Saturday, 04 August 2018 10:51

ዝምታ

Written by  አብይ ተስፋዬ አሳልፍ - (አተአ)
Rate this item
(14 votes)

 በተውኩት ጎዳና እየተመላለስኩ
በረገምኩት ስምሽ መሃላ እያደረኩ
መተዌን ብምልም፣ መርሳቴን ብምልም
እንኳንስ በህይወት ስምሽን ከመጥራት፣ ሞቼ እንኳን አልድንም!
***
ጠባብ ክፍል ውስጥ በምቹ ወንበሮቹ ላይ ከተቀመጠው ሰውዬ ፊት ለፊት አስቀምጠውኛል። ፊቱ ላይ ጭረት መሳይ ቆሻሻ ነገር ስላየሁ ከፊቱ ላይ ልጠርግለት ብዬ ከመቀመጫዬ ላይ ለመነሳት ስሞክር፣ ከወንበሩ ጋር አንድ ላይ እንደሰፉኝ አስተውላለሁ፡፡ ቀጥሎ ከእጆቼ አንጓዎች ላይ ሃይለኛ ስቃይ ይሰማኛል፡፡
ሰውዬው ኮስተር ብሎ ይመለከተኝና ሰላላ በሆነ ድምፁ እንዲህ ይለኛል፡- ‹‹…አልዓዛር … አትታገል፡፡ ታውቃለህ አይደል፡፡ ከታሰርክበት ካቴና ጋር መታገል እጆችህን ይጎዳቸዋል እንጂ መፍትሔ የለውም (በእጆቼ አንጓዎች አካባቢ የቆየውን የሚያመረቅዝ ቁስል በጨረፍታ አየዋለሁ!)፡፡ ምን ፈልገህ ነው!? ..››
ድምጼ የራሴ በማይመስል መልክ ከከንፈሬ ይፈናጠራል … ‹‹…ፊትህ ላይ ያለውን ቆሻሻ ላነሳልህ ነበር! …›› እለዋለሁ፡፡
ፈገግ ይልና ከሚፅፍበት ወረቀት ቀና ብሎ … ‹‹...አንተ ሲያዩህ ቀጫጫ ትመስላለህ፣ ጉልበትህ ግን የሰይጣን ነው፡፡ ባለፈው የዶክተር ናርዶስን አፍንጫ በቴስታ ሰበርክ፡፡ ዛሬ ደግሞ ወደ እኔ ልትመጣ ነዋ! … አታስበው፡፡ ይልቅ አደብ ግዛና ህክምናህን ቀጥል፡፡ ወደ ዋናው ነጥብ እንመለስና…›› እያለ ማውራት ሲጀምር፣ ድምፁ በሰፊ አዳራሽ ውስጥ እንደሚጮህ የነሐስ ደውል በባዶው ጭንቅላቴ ውስጥ መጀመሪያ በጣም ያስተጋባል፡፡ ቀጥሎ እየሳሳ፣ እየሳሳ ይሄዳል፡፡ (ቀና ብዬ ሳስተውለው፤ ሰውየው በጥርጣሬ አጎንብሶ፣ ከፊቱ ላይ ቆሻሻ ለመጥረግ ይዳብስና በለሆሳስ … ‹የተረገመ፤ ምንም ነገር የለምኮ!› ይላል፡፡)
