Saturday, 11 August 2018 10:53

የይቅርታ አቀበት! (ምናባዊ ወግ)

Written by  አብይ ተስፋዬ አሳልፍ
Rate this item
(2 votes)

ከፍቅረኛዬ ከመክሊት ጋር ከተለያየን ወራት ተቆጠሩ፡፡ በእርግጥ ጥፋቱ የእርሷ ቢሆንም ምሽጓ ገብታ አድብታለች (ይቅርታ ሳይጠይቀኝ ብላ መሆን አለበት!)፡፡ የሴትነት ኩራት መሆኑ ነው፡፡ እኔም ኩራቴን ትቼ ይቅር በይኝ ማለት አልቻልኩም፡፡ እሰጋለሁ፤ዛሬ ላልፈጸምኩት ጥፋት ይቅርታ ብጠይቃት፣ ነገም እንዲሁ ይቀጥላል እያልኩ፡፡ (ዝንት ዓለም እኔ ይቅርታ እየጠየቅሁ መኖር አልችልም!) እናም የብቸኝነት መንገዱ የእሾህና የጨርቅ መንገድ ሆኖብኛል! አንዳንዴ በህይወት ጎዳና እየተጓዝኩ መሆኑን እረሳለሁ (በጨርቅ ላይ ስሆን!)፣ አንዳንዴ ደግሞ ሲደብተኝ እሰቃያለሁ (በእሾህ ላይ እየተራመድኩ መሆኑ ነው!)፡፡
የሰው ልጅ በህጻንነቱ የተሰራበትን ፈዛዛ መስመሮች (ስኬችስ!) በአዋቂነቱ ዘመን እያደመቀ የሚኖር መሆኑን የተረዳሁት በነዚህ የብቸኝነት ወቅቶች ነበር (በእሾህ ላይ ስራመድ!)፡፡ ደብሮኝ ከስራ እንደወጣሁ፣ ከአንዲት ካፌ ቁጭ ብዬ የቴዲን ዘፈን እየሰማሁ በራሴ እገረማለሁ። የማይቀየር ሀውልት የሆነ ጠባይ እንቅፋት ሆኖብኛል! (ሃውልት እንኳ ይፈርሳል፣ የኔ አመል ግን አብሮኝ ወደ መሬት የሚወርድ ይመስለኛል፡፡ ልተወው አልተቻለኝም፡፡)
‹‹….መማፀኔ ማሪኝ ማለቴ
ለኔም ሳይገባኝ ነው ጥፋቴ …›› (እያለ ዘፋኙ ያለ ጥፋቱ ይቅርታ እየጠየቀ ይለማመጣል!)
ሰው ለፍቅር ሲል ባያጠፋ እንኳ ይቅርታ ይጠይቃል፡፡ እኔ ግን በፍቅረኝነት መስመራችን ላይ በቀይ የሰረዝኩበትና የደለዝኩበት ቦታ ስለጠፋብኝ ይቅርታ ማለት (ወይም መጠየቅ!) እንኳ አልችልም፡፡ በህጻንነቴ ሴት አያቴ እያቀፈች ስታባብለኝ አደግሁና ሴት ጓደኞቼ ሁሉ እያቀፉ እንዲያባብሉኝ የምፈልግ ሰው ሆኜ ቀረሁ፡፡ እናም ይህ የሚገባት (‹‹ገ›› ላልቶ ይነበባል) ሔዋን ስላላጋጠመችኝ (ይቅርታ የምትጠይቅና አቅፋ የምታባብል ሔዋን!) ተስፋዬ የበጋ ደመና ይመስል ብን ብሎ ይጠፋል፡፡ እኔ አፍ አውጥቼ መማፀን ባይሆንልኝም፤ ልቤ መፍትሔው እንዲያ ነው እያለ ይመክረኛል፡፡ (ዘፋኙም እንዲያ እያለኝ ነው!)
