Sunday, 05 August 2018 00:00

ቀና ቀናውን ለማሰብና ለመማር የሚጠቅም የጠ/ሚ አብይ ጉብኝት

Written by  ዮሃንስ. ሰ
Rate this item
(7 votes)


 • የአገራችንን የፖለቲካ “ዲፎልት ሴቲንግ”፣... ከመጨለምና ከመጥመም ልማድ (ከአዙሪት ዲፎልት) አላቅቆ፣ ወደ ብሩህና ወደ ቀና የአስተሳሰብ ቅኝትና ወደ ስልጣኔ አቅጣጫ ለማሻሻል፣....
 • ከመጠውለግና ከመውረድ “የአዙሪት ሴቲንግ” አውጥቶ፣ ሕይወትን ወደሚያለመልምና የመንፈስ ክብርን
ወደሚያቀዳጅ ከፍታ ለማሳደግ፣... ተጨማሪ አቅምን የፈጠረ አስገራሚ ጉብኝት ነው።
          
    አብዛኛው ሰው፣... ጨዋነትንና ቅንነትን የማፍቀር፣ ሰውንና ህግን የማክበር በጎ ምኞት እንዳለው፣ በእውን፣ በድምቀትና በጉልህ የማየት ድንቅ እድል ሰጥቶናል - የዶ/ር አብይ የአሜሪካ ከተሞች ጉብኝት።
ለአገራችንና ለሁላችንም ኢትዮጵያውያን ጤንነት የሚበጅ የህክምና ጉብኝት ነው ማለትም ይቻላል - በተለይ ደግሞ፣ ለሁሉም ፖለቲከኞች፣ ለሁሉም ምሁራንና ለሁሉም ጸሐፊዎች፣... ማለፊያ የህክምና አጋጣሚ ነው።
በእርጋታም ሆነ በውጥረት ጊዜ፣ በአስደሳችም ሆነ በአሳዛኝ ወቅት ሁሉ፣ ዛሬም ነገም፣ አእምሯችን ሁሌም እውነትን በፅናት ሊጨብጥ እንደሚገባ፣ ብሩህ መንገድ ወለል ፍንትው ብሎ የታየበት ጉብኝነት ነውና። በዚሁ የጉብኝት ወቅት በግላጭ ያየነው ትልቅ እውነት፣... አብዛኛው ሰው፣ ቀናነትንና ጨዋነትን የሚመኝ መሆኑን ነው። ይህ ትልቅ እውነት፣ በአእምሯችን ውስጥ የሁልጊዜ እውቀት እንዲሆንልን፣ ሁልጊዜም ይህንን ደማቅ እውነት እንድናገናዝብ በማገዝ፣ ጤንነትን የሚያስተምር በመሆኑ፣... መቼም ቢሆን ይህንን ትልቅ እውነት እንዳንዘነጋውና ወደ ተለመደው “የአዙሪት ሴቲንግ” እንዳንንሸራተት፣ ተመልሰንም እንዳንወርድ፣ ጥንቃቄን የሚመክር በመሆኑ፣ የጤንነትና የህክምና ጉብኝት ነው።
ሁሉም ፖለቲከኞች፣ ሁሉም ምሁራንና ሁሉም ጸሐፊዎች፣... የብዙ ሚሊዮኖችን የቅንነት ምኞት ቸል እንዳይሉ፣... እንደወትሮው፣ ከተረብና ብሽሽቅ ጀምሮ፣ ወደ መሰዳደብና መወጋገዝ፣ ወደ መወነጃጀልና መናቆር፣ ወደ መጠላለፍና መጠፋፋት አዙሪት ውስጥ እየተንሸራተቱ እንዳይገቡ፣ የድጋፍ ስጦታ ነውም ማለት ይቻላል።
ግን ከዚያም በላይ ነው። ወደባሰ አደገኛ የፅልመት አዙሪት ላለመውረድ ብቻ ሳይሆን፣ ወደተሻለ ብሩህ ከፍታ ለማደግ፣.... ወደ ህሊና፣ ወደ አእምሮ፣ ወደ ሰውነት ይበልጥ እንዲያተኩሩ፣ እጥፍ ድርብ ብርታትን ይሰጣቸዋል። መልካም ምኞትን ይናኝላቸዋል። በዚያውም ልክ፣ ከባድ አደራም ጭምር ነው የሚያስረክባቸው።
አዎ፣... “እውነታውን መቼም ቢሆን አንዘንጋ፣ እውነታውን ሁልጊዜ እንገንዘብ” የምለው ለምን እንደሆነ ይገባችኋል። ...