ነጭ ጋዋኑን እንደለበሰ የደበዘዘ ፊቱን አጠናዋለሁ፡፡ ይህ ጠይም (…ወይም ቀይ!?) ሰውዬ ዶክተር ተሾመ ይሁን ዶክተር ፅጌረዳ ለጊዜው መለየት አልችልምና፣ በጥንቃቄ ከደረቱ ላይ የተጻፈውን ስም ለማንበብ አይኖቼን አጥብቤ አጨነቁራለሁ፡፡ (ፊቱን ካላስታወስኩ ስሙን ማንበብ እችላለሁ ብዬ እያሰብኩ!) ደግሞ እይታዬን እነቅልና፣ ምናልባት የጓደኛውን ጋዋን ቀይሮ የመጣ የረፈደበት ሃኪም ሊሆን ይችላል ብዬ አስባለሁ፡፡ ሊሆን ይችላል … ምናልባት የራሱ ጋዋን ቆሽሾ ስላልታጠበ የጓደኛውን ለብሶ መጥቶ ከሆነስ? (…ግን ጋዋኑ ነጭ ነው ዳልቻ?! እያልኩ አይኖቼን እንደተከልኩ ለደቂቃዎች እቆዝማለሁ!…)
‹‹…እይታህ ያስፈራል! እንዴት ነው ምንጭሮችህን ሳትሰብር ይህን ያህል ማፍጠጥ የተለማመድከው!….›› በሚያስተጋባ ድምፅ፡፡ ለጥቆ ደግሞ በለሆሳስ፤ ‹‹ምላሱ የማይሰራ ሰው አይኖቹ ሰንጣቂ ይሆናሉ!›› ይላል፡፡
በእጁ የያዘውን መጻፊያ (እርሳስ ወይ እስክርቢቶ ወይ የስልክ መጫሪያ ነገር…) እያወዛወዘና ከጠረጴዛው ላይ እያንገጫገጨ ይለፈልፋል፡፡ በሰከንዶች ልዩነት ጠረጴዛውን … ቋ! ቋ! ቋ! … እያደረገ የክፍሉን ፀጥታ ያደፈርሳል። ደግሞ በዚያ እንደ አውሎ ነፋስ ስል በሆነ ድምፁ በለሆሳስ እንዲህ ይለኛል … ‹‹ተናገር የሆነ የምታስታውሰውን፣ አውራ የሆነ የምታውቀውን፣ ዝፈን የሆነ የምታስበውን፣ ብዕር ይዘህ … ሳለው የሚያስጨንቅህን …. ከዚያ ቀስ እያለ ይለቅሃል! ዙሪያህን የከበበህ ጥቁር ደመና ይበታተናል፡፡ ካላወራህ ግን አትፈወስም፡፡….››  ይህ መልዕክት ለጆሮዬ ይደርሰኛል! ሆኖም በየዕለቱ የማስበውን አላወራም፡፡ አልችልማ!
‹‹ከቤዛ ጋር ስላለህ ግንኙነት ጥቂት ንገረኝ እስኪ? ትወያዩ ነበር? ታነጋግራታለህ? ፍቅርህን ትገልጽላታለህ? አብራችሁ ጊዜ ታሳልፋላችሁ?…›› ድምፁ ንፋስ እንዳነሳት እፉዬ ገላ ሽቅብ እየራቀ ሲመጥቅ (እየደበዘዘ ሲሄድ) ይታወቀኛል፡፡ ፊቴ ቁጭ ብሎ ሲያወራ እየሰማሁት ይርቃል። ከንፈሮቹ እየተንቀሳቀሱ እያየሁ ማይም ይሆንብኛል፡፡ አየዋለሁ ግን ድምፅ አይሰማኝም፡፡
የለበስኩት ዥንጉርጉር ነብር መሳይ ልብስ በልኬ ስላልነበረ ገላዬ ላይ ተጣብቋል፡፡ ወገቡ ላይ ለሁለት የሚከፍል ሰፊ ቀበቶ የሚተካ መስመር ያለበት ልብስ ነው፡፡ የሹራቡን እጄታ ሳላስበው አኝካለሁ፡፡ ከእጄታው ላይ የተንጠለጠሉትን ሌሎች ክሮች እየጎተትኩ ቀኑንም ለሊቱንም የማስበው ይህ አሁን የጠየቀኝን ጥያቄ ብቻ ነበር። እርሱ እያወራ፣ ከእኔና ከቤዛ የአብሮነት ጊዜያት አንዲቱን ከጨለማ ትዝታዎቼ ጎትቼ አስባለሁ፡፡
