Saturday, 04 August 2018 10:56

የመድረኩ ንጉሥ የአርቲስት ፍቃዱ ተ/ማርያም ስንብት

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(3 votes)

 የመድረኩ ንጉሥ ፍቃዱ ተ/ማርያም ኩላሊቶቹ ሥራ ማቆማቸው የተሰማ ጊዜ ነበር በመላው ኢትዮጵያውያን አድናቂዎቹ ዘንድ ከፍተኛ ድንጋጤ የተፈጠረው፡፡ ታዲያ ወገኑ ደንግጦ ዝም አላለም። ህይወቱን ለማትረፍ የሚችለውን ሁሉ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ የህክምና ኮሚቴ ተቋቁሞም ለህክምናውና በቀጣይ ህይወቱ የጤና እክል ቢገጥመው እንዳይቸገር በ“ጎ ፈንድ ሚ” አካውንት እርዳታ መሰብሰብ የተጀመረ ሲሆን የኬኬ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ባለቤት አቶ ከተማ ከበደም 1 ሚ. ብር ለህክምናው ለግሰዋል፡፡
ለህክምና የገንዘብ እርዳታ የማሰባሰብ ሃሳቡን ሲሰማ ግን አርቲስቱ ፈቃደኛ አልነበረም፡፡ “እባካችሁ ይህን ነገር አቁሙ፤ ከእነ ክብሬ ልሙት” ነበር ያው፡፡ ለህክምና ህንድ ደርሶ መምጣቱ ከተነገረ በኋላ በመሃል ድምፁ ጠፋ፡፡
ከትላንት በስቲያ ሐሙስ በቀብር ሥነ ስርዓቱ ላይ በሕይወት ታሪኩ ላይ እንደተነገረው፤ አርቲስቱ ለህክምናው ከተሰጠው ገንዘብ ላይ 200 ሺህ ብር ለአንዲት በኩላሊት ህመም ለምትሰቃይ ታዳጊ የለገሳት ሲሆን “እኔ 60 ዓመት ሞልቶኛል፤ ይህች በኩላሊት ህመም የምትሰቃይ የ16 ዓመት ታዳጊ ግን መትረፍ አለባት” ሲልም ተናግሮ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ግን በቀጥታ ያመራው ወሎ ከወልዲያ አለፍ ብላ በምትገኘው ሲሪንቃ ቅድስት አርሴማ ገዳም ነበር -  መንፈሳዊውን ህክምና ለመከታተል፡፡
ከመንፈሳዊ ህክምናው ጎን ለጎን ኩላሊቱን እንዲያስቀይርና እድሜውን እንዲቀጥል በወዳጅ ዘመድ፣ በቅርብ የስራ ጓደኞቹ፣ በቤተሰቦቹና በሽማግሌ ቢጠየቅም ፈቃዱ በጄ አላለም፡፡ “እኔ በፈጣሪ ስራ አልገባም፤ እዚሁ ከእመቤቱ ማርያም ጋር በፅሞና እነጋገራለሁ፤ በፀበል እድናለሁ” የሚል ምላሽ ነበር የሰጠው፡፡ እንደውም ነሐሴ 1 ቀን የሚገባውን የፍስለታን ፆም በገዳሙ አሳልፌ ወደ ቤቴ እመለሳለሁ የሚል ተስፋ ነበረው ሞት ቀደመው እንጂ፡፡
በ1948 ዓ.ም ከአባቱ ከአቶ ተክለማርያም ኪዳኔና ከእናቱ ወ/ሮ እልፍነሽ ወንድሙ በተለምዶ አራት ኪሎ ባሻወልዴ ችሎት ተብሎ በሚጠራው መንበረ ፀባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል አቅራቢያ የተወለደው መልከ መልካሙ፣ ቅንና እሩህሩሁ ፍቃዱ ተ/ማርያም፤ እድሜው ለትምህርት እንደደረሰ “በሚያዚያ 27” እና “በአፄ ናኦድ” ት/ቤቶች ትምህርቱን የተከታተለ ሲሆን ገና የ8ኛ ክፍል ተማሪ እያለ ነበር ነፍሱ ለኪነ ጥበብ የተጠራች መሆኑን አውቆ ወደ ሙያው የገባው፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ጥበባት ትምህርት ክፍልም ለሁለት ዓመት ተኩል ትምህርቱን የተከታተለ ሲሆን በኋላም በስራ አመራር ትምህርት ዲፕሎማ አግኝቷል፡፡
