Saturday, 04 August 2018 09:36

በኮንጎ የኢቦላ ወረርሽኝ ዳግም ተቀስቅሷል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ መንግስት 33 ዜጎችን ለህልፈተ ህይወት የዳረገው የኢቦላ ቫይረስ ወረርሽኝ በቁጥጥር ስር መዋሉን ይፋ ባደረገ በቀናት ዕድሜ ውስጥ ቫይረሱ በአገሪቱ ዳግም በወረርሽኝ መልክ መከሰቱ ተዘግቧል፡፡
የአገሪቱ የጤና ሚኒስትር ከትናንት በስቲያ የሰጡትን መግለጫ ጠቅሶ ዘ ጋርዲያን እንደዘገበው፣ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሰሜን ምስራቃዊ አካባቢ በምትገኘው የኪቩ አውራጃ የተቀሰቀሰው የኢቦላ ቫይረስ ወረርሺኝ አራት ሰዎችን ማጥቃቱ ተረጋግጧል፡፡
በአውራጃዋ ባለፈው ቅዳሜ 20 ሰዎችን ለህልፈተ ህይወት የዳረገ በሽታ መታየቱን ተከትሎ በተደረገው ምርመራ፣ አራት ሰዎች በኢቦላ ቫይረስ መጠቃታቸውን ለማረጋገጥ መቻሉን የጠቆመው ዘገባው፣ በአዲስ መልክ የተቀሰቀሰው የኢቦላ ወረርሺኝ በቅርቡ ተከስቶ ከነበረውና ባለፈው ሳምንት በቁጥጥር ውሏል ተብሎ ከተነገረለት ወረርሺኝ ጋር ግንኙነት ይኑረው አይኑረው የተረጋገጠ ነገር የለም ብሏል፡፡
የአለም የጤና ድርጅት በአዲስ መልክ የተቀሰቀሰውን የኢቦላ ወረርሽኝ ለመግታት በአፋጣኝ የህክምና ባለሙያዎች ግብረ ሃይል ማቋቋሙንና ከአገሪቱ መንግስት ጋር እርብርብ ማድረግ መጀመሩንም ዘገባው አመልክቷል፡፡
ኢቦላ ለዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በቀላሉ የማታሸንፈውና በቋሚነት ፈተናዋ ሆኖ የሚቀጥል አገራዊ ተግዳሮት ነው ያሉት የአለም የጤና ድርጅት ዳይሬክተር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም፤ የአገሪቱ መንግስትና የጤናው ዘርፍ ባለሙያዎች ለችግሩ መፍትሄ ለመሻት ቀጣይነት ያለው እርብርብ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

Read 1673 times