***
የተሰራሁበት ነገር እንኳን ለእርሷ ለእኔም ግራ ይገባኛል፡፡ ብዙ ጊዜ ወሬ አያሰኘኝም፡፡ ከቡናና ከማንበብ ውጪ ብዙም ዘመድ የለኝም፡፡ እርሷን እንኳ የምፈልጋት ልመለከታት ብቻ ነው፡፡ ብዙ ማውራት አልፈልግም፡፡ ያ እኔ ነኝ፡፡ ካልቆሰቆሱኝ አልናገርም፡፡ ከተጨነኩ አልናገርም፡፡ ምን ላውራ… ምን ልተንፍስ ካልኩ አፌ ይለጎማል፡፡ ደስ ያለኝ ቀን ቢሆን እንኳ አውራ ብለው ሲጨቀጭቁኝ ከፈገግታ ውጪ … ወሬ ማውራት አልችልም፡፡ ዝምታዬ ደግሞ ለብዙዎች ይከብዳል፡፡
አያቴ ይህንን ብዙ ጊዜ በራሴ ውስጥ ተቆልፌ መኖሬን ጊዜ ጠብቆ እንደሚፈነዳ ቦንብ ነበር የሚቆጥረው፡፡ ‹‹ዝምታህ እንደ ድቅድቅ ጨለማ ይከብዳል!›› ይለኝ ነበር፡፡ ‹‹በጥልቁ ጨለማህ ውስጥ ዝንት ዓለም እኖራለሁ ብለህ አታስብ። በጥልቁና በዝጉ አለምህ መኖሩ የሚከብደው ህይወትህ በጭለማ ውስጥ በመገኘቱ አይደለም። እንዲያውም ክፋቱ አንድ ቀን ድንገት ወደ አንፀባራቂው ብርሃን ስትወጣ የልቡና አይኖችህን ብርሃን ልታጣ መቻልህ ነው!›› (ፍልስፍናው አይገባኝም!)
ከቤዛም ጋር የሚፈጠረው ይኸው ነበር። የሆነ ቀን ተገናኝተን ቁጭ ስንልና ከደቂቃዎች የጥሞና ሰከንዶች በኋላ እንዲህ ትላለች፡- ‹‹ለምን አታወራም!?..›› (የሁልጊዜ ጭቅጭቋ ዳግመኛ ይወረወርብኛል (ለሺኛ ጊዜ!)፡፡ … ይህንን ጥያቄ ለእርሷ ላለመመለስ ስል፤ ከአገር ጠፍቼ፣ በሊቢያ በረሃና በውቅያኖስ አፍሪካን ባቋርጥ እንኳ አይከብደኝም እላለሁ፡፡) … እናም ዝም ብዬ አይን አይኗን አያታለሁ፡፡ ከንፈሮቼ ለመናገር አይከፈቱልኝም፡፡ ነገር ግን ጉንጮቼ ለፈገግታ አይለግሙብኝምና ፈገግ እላለሁ፡፡
‹‹…ፈገግታህማ ገዳይ ነው!  ማንም ያውቃል። ነገር ግን ብዙ ጊዜ አብረን ስንሆን አታወራኝም … ማለቴ…››
ደግሞኮ ከንፈሮቿ ሲያምሩ! በእውነት ከጡንቻ ወይም ደግሞ ከስስ ስጋ ብቻ የተሰሩ አይመስሉም (ስል እፈላሰፋለሁ!)፡፡  ምናልባት ቼኮሌትና ማር ሳይኖራቸው አይቀርም፤  እንደርሷ ከንፈር ተስፋ መቁረጤን ሁሉ አሽቀንጥሮ የጣለልኝ ነገር ምንም የለም! የእርሷን ከንፈር ለመሳም እንደጓጓሁበት ስባሪ ሰከንድ የራቀ መንገድና የቆየ ጥበቃ አይቼ አላውቅም! ከንፈሮቿ ከንፈሬ ላይ ሲያርፉ የወደቀብኝን የንዝረት መጠን ያህል የጨበጥኩት የኤሌክትሪክ ሃይልም የለም! ለደቂቃ ገነትን ያየሁበት እንዲያ አይነት ስባሪ ሰከንድ ፈፅሞ አልነበረም፡፡
