሶስቴ አማትበው ወደ ለቅሷቸው ሲመለሱ፣ ስማቸው እንደገና ተጠራ፡፡… ደንግጠው ብድግ አሉ፡፡…አሁንም ምንም ነገር የለም፡፡
“ትሰሚኛለሽ እገሊት?” አለ ድምፁ እንደገና። ጉልበታቸው ተብረከረከ፡፡ ሃውልቱን ተደግፈው ቁጭ አሉ፡፡….ራሳቸውን እንደ መሳት አደረጋቸው። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ነፍሳቸው ስትመለስ፤ የት እንዳሉ አስታውሰው ብድግ ለማለት ሲሞክሩ….
“ፀሎትሽን ሰምቻለሁ፤ ነገ ስትመጪ እወስድሻለሁ” አለ ድምፁ፡፡ ሴትየዋ ከዚያ በኋላ የሆነውን ፈፅሞ አያስታውሱም፡፡ በደመ ነፍስ እየሮጡ ቤታቸው ደርሰው…አልጋቸው ላይ ወደቁ፡፡…
* * *
ወዳጄ፡- ሰው በራሱ ጥያቄ ነው፡፡… እያወቀ ሲሄድ ደግሞ መልስ ይሆናል፡፡ ባለበት የሚረግጥ ከሆነ ግን መልሱን ሌሎች እንዲነግሩት ይፈልጋል። … ያኔ… የሃሳብ መስጫ ሳጥን ይሆናል፡፡
ሃሳባውያን ሊቃውንት… “ከሃሳብና አእምሮ ሌላ ምንም ነገር የለም፤… እግዜር እራሱን ጨምሮ። …ውጫዊ ዓለም የምንለው ሃሳባችንን አእምሯችን ውስጥ ስለምንመለከት ነው” ይላሉ። ለምሳሌ፡- ጨለማ ቤት ውስጥ ሻማ ብናበራ፣ በውስጡ ያሉትን ነገሮች እናያለን፡፡ ሻማውን አጥፍተን ብንሄድም፣ ያየናቸው ዕቃዎች በአእምሯችን ውስጥ ይቀራሉ፡፡ ቤቱ ውስጥ ዕቃ ባይኖር እንኳን የሻማውን ብርሃን እናስታውሳለን። ብርሃን ጨለማ ውስጥ ካልሆነ ብቻውን የሚታይበት ቅርፅ የለውም፡፡ አእምሯችን ውስጥ ግን ይቻላል፡፡… ተረት ስናወራና ታሪክ ስንተርክ፣ በተረታችን ወይም በታሪካችን ውስጥ ያሉትን ነገሮች የሚያዳምጡን ሰዎች አያይዋቸውም፡፡ በአእምሯቸው ግን ይስሏቸዋል (image form ያደርጋሉ)… ጆርጅ ቢሾፕ በርክሌይ፤ “ሰው እራሱ ሃሳብ ነው፣ ሃሳብ ከሌለ ሰው የለም…. To be is to be Perceived” በማለት ይገልፀዋል፡፡… የዴስካርተስ ሃልዮት እንዳለ ሆኖ!!
ከዚህ በተለየ መንገድ ደግሞ (materialistic theory) … “ሃሳብ የውጪ ዓለም ነፀብራቅ እንጂ ምንም ሊሆን አይችልም፡፡ የሚታይና የሚዳሰስ ነገር ከሌለ ሃሳብ የለም፡፡ መኖር ከሃሳብ ይቀድማል።… ለምሳሌ፡- ህፃናት ከዜሮ (tabula rasa) ጀምረው ከሚያዩት፣ ከሚሰሙትና ከሚማሩት ነገር ነው የሚሰሩት፡፡ ዋናው የሃሳብ አዋላጅ ልምድ ነው” ባዮች ናቸው፡፡ በሁለቱም በኩል ያለው ሃሳብ ወደ ጥያቄ ሲቀየር፡- ሰው ሀሳብን ይፈጥራል? ወይስ ሃሳብ ሰውየውን ይፈጥራል?... ወደ ሚለው ያመጣናል፡፡
