Saturday, 04 August 2018 10:36

የጠ/ሚኒስትሩ የመደመር ጉዞ “የፖለቲካ ፈውስ የሚያመጣ ነው”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(14 votes)

 “ግንቡን እናፍርስ፣ ድልድዩን እንገንባ” በሚል መርህ ሰሞኑን በአሜሪካ ሦስት ግዛቶች ከኢትዮጵያውያን ጋር የተገናኙትና የተወያዩት ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፤ በስደት ላይ የሚገኙ አክቲቪስቶች፣ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች ወደ ሃገር ቤት እንደሚመለሱ ያስታወቁ ሲሆን ተቃዋሚዎችና ምሁራን በበኩላቸው፤በጠ/ሚኒስትሩ የተመራው የአሜሪካው የመደመር ጉዞ “የፖለቲካ ፈውስ የሚያመጣ በጎ ጅምር ነው” ሲሉ አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የ6 ቀናት የአሜሪካ ቆይታቸውን አጠናቅቀው ወደ ኢትዮጵያ እንደተመለሱ፣ በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ በሰጡት መግለጫ፤ በመጪው  አዲስ ዓመት ለበርካታ ዓመታት ከወገናቸው ተለይተው የኖሩ ፖለቲከኞች፣ አክቲቪስቶችና የሚዲያ ባለሙያዎች ወደ ሃገር ቤት እንደሚመለሱ አስታውቀዋል። በአሜሪካ ቆይታቸው ከዋነኛው ተቃዋሚ ድርጅት ግንቦት 7 ጋር ባደረጉት ሰፊ ውይይትም  መግባባት ላይ መድረሳቸውን የተናገሩት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ድርጅቱ በቅርቡ ወደ አገር ውስጥ ገብቶ ሰላማዊ እንቅስቃሴውን እንደሚጀምር ጠቁመዋል፡፡
በዋሽንግተኑ የፓርቲዎች ውይይት ላይ ተሳታፊ የነበሩት የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀ መንበር  አቶ የሸዋስ አሰፋ በሰጡት አስተያየት፤ ጠ/ሚኒስትሩ  በዋናነት የዲያስፖራውን የመብትና የፖለቲካ ትግል ሲመሩ ከነበሩ ታዋቂ አክቲቪስቶችና ፖለቲከኞች ጋር የፈጠሩት የፍቅር የይቅርታ ግንኙነት፣ ለሃገሪቱ ትልቅ የፖለቲካ ፈውስ የሚያመጣ በጎ ጅምር ነው ብለዋል።
 “ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁሉንም በስም እየጠሩ ነው ሰላምታ ሲያቀርቡ የነበረው” ያሉት አቶ የሸዋስ፤ዶ/ር ዐቢይ በአሜሪካ ባከናወኑት ተግባር ኢትዮጵያዊ ዲያስፖራውን ወደ አንድነት አምጥተውታል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ በዚህ ጉብኝት ላለፉት 27 ዓመታት የተገነባውን የጥላቻ ግንብ ማፍረሣቸውን የመሰከሩት የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀ መንበር፤ከዚህ በኋላም ሽግግሩን የእውነት በማድረግ ህዝብ በመረጠው መንግስት ብቻ የሚተዳደርበትና የሃገር አንድነት የሚጠበቅበትን መሠረት ማጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
አንጋፋው ፖለቲከኛና ምሁር ዶ/ር መረራ ጉዲና በበኩላቸው፤”ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሩ ዲፕሎማሲያዊ ስራ ሰርተዋል፣ ይህም ለሃገራዊ ብሄራዊ መግባባት አስተዋፅኦ ያደርጋል” ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል፤ የፖለቲካ ድርጅቶች የየራሳቸውን ህልሞች ይዘው ነው የሚመጡት ያሉት ዶ/ር መረራ፤ እነዚህ እርስ በእርስ የሚጋጩ ህልሞች በሃገሪቱ የፖለቲካ መድረክ ላይ እንዴት ይስተናገዳሉ የሚለው በጉጉት የሚጠበቅ ነው ብለዋል፡፡
በቅርቡ ከትግል አጋሮቻቸው ጋር “የኢትዮጵያውያን ሃገር አቀፍ ንቅናቄ” የተባለ አዲስ ፓርቲ የመሰረቱት ኢ/ር ይልቃል ጌትነት በሰጡት አስተያየት፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የህዝብን ፍላጎት ለማዳመጥ መሞከራቸውና ጥላቻን ለማሻር ጥረት ማድረጋቸው የሚደነቅ ነው ብለዋል፡፡ “ነገር ግን ይህ በራሱ ትልቅ ስኬት አይደለም፤ ለቀጣይ ለውጥ ግብአት ሊሆን ነው የሚችለው፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ጉዳዩን በዚህ መንገድ ነው መመልከት ያለባቸው” በማለት ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል።   
ህዝብ በሃገሪቱ እንዲመጣ የሚፈልገው ከአገዛዝ ወደ ዲሞክራሲ ስርአት ሽግግር የማይቀላጠፍ ከሆነም ለጠ/ሚኒስትሩ ያለው ድጋፍ  ላይቆይ ይችላል ሲሉም፤ ኢ/ር ይልቃል ስጋታቸውን ገልፀዋል፡፡
ከ8 ዓመታት እስራት በኋላ በቅርቡ የተፈታው ፖለቲከኛው አንዷለም አራጌ በበኩሉ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአሜሪካ ጉዟቸው ያከናወኑት ተግባር አንድነቷ የተጠበቀች ጠንካራ ኢትዮጵያን ለመገንባት ትልቅ መሠረት የሚጥል ነው ብሏል፡፡
“ሰው ስለ አንድነቱና ስለ ፍቅሩ በአንድ ላይ ሲዘምር ሲታይ ያስደስታል፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ እያሳዩት ያለው የሃሳብ ልዕልና የሚከበር የሚወደድ ነው፤ ትልቅነትን እያየሁባቸው ነው” ያለው ፖለቲከኛው፤ ዶ/ር ዐቢይ የሄዱበት  የፍቅር መንገድ ሁሉንም የሚገዛ ነው ብሏል።
የቀድሞው የአየር ሃይል አዛዥ ሜጀር ጀነራል አበበ ተ/ሃይማኖትም፤ በአሜሪካ የተደረገው የመደመር ጉዞ፣ ኢትዮጵያዊ ዲያስፖራውን ወደ አንድነት የሚያመጣና ለአገሩ በጎ አስተዋጽኦ እንዲያደርግ የሚያነሳሳ ነው ሲሉ ጠ/ሚኒስትሩ ያከናወኑትን ተግባር እንደሚደግፉት ለአዲስ አድማስ በሰጡት ቃለ ምልልስ  ገልጸዋል፡፡ በቀጣይም ሁሉን አካታች እንቅስቃሴዎች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ሲሉ መክረዋል - ሜጀር ጀነራሉ፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ፤ 26 በውጭ አገራት የሚገኙ የፖለቲካ ድርጅቶች ከጠ/ሚኒስትሩ ጋር ያደረጉትን ውይይት ተከትሎ ወደ ሃገር ቤት ገብተው የፖለቲካ እንቅስቃሴ ለማድረግ መወሰናቸውን የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የቀድሞ የደርግ ከፍተኛ ባለሥልጣን የነበሩትን ኮሎኔል ጎሹ ወልዴና የOMN ቴሌቪዥን ጣቢያ ባለቤት ጃዋር መሃመድን ጨምሮ በርካታ ተዋቂ ግለሰቦች ወደ አገር ቤት ይመለሳሉ ተብሏል፡፡

Read 9565 times