‹‹…ቁም ነገሩንም፣ ቀልዱንም፣ ፍቅሩንና ንትርኩንም ካላወራንኮ ዋጋ የለውም፡፡ ሰው ከተሰጡት ፀጋዎች ሁሉ የሚልቀው ነገሮችን በንግግር መግለፁ ነው፡፡ ታውቃለህ ያንን እንድታደርግ ብዙ ጊዜ ሞክሪያለሁ፣ አንተ ግን ለዝንት ዓለም በሚመስል መልኩ ተዘግተሃል!››
ቃላት ተስፈንጥረው ምላሷን እየረገጡና ከንፈሮቿ ላይ ቆመው፣ አካባቢውን ከቃኙ በኋላ የሚወድቁ ይመስለኛል፡፡ እንዲያውም አንዳንዶቹ ፊደላት ከከንፈሯ ላይ ቆመው ለመውደቅና ላለመውደቅ የሚታገሉና ከንፈሯን ጨብጠው ተንጠልጥለው የሚቀሩም ያሉ ይመስለኛል፡፡ (ለምሳሌ ስትጠራኝ አልዓዛር ለማለት … አ ... ል! … ስትል … ፊደል … ‹ል›  … እምቢ ይላታል፡፡ እንደ ሃብል ከንፈሯ ላይ ተንጠልጥሎ ይወዛወዛል፡፡)
በአለም ላይ ካሉ ሴቶች በሙሉ እንደ እርሷ የምወደው የለም ብዬ አምናለሁ፤ ሆኖም የምናገረውን ሁሉ ስለምታጣጥል ላነጋግራት ይከብደኛል፡፡ በልቤ አስቤ በሰው ፊት ስለሷ የተነፈስኩትንም ቢሆን ፊቷ አልደግመውም። የምናገረውን አትወደው ይሆናል ብዬ አሰላስላለሁ፡፡ ለመናገር በሞከርኳቸው ቃላት ላይ ሁሉ አቂያቂር ታበዛለችና እፈራለሁ፡፡
ብዙ ጊዜ ሰዓታትን አምጬና ከራሴ ጋር ታግዬ ነጭ ላቤን እያፈሰስኩ ‹እወድሻለሁ!› ስላት፣ ኮስተር ብላ “በድንቄም?” አይነት ታየኝና  ‹‹…አይመስለኝም!…›› ትለኛለች፡፡ ለምን እንደማይመስላት ግራ ይገባኛል፡፡ እኔን … አይወድም (ፍቅር አይገባውም!) … ብላ ታስበኛለች መሰለኝ፣ ልቡ ጠጣርና ድድር ነው ብላ ትወስደኛለች መሰለኝ፡፡ በር የሌለው ህንፃ ነው! ብላ ትገምተኛለች መሰለኝ ፣ መሰለኝ… ያው መሰለኝ ነው!
ለእኔ ደግሞ የመውደድ ተግባራዊነት እንጂ አፋዊነት አይገባኝም፡፡ የፍቅር ተግባራዊነቱ ደግሞ ከአፋዊነቱም በላይ ልቡና ብራና ላይ የሚታተም አርማ ነው፡፡ ሰዎች ሁሉም ነገር የመሃላና የምስክር ማህተም ያስፈልገዋል ብለው ያስባሉ፡፡ አንተ እየማልክ እንድትለፈልፍና ቅዱሱን መፃህፋቸውን በመዳፍህ እየተመተምክ እንድታረጋግጥላቸው ይሻሉ፡፡ በዚህም አይበቃም፣ ሌሎች እንዲሰሙት ማድረግና እንዲመሰክሩልህ መሆን አለበት!
