Print this page
Saturday, 04 August 2018 10:28

“ዘመኑ የፍቅር አብዮት ነው ማለት ይቻላል”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(9 votes)

  · የምናቆመው የዲሞክራሲ ሐውልት፣ ከአክሱምና ላሊበላ የሚልቅ መሆን አለበት
     · የጠ/ሚኒስትሩ ሃሳብ ኢህአዴግ ውስጥ ገዢ ሃሳብ መሆን አለበት
     · ህዝቡ ሲወድህና ሲያከብርህ የሚገባህን ዋጋ ይሰጥሃል
     · ኢህአዴግን የታደገው የኢትዮጵያዊነት ካርድ ነው

   ከ8 ዓመታት በላይ በእስር ላይ ቆይቶ ከወራት በፊት በመንግስት ውሳኔ የተፈታው ታዋቂው ፖለቲከኛ አንዷለም አራጌ፤ በቅርቡ በአውሮፓ የተለያዩ አገራት በመዘዋወር ከኢትዮጵያውያን ጋር በአገሪቱ ጉዳዮች ላይ መወያየቱን ይናገራል፡፡ ጉዞውን አጠናቆ ወደ አገሩ የተመለሰው ፖለቲከኛው፤ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ፤ በውጭ አገራት ስለነበረው ቆይታ፣ ስለ አገሪቱ የለውጥ እንቅስቃሴ፣ እንዴት በፖለቲካው ሊሳተፍ እንዳሰበና ሌሎች አገራዊ ጉዳዮችንም አብራርቷል፡፡ እነሆ፡-


    በቅርቡ ወደ ተለያዩ የአውሮፓ አገራት ያደረግኸው ጉዞ ዓላማ ምን ነበር?
በመጀመሪያ የሄድኩት ወደ ጀርመን ነበር። ዓላማው ደግሞ በጀርመን የኢትዮጵያውያን የውይይትና የትብብር መድረክ ላይ ለመካፈል ነበር፡፡ መድረኩ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ያወያያል፡፡ በአጋጣሚ እኔ በሄድኩበት ወቅት የአፄ ቴዎድሮስ 150ኛ የህልፈት ዓመት ይከበር ስለነበር እሱን በሚመለከት የተዘጋጀ ስብሰባ ነበር፡፡ በዚያ ላይ በእንግድነት ለመናገር ተጋብዤ ነው  የሄድኩት። አጋጣሚውን ተጠቅሜ በዚያው ሆላንድ፣ ፈረንሳይና ቤልጂየም ሄጃለሁ፡፡ ስዊድንና ኖርዌይም ተጋብዤ ነበር፤ ነገር ግን በጊዜ እጥረት የተነሳ ለመሄድ አልቻልኩም፡፡
ጀርመን ፍራንክፈርት የነበረው ስብሰባ ትልቅ ነበር፤ አቀባበሉም ከሚገባኝና ከምጠብቀው በላይ ነበር፡፡ በሚገርም ሁኔታ አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ከሩቅ መጥተው ኤርፖርት ውስጥ አድረው ነው የተቀበሉኝ፡፡ ይሄ ለኔ ከሚገባው በላይ ነው። ኢትዮጵያውያን ምን ያህል የነፃነት ፍላጎት እንዳላቸው የተረዳሁበት አጋጣሚ ነው፡፡ ጀርመን በርሊን ውስጥም ትልቅ ስብሰባ ነው ያደረግነው፤ ኮሎኝ ውስጥም በተመሳሳይ፡፡ ብዙዎቹ ያገኘኋቸው ሰዎች ከኢትዮጵያ ከመጡ ከ30 እና 40 ዓመት በላይ የሆናቸው ናቸው፡፡ በቤልጂየም ከእነ ዶ/ር ነገደ ጎበዜ ጋር ተገናኝተን ተወያይተናል፡፡ ብዙ ኢትዮጵያውያንን አግኝቻለሁ፡፡ በሃገራችንም ጉዳይ ላይ ተወያይተናል፡፡ በአጠቃላይ ቆይታዬም እጅግ መልካምና ጥሩ ነበር፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ ከሰሞኑ በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጋር ተወያይተዋል፡፡ ውይይቶቹን እንዴት አገኘሃቸው?