ከካፌው ጥግ ላይ ያሉትን ወጣት ጥንዶች አፍጥጬ አስተውላለሁ፡፡ ልጅቱ ፀጉሯን በልጁ ትከሻ ላይ በተን አድርጋ ተረጋግታለች፡፡ ያስቀናል። አሁንስ እኔም ደገፍ ብዬ የማለቅስበት ትከሻ ባገኘሁ ስል ተመኘሁ (እንደ ህጻንነቴ!)፡፡ በጠራው የካፌው የፊት ለፊት መስተዋት ውስጥ ወደ መንገዱ እያስተዋልኩ፣ ውስጤን አዳምጣለሁ፡፡ ዛሬ በተለየ ሁኔታ ማልቀስ ተመኘሁ፡፡
ከአያቴ ትምህርቶች አንዱ እንዲህ ነበር!
***
ታዳጊ እያለሁ (አራተኛ ክፍል!?) ለክረምት ዕረፍቴ ገጠር ሄጄ አያቶቼ ጋር ነበርኩ፡፡ ታዲያ አንድ ቀን ወንድ አያቴ ውጪ አገኘኝና ጮኸብኝ። እናም ወደ ቤት ገብቼ ኩፍ ብዬ ከመደብ ላይ ተቀመጥኩ። ከህጻንነቴ ጀምሮ አኩራፊ ነኝ መሰለኝ፣ ከንፈሬን አንጠልጥዬ መቀመጥ አበዛለሁ፡፡ እንዲያ ስሆን ደግሞ የምታውቅልኝና የምታባብለኝ ሴት አያቴ ብቻ ናት፡፡ የወለደችኝ እናቴ እንኳን ሳናድዳት ‹ሒድ አያትህ ታንቆሻብልህ!› ትለኛለች! (መክሊትማ ምን ትለኝ!?)  
እማመይ (ሴት አያቴ!) የወተት እንስራዋን እያወዛወዘች (እየናጠች!)፣በፈገግታ አንገቷን መለስ አድርጋ አየችኝና፤ ‹‹ … ጌታ! ዛሬ ደግሞ መጥቶብሃል መሰለኝ ለንቦጭህን ጥለሃል!›› አለች። ጥብቆዬን ወገቤ ላይ እየጎተትኩ ዝም አልኩ፡፡ ከአጭር ቁምጣዬ ስር አሸሾ መስለው የተዘረጉ እግሮቼ ይበሉኝ ስለነበር፤ ቆሻሻ በሞላባቸው ጥፍሮቼ እየፈተግሁ ዝም አልኳት። (ትናገረኝ፣ ይረዳዱ ግድ የለም! ሁለተኛ እዚህ ገጠር አልመጣም ስል አስባለሁ፡፡)
‹‹ማኩረፍ ጥሩ አይደለም’ኮ፡፡ የተበደልከውን መናገር መልመድ አለብህ፣ አለበለዚያ ሁሉን በሆድህ እያደረግህ እንደተዳፈነ እሳትና እንደ ገጠር ቤት ጭሱን እያጫጫስክ መኖር የለብህም። ደግሞ አያትህ የሚመክሩህን መስማት አለብህ፡፡ ስንት ጊዜ እንዲያ እያልኩ አልመከርኩህም ወይ ጌታ?!››  
‹‹ነግረሽኛል!›› እልህ ይይዘኛል፡፡ ጉሮሮዬ ላይ ይታገለኛል፡፡
‹‹ደግሞ አትነፋነፍ፡፡ በአፍንጫህ አትናገር፡፡›› … በፈገግታ ፊቷን አስውባ ወተቷን ትንጣለች፡፡
‹‹…ተባብራችሁ ልትገሉኝ ነው እንዴ!? በቃ እሄድላችኋለሁ፡፡ የናንተ ገጠር ብርቅ መሰላችሁ። ወደ ቤቴ እሄዳለሁ ሁለተኛ አልመጣም፡፡ እህህህህ…›› … እንባዬ ዱብ ዱብ እያለ ማልቀስ እጀምራለሁ፡፡ መንታ መንታ እየሆነና በነጫጭባ ፊቴ ላይ እያቋረጠ ቁልቁል ይንፎለፎላል፡፡  
