Print this page
Saturday, 04 August 2018 10:47

እየተስተዋለ የሚኬድ መንገድ!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(5 votes)


    እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…በዚህ ክረምት የዚች ከተማ፣ የአንዳንድ እህቶቻችን አለባበስ ግርም የሚል ሆኗል፡፡ (እግረ መንገድ… ‘ሴት እህቶቻችን’ የሚሉት አገላለጽ ላይ ማብራሪያ ይሰጠንማ! በቀደም ሰዎች ሲጠይቁ  ስለሰማን  ነው።)
እናላችሁ…“ዶፉን ሊያወርደው ይችላል” የለ፣ “ብርዱ አይደለም ሰው፣ አገር ያደርቃል” ብሎ ነገር የለ… ብቻ ከውስጥ ሱሪ ትንሽዬ ረዘም ያለች ብጣሽ ጨርቅ ጣል አድርጎ መውጣት ተለምዷል። (ወላ… “አሁን ይቺ ቲንኤጀር ጂንስ ምናምን ብትለብስ የለ… ወላ “ሲክስቲ ፕላስ ምናምን ሆና መሬት የሚጠርግ ቀሚስ በመልበሻዋ…” የለ!
ወይ አዲስ አበባ ወይ አራዳ ሆይ
የጣቃ ጨርቅ እጥረት አስቸገረሽ ወይ
ብንል አይፈረድብንም! አሀ…ቢያንስ ሬስቱራንቶች ውስጥ ሳንሳቀቅ ዓይናችንን ዝቅ ማድረግ እንፈልጋለና!)
እግረ መንገድ…ይሄ የቁንጅና ውድድር ላይ ሰፋ ያለች መሀረብ የምታካክል ጨርቅ ጣል እያደረጉ መድረክ ላይ ወዲህ፣ ወዲያ የሚሉት ነገር አለ አይደል…ብዙ ተቃዋሚዎች ነበሩት። ሴቶቹን በሱቅ መስኮት እንደሚደረደር እቃ ማየት ነው የሚሉ ብዙ አሉ፡፡ ሰሞኑን የሚስ አሜሪካ አዘጋጆች በውድድሩ ጊዜ በዋና ልብስ የሚደረገውን ክፍል “ሳንተወው አይቀርም” እያሉ ነው፡፡ ምክንያቱም የሴቶችን ክብር የሚያዋርድ ነው ተብሏልና፡፡ እኛ ዘንድ እህቶቻችንን ለዋና ልብስ በቀረበች ቢጢሌ ጨርቅ ለማየት የግድ የቁንጅና ውድድር አያስፈልገንም፡፡ የፒያሳና የቦሌ መንገዶች የት ሄደው ነው!
ስሙኝማ… እንግዲህ ያለንበት ጊዜ ስለ ለውጥ የሚወራበት ሰሞን አይደል … ቃለ መጠይቅ፣ ትንታኔ፣ ‘ፖለቲካ 101’ ምናምን እየከሰከስን ነው። “ሎካል ቴሌቪዥን ከማይ አንደኛውን የአእምሮ ሀኪም ቤት ብገባ ይሻላል” ስንል የነበርነው ሁሉ አይደለም ኋላ ላይ የመጡትን፣ አንድ ለእናቱ የነበረውንም ጣቢያ ማየት ጀምረናል፡፡ (ይሄ ነገር ለምንድነው በድንቃ ድንቅ መዝገብ ላይ የማይሰፍርልን!)
