Saturday, 11 August 2018 10:56

ውሻው

Written by 
Rate this item
(13 votes)

 ሻምበል ባህሩ ገርበብ ብሎ በተከፈተው ፍሬንች ዶር አሻግረው ውጪውን እየተመለከቱ ቁዘማ ላይ ናቸው፡፡ ጥሪ መደበሪያቸው የነበረው ቴሌቪዥን ባይበላሽ ኖሮ፣ ይሄኔ እዚያ ላይ ነበር የሚጣዱት፡፡ ግን ከዚያ ከተረገመ መደበሪያ ማሽን ጋር ከተፋቱ ዓመት ሊሞላቸው ነው፡፡ ፊቱ ላይ ዳንቴሉን ጣል እንዳደረገ፣ እዚያው ኮመዲኖ ላይ ቦታውን እንደያዘ ነው፡፡ ቴሌቪዥኑም የተቀመጡበት ሶፋም የተገዙት ከስድስት ዓመት በፊት ነው፡፡ አንድያ ልጃቸው ብርቅነሽ አረብ አገር በሄደች በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በላከችው ገንዘብ ነው እነዚህ ነገሮች የተገዙት፡፡ ወለላቸውን ሊሾ ያደረጉትና ፍሬንች ዶር የገጠሙትም ያኔ ነው፡፡ (በድሆች መንደር ውስጥ እንደዚህ ዓይነት ለውጥ ከታየ፣ ወደ አረብ አገር የሄደች ልጅ መኖሩን የሚያመለክት ነገር ነው)፡፡
ቤታቸውን ቤት፣ ቤት ያሸተተችው ይህች ብርቄ አሁን የለችም፡፡ በአሰሪዋ ተገድላ አፈር ከተጨናት አራት ዓመት ከሦስት ወር ሆኗታል፡፡ ትሩፋቶቿ ብቻ ናቸው አሁን የቀሩት፡፡
ፀሐይዋ አቅሟን አበርትታ ስትጠጋው በራቸው ስር ተኝቶ የነበረው ውሻ ተነስቶ ሱክ ሱል እያለ ሲሄድ ሻምበል ባህሩ በዓይናቸው ሲከተሉ ቆዩና፤ “እኔ እኮ የዚህ ውሻ ነገር አንዳንዴ ግራ ያጋባኛል” አሉ፡፡ የንግግሩ መዳረሻ እጠባቧ ጓዳ ውስጥ እየተንጎዳጎዱ የነበሩትን ባለቤታቸውን ታሳቢ ያደረገ ነበር፡፡ ከወ/ሮ ባዩሽ ግን ምንም የተሰማ ነገር የለም፡፡
“የዚህ የቦቢ ነገር አንዳንዴ በጣም እኮ ነው የሚገርመኝ፤ ዝም ብዬ ሳየው ብዙ ነገሩ በግ እየመሰለኝ ነው፡፡” አሉና ቀጠሉ፡፡ ከአፍታ ዝምታ በኋላ፤ “ፀጉሩ ራሱ የበግ ለምድ እኮ ነው የሚመስለው፡፡” ከውስጥ በኩል ብቻ በጭቃ ወደተመረገው በር አልባ ኩሽና እያመራ ያለው ውሻ ላይ ነው አሁንም ዓይናቸው ያለው፡፡
“ጭራው ራሱ እኮ የቆላ በግ ላት ነው የሚመስለው፡፡” ሌላ ማመሳሰያ ተከተለ፡፡
“አሁንስ ይሄን ውሻ በግ አደረጉት እኮ!” አሉ ባላቸውን በአንቱታ የሚያወሩት ወ/ሮ ባዩሽ እዚያው ጓዳቸው ውስጥ እየተንጎዳጎዱ፡፡
“ምን! አይመስልም ልትይኝ ነው?” አሉ ባል ድምፃቸውን ዘለግ አድርገው፡፡ መልስ ግን አላገኙም፡፡ ውሻው ኩሽናው ውስጥ ገባና ተዘረጋ። እነ ሻምበል ባህሩ ከአራት ጎረቤቶቻቸው ጋር የሚጋሩት ኩሽና ነው፡፡ ለቦቢ ደግሞ ከከረረው የፀሐይ ቃጠሎ የሚሸሸግበት ሁነኛ ታዛው ነች፡፡
“ካልሽ እንደውም አጯጯሁ ራሱ ከሌሎቹ ውሾች የተለየ ነው፡፡ ምን! አይደለም ልትይኝ ነው!”
“አንድ ፊቱን እኮ በግ ነው ሊሉኝ ነው ምንም አልቀረዎት፡፡” አሉ ሚስት ረከቦትና ጀበና አንጠልጥለው ይዘው እየወጡ፡፡
“ቆይ ቢያንስ” አሉ ሻምበል ባህሩ፡፡ ሌላ ትንሽ ዝምታ ሆነ፡፡ “ኧረ’ዲያ!› አሉ ወደ ባለቤታቸው አዘምሞ የነበረውን አንገታቸውን ወደ ውሻው አቅጣጫ እየመለሱ፡፡
