Saturday, 04 August 2018 10:29

ሰላምና መረጋጋት የፈጠረው ኢኮኖሚያዊ መነቃቃት

Written by  ተስፋዬ ታደሰ
Rate this item
(2 votes)

 ኢትዮጵያ  የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ስርዓት አቀንቃኝ ከሆነች 27 ዓመታትን አስቆጠረች። በእነዚህ ዓመታት ዲሞክራሲን ትካነው ዘንድ  በዜማ፣ በግጥምና በውዝዋዜ ሞክራዋለች፡፡ ዲሞክራሲ በሀገሪቷ ውስጥ ተዘርቶ፣ አብቅሎና አብቦ ፍሬ እንዲያፈራ የተደረጉት ልምምዶችና ትግበራዎች የማይካድና በብዙ መልኩ ሊመነዘር የሚችል አዳጊ ለውጥና  ውጤት አምጥተዋል።  ለውጡ ለውጥ እየፈለገ፣ እድገቱ  ሌላ እድገት  እየፈለገ፣ ስልጣኔው  ፍላጎትን እየጨመረ በመምጣቱ ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት የሀገሪቷ ሰላምና ፖለቲካ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ወድቆ ነበር፡፡ ሀገሪቷን ከወደቀችበት አደጋ ለማውጣት ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ በሰላማዊ መንገድ የአመራር ለውጥ አድርጓል፡፡ የመፍትሄ እርምጃው የአመራር አካላትን በመቀየር ተጀምሮ የአመራር ጥበብና የፖሊሲ ለውጥ ስለታከለበት ለሦስት ዓመታት በቀውስ፣ በአለመረጋጋት፣ በመጠራጠር፣ በስጋትና በመፈራራት ስትናወጥ የነበረችው ሀገር፤ በሦስት ወራት ውስጥ በፍቅር፣ በሰላም በመረጋጋት፣ በአንድነት፣ በይቅር ባይነትና በመደመር  ማዕበል ተናወጠች፡፡  ከመጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ  መንግስት ባካሄዳቸው የለውጥ እንቅስቃሴዎች የተገኘው ሰላም፣ መረጋጋትና አንድነት ያልገባበት ቤት፣ ያልጠለቀበት የሰው አእምሮ ስለሌለ በዚህ ዙሪያ ዝርዝር ነገር በመጻፍ፣ የአንባቢዎቼንም ሆነ የእኔን ጊዜ ማባከን አልፈልግም፡፡
ብጥብጥና የሰላም እጦት እንኳን ለሰውና ሀገር ቀርቶ ለእናቴ ጠላም አይበጅም፡፡ እኔ በተወለድኩበት አካባቢ አባባል፤ የዶሮ አይን የመሰለ የሚባለውና ብዙዎች ለመጠጣት የሚመኙት እናቴ የምትጠምቀው ጠላ፤ በስነ ስርዓት ካልተያዘና ከተበጠበጠ፣ ከሰው ጉሮሮ ሳይደርስ አተላ ነው ተብሎ  ወዲያውኑ ይደፋል፡፡
በአሁኑ ሰዓት ተቋማት ከተቋማት ጋር፣ ህዝቡ ከመንግስት ጋር በመቀናጀት የተጠናከረ የህግ ማስከበር ስራ እየተከናወነ በመሆኑ ሀገራዊ ሰላምና መረጋጋት አስተማማኝ እየሆነ መጥቷል፡፡ ይህም በመሆኑ የአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የምግብ ምርቶች ዋጋ መቀነስ እያሳየ፣ ሀገራዊ የግብይት ስርዓቱ እየተረጋጋ ይመስላል፡፡ የመልካም አስተዳደር ችግር ምንጭ ሆኖ የቆየው የመሰረታዊ ሸቀጥ አቅርቦትም፣ የነበሩበት የአቅርቦትና የስርጭት ችግሮች ተፈተው፣ በተቀመጠው አሰራር መሰረት እየቀረቡ ሲሆን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የዘለቀውን  የዳቦ ስንዴ አቅርቦት ችግር ለመፍታት በልዩ ትኩረትና በቅንጅት በመሰራቱ  መሻሻል እየታየ ነው፡፡