በ1967 ዓ.ም በአዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አዳራሽ (ማዘጋጃ ቤት) ተቀጥሮ በተዋናይነት የኪነ ጥበብ ጉዞውን ጀመረ፡፡
የመድረኩ ንጉስና ታላቁ ቤተ ተውኔት ብሔራዊ ቴአትር የተገናኙት በ1985 ዓ.ም ነበር፡፡ በዚህ ቴአትር ቤት በሚሰራቸው የጥበብ ውጤቶች፣ ለጥበብ ባለው ወኔና ፍቅር፣ በትወና ክህሎቱና ጥበቡ፣ ብዙዎች ከመደነቅም አልፈው በተውኔት ጥበብ ፍቅር እንዲወድቁና እንዲማረኩ ለማድረግ የቻለ ታላቅ የጥበብ ሰው ነው፡፡ እከዮቹና ታናናሽ የጥበብ ባልደረቦቹ የሙያውን ዲሲፕሊን እንዲከተሉ መሰረት የጣለ ትልቅና የማይተካ ሚና የነበረው ባለሙያ እንደነበርም ይነገርለታል፡፡ በሙያው የማይደራደር፣ ሙያውን አክብሮ፤ ያስከበረ ጠንቃቃና ሰውን ሁሉ አብዝቶ የሚወድ፣ መካሪም አባት ነበር - አርቲስቱ፡፡
ምርጡ ተዋናይ ፍቃዱ ተክለማርያም ተቀጥሮ ሙያውን በደንብ መተግባር ከጀመረበት ከ1967 ዓ.ም ህይወቱ እስካለፈበት ጊዜ ድረስ በብቃቱ ሳይዋዥቅ ለ43 ዓመታት በመድረክ ላይ ነግሶ፣ ሙያውን አንግሶ መኖሩን የሙያ ባልደረቦቹ ይመሰክሩለታል፡፡
በ43 ዓመታት የመድረክ ንግስና ዘመኑ ከ150 በላይ የመድረክ፣ የቴሌቪዥን፣ የሬዲዮና የስክሪን ድራማዎችን በብቃት የተወነው አንጋፋው የኢትዮጵያ ብሔራዊ የጥበብ ጀግናው፤ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይወሰን በምስራቅ ጀርመን፣ በካሜሩን፣ በስዊድንና በአሜሪካ በመዘዋወር የትወና ብቃቱን አሳይቷል፡፡
ጋሽ ፍቃዱ በትወና አለም ኤዲፐስ ንጉስ፣ አፄ ቴዎድሮስ፣ ንጉስ አርማህና ሐምሌት ላይ ንጉሥ ሆኖ በመጫወት፣ የመድረክ ንጉሥነቱን በወርቅ ቀለም ለመፃፍ ችሏል፡፡ በባለካባና ባለዳባ፣ በመርዛማ ጥላ፣ በእሳት ሲነድ፣ ቤቱ፣ የሰርጉ ዋዜማ፣ ኦቴሎና በስተመጨረሻም ከህመሙ ጋር እየታገለ “የቃቂ ውርድዮት” በተሰኘው ትውፊታዊ ቴአትር ላይ በብቃት ተውኗል፡፡ በቴሌቪዥን ተከታታይ ድራማዎችም፡- ያልተከፈለ ዕዳ፣ ባለጉዳይ፣ የአበቅ የለሽ ኑዛዜ፣ ገመና፣ ሰው ለሰው እና መለከት በተባሉት ድራማዎች ላይ እንዲሁ ብቃቱን አሳይቷል፡፡ በወርቃማና በባለግርማ ሞገስ ድምፁ ነፍስ ዘርቶ በሬዲዮ ከተረካቸው ልቦለድ መፅሐፍት መካከል ሞገደኛው ነውጤ፣ ጥቁር ደምና ሳቤላና ይጠቀሳሉ፡፡
አርቲስት ፍቃዱ በጎ አድራጊና እሩህሩህም ነበር። በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የቲቢ በሽታ አምባሳደር ሆኖ ህሙማንን በመጎብኘትና አጋርነቱን በመግለፅ እንዲሁም ለማህበረሰቡ ስለ በሽታው በማስተማር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከተ ሲሆን “ሀበሻ የአረጋዊያንና የአዕምሮ ጉዳተኞች መርጃ” የተሰኘ የበጎ አድራጎት ድርጅት በግሉ አቋቁሞ አረጋዊያንና የአዕምሮ ህሙማንን ሲረዳ እንደነበር ታውቋል፡፡ ይህ የአገር ኩራት የሆነ ወርቃማ የኪነ ጥበብ ሰው፤ የልፋቱንና የንግስናውን ያህል አልተጠቀመም። በገንዘብ የማይተመን የሰው ፍቅር ግን በእጅጉ አትርፏል፡፡  ለኪነ ጥበቡ እንደሻማ እየቀለጠ ለሌሎች ብርሃንም ሆኗል። በእርግጥ በ1996 ዓ.