እናላችሁ…የተንታኙ ብዛት፣ የ‘ምሁራዊ ገለጻ’ አቅራቢው ብዛት፣ ‘እንዲህ ሊበራሊዝም’፣ ‘እንደዛ ምናምኒዝም’ የሚሏቸውን ነገሮች ሽቅብ የሚሰቅልና ቁልቁል የሚያፈርጠው ብዛት…ምን አለፋችሁ፣ የእኛው ‘ሪያሊቲ ሾው’ በሉት፡፡ አሪፍ ነው…አለ አይደል… ሁሉም ሀሳቡን መግለጽ ሲችል አሪፍ ነው። ታዲያላችሁ…በዚህ መሀል፣ አሁን ‘እንደ ትናንት’ እየቆጠርነው ባለ ጊዜ ሲስቅ የኖረም፣ ሲያለቅስ የኖረም ‘በደሉን’ የሚገልጽ መአት ነው፡፡
ግን ምን ኮሚክ ነገር አለ መሰላችሁ… ምንም ሲጎድለበት ያላየነው፣ ግድግዳው እንደተፈረፈረ ጭቃ ቤት አጥንቱ አደባባይ ሲወጣ ያላየነው ሁሉ…“ከሰው ዝቅ ከእንስሳት ከፍ” ብሎ ሲኖር የቆየ ተበዳይ ሆኖ እያየን ነው፡፡
በየቀኑ ሲደንስና ወላ ቺቺንያ፣ ወላ ‘አዲሱ ቦሌ’ ሲጨፍር፣ እንትናዬዎች ሲያማርጥ (እነሱም ‘ሲያማርጡት፣’ ቂ…ቂ…ቂ…)፣ ዱባይ፣ ባንግኮክ ምናምን እያለ ሲንሸራሸር የነበረው… “ያለፉት ሀያ ምናምን ዓመታት ኑሮ አይበለው!” ሲል ስንሰማው…አለ አይደል…ግራ ይገባል፡፡ “ኦ እውነት! የት ነው ያለሽው?” ብንል አይፈረድብንም፡፡
መኪናውስ!…መጀመሪያ ላይ “አቦ ሰፈሬ የምሄድበት የታክሲ ስጠኝ…” ከማለት በአስደናቂ ቅልጥፍና ተገለባብጦ ወደ ቤቢ ፊያት፣ ብሎም ወደ ቀስት፣ ብሎም ወደ ኮሮላ፣ ብሎም ወደ ወያኔ ዲ ኤክስ፣ ብሎም ወደ ራቭ ፎር…የተደረገው በመቶ ሜትር ፍጥነት ማራቶን የመጨረሱስ ነገር! ኸረ… ተሸፍነን ብንተኛም ገልጦ የሚያይ አንድዬ ይታዘባል!
አሀ… የደስታ ጡንቻዎቹ ሁሉ ሥራ አቁመው “ፈገግታ ማለት ምን ማለት ነው?” ሊል ጫፍ የደረሰው ምን ይበል! ሀሳብ አለን…‘የበሉበትን ወጭት መስበር’ በሚል በአይነቱ…አለ አይደል…ልዩና በ‘ቪ.ቪ.ቪ.ቪ.ቪ. አይ ፒ’ ደረጃ ኮንሰርት ይዘጋጅልን፡፡ (ከ‘ቪ.አይ.ፒ.’ አልፎ ‘ቪ’ መደጋገም መጀመሯን እያየን ስለሆነ ነው፡፡ ግን ‘ቪ’ እየተደጋገመች ከምንሰለች፣ ቪ10 እያሉ ይጻፉልን! በነገራችን ላይ ቪ.አይ.ፒ. ለመሆን ፎቅ ላይ መቀመጥ ብቻ ይበቃል እንዴ! ለማወቅ ያህል ነው።)
እናማ…ትናንት ሰዉን ከእነመፈጠሩ እንዳልረሳነው፣ መገናኛ ብዙሃንን፣ “ከበታቻችን ነው” የምንለውን ህዝብ ለማየት አጉሊ መነጽር ‘በትእዛዝ የሚሠራበትን’ ቦታ ለመጠየቅ ምንም ያልቀረን…አሁን ተሽቀዳድሞ “ካለፉት ዘመናት እዬዬ ብቻ ነው የተረፈኝ” አይነት ‘የአንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች አስተያየት’ ነገር ቀሺም ነው፡፡ አንድዬም እኮ ይታዘባል፡፡ “ሻኛህ ሲከመር፣ ዳሌህ ሲሰፋ፣ የባንክ ደብተርህ ቁጥር መጻፊያ ስፍራ ሲያጥረው… ህዝቡን ረስተህ፣ አገርን ረስተህ፣ እኔን ሁሉ ረስተህ ኖረህ ጭራሽ አሁን ተበዳይ ሆነህ አረፍከው!” ይላል።