በህገ-ወጥ መንገድ የተያዙ የውጪ ምንዛሬ ገንዘቦች ወደ ባንክ መመለስ መጀመራቸው ሰላማችን ለኢኮኖሚያችን የሰጠው ሌላው ዋስትና መሆኑን መረዳት አያዳግትም፡፡ በአሁኑ ወቅት በቀን፣ በአማካይ 4 ሚሊዮን ዶላር ወደ ባንክ እየገባ ይገኛል፡፡ በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የተፈጠረውን ሰላምና መረጋጋት እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅመው፣ የሀገሪቷን ኢኮኖሚ ወደፊት ለማራመድ በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን አዎንታዊ ሚና ለመጫወት፣ የዲያስፖራ ትረስት ፈንድ ተከፍቶ፣ እያንዳንዳቸው  በቀን አንድ ዶላር  መለገስ  ጀምረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት ጋር የነበራትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በማጠናከር አስደማሚ ውጤት አስመዝግባለች፡፡ በተለይ ከኤርትራ ጋር ያወረደችው ሰላምና እርቅ በአርአያነት ተጠቃሽ እርምጃ ለመሆን በቅቷል፡፡ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የፈጠረችው ዲፕሎማሲያዊ  ግንኙነት አማራጭ ወደቦችን እንድትጠቀም ያስቻላት ሲሆን የወደብ አማራጮች መስፋት ደግሞ በሀገራችን ገበያና ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ጫና የሚፈጥረውን የሎጂስቲክስና የትራንስፖርት ወጪ ይቀንሳል፡፡ የዘንድሮው የክረምት ወራት ለግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ተስማሚ የሆነ ዝናብ ይዞ መጥቷል። ለእኛ ብቻም አይደል! ዝናብ በኤርትራ ምድር የወረደው የኢትዮጵያ አውሮፕላን 465 ሰዎችን ይዞ ኤርትራ ባረፈበት እለት እኮ ነው! የግብርናው ዘርፍ የኢኮኖሚያችን ነጭ የደም ህዋስ እንደመሆኑ መጠን ተፈጥሮ የለገሰችን የክረምት ዝናብ በቀጣይ የግብርናውን ምርት ያሳድጋል፤ይህም ተጨማሪ የሥራ እድልና የገበያ መረጋጋትን ይፈጥራል፡፡
ሀሳቤን ሳጠቃልለው፤ በእጅ የያዙት ወርቅ ከመዳብ ይቆጣራል እንዲሉ፣ አሁን በእጃችን የገባው ሰላምና መረጋጋት እንዳያመልጠን መጠበቅ፣ መንከባከንና ማስቀጠል ይገባናል። ይህንን ማድረግ ያለበት ደግሞ እኔ፣ አንተ፣ አንቺ፣ እናንተ፣ እኛ ነን፡፡ የእኛ ሰላም ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ሀገራትም ሲተርፍና ሲጠቅም ስላየነው፣ እነሱም እንዲጠብቁትና እንዲያከብሩት አስቀድመን፣ እኛ ለእኛ የሰላም ዘብ በመሆን፣ የብጥብጥና የሁከት መነሻ በሮችን መዝጋት አለብን።
በሀገራችን የተፈጠረው ሰላምና መረጋጋት አስከትሎት የመጣው ኢኮኖሚያዊ መነቃቃት ሳይቀለበስ ወደፊት የሚቀጥለውም በእኛው ተዋናይነት ነው፡፡ መንግስት ባደረገው ሀገራዊ ጥሪ፣ በህገ-ወጥ መልክ ተይዘው የነበሩ የውጭ ምንዛሬዎች ወደ ባንክ መግባታቸውና ቀጣይም የውጪ ምንዛሬ የማግኘት እድሎች ያላቸው ኢትዮጵያውያን በባንክ ስርዓት እንዲያንቀሳቅሱት የተፈጠረው ምቹ ሁኔታ፣ ሀገሪቷ ወገቧን ይዞት ከነበረው የውጪ ምንዛሬ እጥረት ሊያላቅቅ የሚችል ስለሆነ፣ የተጀመሩትና በጥቂት ጊዜ ውስጥ ለውጥ የታየባቸው ስራዎች ይበልጥ ተበረታተው መቀጠል አለባቸው እላለሁ።

Read 1475 times