በዚህ ሂደት ውስጥ ትልቁ መረሳት የሌለበት ነገር፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ትልቅነት ነው፡፡ አንደኛው በአድዋ ጊዜ ያሳየው ትልቅነት ነው፡፡ በጊዜው እየተጨቆነም ቢሆን ለነፃነቱ ያሳየው ቀናኢነት ትልቅነት ነው፡፡ ሁለተኛውን የኢትዮጵያውያን ትልቅነት ያየሁት በምርጫ 97 ላይ ነው። ዲሞክራሲ ብዙ ዓመት ይፈጃል እየተባለ ነው ሲነገረን የነበረው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ግን አለምን በሚያስደምም ደረጃ ወጥቶ፣ በጨዋነት የሚፈልገውን መርጦ ወደ ቤቱ ተመልሷል። ሌላው የኢትዮጵያን ህዝብ ትልቅነት እያየሁ ያለሁት አሁን ነው፡፡ ከዚህ በፊት በሃገር ውስጥም በውጭ ሃገርም የኢትዮጵያ ህዝብ ተቃውሞ ሲያቀርብ የነበረው ያልሰለጠነ በመሆኑ ሳይሆን መቃወም የሚገባው አገዛዝ ስለነበረ ነው፡፡ አሁን ደግሞ በሚገርም ሁኔታ በፅናት ለ27 ዓመት የተቃወሙ ኢትዮጵያውያን፣ ከኢህአዴግ ውስጥ ለወጡ መሪዎች ምናልባት በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ፍቅራቸውን ሲቸሩ ታይቷል፡፡ ይሄ ህዝቡ ምን ያህል የሚያገናዝብ እንደሆነ የሚያሳይ ነው፡፡ እስካሁን ሲታይ የነበረውን ተቃውሞና የደረሰበትን በደል ለተመለከተ ምናልባት መግደርደር ነበረበት ሊል ይችል ይሆናል፤ ግን የኢትዮጵያ ህዝብ ባህሪ እንደዚያ አይደለም፡፡ መብቱን የሚያከብርለት ሰው ሲያገኝ ከየትም ሃይማኖት፣ ከየትኛውም ዘር ይምጣ፣ የየትኛውም የፖለቲካ አባል ይሁን የሚገባውን ክብር ይሰጠዋል፡፡ የሚገባውን የሚያከብር፣ የማይገባውን የማያከብር የሰለጠነ ህዝብ ነው ህዝባችን፡፡
ትናንት በአውሮፓና በአሜሪካ ከተሞች ሲቃወሙ የነበሩ እንደ እነ ታማኝን የመሳሰሉ ታዋቂ ሰዎች፣ የኢህአዴግን መሪዎች በፍቅር ሲቀበሏቸው አይተናል፡፡ ህዝብ ሲወድህና ሲያከብርህ የሚገባህን ዋጋ ይሰጥሃል፡፡ ለማም ዶ/ር ዐቢይም ኢህአዴግ ናቸው፤ ግን ህዝብን በማክበራቸው አፀፌታውን አግኝተዋል፡፡ የዶ/ር ዐቢይ ጉብኝት ለኔ ትልቅ ነገር ነው፡፡ መቼስ ከፍቅርና ከእርቅ በላይ አስፈላጊ ነገር የለም፡፡ ሰው ሲከበር ሲወደድ ማየት ለኔ ያስደስተኛል። ይሄ ደግሞ ከጤነኛ አዕምሮ የሚመጣ ነው፡፡ ሰው ስለ አንድነቱ፣ ስለ ፍቅሩ አንድ ላይ ሲዘምር ሲታይ የፈጣሪ ስራ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በሆነው ነገር ሁሉ ደስተኛ ነኝ፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ እያሳዩት ያለው የሃሳብ ልዕልና የሚከበር የሚወደድ ነው፤ ትልቅነትን እያየሁባቸው ነው፡፡ እያሳዩት ያሉት ትህትናና አለመታበይ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ዛሬ አጋጣሚ ሆኖ ዘመንና ሃሳብ የተገናኙበት ወቅት ይመስላል፡፡ ቀደም ሲል በኛም በሌላውም የሚነሱ ሃሳቦች ወደ መድረኩ መጥተዋል፡፡ ዘመኑ የፍቅር አብዮት ነው ማለት ይቻላል፡፡
አሁን በአጠቃላይ እየታየ ያለውን አገራዊ  ለውጥ እንዴት ትገልፀዋለህ?