ም ከኢትዮጵያ የስነ ጥበብና የመገናኛ ብዚኃን ሽልማት ድርጅት በትወና ዘርፍ የረጅም ጊዜ አገልግሎት ተሸላሚ ለመሆን በቅቷል፡፡ ለአራት አስርት ዓመታት ሙያውን አክብሮና በትጋት ሲሰራና ሲለፋ የኖረው አንጋፋው አርቲስት፤ ሁለት ኩላሊቶቹ ሥራ አቁመው በህመም ሲሰቃይ የቆየው አርቲስቱ፣ በሲሪንቃ ቅድስት አርሴማ ገዳም ገብቶ ፀበል ሲጠመቅ የነበረ ሲሆን ከፍስለታ ፆም በኋላ ወደ ቤቱ ሊመለስ ቢያቅድም ያሰበው አልተሳካም፡፡ ባለፈው ማክሰኞ ሐምሌ 24 ቀን 2010 ዓ.ም አመሻሽ ላይ አንጋፋው የኢትዮጵያ የጥበብ ንጉሥ ላይመለስ እስከወዲያኛው አሸልቧል፡፡
ረቡዕ ማለዳ አስክሬኑ ወደ አዲስ አበባ መንገድ ሲጀምር ከወልዲያ ጀምሮ እስከ ደሴ፣ ኮምቦልቻና ደብረ ብርሃን ከተሞች ህዝቡ እያነባ ከፍተኛ አሸኛኘት በማድረግ ለአርቲስቱ ያላቸውን ክብርና አድናቆት ገልጿል፡፡
ከትላንት በስቲያ ሐሙስ የአንጋፋው አርቲስት አስክሬን ለረጅም ጊዜ ነግሶ በኖረበት ብሔራዊ ቴአትር ከገባ በኋላ በበርካታ የሙያ አጋሮቹ፣ በአድናቂዎቹና በከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች የመታሰቢያና የአሸኛኘት ሥነ ስርዓት ተደርጎለታል፡፡
ሐሙስ ከቀኑ 8፡00 ላይ በመንበረ ፀባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በተካሄደው የአርቲስቱ ሥርዓተ ቀብር ላይ ም/ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮን፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ወ/ሮ ፎዚያ አሚን፣ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ሂሩት ወ/ማርያም፣ እጅግ በርካታ ተዋንያን፣ ደራሲያን፣ ታዋቂ ሰዎችና በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ የከተማዋ ነዋሪዎች ተገኝተዋል፡፡ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ወ/ሮ ፎዚያ አሚን ባስተላለፉት መልዕክት፤ ኪነ ጥበብ ለአንድ አገር ያለውን ፋይዳ ጠቅሰው፤ “ኪነ ጥበብን በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል ካደረጉ አንጋፋና ኮከብ የኪነ ጥበብ ሰዎች መካከል አንዱና ግንባር ቀደሙ ፈቃዱ ተ/ማርያምን ማጣት ለአገር ትልቅ ጉዳት ነው” በማለት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገልፀዋል፡፡ ጠ/ሚኒስትር  ዐቢይ አህመድና ምክትል ጠ/ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን ገልፀዋል፡፡ አንጋፋው አርቲስት ፍቃዱ ተ/ማርያም ባለትዳርና የአንድ ልጅ አባት ነበር፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል በአርቲስት ፍቃዱ ተ/ማርያም ህልፈት የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን እየገለጠ ለቤተሰቦቹና ለጥበብ ባልደረቦቹ እንዲሁም አድናቂዎቹ መፅናናትን ይመኛል፡፡

Read 1639 times