Saturday, 04 August 2018 10:09

“ለ5 ዓመታት ካሣና ምትክ ቦታ ሳናገኝ ተንገላተናል”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

 ካሣና ምትክ ቦታ ሳይሰጠን ላለፉት 5 አመታት ከእነ ቤተሰቦቻችን ለእንግልትና ለጎዳና ህይወት ተዳርገናል ያሉ የአዲስ አበባ ቅሬታ አቅራቢ ነዋሪዎች፤ ከትናንት በስቲያ ሐሙስ በጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት ደጃፍ በመሰባሰብ አቤቱታቸውን በሠላማዊ ሰልፍ አሰምተዋል፡፡
ከ500 በላይ የሆኑት አቤቱታ አቅራቢዎች ቦሌ ክ/ከተማ ወረዳ 3 ውስጥ ለሚገነባው ብሔራዊ ስቴዲየም ቦታችሁ ይፈለጋል፣ በፍጥነት ተነሱና ካሣና ምትክ ቦታው ተዘጋጅቶ ይሰጣችኋል ተብለው ቃል እንደተገባላቸው፣ በኋላ ግን የከተማ አስተዳደሩ ቃል የውሃ ሽታ ሆኖ እንደቀረባቸው ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡
አባወራዎቹ በተፈናቀሉበት ቦታ ላይ ለ15 ዓመታትና ከዚያ በላይ ግብር እየከፈሉ፣ መሠረተ ልማት እያሟሉ መኖራቸውንም ተናግረዋል፡፡    ኮሚቴ አቋቁመው ላለፉት አራት ዓመታት የከተማ አስተዳደሩን እየተመላለሱ ስለ ጉዳያቸው ሲጠይቁ መቆየታቸውን የገለጹት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ ከከተማ አስተዳደሩ ግን ቁርጥ ያለ ምላሽ አለማግኘታቸውን ጠቁመዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት አብዛኞቻችን በጎዳና ላይ ሸራና ፕላስቲክ ወጥረን ጎስቋላ ኑሮ እየመራን ነው የሚሉት አቤቱታ አቅራቢዎቹ፤ ልጆቻችንም ከትምህርት ገበታቸው ተፈናቅለው ይገኛሉ ብለዋል፡፡
በወቅቱ ካሣና ምትክ ቦታ ይሰጣችኋል፣ የኮንደሚኒየም ቤት እንዳትመዘገቡ ተብሎ እንደተነገራቸው በመግለፅም፤ ከምንም ሳንሆን ባዶ እጃችንን እንድንቀር ተደርገን፣ ግፍ ተፈጽሞብናል ሲሉ አማርረዋል፡፡  
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ችግራቸውን ተገንዝበው አፋጣኝ ምላሽ እንዲሠጧቸው ባለፈው ሐሙስ በሠላማዊ ሰልፍ የጠየቁት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የሂደቱን ዝርዝር ሃሳቦች የሚገልጽ ማመልከቻ ማስገባታቸውንም ጠቁመዋል፡፡

Read 1654 times