ወቅቱ የአብዮት ወቅት ነው፡፡ አሁን እየተካሄደ ያለው አብዮት ነው፡፡ ትናንት መንገድ ላይ ስንሄድ እየተገላመጥን ማየት ይጠበቅብን ነበር፤ አሁን ተገላምጦ ማየት አይጠበቅብንም፡፡ ከከተማ እስከ ገጠር ይሄ መንፈስ ነው ያለው፡፡ ፍርሃት እየተሸነፈ ነው፤ ፍርሃት እየተቀበረ ነው፡፡ ግን አብዮቱ ወይም ለውጡ ግልፅ መስመሮች አልታዩበትም፡፡ ገና ከጉሙ በደንብ አልወጣንም፡፡ ሰው ፈንጠዝያ ላይ ነው ያለው፡፡ አሁን በዶ/ር ዐቢይ የሚውጠነጠኑ ሃሳቦች እንዴት ነው መሬት ላይ የሚወርዱት? ተቋማዊ ዋስትና ኖሯቸው፣ ተቋማቱ እንደ ምሰሶ ሆነው ወደ ኋላ የማይመለስበትን ሁኔታ እንዴት ነው የምንፈጥረው? የሚለው ነገር ለኔ አልተመለሰልኝም፡፡ ሰው አሁን ድጋፉን እየሰጠ ያለው ለውጥ እንዲመጣ ነው፡፡ አስተማማኝ የዲሞክራሲ ተቋማት እንዲገነቡ ያለውን ፍላጎት ነው እየገለፀ ያለው፡፡ ሙሉ ለውጥ መጥቷል ብሎ አይደለም እየተንቀሳቀሰ ያለው፡፡ ሩጫው ገና ነው። ህዝቡ ለውጥ ይፈልጋል፤ ለለውጡም ድጋፍ እየሰጠ ነው የሚገኘው፡፡ ስለዚህ ከጋዜጠኞች፣ ከፖለቲከኞች፣ ከሰብአዊ መብት ተሟጋቾች የለውጡ ሂደት ወዴት ሊያመራ እንደሚገባው የሚያመላክቱ ሃሳቦች መፍለቅ አለባቸው፡፡ ያ ሲፈጠር ነው አሁን ካለው ጉም እየተላቀቅን፣ ወደ ትክክለኛውና የሚፈለገው ለውጥ መሄድ የሚቻለው፡፡ እነ ዶ/ር ዐቢይም ቢሆኑ በዚህ ረገድ ትንሽ ግልፅ የሆኑ አይመስለኝም፡፡ ቀናኢ የሆነ አስተሳሰብ አየሩን እንዲሞላው ከማድረግ በዘለለ እንዴት ሃሳቡ መሬት ላይ ይወርዳል የሚለው ግልፅ አይደለም፡፡
እንዴት ነው ከጉሙ መውጣት የምንችለው ብለህ ታስባለህ?
ይሄ በደንብ መወያየት የሚያስፈልገው ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ እስካሁን ድረስ የረጋ ውቅረ መንግስት ኖሮን አያውቅም፡፡ መንግስታት ይቀያየራሉ፤ ግን የረጋ ውቅረ መንግስት ስለሌለን አንዱ አንዱን እያፈረሰ ነው የቀጠለው፡፡ ውቅረ መንግስቱ የፀና ሆኖ ቀጣይነት ያለው እንዲሆን መነጋገር አለብን፡፡ ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚመጣው መንግስት በኃይል መሆን የለበትም፤ በህዝብ ፍቃድ መሆን አለበት፡፡ ያ አስተማማኝ ውቅረ መንግስት ኢትዮጵያ ላይ እውን እንዲሆን ሁሉን አቀፍ ውይይት ያስፈልገናል፡፡ እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ህዝቡ የታገለው ስር ነቀል ለውጥ እንዲመጣ  ነው፡፡ አሁን ያለው ነገር በቂ አይደለም። ጉሙን ማጥራት ያስፈልጋል። ለማጥራት ደግሞ ሚዲያዎች  የውይይት መድረክ አዘጋጅተው፣ የተለያዩ ሃሳቦች ማንሸራሸር አለባቸው፡፡ ዶ/ር ዐቢይ ብቻቸውን ቀና አመለካከት ቢኖራቸውም፣ እሳቸው የሾሟቸው ካልተጋሩት  ያን ያህል ትርጉም አይኖረውም። አሁን መወያየት ያለብን ውቅረ መንግስትን ለማፅናት ምን እናድርግ በሚለው ላይ ነው፡፡ ዶ/ር ዐቢይ  ወይም ኢህአዴግ ብቻ “ይሄን እናድርግ፣ ያንን እናድርግ” ብለው መቀጠል የለባቸውም፡፡ ይሄ ከሆነ አስተማማኝ አይሆንም፤ ሊቀለበስም ይችላል፡፡
በውጭ ሃገር ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶች ወደ ሃገር ውስጥ መግባታቸው በአገሪቱ የፖለቲካ አውድ ላይ ምን ለውጥ ያመጣል?
