Print this page
Saturday, 04 August 2018 10:58

ዋ ፍቄ!

Written by  ነቢይ መኮንን
Rate this item
(25 votes)

አየሁ ብሔራዊን ደረጃ ላይ ቆሜ
ክፉ ማየት ከፋ፣ ጠናብኝ ህመሜ!
ዋ ፍቄ!
ሳጥንህ በሳንሳ
በሸክም ሲነሳ
ተፋጥጬህ በደንኩ፣ በህይወት አበሳ!
ይኸው ጉዴን አየሁ፣ ስንት ዘመን ኖሬ
የግዴን ከዕውነት ጋር የፊጥኝ ታሥሬ፡፡
ተብረከረከብኝ፣
መቆም እንኳ እንቢ አለኝ፤
       “ቶርች” የለመደ እግሬ!
ፍቄ ምን በደልኩህ? ምን አረኩህ ፍቄ?
ብቻህን ብቻዬን፣ በይፋ አግኝተኸኝ
ሞት አላቅ ይመስል፣ ሞተህ አሳየኸኝ
ሳጥን እንደካባ ለብሰህ መጣህብኝ?!
***
መድረክ ሆይ ያውልህ
ንጉሥክን ተቀበል አፈርክን ነስንሰህ!
ዛሬስ መራራ ነው
መንኗል ከልቡ፣ ዓለም አይወድልህ
      ፍቄ በጄ - አይልህ!
***
ዋ ፍቄ!
ከዕንባ ተናንቄ
ቆምኩኝ መድረክ ግርጌ፡፡
አየሁኝ እራስጌህ፣ የአበቦች ክምችት
መቼትክን ከቦታል፣ የሀዘን ምልክት
“አብቤአለሁና ከሳጥኔ ማህል
እመቃብሬ ውስጥ አበባ ይተኛል”
አበባ አታምጡ በል!
አበባ አልፈልግም በላቸው እባክህ
ሽኝቱም ይቅርብህ
ተሸኝቶ አያቅም አበባ ባበባ
ሀዘን ምን ግድህ ነው፣ መስኖህ ይሁን እንባ
የጥበብን ችግኝ ነገን የሚያረባ!
“ሂድ የናቴ ልጅ ሂድ”
ልበልሃ ዛሬ ገብርዬን እንዳልከው
መቼም ዕውነታችን ተውኔትን መድገም ነው!
ዋ ፍቄ!
ሸኚህ ይቁም በቃ
ሥራህን ይረከብ፣ መንፈስክን ደጅ ይጥና
ቆርጦ መሄድ ይማር፣ እንደ ዕምነቱ ጫና
             በየዕምነቱ ቃና!
መድረክህ ታማኝ ነው እንዳንተ አልጨከነም
እንዳንተም ብቻውን፣ ሩቅ አልመነነ፣
ገዳም አልገደመ
ንፍሮ ዳቤ አላለም
ጠበቀ እስክትመጣ፣ መብራት ሳያጨልም!!
***
ተመስጌን መድረክ ሆይ
ይሄው አየን ይሄው
ሞት የማያቅ ንጉሥ
ሞትን አሸንፎ ህይወቱ ጠበበው!
***
ዋ ፍቄ!
ዛሬ ቴያትር አለህ ክብርህን ያቀፈ፤
ማንም ያልተወነው፤
ታምርክን እንድናይ
ሞተህ መድረክ ወጣህ
ላዩ እንዳልኖረ ሰው!
ያልታየ ማሳየት የጥበብ ምስ ነው
ያንተም ቋንቋ ይሄው ነው
ሞት የማይለውጠው!
ታውቀዋለህ ፍቄ!
ሰው እንደከተሜ
ዓለምና ገዳም
ኪኒንና ጠበል
በጥብጦ ቀላቅሎ መኖር ይፈልጋል፡፡
አንተ አንድዬ መንገድ ያልተሄደበትን
መርጠሃል ገዳምክን
     ቤተ - ገነትህን!
እንግዲህ ታዳሚህ መንፈስክን ደጅ ይጥና
ቆርጦ መሄድ ይማር፣ በየዕምነቱ ጫና
መራራነት ይልመድ፣ ካንተ ልዕልና!   
 ሐምሌ 25, 2010 ዓ.ም
(ለፍቃዱ ተ/ማርያም በብሔራዊ ቴያትር)

Read 5276 times