በብሽሽቅና በመናቆር እልህ አማካኝነት እየተባባሱ የተከሰቱ አሳዛኝ ውድቀቶችና አደገኛ የቁልቁለት ውድቀቶች፣ በጣም አሳሳቢና አስጨናቂ እንደሚሆኑብን ቢታወቅም፣ ምንኛ በፍጥነት እንደሚዘነጉ፣.. በተደጋጋሚ ታዝባችኋል።
የቀናነት፣ የጨዋነት፣ የሰው አክባሪነት፣ የህግ አክባሪነት ብሩህ የስልጣኔ መንገዶች፣ በየእለቱ እንደልብ የማይፈጠሩ፣ ግን ደግሞ በዚያው ልክ ምንኛ ያማሩና ምንኛ ብርቅ ድንቅ እንደሆኑ ብናይም እንኳ፣... እንደዋዛ፣ በምን ያህል ፍጥነት እንደሚዘነጉና ቸል እንደሚባሉም በተደጋጋሚ የታየ፣ የኢትዮጵያም፣ የአለምም ታሪክ ነው። ያለምክንያት አይደለም።
ወደ ብሩህና ወደ ቀና፣ ህይወትን ወደሚያለመልምና ሰው የመሆን ክብርን ወደሚያቀዳጅ ትክክለኛ የአስተሳሰብ ቅኝት ማደግና ወደ ስልጣኔ ጎዳና መራመድ፣... ከባድ ስራ ነው። መቼም የማይታክት አስተዋይነትንና አገናዛቢነትን፣ ሁልጊዜ በእውነትና በእውቀት የሚፀና ብሩህና አሳቢ አእምሮን ይጠይቃል። ይሄ ቀላል ስራ አይደለም። ይህም ብቻ አይደለም። በማይረግብ ትጋት፣ በመልካም ጎዳና ለመልካም ውጤት የመስራት ጥረትን ይጠይቃል - በትክክለኛ አቅጣጫ ወደ ከፍታ ለመጓዝ። የሞራል መልህቅን የጨበጠና በህይወት ዘመን ሁሉ የሚቀጥል ጉዞ ነው ብለዋል - ጠ/ሚ አብይ። ይሄ ቀላል ስራ አይደለም።
ይህም ብቻ አይደለም። ራስን የመግዛት ጥንቃቄንና ራስን ወደ ላቀ ብቃት የማሸጋገር ለውጥን ይጠይቃል። የኦሮሚያ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ እንዳሉት፣ የመሻሻል ለውጥ፣ የብልፅግናና የስልጣኔ ጉዞ የሚጀመረው፣ እያንዳንዳችን ራሳችንን ለማሻሻል በምናደርገው ለውጥ ነው። ይህም ቀላል ስራ አይደለም።
በተቃራኒው፣ የመጨለምና የመጥመም፣ የመጠውለግና የመውረድ አዙሪት፣ እንዲሁም ወደ አዙሪት ያስገባን የተሳሳተ የአስተሳሰብ ቅኝት፣... ምንም ጥረት አያስፈልገውም። ጠ/ሚ አብይ እንዳሉት፣ የተለመደው ነባር አቅጣጫ፣ በጣም ቀላል ነው።
በአጭሩ፣ ብሩህና ቀና የስልጣኔ ጉዞ ግን፣ ከባድ ስራ ነው። የውድቀት አዙሪት ጥረትን አይጠይቅም።
እስከዛሬ እንዳየነው፣ የአገራችን በርካታ ፖለቲከኞች፣ ምሁራንና ጸሐፊዎችን፣ ለበርካታ ለዘመናት ምርኮኛ ባደረገው የተለመደ አዙሪት ለመቀጠልና ቁልቁል ለመውረድ ምን ጥረት ያስፈልገዋል? አይንን መጨፈንና በዘፈቀደ መንሸራተት ብቻ!    