ይሄ ነብይነትን የሚጠይቅ አይነት ነገር ነው። በእንዲህ ያለ የአብዮት ወቅት ያልተጠበቀ ነገር ሊከሰት ይችላል፡፡ ተስፋ የማደርገው ከእስካሁኖቹ የአብዮት ሂደቶች በተለየ ቀና አስተሳሰብ የተንፀባረቀበት ከመሆኑ አንጻር ምናልባት ጥሩ ይሆናል ብዬ ነው፡፡ አሁን እየተዘራ ያለው ቀና መንፈስ በሁሉም ልብ ውስጥ ይሰርፃል፣ ያድጋል የሚል እምነት አለኝ። ፓርቲዎች የእስካሁኑን እንቶ ፈንቶ ትተው፣ ለሃገር የሚበጅ ነገር ለመስራት ይሰባሰባሉ ብዬ አስባለሁ። መሰባሰብም አለባቸው ብዬ አምናለሁ። በተለይ ደግሞ ይህ የስድብ ዘመቻ መቆም አለበት። መዘላለፍ መሰዳደብ በዚህ ዘመን ሊሞት ይገባዋል፤ እየሞተም ነው ብዬ አስባለሁ። አንዱ ሌላውን ለማዋረድ፣ አንዱ ሌላውን ለማንኳሰስ፣ አንዱ ሌላውን ለመግደል የሚደረግ ሩጫ፣ ጠ/ሚኒስትሩ እንደሚሉት፤ “የትንሽነት እርምጃ” ማቆም አለበት፤ ወደ ትልቅነት መምጣት አለብን፡፡ በመከባበር በመደማመጥ ለአንድነታችን ተሰባስበን መንቀሳቀስ አለብን ብዬ አስባለሁ፡፡ ወደ ሃገር ውስጥ እየገቡ ያሉ ፓርቲዎችም፣ እንደ ፖለቲካ አስተሳሰባቸው ይሰባሰባሉ ብዬም አስባለሁ፡፡ ይሄ ለውጥ ከማንም በላይ ለኢህአዴግ ጠቃሚ ነው። ኢትዮጵያዊነት ለህብረ-ብሔራዊ አስተሳሰብ አራማጅ ፓርቲዎች ብቻ ሳይሆን ለኢህአዴግም ለራሱ መድህን ሆኖታል፡፡ ኢህአዴግን የታደገው የኢትዮጵያዊነት ካርድ ነው፡፡ ዶ/ር ዐቢይ እና አቶ ለማ ለኢህአዴግ በሚያስፈልገው ትክክለኛው ጊዜ ደርሰውለታል፡፡ ከኢህአዴግ ድርጅቶች ደግሞ ህወኃት ከዚህ ሂደት ካወቀበት የበለጠ ተጠቃሚ ነው፡፡ ይሄ ግን የገባቸው አልመሰለኝም። ግን በጣም ተጠቃሚ የሚሆነው ህወኃት ነው። ስለ ይቅርታ፣ ስለ ፍቅር እየተሰበከ ነው፡፡ በዚያው ልክ ከማንም በላይ የበደለን ህወኃት ነው። እኔ በግሌ በደልን ለመቁጠር አልፈልግም፣ ይቅር እንድንላቸው እፈልጋለሁ፣ እነሱም ይሄን እድል መጠቀም አለባቸው፡፡ ለ27 ዓመታት አንገታችን ላይ ቆመው፣ ከእነ ህፃናት ልጆቻችን ሲያስለቅሱን ኖረዋል፡፡ እኔ በይቅርታ ሁሉን ረስቼ ፍቅር ለመስጠት ዝግጁ ነኝ፡፡ ከዚህ በላይ ለእነሱ የሚጠቅም እድል አይኖርም፡፡ ጊዜውን ተጠቅመውበት ትግሉን የራሳቸው አድርገው፣ የትግሉ አካል ሆነው ቢሳተፉ ጥሩ ነው፡፡ ሌላው በአንድ በኩል