ኮሚክ ነገር እኮ ነው… የእነሱ ኑሮ የምድር ሲኦል ምናምን ሆኖ ከኖረ፣ ሌላው ምን ይበል! ቆይማ…ከቀበሌ ቤት፣ ወደ ኮንዶሚኒየም፣ ከዛ ወደ አሪፍ አፓርትመንት፣ ከዛ ወደ ቪላ የተደረገው ‘ሽግግርስ!’ ያለ ጠፈር መንኮራኩር፣ ያለ ድሪምላይነር ---- ሳይንስ እስካሁን ባልደረሰበት ፍጥነት የተደረገው የሽቅብ ጉዞስ! የምር እኮ…የቀበሌ ቤት ከላይ ጣራው እያፈሰሰ፣ ከስር ጎርፉ እየረሰረሰ ሲኖር የነበረው፣ በእርግጥም ‘የምድር ሲኦል’ የሚሉት አይነት ህይወት ሲገፋ የነበረው፣ ያንን ያህል እሪ አላለም። የትናንት ምሬቱ የነገ ተስፋውን እንዳያጨልምበት ይፈልጋልና! የቂምና ቁርሾ መርዝን ከውስጣችን እናጥራ በሚባልበት ጊዜ … ያኔ ቪላ ደረጃ ተደርሶ ‘በዚህኛው ዘመን’ ደግሞ ቤተ መንግሥቱ ከእነ ነፍሱ ተፈልጎ ነው እንዴ!  (እኔ የምለው…አርቲስቶች እየተዘዋወሩ ጎበኙ ማለት እኮ “የጨረታው ሰነድ ነሃሴ ምናምን ተጫራቾች ባሉበት ይከፈታል” ማለት አይደለም፤ ቂ…ቂ…ቂ…)
እኔ የምለው… አንዳንድ ነገሮች፣ ልንላቀቃቸው ሲገባ፣ መቼም የሚለቁን አይመስሉም፡፡ ይሄ አንድ ነገር በተፈጠረ ቁጥር ቀድሞ ለመታየት መሯሯጥ፣ ጥቅም ያለው መስሎ ከታየም ቀድሞ የኬኩን ክሬም ለመጨርገድ፣ ቀድሞ ምናልባትም በህልም ብቻ ያለ የንጉሠ ነገሥትነት ዘውድ ለመጫን የሚደረግ ሩጫ አይለቀንም ማለት ነው! እንደምንሰማው ከሆነ፣ ወደ ፊያሜታ አገር ለመሄድ፣ ቀድሞ “አስመራ፣ አስመሪና!” ለማለት የውስጥ ለውስጥ ፍልሚያው ጦፏል ነው የሚባለው! እውነት ከሆነ… አይደለም በሚል የሚያጠራጠሩ ብዙ ምክንያቶችም  የሉንም… ይሄ መቼም ከማስተዛዘብም ወደ አሳፈሪነት ደረጃ የሚወርድ ነው፡፡
ስሙኝማ… እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ይሄ የግለሰቦች ስም ጉዳይ አስቸጋሪ እየሆነ ነው፤ በተለይ በማህበራዊ ሚዲያው ብዙ ሰዎች ስማቸው እየተነሳ “ይሄን አድርጓል”፣ “እንዲህ ፈጽሟል” ሲባል እናያለን፡፡ እንዲህ አይነት ነገሮች እኮ አሁን ደግፈናቸዋል፣ እኛንም አገርንም ይለውጣሉ እያልናቸው ካሉት ሀሳቦች ጋር ተቃራኒ ናቸው! ያለ ማስረጃ፣ ያለ ተጨባጭ ምክንያት የሰዎችን ስም አንስቶ መጣል እኮ አብሮ ከመኖር መርህ ጋር የሚጣጣም አይደለም! “ዘረኝነት ይጥፋ”፣ “ጎሰኝነት ታሪክ ይሁን” በምንልበት ጊዜ የግለሰቦችን ስም ከአካባቢ፣ ከጎሳ፣ ከብሔር ጋር ማያያዝ እኮ ልንሄድበት ጀምረናል ያልነውን መንገድ አቅጣጫ መሳት እኮ ነው!