አትቆጣም፡፡ … ድምጽዋን እንኳ ከፍ አታደርግም፡፡ አፈጥባታለሁ፡፡ አንገቷ ስር (ከማጅራቷ አካባቢ) አጠር ብለው የሚንጨባረሩትን ቀያይ ፀጉሮች በጣም ነው የምወዳቸው፡፡ የናና ቅጠል መሳይ ከንፈሮችና የፈረስ ጭራ የመሰሉ የአይን ቆቦቿ መገለጫ የላቸውም፡፡ በፍጥነት ስታወራ ደግሞ … የሸንኮራ ዘሃ መሳይ ደቂቅ ምራቋ ሲፈናጠር በአየር ውስጥ በአይኖቼ እከተለዋለሁ፡፡ እናም በማይክሮስኮፕ የደም ሳምፕል እንደሚመለከት ባለሙያ  አትኩሬ በትጋት እቃኛለሁ፡፡
‹‹…አንተ?!…›› ትላለች በመገረም ...
‹‹..ወዬ! ማር..›› ድንግጥ ብዬ
‹‹…ኤጭ … ማር አትበለኝ! ሰው ስላለው ብቻ አንተም እንዲያ ልትለኝ አይገባም፡፡ አያምርብህም! ማር ስትለኝ ገበሬ የሆንክ ይመስለኛል፡፡ ማር ስትለኝ፣ እኔ ለመላስና ለመቀመስ ብቻ የተሰራሁ ይመስለኛል…››
አቋሞቿ እንደ ዲያስራ ፖለቲከኛ ግራ ያጋቡኛል፡፡ ነገሯ ሁሉ እንደ አይጥ ወጥመድ ነገር ነው፤ ተናገር ተናገር ትለኝና፣ በምናገረው ነገር ቀብ አድርጋ ትይዘኛለች፡፡ ቢሆንም ፊት ለፊቷ ጠጋ ብዬ ሳወራት፣ እስትንፋሷ ሜንት ሜንት ይላል። የራሴ ትንፋሽ እንኳ እንዲህ አይጥመኝም።  አይኖቼን ለመጨፈን እፈልጋለሁ፡፡ ከዚያ ቀስ ብዬ፣ ነገር ግን በጥልቀት የአካባቢውን አየር መተንፈስ እመኛለሁ፡፡   
‹‹…አጠገብህ እያለሁ እንደሌለሁ አታድርገኝ  አ … ል! …››
‹‹እሺ! እናት… ግን...››
‹‹…እንዴ ምንድነው? ደግሞ ምንጊዜ ቀየርከው! ቅድም ማር፣ አሁን ደግሞ እናት … ሆሆይ!›› ትገረማለች፡፡ እኔ ፈገግ እላለሁ፡፡
ይህ ነገር ምንድነው? እላለሁ በመገረም፡፡ በእውነት ስለምትወደኝ አይደለም እንዴ ይህቺን የመሰለች ልጅ አብራኝ ጊዜዋን የምታሳልፈው? ባትወደኝስ እዚህ ምን ትሰራለች? ባትወደኝስ ለምን ትከራከረኛለች? ባትወደኝስ ለምን ትነዘንዘኛለች? ከረጅም ጊዜ የብቸኝነት ጉዞ በኋላ የፍቅር ምርኮዬንና ኮተቴን ሁሉ ያሳረፍኩባት ወደቤ ናት፡፡ ያሳረፍኩባትን የፍቅር ሸክም ከዚህ ወደብ ላይ አንስቼ ወደ ሌላ ልጭነው አይቻለኝም። ከአቅሜም ከፍላጎቴም በላይ ነው፡፡ (ፈገግታዬ ፊቴ ላይ ይፈነጥቃል!)
