Saturday, 04 August 2018 11:02

4ኛው “ንባብ ለህይወት” የመፅሐፍት ኤግዚቢሽን ተከፈተ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

 “በሁሉም ወረዳና ክፍለ ከተማ የማንበቢያ ቦታ እንዲኖር እሰራለሁ” - ም /ከንቲባ ኢ/ር ታከለ ኡማ
           “ንባብ ለህይወት”ን በመላ አገሪቱ ለማካሄድ ታቅዷል


    አራተኛው ዙር “ንባብ ለህይወት” የመፅሐፍት ኤግዚቢሽንና የኪነ ጥበባት መድረክ ባለፈው ሐሙስ ረፋድ ላይ በኤግዚቢሽን ማዕከል ተከፈተ፡፡ በዘንድሮው ኤግዚቢሽን ላይ ከ200 በላይ የመፅሐፍት መደብሮች፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የጥናትና ምርምር ተቋማትና ሚዲያዎች የተሳተፉ ሲሆን የዓመቱ የወርቅ ብዕር ተሸላሚ የፊታችን ሰኞ ይፋ እንደሚደረግ “ንባብ ለሕይወት” ፕሮጀክት መስራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ቢኒያም ከበደ ገልፀዋል፡፡
ባለፉት ሦስት ዓመታት በተካሄዱት የ“ንባብ ለህይወት” ኤግዚቢሽኖች በታየው አበረታች ውጤት የዘንድሮውን ከሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት ጋር በመነጋገርና በመተባበር የተለየ ለማድረግ መሞከሩን አቶ ቢኒያም ተናግረዋል፡፡
በመክፈቻ ሥነ ስርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢ/ር ታከለ ኡማ ባደረጉት ንግግር፤ “እዚህ ቦታ የተገኘሁት ለንባብ ታላቅነት ተጨማሪ ድምፅ ልሆን ነው” በማለት በግላቸው ከንባብ ያገኟቸውን ትሩፋቶችም ገልፀዋል። “ከደራሲ ገጣሚና ባለቅኔው አጎቴ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን የማንበብን ትልቅነት ተምሬያለሁ” ብለዋል - ምክትል ከንቲባው በንግግራቸው፡፡
“ምሁራን ንባብን ከሶስት ነገሮች ጋር ያመሳስሉታል” በማለት ያብራሩት ከንቲባው፤ አንደኛው- አንባቢ ሰው ከወንዝ ዳር እንደበቀለ ዛፍ ያደርጋል፤ አዕምሮን ያለመልማል፣ በቀላሉ በሚነፍስ ንፋስ አይወዛወዝም፣ የፀናና ጠንካራ ይሆናል፤ ሁለተኛው አንባቢ ሰው ከንብ ይመሰላል፡፡ ንብ ብዙ ኪሎ ሜትር ተጉዛ ቀስማ፣ ከሁሉ ነገር ጣፋጭ የሆነውን ማር ትሰራለች፤ ማር ደግሞ ፍቅር ነው፤ መድኃኒት ነው፤ አንባቢ ሰውም እንደ ንቧ ታታሪ ሆኖ ጣፋጭ ውጤት በማምረት፣ ለአገሩም ለወገኑም ጠቃሚ ይሆናል ብለዋል፡፡
በሶስተኛ ደረጃ፤ አንባቢ ሰው ከሰውም ከመፅሐፍትም ጋር ጓደኝነቱን ያጠናክራል ያሉት ከንቲባው፤ ወጣቶች አዛውንቶችም ሆኑ የከተማው ነዋሪዎች ከጓደኞቻቸው ጋር ለመወያየትም ሆነ መፅሐፍትን ለማንበብ ምቹና ፅዱ መናፈሻ እንደሚያስፈልጋቸው ጠቁመው፤ በእያንዳንዱ ወረዳና ክ/ከተማ እነዚህን መናፈሻዎች ለመስራት ጥረቴን እቀጥላለሁ ሲሉ ቃል ገብተዋል፡፡ “በዚህ ጉዳይ ላይ ለመመካከር ፍላጎት ካለው ጋር እተባበራለሁ፤ ሁሌም በሬ ክፍት ነው” ያሉት ከንቲባው፤ ለ“ንባብ ለህይወት” ሀሳብ አፍላቂዎችና ለዝግጅቱ አስተባባሪዎች ያላቸውን አድናቆት ገልፀዋል፡፡
