Print this page
Monday, 13 August 2018 00:00

ሩስያና ቻይና አሜሪካን፣ አሜሪካ የኢራንን አጋሮች አስጠንቅቀዋል

Written by 
Rate this item
(2 votes)

በቅርቡ ከአሜሪካ ለተጣለባት የቀረጥ ጭማሪ አጸፋዊ ምላሽ ለመስጠት የወሰነቺው ቻይና፣ ወደ ግዛቷ በሚገቡ የአሜሪካ ምርቶች ላይ የ25 በመቶ የቀረጥ ጭማሪ እንደምታደርግ በይፋ ያስታወቀች ሲሆን ሩስያም “ተጨማሪ ማዕቀብ የምትጥይብኝ ከሆነ፣ የአጸፋ እርምጃ እወስዳለሁ” ስትል አሜሪካን ማስጠንቀቋ ተዘግቧል፡፡
የአሜሪካ መንግስት ባለፈው ወር 34 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የ25 በመቶ የቀረጥ ጭማሪ በምርቶቿ ላይ የጣለባት ቻይና፤ ለዚህ ምላሽ ለመስጠት በማሰብ ነዳጅ፣ የህክምና ቁሳቁሶችና ኬሚካሎችን ጨምሮ ከአሜሪካ በሚገቡ የተለያዩ ምርቶች ላይ ከነሃሴ ወር መጨረሻ አንስቶ 16 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የ25 በመቶ የቀረጥ ጭማሪ እንደምታደርግ የአገሪቱ የንግድ ሚኒስቴር ባለፈው ረቡዕ ባወጣው መግለጫ ማስታወቁን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የአሜሪካ መንግስት ከመጪው መስከረም ወር ጀምሮ ከቻይና በሚገቡ ምርቶች ላይ ተጨማሪ 200 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የቀረጥ ጭማሬ ለማድረግ ማሰቡን የጠቆመው ዘገባው፤ ቻይናም በምላሹ በአሜሪካ ምርቶች ላይ 60 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የቀረጥ ጭማሪ እንደምታደርግ ማስጠንቀቋን አመልክቷል፡፡
በተያያዘ ዜናም፣ ከወራት በፊት ተመርዘው በተገደሉት የቀድሞው ሩስያዊ ሰላይ ሰርጌ ስክራፓል ግድያ ላይ ቀንደኛ ተሳታፊ ነበረች በሚል በሩስያ ላይ አዲስ ማዕቀብ እንደሚጥል የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ባለፈው ረቡዕ ማስታወቁን ተከትሎ፣ የሩስያ መንግስት በምላሹ ለአሜሪካ ሲሸጠው የቆየውን የሮኬት ሞተር ምርቱን ሊያቋርጥ እንደሚችል አስጠንቅቋል፡፡
አሜሪካ በሰላዩ ግድያ ላይ ተሳትፎ እንደሌላት በተደጋጋሚ ስታስታውቅ በቆየቺው ሩስያ ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ ለመጣል የያዘቺውን ዕቅድ የምትገፋበት ከሆነ፣ ሩስያ ስትሸጥላት የነበረውንና አርዲ-180 በመባል የሚታወቀውን የጠፈር መንኮራኩሮች ሞተር ምርቷን ለማቋረጥ እንደምትገደድ የአገሪቱ ፓርላማ የአለማቀፍ ጉዳዮች ኮሚቴ ሊቀመንበር ሊዮኒድ ስላትስኪ ማስታወቃቸውን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ማክሰኞ በትዊትር ገጻቸው ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ከኢራን ጋር የንግድ ግንኙነት ያላቸው አገራት በአፋጣኝ ግንኙነታቸውን ካላቋረጡ፣ ከአሜሪካ ጋር ያላቸው የንግድ ግንኙነት እንደሚቋረጥ ማስጠንቀቃቸውን የዘገበው ደግሞ ሮይተርስ ነው፡፡

Read 2419 times
Administrator

Latest from Administrator