‹‹ምን ያስቅሃል!?…›› ኮስተር ትልብኛለች፡፡
‹‹ምንም ማ…›› እተወዋለሁ፡፡ ታፈጣለች፡፡
በእውነት ከማርና ከፅጌረዳ በላይ ነው የማስባት፡፡ ታዲያ ምን ብዬ ልግለፃት!? ሰው ሁሉ የሚያፈቅረውን እንዲያ እያለ ሲጠራ ነው የሰማሁትና፣ ያንኑ ነበር የምደግመው፡፡ የፈጣሪ ያለህ! ፍቅር ሁሉ መጽሃፍ ላይ እንደማነበው ይቀልለኛል ብዬ ነበር የማቅደው፡፡ ፍቅር ቅድሚያ የሚፈልገው ነገርም የራሴን የታመነና እውነተኛ ልብ ብቻ ነው ብዬ አስብ ነበር፡፡ ነገር ግን ከዚያም በላይ ነው፡፡ ፍቅር ሁለት የማይተዋወቁ ወቅቶች አንድ ለመሆን የሚጥሩበት የእብድ አለም መሰለኝ። ክረምት ዝናቡን፣ በጋ ደግሞ አቧራና ፀሃዩን አዋጥተው ቀኑን ለማሳመር የሚያደርጉት ፀሃያማ፣ ንፋሳማና አቧራማ የጨረባ ተዝካር የዋለበት ቀን፡፡  ካጎነበስኩበት ቀና ብዬ አያታለሁ። የፅጌረዳ አበባ የሚመስለው የታችኛው ከንፈሯን ነክሳ፣ አይኖቿ ሳታርገበግብ ተክላብኛለች፡፡
በሁኔታው እንዳልዝናና ትቆጣለች፣ ዝም ስል ትነተርከኛለች፣ ሳወራ ይጨንቀኛል፡፡ በፊት በፊት አብሬያት ለመጓዝ ሳስብ እንኳ፣ ሰው ሁሉ የሚታዘበኝና እኔን የሚመለከተኝ እየመሰለኝ እፈራለሁ፡፡ እደነግጣለሁ፡፡ አሁን ቢያንስ አብሬያት ሆቴልና ካፌ መቀመጥ ችያለሁ፡፡ ጥቂት አወራታለሁ፡፡ ሲደብራት ትሰማኛለች። ካልፈለገች ትዘጋኛለች፡፡ ዝምታዬ ለእኔም እየከበደኝ ሲመጣ ለማውራት መጣጣር ጀመርኩ፡፡ ጥቂት ወይን ከወሳሰድኩ በኋላ ወሬዬን መቆጣጠርና ምላሴን መግታት የተሳነኝ ይመስል እንዲህ እላታለሁ፡-
‹‹…የአፄ ቴዎድሮስ ታማኝ የነበረው ገብርዬ አንድ ጊዜ እንዲህ አደረገ፡፡ አፄውና ባለቤታቸው ሲነጋገሩ ባለቤትየው አፄውን ስትሰድባቸው ይሰማል፡፡ ከዚያ …. ከቀኝ ጎኑ ጎራዴውን ላጥ አድርጎ…››
‹‹በቃ በቃ በቃ!…›› እነዚያን የስዕል እርሳስ የሚመስሉ ጣቶቿን በአየር ላይ ትሰነዝርና ታስቆመኛለች፡፡ ከንፈሬን በጠቋሚ ጣቷ ደምስሳ ለደቂቃ ትይዝና ትቆያለች፡፡ በዚያች ደቂቃ ደግሞ እንቅስቃሴዎች ይቆማሉ፣ የልብ ምቴ ለብቻው ከፍና ዝቅ ሲል ልቤ ደረቴ ስር ትንፈራፈራለች፤ የቀዘቀዘው ደሜ ደግሞ በጠበቡት ቱቦዎች ውስጥ ለመፍሰስ ይታገላል፡፡
ቀና ብዬ ሳያት አይኖቿ ላይ በሚያንፀባርቁ የእንባ ነቁጦች መሃል ሰንጥቃ ታየኛለች፡፡ እናም …  ‹‹…ግሎባላይዝድ የሆነ ወሬ አውራኝ፡፡ ትራጀዲ አታውራ፣  አስቀኝ … ዘመኑ ራሱ ትራጀዲ ነውና አንተ ጨዋታህን ኮሜዲ አድርገው፡፡››