ወደዚህ አዙሪት የሚጎትቱና ምርኮኛ የሚያደርጉ ሰበቦች ደግሞ ሞልተዋል። “ያኛውን ብሽሽቅ በድል ሳላጠናቅቅማ፣ ያኛውን ነቆራ በበላይነት ሳልዘጋማ፣ ያለዳኝነት በአየር ላይ የሚካሄድ ያኛውን የመወነጃጀል ሙግት በአሸናፊነት ሳልደመድምማ፣... በአፍታ ይህንን አዙሪት በበላይነት አጠናቅቄ፣... ከዚያ በኋላ በብሩህ የቀናነት መንገድ”... የሚል ስሜት በርካቶችን ያታልላል። ነገ ወደ ብሩህ ቀና መንገድ ለመደመር ብሎ... ዛሬ ወደ ብሽሽቅ? ለዛሬው ብሩህና ቀና የመደመር መንገድ በመቆርቆርም... ነገ ወደ ብሽሽቅ? እንዲህ ያታልላል።
የብሽሽቅ፣ የመወነጃጀልና የመናቆር አዙሪት፣ ለዘመናት ገንኖ ያለማቋረጥ ከመስተጋባቱና ከመራገቡ የተነሳ፣ ማብጠልጠል፣ ማጣጣል፣ ማንቋሸሽ የበዛበት፣ እጅጉን የወረደ ጭፍንነት፣ እንደ መደበኛ የአስተሳሰብ ቅኝት ስለተንሰራፋ፣... ከእድሜው ጋርም ስፍር ቁጥር የሌላቸው የማመካኛ ሰበቦች መፈልፈያም ስለሆነ፣... ተዘውትሮ እየተነገረና እየተሰማ በጣም ከመለመዱ የተነሳ፣... በርካታ ፖለቲከኞች፣ ምሁራንና ጸሐፊዎችን በስሜታዊነት የሚማርክ አስቸጋሪ ልማድ ቢሆንባቸው አይገርምም። ለባሰባቸውም፣ እንደ ሱስ እስከመሆን ይበረታባቸዋል።
በአጭሩ፣... “ዲፎልት ሴቲንግ” ሆኖብናል - ለዘመናት የዘለቀ፣ የአገራችን የፖለቲካ “ዲፎልት ሴቲንግ”።
ይህንን መቀየር፣ ከባድ ስራ ነው። ከዚያም በላይ የሁሉም ሰው ስራ ነው። አቶ ለማ መገርሳ እንዳሉት፣ ራሳችንን በመለወጥ መጀመር አለብን።
ደግሞም፣ ቀናነት ከምንም በላይ ለየራሳችን ነው! ወደ ቀናነት መራመድ፣ ከሁሉም በፊት ለራስ ነው። “ወደ ቀናነት መራመድ” የሚል አገላለፅ የተጠቀምኩት፣... እንደ እውቀት፣ እንደ ሙያ፣... ቀናነትም እንዲሁ እያደገ፣ እየሰፋ፣ እየለመለመ የሚሄድ እንጂ፣ በእስከዛሬ ስህተትና ጉድለት ሳቢያ፣ ታስሮና ታጥሮ የሚቀር ጉዳይ አለመሆኑን ለማመልከት ነው። የእስከዛሬው ስህተታችን ምንም ቢበዛ፣... በዚያው ስህተት ውስጥ ተዘፍቀን እንድንቀር የሚያደርግ እርግማን አይደለም።
ከዛሬ ጀምሮ፣... ከእለት እለት፣ ከሳምንት ሳምንት፣ ከዓመት ዓመት፣... የየአቅማችን ያህል ለመሻሻል፣... ወደ ተጨማሪ አገናዛቢነት፣ ወደ ተጨማሪ ትጋት፣ ወደ ተጨማሪ ብሩህነትና ቀናነት መራመድ እንችላለን - በእውቀት ደረጃና በእውቀት ጉጉት ፣ በሙያ ክህሎትና በሙያ ፍቅር፣ በቀናነት ባህርይና በቀናነት ክብር፣... አንድ ሁለት እያልን፣ ደረጃ በደረጃ ሕይወትን ይበልጥ በሚያለመልም ብሩህና ክቡር የስልጣኔ ጎዳና መራመድ እንችላለን።