ከተቀመጠችበት ተስፈንጥራ መጥታ ታቅፈኝና፤ ‹‹አይዞህ የኔ ባሪያ፤ አይዞህ ጌታዬ፤ አይ አመል ከየት እንዳመጣሃው እኮ!››
‹‹ለምንድነው ባሪያ የምትይኝ ደሞ፡፡ እህህሀ…››
‹‹ስለምወድህ ነዋ ጌታ! የምትወደውን ሰው ቆራጣም፣ ቆማጣም ብትለው ፍቅር ነው! የጠላኸውን ሰው ደግሞ የኔ ሸሞንሟና ብትለውም ስድብ ነው። አይደለም’ንዴ ጌታ!? ይህንን ማወቅ አለብህ’ኮ!›› እንባዬን ከፊቴ ላይ ጥርግርግ አድርጋ ትስመኛለች፡፡ ‹‹…ደግሞ እንዲህ ነጭ የምትሆነው ምንድነው! ጭቃ ውስጥ ነበርክ እንዴ!? ወይ አንተ ልጅ፤ በል ታጠብ አሁን ሲመጡ ከአባትህ ጋር አስታርቅሀለው፡፡ እኔ እቆጣልሃለው፡፡ አይዞህ የኔ ባሪያ…››  
‹‹…ባሪያ አትበይኝ! እማመይ!…››
እየሳቀች  ‹‹ሆሆይ! … እሺ የኔ ጌታ! ይገርማል’ኮ። እንዲያው አንተን የመሰለ ልጄን ባሪያ እላለሁ!?››
ህክምናዎቼ እነዚህ ቃላት ነበሩ! አባባይ በዚያ በኩል በኩርኩም እየገጨ፣ በሆነ ባልሆነው እየተቆጣና እየመከረ ሁለት ወር መከራዬን ሲያሳየኝ መጥቼ የማለቃቅስባት እማመይ ናት፡፡ አቅፋ የምታባብለኝና ተቆጪዬን የምትቆጣልኝ! ማረፊያዬና መተከዢያዬ! (እና አሁን ጎርምሼ ሳጤነው ሴት ጓደኛዬ እንዲያ እንድትሆንልኝ ነበር ዋናው ምኞቴ - ከንቱ ምኞት!)
ቀጥሎ አባበይ ሲገባ፣ እንደተቃቀፍን ያገኘናል። ከዚያም ፈገግ ብሎ፤ ‹‹…ስንት ስራ እያለ እናትና ልጅ ተቃቅፋችሁ ቁጭ ብላችኋል፡፡ እኔ ደግሞ ይሄ ወስላታ የት ገባ ብዬ፡፡ ጌታመሳይ ተነስና ሸማዬን አምጣልኝ፡፡ ከበረቱ አጠገብ ጥዬው መጣሁ፡፡ ደግሞ ያ የነጋሲ ውሻ እንዳይነክስህ ተጠንቅቀህ ሂድ!…››
ፈንጠር ብዬ ስነሳ (አኩርፌ እምቢ ማለት አልችልም!) እማመይ እጄን እንደያዘች ጎትታ ታስቀምጠኝና፤ ‹‹…ይበሉ፤ መጀመሪያ ልጄን ይቅርታ ይጠይቁት፡፡ ምን አድርገው ነው ያስቀየሙብኝ። ጭራሽ አማርረው ክረምቱን እንኳ ሊያስቀሩብኝ ነው’ንዴ!? አበዙት አንቱ ሰውዬ። ሁለተኛ ልጄን እንዳይናገሩብኝ፡፡ ተማርሮ አልመጣም ቢል ከእኔ ነው የሚጣሉት፡፡ ውርድ ከራሴ የጌታ አባት!...››