ወዳጄ፡- ከሳይንስና ከጥበብ መወለድ በፊት ሰው ነበር፡፡ ያኔም ጥያቄዎች ነበሩ፡፡ የጊዜው ሰው መልሶቹ የት እንዳሉ ስላልገባው፣ የሚመልሱለት የመሰለውን አማልክት ፈጠረ፡፡ ለፍቅር- የፍቅር አምላክ፣ ለጦርነት- የጦርነት አምላክ፣ ለጥበብ- የጥበብ አምላክ፣ ለጤና፣ ለምግብ፣ ለጎርፍ፣ ለነፋስ፣ ለእሳት…ለሌሎች ነገሮች ሁሉ፡፡…ጊዜ ሲለወጥ፣ የነቃ ትውልድ ሲፈጠር፣ ዕውቀት ሲዳብር አማልክቶቹ ተፈረካከሱ፡፡ እሩቅ ያሉና የማይደረስባቸው የሚመስሉት ተደፈሩ፡፡… ከሚቲዮሎጂ ወደ አስትሮሎጂ፤ ከአልኬሚ ወደ ፊዚዮግኖሚ… እያሉ እያሉ ቲዎሎጂ ጋ ደረሱ። ጉስታቭ ሌቦን እንደሚለው፤ አለማመን በራሱ እምነት ሆነ። ድንቁርና ቦታውን ለሳይንስ፣ ለጥበብና ለፍልስፍና እየለቀቀ መጣ፡፡ ፕላኔቶችን መጎብኘት፣ ውቅያኖስን ማቋረጥ፣ ተራራውን መናድ፣ በውሃ ውስጥና በጠረፍ ላይ መኖር ተቻለ። የኮምፒዩተር ጥበብ ተፈለሰፈ። ዓለማችንን ለቴክኖሎጂ የዳሯት የሰለጠኑ ሰዎች የበቀሉት በነፃነት ማሰብ፣ በነፃነት ሃሳብን መግለፅና መፃፍ ስለተቻለ ነው፡፡ ድሃና ጎታታ አገሮች ዳዴ እያሉ የሚንገታገቱት፣ የነፃነት ትርጉም ባልገባቸው ኋላ ቀርና ደንቆሮ ባለስልጣኖች ስለሚመሩ ነው፡፡
ዘመናዊ ፍልስፍናም ከላይ ላነሳናቸው ጥያቄዎች መልስ እየሰጠ ነው፡፡ በዚህ ዘመን ሃሳብ፣ አእምሮና ሰው አንድና አንድ ነገር ብቻ መሆናቸው የተረጋገጠ ይመስላል፡፡ እንደ ምሳሌ፡- አንድ ሳንቲም ሁለት ገፆች አሉት፡፡ የትኛው ፊት የትኛው ጀርባ መሆኑ አይታወቅም፡፡ ሁለቱም የታተሙበት መደብ ደግሞ ከመሃል አለ፡፡… ሰው መደብ ነው፡፡ ሀሳብና አእምሮ ደግሞ አንዱ ከሌላው የማይለይ ገፅታዎቹ ናቸው፡፡ እዚህ ጋ ማቴሪያሊስቶቹና ሃሳባውያኑ ይጨባበጣሉ!!... ሁላችንም የጥያቄዎቹ መልስ ነን እያሉ!!
ወደ ጨዋታችን እንመለስ፡- ሴትየዋ ቤታቸው እንደደረሱ አልጋቸው ላይ ወደቁ ብለናል፡፡ በማግሥቱም አልተነሱም፡፡ ከጥቂት ቀናት በኋላ አገገሙ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ቤተ ክርስቲያን ግቢ ድርሽ ብለው አያውቁም፡፡ … ዕድርተኛ ለመቅበር እንኳን፡፡ የባለቤታቸውን ፎቶግራፍ “ያቃዠኛል” በሚል ሰበብ ከግድግዳው ላይ አስወርደዋል፡፡ በአጋጣሚ የሞት ወሬ ከተነሳ የሚገቡበት ይጨንቃቸዋል፡፡ ሚስጥራቸውን ማንም የሚያውቅ አይመስላቸውም፡፡ በውጭ አገር የሚኖሩት ሁለት ልጆቻቸው፣ እዚህ ካሉ ጓደኞቻቸው ጋር ተማክረው፣ በሪሞት ኮንትሮል በሚሰራ ስፒከር፣ እንግዳ በሆነ ፍጡር ድምጽ ተመስለው እንዳስደነገጧቸውና ከአጉል ልማድና ለቅሷቸው እንደገላገሏቸው አያውቁም፡፡
ወዳጄ፡- በሴትየዋ ጭንቅላት ውስጥ የተፈጠረው ሃሳብ ወይም ስዕል የሃሳባውያኑን ወይስ የማቴሪያሊስቶቹን አስተሳሰብ ሚዛን የሚረግጥ ይመስልሃል?
* * *
አንድ የመጨረሻ ጥያቄ፡- ከ ‹ሠላም› በኋላ ምን አለ?
ሠላም!!!

Read 1608 times