ለዚህ የሚያበረታታና የሚያነቃቃ ነገር ማግኘታችንም፣ መታደል ነው። መበርታትና መነቃቃት ግን የእያንዳንዳችን ድርሻ ነው። በየመስካቸው፣... በእውቀት፣ በሙያና በብቃት የላቁ ሰዎች ለማግኘት ስንታደል፣... አስተማሪ ሆነውልን እውቀትን ለመማር፣ አሰልጣኞች ሆነውልን ሙያን ለመካን፣ የብቃት አርአያ ሆነውልን ለላቀ ብቃትና ሰብእና ለመነቃቃት በጣሙን የተመቸ ይሆንልናል። ነገር ግን፣ ካላባከንነው ነው። ይህንን እድል ውጤታማ የምናደርገው፣ ለእውቀት አእምሯችንን በአገናዛቢነት የመጠቀም፣ ለክህሎት የመትጋትና ለብቃት የመቃናት የእያንዳንዳችን ሃላፊነት ከተወጣን ብቻ ነው። አእምሯችን ውስጥ ገብቶ ሊያገናዝብልን የሚችል አስተማሪ፣ ልምምድ የሚሰራልን አሰልጣኝ፣ ብቃትን እንደ ራሽን የሚያካፍለን ጀግና፣... የትም የለም፣ መቼም ሊኖር አይችልም። የሚያለማምደን እንጂ የሚለማመድልን አሰልጣኝ የምንፈልግ ከሆነ፣ ብርቅና ድንቅ እድልን እንዳባከንን ይቆጠራል።
በአጭሩ፣ የእያንዳንዱ ሰው የራስ ጥረት ያስፈልጋል - የእያንዳንዱ ሰው ራሱን የማሻሻል ለውጥ። ከሁሉም በፊት፣ አገናዛቢነት፣ ትጋትና ቅንነት ለራስ ነው። ይህ ጥረት ካለ፣ የሚያበረታታ ነገር አይጠፋም - ለምሳሌ፣ ሰሞኑን እንዳየነው፣ አብዛኛው ሰው ጨዋነትንና ቅንነትን እንደሚመኝ በድምቀት የሚያሳይ ጉብኝት፣ ትልቅ የመንፈስ ብርታት ነው - የኋሊት ላለመንሸራተትና ወደ ከፍታ ለመራመድ። በጅምር ላለመቅረት፣ ወደ ስልጣኔ የሚያዘልቅ ጉዞ ለመቀጠል!   
በየዘመኑ፣ የአገራችን ፖለቲካ፣... ፈካ፣ ቀና፣ ብቅ እንዲል በርካታ ሙከራዎችና ጀምሮች ታይተዋል። እንደየዘመኑ የእውቀትና የአቅም ደረጃ፣ በርትተው የጣሩ መሪዎችና ምሁራን አልጠፉም። ፈታኝነቱ፣... ወደ ተለመደው የጨለመ፣ የጠመመና የወረደ “ዲፎልት ሴቲንግ” እየተመለሰ ያስቸግራቸዋል። “የፖለቲካ ባህል”ን መቀየር ከባድ ስራ ነውና።
የዛሬው ጅምር፣ ለአስር እና ለሃያ ዓመት ብቻ ሳይሆን፣ ለሃምሳና ለመቶ፣ እና ከዚያም በላይ እየተሻሻለ የሚቀጥል የስልጣኔ ጉዞ እንዲሆን የሁሉም ሰው ጥረት ያስፈልጋል። ለዚህ ጥረት ተጨማሪ ብርታት ማግኘት መታደል ነው። የዶ/ር አብይ ጉብኝት፣ ለጥረትና ለትጋት፣ ለብሩህነትና ለቅንነት፣ ለሰው አክባሪነትና ለህግ አክባሪነት ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር ጉብኝት ነው። አብዛኛው ሰው፣... ቅንነትንና ጨዋነትን የሚናፍቅ፣ ሰውንና ህግን የማክበር ፍላጎትን የሚመኝ መሆኑን፣... በሃሳብ ደረጃ ብቻ ሳይሆን፣ በአካል በአይን ያየነው ደማቅና ትልቅ እውነት መሆኑን፣ ሁልጊዜ እንገንዘብ፣ መቼም ቢሆን አንዘንጋ።

Read 2007 times