Saturday, 04 August 2018 11:03

ከአንድ ብር አልቤርጎ እስከ ዓለም አቀፍ ሆቴል

Written by  መንግስቱ አበበ
Rate this item
(1 Vote)

  የዛሬ እንግዳዬ የሆኑት የኔክሰስ ሆቴል ባለቤትና ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ዳዊት ገ/ጻድቅ ተክሌና ጓደኛቸው አቶ ኪዳነማርያም ገ/እየሱስ አሁን የሚኖሩት በተለምዶ ጃክሮስ እየተባለ በሚጠራው የመኖሪያ መንደር ነው፡፡
አቶ ዳዊት፣ በ1968 ከሦስት ጓደኞቻቸው ጋር ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ፣ አስጠግቶ መጠለያ (ማረፊያ) የሚሰጣቸው ዘመድ አልነበራቸው፡፡ ስለዚህ አሁን በአንድ መንደር ከሚኖሩት ጓደኛቸው ከአቶ ኪዳነማርያም ጋር፣ መርካቶ ውስጥ፣ ለሁለት የአንድ ብር አልጋ ተከራይተው ይተኙ ነበር፡፡ ከአንድ መነኩሴ አጎታቸው መቶ ብር ተበድረው ሱቅ በደረቴ ይሠሩ ነበር፡፡ ጓደኛቸውም መቶ ብር ከአንድ ዘመዳቸው ተበድረው ይሠሩ ነበር፡፡ ሦስተኛው ጓደኛቸውም በ1977 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡
የሱቅ በደረቴው ንግዳቸው እየሰመረ ሲሄድ፣ አማኑኤል ቤቴክርስቲያን አካባቢ፣ አንድ ቤት በሁለት ሺህ ብር በሽመና ሥራ ይተዳደሩ ከነበረ ሰው ገዝተው መኖር ጀመሩ፡፡ ብዙም ሳይቆዩ፣ የከተማ ቦታና ቤቶች አዋጅ ወጣ፡፡ ከዚያም ቀበሌ ተመስርቶ “ቤት አስመዝግቡ” ሲባል፣ የሸማኔው ንብረት መሆኑን የሚገልጽ ውል ይዘው ሄዱ፡፡ ቀበሌውም “ይኼኮ የእናንተ አይደለም” አላቸው። “የእኛ ነው፤ ገዝተነዋል” በማለት ተከራከሩ፡፡ ቀበሌውም፤ “ብትገዙም በእናንተ ስም አልዞረም። ስለዚህ የሸጠላችሁን ሰው ፈልጉና ስም ያዛውርላችሁ” በማለት መከሯቸው፡፡
ቤቱን የሸጠላቸው ሰው ገንዘቡን እንደተቀበለ ወደ አገሩ ወደ ጎጃም ደምበጫ ሄዷል፡፡ ሄደው እንዳይጠይቁት አድራሻውን አያውቁትም፤ ግራ ገባቸው፡፡ በመጨረሻም፣ የሰውዬውን አድራሻ እንደምንም አጠያይቀው፣ ጎጃም ውስጥ የደምበጫ ነዋሪ መሆኑን ደርሰውበት ወደዚያው አመሩ። ሰውዬው ሲያያቸው፣ “ልጆቼ፣ ምን እግር ጣላችሁ?” በማለት ተቀበላቸው፡፡ እነሱም፣ “ቤቱን ስትሸጥልን ስም ስላላዘዋወርክልን ተቸግረን ነው የመጣነው፡፡ እንሂድና ስም አዛውርልን” አሉት፡፡ ሰውዬውም፤ “ምን ችግር አለው፤ ሄጄ አዛውርላችኋለሁ፡፡ ለማንኛውም እስቲ ጎረቤት ላማክር” ብሎ ሄደ፡፡  ጎረቤቶቹም፤ “እንዴት አምነሃቸው ትሄዳለህ? ቢገድሉህስ?” አሉት። ሰውዬውም እቤቱ ገብቶ ጎራዴ መዞ “ሂዱ፤ ከዚህ ጥፉ” በማለት መታቸው፣ ሚስቱ እንደምንም አረጋግታ አዳነቻቸው፡፡
ወጣቶቹም፣ ወደ ደምበጫ ቀበሌ ሄደው የደረሰባቸውን በደል ተናገሩ፡፡ ቀበሌውም “ከአዲስ አበባ ደብዳቤ አምጡ እንጂ እኛ አስረን እንልከዋለን” አሏቸው፡፡ አዲስ አበባ መጥተው ደብዳቤውን አስጽፈው ወስደው ሰጡ፡፡