ከንፈሮቿን እንደ ቢራቢሮ ክንፎች እርግብግቦሽ በጥንቃቄ አስተውላለሁ፡፡ እናም በትካዜዬ መሃል ድንገት ጥሩ የሚመስል ጨዋታ ብልጭ ያለልኝ ይመስለኛል  ‹‹…አንድ ጊዜ አልበርት አንስታይን ህፃን ሆኖ እያለ…›› እያልኩ የወሬ አትሮኑሴን ስዘረጋ በፈገግታና በመኮሳተር መሃል ሆና …
‹‹…አልዬ!…›› በለስላሳና በሚያባብል ድምፅ ‹‹…የአልበርት አንስታይንን ሳትነግረኝ በፊት፤ መጀመሪያ ያንተን ህፃንነት አውራኝ?…››  
ተስፋ እቆርጣለሁ፡፡ እኔ ምን የሚነገር ህጻንነት አለኝና ነው፡፡ ዘንግ የመሰሉ እግሮቼን ቂጡ እንደ መነፅር በተከፈተ ቁምጣ ውስጥ ሸጉጬ የሮጥኩባቸውና አፈር መስዬ የጨርቅ ኳስ ሳነጥር የኖርኩት ህፃንነት ምኑ ይወራል፡፡ የጎማ ጥልፍልፍ ሸበጥ እግሬ ላይ መስመር ሰርቶ እየቀደደኝ ያደግሁበትና የጭቃ ግድቤን ስገነባ የኖርኩበት ህጻንነት ምኑ ይተረካል! ብዬ እጨነቃለሁ፡፡ የኔታ እንኳ ቀለም አይዘልቅህም፣ ወሬ አይዋጣልህም ይሉኝ ነበር፡፡ ዝም በል! እያሉ ደጋግመው ያሳረፉብኝ አለንጋ እንኳ ይኸው ጀርባዬ ላይ መስመሩ ደምቆ አብሮኝ  አለ፡፡ እናም ዝምታ በህጻንነቴ ከየኔታ አለንጋ፣ በጉርምስናዬ ደግሞ  ከኮረዶች ትረባ ማምለጫዬ ነው፡፡
ወደ ልቡናዬ ስመለስ ወሬዬን ሁሉ አቁሜ እተክዛለሁ፡፡ ለአርባ ደቂቃ ያህል ተኳርፈን እንቆይና ወደየቤታችን እንለያያለን፡፡ ከቤታቸው በር ላይ ስሸኛት ፊቷን አዙራ በኮብልስቶኑ ላይ እየነጠረችና ቱቦ እየዘለለች ስትሔድ ሳያት … በህልሜ ይመስለኛል፡፡ ለሩብ ሰዓት ያህል ከዚያች ከተተከልኩባት ቦታ አልነሳም፡፡ ጥበቃ እንደቆመ ወታደር አይኖቼን አድማሱ ስር ሰክቼ እቆያለሁ። በልቡናዬም … ዋ ቁንጅና! ዋ ፍቅር! ዋ ስስትና ናፍቆት! ዋ ዝምታ! እላለሁ፡፡
እናም በዚያች ደቂቃ እንዲህ አስባለሁ፡፡ አሁን እንዲህ ተማምኜ ከቆምኩበት የፍቅር መራዥ ከፍታ ብወድቅ የት አርፋለሁ! (አሁን ደጋግሞ ይቆጨኛል፤ ማሰብ ነበረብኝ፡፡) አያድርገው እንጂ እሱን ከማሰብ ይልቅ በአብሮነት ስላሉት ቆይታዎች ብቻ ነው ጊዜ ሰጥቼ  የማሰላስለው፡፡ ግና ስህተት ነበር፡፡ የቆመ ሁሉ ስለ መውደቅ ማሰብ አለበት፡፡ በልቤ ግን ሁልጊዜ ደጋግሜ እላለሁ … አልወድቅም! ኸረ በጭራሽ አልወድቅም!