የፕሮጀክቱ ኃላፊ አቶ ቢኒያም የዘንድሮውን “ንባብ ለህይወት” ለየት የሚያደርገው ምን እንደሆነ ሲገልፁ፤ ከዚህ ቀደም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የጥናትና ምርምር ውጤቶቻቸውን ለሌሎች ለማስተላለፍ የነበረውን ክፍተት ለመሙላት የኦንላይን አገልግሎታቸውን እንዲያስተዋውቁ መጋበዛቸውን ጠቁመው፤ በዚህም መሰረት ጅማ፣ ጎንደርና ወልድያ ዩኒቨርሲቲዎችን ጨምሮ 11 ዩኒቨርሲቲዎች በኤግዚቢሽኑ ላይ መሳተፋቸውን ተናግረዋል፡፡
“ንባብ ለህይወት”ን በተጠናከረ መልኩ ለማስቀጠልና አንባቢ ትውልድን ለመፍጠር ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በቋሚነት ለመስራት ስምምነት መፈራረማቸውን የገለፁት የፕሮጀክቱ ኃላፊ፤ ከወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ ርስቱ ይርዳው ጋር በተደረገ ውይይትም፣ በአቅም ውስንነት “ንባብ ለህይወት” በአመት አንዴ አዲስ አበባ ውስጥ ብቻ መሆኑ ቀርቶ በመላ አገሪቱ እንዲካሄድ ቅድመ ስምምነት ላይ መደረሱን አስታውቀዋል፡፡
በዘንድሮው “ንባብ ለህይወት”፤ በአዳራሽ ቁጥር 1 እና በኪነጥበብ መድረኩ አዳዲስ መፅሐፍት በየቀኑ እንደሚመረቁ የተገለፀ ሲሆን ትላንት ምሽት ከ11  ሰዓት ጀምሮ የግጥም በጃዝ የተመረጡ ገጣሚያንና ወግ አቅራቢዎች በኢትዮጵያዊነት፣ በአንድነትና በፍቅር ላይ የሚያጠነጥኑ የጥበብ ስራዎቻቸውን ለታዳሚ አቅርበዋል፡፡
በቀጣይ መድረኮች “ንባብና ጋዜጠኝነት” በሚል ርዕስ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ቅድመ ምረቃ ትምህርት ክፍል ጋር በመተባበር ጥናታዊ ፅሁፍ የሚቀርብ ሲሆን “ንባብና ህክምና” በሚል ርዕስም ሀኪሞች ከህሙማን ጋር ከመግባባት ክህሎት ጀምሮ እስከ ህክምና ድረስ በንባብ ምን ሊያዳብሩ ይችላሉ በሚል የመነሻ ጥናት፣ ውይይት እንደሚደረግም ተገልጿል፡፡
ከትናንት በስቲያ ሐሙስ የተከፈተውና ለአምስት ተከታታይ ቀናት የሚቆየው “ንባብ ለህይወት”፤ ከነገ በስቲያ ሰኞ የወርቅ ብዕር ተሸላሚውን የኪነ ጥበብ ባለውለታ በመሸለም ይጠናቀቃል፡፡ በመጀመሪያው “ንባብ ለህይወት” የወርቅ ብዕር ተሸላሚ የነበሩት አምባሳደር ዘውዴ ረታ ሲሆኑ በሁለተኛው ዙር ደራሲ አዳም ረታ፣ በሶስተኛው ደግሞ የአዋቂም ሆነ የህፃናት መፅሐፍትን በመፃፍና በመተርጎም ለረጅም ዓመታት ያገለገሉት ደራሲና ተርጓሚ አማረ ማሞ መሆናቸው ይታወሳል፡፡ 

Read 4321 times