ስለ ፍቅር፣ ይቅርታ እያወራን በጎን የሚካሄደው ስድብና መዘላለፍ መቆም አለበት፡፡ የበደሉንን ከልባችን ይቅር እንበል፡፡ በዚህ ረገድ ትልቅነታችንን ማሳየት አለብን፡፡ የዶ/ር ዐቢይ ሃሳብ ኢህአዴግ ውስጥ ገዥ ሃሳብ መሆን አለበት። እንደ አንድ ትልቅ አጀንዳ ይዞ ሊሰራበትም ይገባል። በሌላ በኩል ተቃዋሚዎች ለድርድርና ውይይት በሚመች መልኩ መሰባሰብ አለብን፡፡
በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የተፈጠረውን የእርቅና የፍቅር ግንኙነት በተመለከተ ምን አስተያየት አለህ?
በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል በተፈጠረው መቀራረብ በእጅጉ ደስተኛ ነኝ፡፡ ነገር ግን ግንኙነቱ በምን ላይ የተመሰረተ ነው የሚለው ግልፅ አይደለም፡፡ በጦርነቱ 127 ሺህ ኢትዮጵያውያን ልጆቻችን አልቀዋል፡፡ በኤርትራም በኩል በተመሳሳይ ብዙ ወገኖች አልቀዋል፡፡ ከዚህ ሁሉ በኋላ ወደ ፍቅር መመለሱ ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ ከዚህ የእርቅ ሂደት ምን አተረፈች ብዬ ስጠይቅ መልስ አጣለሁ፡፡ መታረቃችን ትልቅ ነገር ነው፤ ነገር ግን ኢትዮጵያ ምን ትርፍ አገኘች ብዬ ስጠይቅ መልስ የለኝም፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ በግልፅ ተጠቃሚው የኤርትራ መንግስት ነው፡፡
ለሁሉም ነገር ትልቁ መፍትሄ ዲሞክራሲ ነው። ዲሞክራሲ ከመጣ የወደብ ጉዳይ አያጣላንም፡፡ እንኳን የኢትዮጵያና የኤርትራ የአፍሪካ ቀንድም እየተሳሰረ፣ አፍሪካም 50 ዓመት ባልፈጀ ጊዜ አንድ ልትሆን ትችላለች፡፡ ለዚህ ደግሞ በቅድሚያ በየሃገራቱ ዲሞክራሲያዊ ስርአቶች መፈጠር አለባቸው፡፡ አሁን አፍሪካ ቀንድ ላይ ለውጥ ለማምጣት አስተማማኝ ዋስትናው ዲሞክራሲ ብቻ ነው፡፡ ዲሞክራሲያዊ የሆኑ ሃገሮች እርስ በእርሳቸው ሲበላሉ አይታይም፡፡ አሁን ያለው ለውጥ በጎ ነው፤ ኢትዮጵያ ወደፊት ከፍቅርና ከወንድማማችነት ትጠቀማለች ብዬ አስባለሁ፡፡
የለውጡ አካል የሚመስለው አወዛጋቢው የብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ጉዳይ እንዴት ሊፈታ ይገባዋል ትላለህ?