ቀበሌውም፣ ሰውዬውን ጠርቶ፣ “ይኼው ደብዳቤ አምጥተዋል፡፡ ሄደህ ስም አዛውርላቸው” አለው። ሰውዬው “እንቢ” ማለት አልቻለም። ከልጆቹ ጋር ወደ አዲስ አበባ መጥቶ ስም አዛወረላቸው፡፡ እነሱም ደስ ብሏቸው ከመሳፈሪያው በተጨማሪ አስደስተው እንደመለሱት አቶ ዳዊት አጫውተውኛል፡፡
የኔክሰስ ሆቴል ባለቤት፣ በትግራይ ክልል አሁን ወደ ጣቢያ በተለወጠችው፤ ያኔ ግን ወረዳ በነበረችው አምባሲኔት ወረዳ ከገበሬ ቤተሰብ በ1951 ዓ.ም ተወለዱ፡፡ ለቤተሰባቸው ሦስተኛ ልጅ የሆኑትን አቶ ዳዊት፣ ሦስት ወንድሞች እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ የዛሬው ባለሀብት በ16 ዓመታቸው፣ በ1968 ከሦስት ጓደኞቻቸው ጋር በመሆን ወደ አዲስ አበባ መጡ፡፡
ከመነኩሴው አጎታቸው በተበደሩት መቶ ብር ጥቃቅን ንግድ ሲሠሩ ከቆዩ በኋላ ንግዱ ሰምሮላቸው መቶ ብሩን ለመነሱሴው አጎታቸው መለሱላቸው። ጓደኞቻቸውም ከዘመዱ የተበደረውን መቶ ብር መመለሳቸውን ተናግረዋል። ንግዱን እያሻሻሉ ሲሰሩ ቆይተው ኢሕአዴግ ሥልጣን ከመያዙ በፊት መርካቶ ውስጥ በሁለት መቶ ሺህ ብር የጨርቃ ጨርቅ ሱቅ ገዙ። በዚህ ሱቅ ሲሰሩ ከቆዩ በኋላ በ1989 የጨርቃ ጨርቁን ሱቅ ሸጠው ተክለሃይማኖት አካባቢ አንድ ሱቅ ገዝተው፣ ወደ ብረታ ብረት ንግድ ገቡ፡፡ በዚህ የንግድ ዘርፍ ሲንቀሳቀሱ ቆይተው አሁን ኔክሰስ ሆቴል ያረፈበትን ቦታ በ2.5 ሚሊዮን ብር ገዙ።  ቦታውን የገዙት ለቢሮ ነበር፡፡ ግንባታ እንደጀመሩ ኮንሰልታንታቸው አቶ ጌታሁን ሳህሌ፣ “ሥራህ ያለው መርካቶ፣ ቢሮህ የሚኖረው ገርጂ፣ በጣም ይራራቃሉና ለምን ቤት አታደርገውም?” በማለት መከሯቸው። ሐሳባቸውን ተቀብለው ሥራው ተጀምሮ እየሠሩ ሳለ፣ 1ኛ ፎቅ ሲደርሱ “ወደ ሆቴል ብታዞረው ይሻላል” አሏቸውና እንደተመከሩት አድርገው፣ በ2001 ዓ.ም የመጀመሪያውን ባለ 66 ክፍሎች ኔክሰስ ሆቴል በ150 ሚሊዮን ብር አጠናቅቀው አገልግሎት ጀመሩ፡፡ ከጎን የነበረውን ቦታ ለማስፋፊያ መንግሥትን ጠይቀው ስለተፈቀደላቸው፣ ግንባታው በ2005 ዓ.ም ተጀምሮ ዘንድሮ በግንቦት ወር 85 ክፍሎች ያሉት ሆቴል 410 ሚሊዮን ብር ፈጅቶ ሥራ ጀምሯል፡፡ ኔክሰስ ሆቴል በአጠቃላይ 151 ክፍሎች ሲኖሩት፣ 560 ሚሊዮን ብር ፈጅቷል፡፡
በደርግ ዘመን ንግድ ለመሥራት አስቸጋሪ ነበር። ሞያሌና በድሬዳዋ- ጂቡቲ በኩል ካልሆነ በስተቀር ሁሉም መስመር ዝግ ነበር፡፡ አቶ ዳዊትም ወደ ድሬዳዋ ሄዱ፡፡ በጂቡቲና በድሬዳዋ ድንበሮች መካከል የሚካሄድ የሁለት ሺህ ብር ንግድ ነበር፡፡ ንግድ ፈቃድ ማውጣት አይችሉም፡፡ ፈቃዱ ካላቸው ሰዎች ጨርቅ፣ ሽቶ… እየገዙ አዲስ አበባ አምጥተው ይሸጡ ነበር። በእንዲህ ዓይነት እንቅስቃሴ ንግዳቸው መደርጀቱን አቶ ዳዊት ይናገራሉ፡፡
