Saturday, 04 August 2018 10:23

እነ አቶ ልደቱ አያሌው “ኢዴፓ” መፍረሱን ይፋ አደረጉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(13 votes)


              “ኢዴፓ አልፈረሰም፤ፈረሰ ያሉትን በህግ እንጠይቃለን” - ዶ/ር ጫኔ ከበደ፤የኢዴፓ ፕሬዚዳንት

    በምርጫ ቦርድ የተዛባ ውሣኔ ምክንያት ከተመሠረተ 25 አመታት ያስቆጠረው የኢትዮጵያውያን ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) በይፋ መፍረሱን እነ አቶ ልደቱ አያሌው ያስታወቁ ሲሆን የፓርቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጫኔ ከበደ በበኩላቸው፤ “ፓርቲው አልፈረሰም፤ ፈረሰ ያሉትን በህግ እንጠይቃለን” ብለዋል፡፡
የቀድሞ የፓርቲው ፕሬዚዳንት አቶ ልደቱ አያሌውን ጨምሮ በፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ በቅርቡ መመረጣቸውን ያስታወቁት አቶ አዳነ ታደሰና ሌሎች 16  የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ ኢዴፓ በይፋ መፍረሱን ለመገናኛ ብዙኃን አስታውቀዋል፡፡
ፓርቲው በይፋ መፍረሱን በተመለከተም በነገው ዕለት ሐምሌ 29 ቀን 2010 ዓ.ም በቅሎ ቤት አካባቢ በሚገኘው የኢዴፓ ፅ/ቤት ለመገናኛ ብዙኃን በሚሰጥ መግለጫ እንደሚነገር እንዲሁም የፓርቲው አመራሮች ቀጣይ የፖለቲካ ተሣትፎ ጉዳይ ላይ የጋራ ምክክር እንደሚደረግ አቶ አዳነ ታደሰ ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡
“ፓርቲው የፈረሰው በምርጫ ቦርድ የተዛባ ውሳኔ ምክንያት ነው” ያሉት አቶ ልደቱ አያሌው፤ ”ፓርቲውን ለመታደግ ለጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት አቤቱታ ብናቀርብም ምላሽ አላገኘንም” ብለዋል፡፡  
በጉዳዩ ላይ አዲስ አድማስ ያነጋገራቸው የኢዴፓ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጫኔ ከበደ በበኩላቸው፤ ”እኔ ካልመራሁት በሚል ፓርቲው ፈርሷል ማለት በህግ ያስጠይቃል፣ በፓርቲው ህልውና ላይ የመጨረሻውን ውሣኔ ማሳለፍ የሚችሉት ግለሰብ አመራሮች ሳይሆኑ የፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ ነው” ብለዋል፡፡
ፓርቲው መደበኛ የፖለቲካ እንቅስቃሴው እያከናወነ መሆኑን የጠቆሙት ዶ/ር ጫኔ፤ በየክልሉ የሚገኙ ፅ/ቤቶችን የማጠናከር ተግባር መከናወኑንና ይህን ተከትሎም ጠቅላላ ጉባኤ ለመጥራት የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ “ፓርቲው ፈርሷል” የሚሉ ወገኖችንም በህግ ለመጠየቅ ፓርቲው እንደሚገደድ ዶ/ር ጫኔ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡  

Read 13460 times