እኔ ሚኒሶታ ላይ በታየው ህብረ-ቀለማዊ ሁኔታ ደስተኛ ነኝ፡፡ ሁሉም ነገር ወደ አደባባይ መውጣት አለበት፡፡ መታመቅ ነው ትልቅ ችግር የሚያመጣው፡፡ ሃሳቦች ሲበዙ ቆይቶ መልክ እየያዘ ይመጣል፡፡ ይህን ሁኔታ የሚያስተናግድ ዲሞክራሲዊ ሁኔታ ግን ያስፈልገናል፡፡ አርማ ያለውን ባንዲራ ህዝቡ እንዳልተቀበለው በግልጽ አሳይቷል፡፡ ከዚህ በላይ ሪፈረንደም ሊኖር አይችልም፡፡ ህዝብ በባንዲራው ጉዳይ ሪፈረንደም አድርጓል ማለት ይቻላል፡፡ ስለዚህ ህዝብ የወሰነውን መጨረሻ ላይ መቀበልና ማፅደቅ የዲሞክራሲ ባህሪ ነው፡፡
ብዙዎች የለውጥ ሂደቱ እንዳይቀለበስ ስጋት አላቸው፡፡ በለውጡ ሂደት ውስጥ በምን መልኩ መጓዝ ይገባል ብለህ ታምናለህ?
አንደኛ ውይይቶች መጀመር አለባቸው፡፡ እንዴት? ወዴት? በምን አግባብ ነው የምንጓዘው በሚለው ላይ ውይይቶች ያስፈልጉናል፤ መጀመርም አለባቸው፡፡ ህዝቡም እየደገፈ እየመከረ ወደፊት መሄድ አለብን፡፡ መሰዳደብና መወጋገዝ የትም አያደርሰንም፡፡ የይቅርታ መንፈስ ለሁላችንም ይጠቅመናል፤እሱ ላይ ጠንክረን እንስራ፡፡ የሚጠቅመውን በልበ ሰፊነት እየተመካከርን፣ ዲሞክራሲን በኢትዮጵያ ውስጥ ማምጣት ከቻልን ትልቅ የትውልድ ሃውልት አቆምን ማለት ነው። እኛ የምናቆመው የዲሞክራሲ ሐውልት፤ ከአክሱምና ከላሊበላ የሚልቅ መሆን አለበት፡፡    
ወደፊት በፖለቲካው መስክ እንዴት ለመሳተፍ አስበሃል?
አሁን በፖለቲካና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የምንወያይበትን ቢሮ እያደራጀሁ ነው፡፡ እኔ ህብረ ብሔራዊ አመለካከት ነው ያለኝ፡፡ ሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል የኔ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ስሞት አጥንቴ ተፈጭቶ ሁሉም ቦታ ቢበተን ደስተኛ ነኝ፡፡ ለእኔ የትኛውም የሃገራችን ክፍል መቀመጫ ቤቴ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ለሁላችንም ትርፍ እንጂ ኪሳራ አይደለም፡፡ ኢህአዴግም ለጥቂት የተረፈው በኢትዮጵያዊነት ነው፡፡ አሁን የማደራጀው ቢሮ ሃሳቦች የሚመነጩበትና አንድ ትልቅ ህብረ ብሔራዊ ኃይል የምንፈጥርበትን ሁኔታ የሚያመቻች ነው፡፡ የይድረስ ይድረስ እንዳይሆን ተጠንቅቀን ነው ከጓደኞቼ ጋር እየሰራን ያለነው፡፡ እስካሁን ጥሩ ደረጃ ላይ ነን፡፡
የፖለቲካ ተመክሮህን የተመለከተ መጽሐፍ የማዘጋጀት ሃሳብ የለህም?
አንድ ያዘጋጀሁት መፅሐፍ ቅዳሜ (ዛሬ) ለአንባቢያን ይደርሳል፡፡ ርዕሱ “በዘመናት መካከል” የሚል ነው፡፡ እስር ቤት ውስጥ ሆኜ የፃፍኳቸው መጣጥፎች፣ ግጥሞች የተካተቱበት ነው፡፡ ለፕሬዚዳንት ኦባማ የፃፍኩት ደብዳቤ፣ ለባለቤቱ የፃፍኩት ግጥምና ሌሎች ስብስብ ስራዎችን የያዘ፣ በ308 ገፆች የተዘጋጀ መፅሐፍ ነው፡፡ ወደፊት የዚህ ዘመን ታሪክ  ሲፃፍ ማጣቀሻ፣ አስረጅ ይሆናል ብዬ በማሰብ  ነው የፃፍኩት። ለወደፊት ታትመው የሚወጡ መጽሐፍትም እያዘጋጀሁ ነው፤ ይወጣሉ፡፡

Read 5862 times