በደስታ የምትሞቅ ልቤ ከደረቴ ስር ትንፈራፈራለች። (እሰይ እላለሁ በልቤ!) እና ወደ ደረቷ አጥብቃ ትይዘኛለች፡፡ በእድሜ ብዛት የተጨማደዱ ቆዳዎቿ ይመቹኛል፡፡ እቅፏ ይሞቀኛል፡፡ ጭስ ጭስ የሚለው ቀሚሷ እንደ በፍታ ክሳድ በላዬ ላይ ይከደናል። እምባዬን እረሳና ደስታዬ ከፍ ከፍ ይላል፡፡
አባበይ ፊቱ በደስታ እንደሞላ ጥቂት ቆም ብሎ ያተኩርብናል፤ ከዚያም በፈገግታ ጉንጩን ግራና ቀኝ እየለጠጠ ‹‹…ጥሩ ነው! እናትና ልጅ ተባበሩ፡፡ ደግ ነው። የተቆጣሁት ቅድም ካፊያው እያካፋ እያለ፣ ከውሃው መውረጃ ቦይ ውስጥ በቆሻሻ ሲንቦራጨቅ አግኝቼው ነው፡፡ እና ሁለተኛ እንዳይደገም ነበር ያልኩት። የማይመቱት ልጃችን በቁጣ ማልቀስ ጀመረ! እሰይ ይሁን ጌትዬ ይቅር በለኝ! ባላጠፉት ጥፋትም ይቅር በሉኝ ማለት ደግ ነው! ሁለተኛ ግን እንዳትደግመው። እንዲያ ስታደርግ ባገኝህ አልቆጣህም፣ እንዲያውም ሾጥ ነው የማደርግህ! በል አሁን ይቅር በለኝ!...›› (ከአንገቱ ጎንበስ ይላል!)
‹‹…ይቅርታ አድርግላቸው በል! ሁለተኛ አንተም እንዲያ እንዳታደርግ፣ እሺ በል!››
‹‹…እሺ!››
አባበይ ቀና ብሎ ‹‹…ጎበዝ የኔ ልጅ! በል አሁን ቶሎ ሸማዬን አምጣ! መጀመሪያ ና ሳመኝ!›› እየተንደረደርኩ ስሔድ እቅፍ አድርጎ ይስመኝና እንዲህ ይለኛል፡፡ (ይህቺን አረፍተ ነገር ሁልጊዜም አስታውሳታለሁ!)
‹‹…ጌታመሳይ! በዚህ ዓለም ከሰዎች ጋር ስንኖር የሚያግባቡንና እዝነትን የሚለግሱን፣ በተለየ ሁኔታ በጣም አስፈላጊያችን እነዚህ ናቸው፡፡ (ደረቱን እየነካካና ትከሻውን እየደበደበ) ለምን እንደሆነ ታውቃለህ!?››  
‹‹…ትከሻ፤ ጭንቅላትንና አንገትን ተሸክሞ ስለሚቆም ይሆናል፣ ደረቱን ግን እንጃ!›› … ሃዘኔን ረስቼ  ወሬዬን እቀጥላለሁ፡፡
‹‹…አይደለም፣ ትከሻ በችግርና በእንባ ግዜ የሚያገለግለው ለራሱ አካል ብቻ ሳይሆን ለሌላም ስለሆነ ነው፡፡ ሌሎች ደገፍ ብለው እንባቸውን የሚያወርዱበትና የሚደገፉት ነው፡፡ ትከሻ የደካሞችና ልባቸው የተሰበረ ሰዎች ማረፊያ ነው፡፡ ትከሻ የሃዘንተኞች መተንፈሻ ነው፡፡ ይህቺ ከደረትህ ስር የምትገኘው ልብ ደግሞ የይቅርታ መስኮት ናት፡፡ ቤትህ እንዳይጨልም ስትፈልግ መስኮትህ ክፍት መሆን አለበት፡፡ ስለዚህ ልብህ ለይቅርታ የተከፈተ ይሁን። ወደፊት ስታድግ በሀዘን ጊዜ ሰዎች ትከሻህን ደገፍ እንዲሉበት መስጠት አለብህ፡፡