ረከቦትና ጀበናውን አስቀምጠው ወደ ጓዳ እየተመለሱ ነው ወ/ሮ ባዩሽ፡፡ የብረት ምጣድ የቆለሉበትን ከሰል ምድጃ ይዘው ተመለሱና፣ የተከበረ ቦታው ላይ አኑረው ተመልሰው ገቡ፡፡
“ባዩ! አንቺ ባዩሽ” እያሉ መጡ፤ የሆኑ ሴትዮ፡፡ ድምፃቸውንም ተከትለው በሩ ላይ ተከሰቱ፡፡
ከፊት ለፊት የተቀበሏቸው ሻምበል ባህሩ ናቸው፡፡
 “እንዴ ሻምበል--- እንዴት ዋልክ?”
“እንዴት ዋልሽ አስካለች? ግቢ፣ አረፍ በይ” እረፍት ጋበዙ፡፡
“ምኑን ተቀመጥኩት ብለህ ነው--”
“አስኩ መጣሽ! እንውጣ አይደል፣ ወይ የኔ ነገር! አቀራርቤው ብሔድ ይሻላል ብዬ እኮ ነው” እያሉ እጣን ማጨሻና የተቋጠረች ትንሽዬ ላስቲክ ይዘው ከጓዳ ወጡ፡፡
“በይ ነይ ውጪ፤ እነ ገነት ከመጡ ቆዩ” አሉ ወ/ሮ አስኩ፡፡
ወ/ሮ ባዩሽ በእጃቸው የያዙትን አስቀመጡና እዚያው ከቡናው ቦታ ጎን የግድግዳውን ጥግ ይዞ የተቀመጠው ኮመዲኖ ላይ የነበረውን ነጠላቸውን አንስተው አዘቀዘቁ፡፡
“ምግብ እንደሆነ ስትመጪ ብለዋል እንግዲህ፡፡ በይ ነይ እንውጣ”
“በል እንግዲህ ሻምበል” አሉና ወ/ሮ አስካለች በሩን ለቀቁ፡፡
“በሉ እሺ!” ሸኟቸው ሻምበል፡፡
ራቅ ብላ የምትታየው ኩሽና ውስጥ የተኛው ቦቢና ሻምበል ባህሩ ብቻ ቀሩ፡፡
“ውሻ ሰውን እየጮኸ ስለሚጠብቀውና በታማኝነት ስለሚያገለግለው ተወደደ እንጂ ከበግ ምንድን ነው የሚለየው? ሰው ደግሞ ስላገለገለው ብቻ ታማኝ ጓደኛ ምናምን እያለ ዝም ብሎ መካብ ይወዳል፡፡ ክቦ ክቦ ሲያበቃ እንደገና ያ አልበቃ ብሎ ውጉዝ በማድረግ ይጠብቀዋል፡፡ ከእነ በግ ለይቶ የሱን ስጋ እርም ማድረግ ምን የሚሉት ነገር ነው እስኪ አሁን፡፡ ፍጡር ፍጡር ነው፡፡ ስጋም ስጋ ነው፡፡ እንደውም ስጋው በጣም መድኃኒትነት አለው ነው የሚባለው፡፡” ይሄ ሁሉ ጭንቅላታቸው ውስጥ ነበር የሚመላለሰው፡፡ ወ/ሮ ባዩሽ ሲመጡ ፊት ለፊት የተቀበላቸው ትሪ ላይ የተከመረ ስጋ ነው፡፡ ከየት የመጣ ስጋ ነው ብሎ መጠየቅ አላስፈለጋቸውም፡፡
“ወዬው ጉድ …. ጉድ!” ሊጮሁ ሁሉ ከጅለው ከአፋቸው ላይ ነው የመለሱት፡፡
“ኤዲያ! ምን እዚህ እንትን ትላለች! ባክሽ ወታደር ቤት እያለን ስንቱን በልተናል፡፡ እነዚህ ቻይናዎቹ ውሾችን እየበሉ ጨረሷቸው ብለሽ የነገርሽኝ ራስሽ አይደለሽ? በቀኖና ታስረን እንጂ እኛስ ምን ለየን? ደሞም በዚህ መርከስ እንደዚያ የሚያደርግ ከሆነ መርከሱ ያዋጣል፡፡ መድኃኒት ነው ደግሞ--”
ወ/ሮ ባዩሽ ምራቃቸውን ቱ … ቱ … እያደረጉ እግዚኦታቸውን ያነበንቡታል፡፡ ከጓዳ ሳሎን፣ ከሳሎን ጓዳ እየተንቆራጠጡ ነው ቱ … ቱ…. ዋቸውን የሚያዘንቡት፡፡
“ይልቅ እምትሰሪልኝ ከሆነ ስሪልኝ፡፡ አለበለዚያ…” ብለው ሳይጨርሱ ባለቤታቸው ተቀበሏቸው፡፡
“ማ እኔ ባዩሽ!” አሉና መፀየፋቸውን በቁጣ እያቀጣጠሉ ተንቦገቦጉ፡፡ ከዚያም ጓዳ ገብተው ጠፉ፡፡
(ሰሞኑን ለንባብ ከበቃው “ሌላ ዓለም” የተሰኘ የአጭር ልብወለድ መድበል የተወሰደ)

Read 2683 times