“የብረታ ብረቱ ሥራ ጥሩ ነበር፡፡ በዶላር እጥረት አሁን ንግዱን አቁመናል፡፡ ከቱርክ፣ ከቻይና፣ ከዩክሬን ብረት እያመጣን እንሸጥ ነበር” ብለዋል፡፡ በእንዲህ ዓይነት ሥራ ንግዳቸው መደርጀቱን አቶ ዳዊት ይገልፃሉ፡፡ ከቅርብ ዓመት ወዲህ ግን የውጭ ምንዛሪ (የዶላር እጥረት) ስለገጠማቸው እንደበፊቱ እንቅስቃሴ የለም፡፡ ከሁለት ዓመት ወዲህ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ክፉኛ እንዳጋጠማቸው ባለሀብቱ ይናገራሉ። ከመንግሥትና ከግል ባንኮች ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ተበድረው ስለሆነ የሚሠሩት፣ አሁን ወለዱ እንደተጠራቀመባቸውና የሆቴሉ ማስፋፊያም የዘገየው በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ “ከሰሞኑ ዶላር እየገባነው ይባላል፡፡ ግን በየባንኩ ወደ 2 ሚሊዮን ዶላር ፐርፎርማ አለን፤ የደረሰን ነገር ግን የለም፡፡ የለንም ነው የሚሉን” ብለዋል፡፡
አቶ ዳዊት፣ በአሁኑ ወቅት ምንም ዓይነት የወደፊት ዕቅድ የላቸውም ማለት ይቻላል። ምክንያቱ ደግሞ የአገሪቱ ሰላም መጣት ነው። “ሰላም ከሌለ፣ ምንም ነገር የለም፡፡ ለሁሉም ወሳኙ የሰላም መኖር ነው” ይላሉ፡፡ ቀደም ሲል ኔክሰስ ሆቴልን በክልሎች የማስፋፋት፣… ሐሳብ ነበራቸው፡፡ የሰላም መጥፋት፣ በሐሳባቸው እንዳይገፉ እንቅፋት ሆኖባቸዋል፡፡ “ሰላም ከሌለ፣ ስጋት ድብርት፣… ይወርዳል፡፡ ሐሳብህን ሰፋ አድርገህ ማሰብ አትችልም፡፡…” ብለዋል፡፡
ኔክሰስ ሆቴልን ልዩ የሚያደርገው የመዋኛ ገንዳው እንደሆነ ይነገራል፡፡ እንደ አየር ፀባዩ የሚሆን ነው፡፡ ዝግ ወይም ክፍት፡፡ በዝናብ ጊዜና ማታ ይዘጋል፤ ቀን ደግሞ ይከፈታል፡፡ አቶ አብይ ተፈሪ የሆቴሉ ፍሮንት ዴስክ ማናጀር ናቸው። ሆቴሉ፣ 7 ዓይነት አልጋዎች እንዳሉት ገልጿል። 60 ስታንዳርድ ደብል፤ 20 ስታንዳርድ ትዊን፣ 4 ኮርነር  ስዊት ቢዝነስ ደብል፣ 10 ቢዝነስ ሱት፣ 6 ቢዝነስ ትዊንና አንድ ፋሚሊ ክፍሎች አሉት ብለዋል፡፡ ዋጋቸውም ከ80 ዶላር እስከ 180 ዶላር መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የመኝታ ክፍሎቹ ዓለም አቀፍ ደረጃን ያሟሉ ናቸው፡፡ ክፍሉ የሚከፈተውና መብራት የሚበራው በካርድ ነው፡፡ ክፍሎቹ፣ በቅዝቃዜ ጊዜ የሚያሞቅ፣ በሙቀት ጊዜ ደግሞ የሚያቀዘቅዝ ኤሲ ሲስተም አለው፡፡ ክፍሎቹ ጢስ ጠቋሚና ውሃ የሚራጭ መሳሪያ፣ መስኮቶቹ ከውጭ የሚመጣ ድምፅ የሚቀንስ ብርሃን ሰውን እንዳይረብሽ የሚያደርግ መጋረጃ፣ ቦክስ ሻወርና ገንዳ፣ በየክፍሉ ሙቅና ቀዝቃዛ ውሃ፣ ካዝና፣ የተለያዩ መጠጦች የያዘ ፍሪጅ፣ የሻይና የቡና ማፊያ ስልክ፣ ቲቪ፣ ነፃ ትራንስፖርት ከኤርፖርት ወደ ሆቴል፣ ከሆቴል ወደ ኤርፖርት ነፃ ቁርስ፣ ሳውና፣ ስቲም፣ ጂም፣ እንዳሏቸው ገልጿል፡፡ ክፍሉ ውስጥ እሳት ቢነሳ፣ ምንጣፍ ይለበለባል እንጂ አይቃጠልም፣ በሮቹም ለ30 ደቂቃ እሳት መቋቋም የሚችሉ ናቸው፡፡ ከ15-450 ሰው መያዝ የሚችሉ 5 የመሰብሰቢያ አዳራሾችም አሉት፡፡ አንድ የዕቃና ሁለት የእንግዳ መጓዛ ሊፍቶች አሉት፡፡

Read 2793 times