ምክንያቱም ትከሻ ራስ ወዳድ ባለመሆኑ ለሌሎችም ማረፊያ ነው፡፡ ልብህ ደግሞ ሁልጊዜ ለይቅርታ መከፈት አለበት፣ ይቅር ማለትና ይቅርታ መጠየቅ መለማመድ አለብህ፡፡ እናትህ ሁልጊዜ እንደምታደርግልህ ማለት ነው፡፡ ገብቶሃል ጌታ!››
‹‹…ገብቶኛል አባበይ፡፡ ሰዎች ሲያለቅሱ አቅፈን ማባበል አለብን ማለት ነው! አይደል?!››
‹‹…ነው ጌትዬ ተባረክ፣ ማባበል ብቻ ሳይሆን ይቅርታ ሲጠይቁንም እሺ ማለት፣ እንዲሁም ሰላም ለልባችን ተስፋና ለህይወታችን ጥሩ መንገድ ስለሆነ ይቅርታ መጠየቅ መልመድ ጥሩ ነው። እደግ፡፡ በል ቶሎ ሸማውን አምጣ፡፡ ካፊያው ድጋሚ ሊጀምር ነው።››
እንደ ወስፈንጥር ወደ ውጪ እወነጨፋለሁ! ላኮረፍኩበት ይቅርታ ተጠይቂያለሁ፣ በሃዘን ሳነባ መደገፊያ ትከሻ አግኝቼያለሁ፡፡ እናም እድለኛ ነኝ።
ውጪው ብን ብን የሚል ካፊያ ማካፋት ጀምሯል፤ ለእኔ ግን ብሩህ ነው፡፡ ምክንያቱም በውስጤ ያለው ደስታ አካባቢዬን እያዳረሰው ስለሆነ፡፡ ደስታ ደግሞ ስታካፍለው ይባዛል! ስታመነጨው ይንፎለፎላል! ወደ ፊትህ ስታወጣው ወደ አካባቢህ ይሰራጫል!
***
አሁን ቁጭ ብዬ ሳስበው የልጅነት ስውር መስመሮቼ እንዲያ የተሰመሩ ናቸው፡፡ እነዚያን ጭረቶች እያደመቅሁ ነው የምኖረው፤ ግና የሚገርመኝ ሲከፋኝ ትከሻ የምሻ ሆኜ ሳለ ይቅርታ መጠየቅ (‹‹ጠ›› ጠብቆ ይነበባል) ግን አልለመድኩም፡፡ (ይቅርታ መጠየቅ እንዴት ሳልማር እንደቀረሁ ይገርመኛል!) ሆኖም በዚህች ሰከንድ እርግጠኛ ነኝ፣ ደገፍ ብዬ የማለቅስበት ትከሻ ያስፈልገኛል፡፡
ሙዚቃው ካለቀ ከሰዓታት በኋላ፣ ከተሰፋሁበት የካፌው ወንበር ላይ ተነስቼ ወደ ውጪ ወጣሁ፡፡ ሰማዩ ጠቋቁሯል፣ ካፊያ ብን ብን ይላል፡፡ ፊቴ ላይ ግን ፈገግታ ረብቦ ወደ ፊት ለፊቴ ገሰገስኩ፡፡
ከኋለኛው የአንጎሌ ክፍል የቅድሙ ስንኝ ተጣብቆብኛል፡፡ ከእነ ዜማው ያንጎራጉርብኛል፡፡ ቤቴ ገብቼ እንደተቀመጥኩ ይመጣብኛል፡፡ ምሳ እየበላሁ ይዘፍንብኛል፡፡ ማታ ተኝቼ፣ ጠዋት ስነቃም አንጎሌ ያንጎራጉራል፡፡
‹‹….መማፀኔ ማሪኝ ማለቴ
ለኔም ሳይገባኝ ነው ጥፋቴ…››
እናም በመጨረሻ፤ ከቀናት መናወዝ በኋላ፣ በድጋሚ ራሴ ይቅርታ ልጠይቃት ወሰንኩ፡፡
***
(መነሻ ሐሳብ ፡ -”What is the most important part of the body?”)

Read 1338 times