እግረ መንገድ፣ ይቺን ስሙኝማ…አንድ ቀን፣ አንድ ሰው መጣና ሶቅራጥስን “ስለ ጓደኛህ ገና አሁን ምን እንደሰማሁ ታውቃለህ?” ይለዋል፡፡
ሶቅራጥስም “አንድ ጊዜ ቆየኝ” ይላል፡፡ «ምንም ነገር ሳትነግረኝ በፊት፣ ‘የሦስት ማጣሪያዎች ፈተና’ የምለውን ማለፍ አለብህ” ይለዋል፡፡
“ሦስት ማጣሪያዎች?”
“ትክክል!” አለ ሶቅራጥስ፤ “ስለ ጓደኛዬ ለእኔ ከመንገርህ በፊት ጊዜ ወስደን ልትል ያሰብከውን ነገር ማጥለያ ላይ አድርገን ብናጣራ ጥሩ ይሆናል። የመጀመሪያው ማጣሪያ ‘እውነት’ ነው። የምትነግረኝ እውነት ለመሆኑ ሙሉ ለሙሉ እርግጠኛ ነህ?”
“ሙሉ ለሙሉ እንኳን እርግጠኛ አይደለሁም” ይላል ሰውየው፤ “እንደ እውነቱ ሲያወሩ ሰምቼ ነው…”
“ጥሩ” አለ ሶቅራጥስ፤ “ስለዚህ እውነት መሆንና አለመሆኑን አታውቅም ማለት ነው፡፡ አሁን ሁለተኛውን ማጣሪያ እንሞክር፡፡ ማጣሪያው ‘መልካምነት’ ነው፡፡ ስለ ጓደኛዬ የምትነግርኝ ነገር መልካም ነው?”
“አይደለም፣ እንደውም የእሱ ተቃራኒ ነው፡፡”
“እንግዲያው--» አለ ሶቅራጥስ፤ «ስለሱ የሆነ መጥፎ ነገር ልትነግረኝ ፈልገሀል፣ ግን እውነት መሆኑን እርግጠኛ አይደለህም፡፡ ግን አሁንም ፈተናውን ልታልፍ ትችላለህ፡፡  ምክንያቱም አንድ ማጣሪያ ቀርቷል፡፡ ማጣሪያው ‘ጠቃሚነት’ ነው። ስለ ጓደኛዬ የምትነግረኝ ነገር ለእኔ ጠቃሚነት ይኖረዋል?”
“እንደ እውነቱ፣ አይኖረውም” ይላል ሰውየው።
“ስለዚህ” አለ ሶቅራጥስ፤ “ልትነግረኝ የፈለግኸው ነገር እውነተኛ ካልሆነ፣ መልካም ካልሆነ፣ ጠቃሚነት የሌለው ከሆነ ለምንስ ብለህ ትነግረኛለህ?” አለው ይባላል፡፡ ብዙ ግለሰቦች ላይ ሲነሱ የምንሰማቸው ነገሮች እንዲህ ናቸው… እውነተኛነታቸው ያልተረጋገጠ፣ መልካም ያልሆኑና ለማንም ምንም ጠቀሜታ የማይሰጡ! እናማ…ነገራችን “ሳሩን አየህና ገደሉን ሳታይ” እንደሚባለው እንዳይሆን፣ ሁሉም ነገር እየተስተዋለ ቢሆን አሪፍ ይሆናል፡፡ ለሁላችንም የሚበጀው እየተስተዋለ የሚኬድ መንገድ ነውና!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 5814 times