***
ዝንተ ዓለም የማስብ የነበረው እንግዲህ ያንን ነው፡፡ … እና በዚህች ደቂቃ ሰውየው በእጁ የያዘውን መጻፊያ (እርሳስ ወይ እስክርቢቶ ወይ የስልክ መጫሪያ ነገር…) እያወዛወዘና ከጠረጴዛው ላይ እያንገጫገጨ ይለፈልፋል፡፡ በየሰከንዶች ልዩነት ጠረጴዛውን … ቋ! ቋ! ቋ! … እያደረገ የክፍሉን ፀጥታ ያደፈርሳል፡፡
ድንገት አካባቢዬን የሚያጨልም ክረምትና ጥቁር ዳመና ከበበኝ፡፡ በጭንቅላቴ ውስጥ ትልልቅ የመብረቅ ብልጭታዎች ተከሰቱ (ቀጥሎ የሚከሰተው እንዲህ እንደሚሆን በልቤ አውቃለሁ (ሰዎች እንደነገሩኝ!) … ቀጥሎ የሚሆነው … ከእጅ ላይ እንደወደቀ ነጠላ እጥፍጥፍ ብዬ እወድቃለሁ፡፡ እንደ ጨፋ ወንዝ ዳርቻ ጥቂት አረፋዎች ያስደፍቀኛል፡፡ ዝንት ዓለሜን እረሳና በሰማያት እቀዝፋለሁ፡፡ መቅኒዎቼን የሚጨምቅ ቅጥቃጤ ይዘምትብኛል፡፡ ከግማሽ ሰዓት በኋላ በባዶ ጭንቅላትና በሚወቅር ራስ ምታት ሰልፈኛ ታጅቤ ወደ ምድር እመላሰላሁ፡፡ የት ነበርኩ?  ምን ተፈጠረ እላለሁ?
ቀስ እያለ በደበዘዘው እይታዬ ውስጥ ነጭ ለባሹ ሰውዬ ከመቀመጫው ዘሎ ሲነሳ ይታየኛል። ቀጥሎ ወደ እኔ ሲንደረደር ብዥዥዥ …. የሚል እይታ የሚሰጡኝ ቅንድቦቼ፤ ከትልቅ የበርሜል ብረት እንደተሰራ በር ጥርቅም ብለው ይዘጋሉ፡፡ በዚያች ቅንጣቢ ሰከንድ አናቴ ውስጥ ፍንዳታው ተከስቶ ነበር፡፡
ከፍንዳታው ቅንጣት ሰከንድ በፊት ሰውየው ‹….ነርስ!… ነርስ!…› እያለ ሲጮህ የሰማሁት ይመስለኛል፡፡ እጆቼ እንደተጠፈሩ እያንዳንዱ ሴሎቼ በውጥረት ሲነረቱ ይታወቀኛል፡፡ ከምድር የከበደ የመከዳትና የመተው! (ጠብቆ ይነበባል!) ታሪኬን ላለማመን እየታገልኩ፣ በተቆፋፈረ መንገድ ኩርባ እንደሚዞር ኤኔትሬ እንገጫገጫለሁ። ቀጫጫ እጆቼ ካቴናዎቹ ውስጥ እንደ ብሎን በቀስታና ልብን በሚሰልብ ህመም ይጨመቃሉ፤ ከዚህ ሁሉ በኋላ ግን  በሚያንዘፈዝፈው ቅጥቃጤ እየተሰበቅሁ፣ ወደ አጨናናቂው ህይወት ብቅ እላለሁ፡፡ ይኸው ነው፡፡ ሳልዘጋጅ ከከፍታ ወድቄያለሁ፣ ተጋልጫለሁ፣ የተዘጋውን የራሴን ዓለም ድንገት ለሚበረግድ አውሎ ነፋስ ከፍቼ ስለሰጠሁ፣ በሮቼ ተገነጣጥለዋልና በምላሴ ሸሽጌ የማቆየው ሚስጥር የለኝም፡፡ (ሁሉም አውቆታልና ሁሉንም የማላይበት ቦታ መኖር እመኛለሁ!)
ግን አሁንም አጥብቄ ዝም እላለሁ፡፡ ዝም!!

Read 3451 times
More in this category: « ዳቦው ውሻው »