Saturday, 28 July 2018 16:05

ጥበብ የጋዜጠኛ ሔኖክ ስዩም “ጎንደርን ፍለጋ” መፅሐፍ ሰኞ ይመረቃል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

 የተጓዡ ጋዜጠኛ ሔኖክ ስዩም “ጎንደርን ፍለጋ” የተሰኘ መፅሐፍ ከነገ በስቲያ ሰኞ ከቀኑ 11፡30 ጀምሮ በጣይቱ ሆቴል ይመረቃል፡፡ መፅሐፉ በ10 ምዕራፎች የተከፋፈለና 17 ታሪኮችን ያካተተ ሲሆን ከታሪኮቹ መካከልም “ናበጋን በበጋ” ወደ አለቃ ገ/ሃና አገር የተደረገን ጉዞ ጨምሮ ከደጃዝማች አያሌው (አያሌው ሞኙ) የትውልድ ቀዬ እስከ የጦር ሜዳ ጀብዱ፣ የኢማም አህመድ (ግራኝ አህመድ) ሰራዊት ያላጠፋቸውን የጎንደር ገዳማትንና ሌሎችንም የጎንደርን ታሪካዊ ጥንታዊ ሀብቶች በምናብ የሚያስቃኙ ታሪኮች ይገኙበታል፡፡
ደራሲና ሃያሲ ዓለማየሁ ገላጋይ በመፅሐፉ ጀርባ ላይ ባሰፈረው አስተያየት፤“… ጎንደርን ፍለጋ የትውልድ ጥሪ ነው… የጎንደር ምድር ከፈጣሪዋና ከአባቶቻችን የተቀበለችውን የዘር ፀጋ ለፍሬ አብቅታ የዚህን ትውልድ ዕይታ የምትጋብዝበት ጉዞን በትርክት የተካ ጥሪ ነው…” ብሏል፡፡  በ244 ገፆች የተቀነበበው መፅሐፉ፤ በ130 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡
ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም ከዚህ ቀደም “የመንገድ በረከት የተሰኘ የደቡብ ኢትዮጵያን ቅርስና ተፈጥሮ የሚያስቃኝ መፅሐፍ ለንባብ ከማብቃቱም በላይ “ሀገሬ ሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን”ን በመመስረት ላለፉት 10 ዓመታት በቱሪዝም፣ በቱሪዝም ፌስቲቫል አዘጋጅነት፣ የተለያዩ ጠቃሚ ዳይሬክተሪዎችን በማሳተም፣ በጄቲቪ እና በድሬቲዩብ የጉዞ ማስታወሻዎቹን በማቅረብና በየሁለት ወሩ ቱባ መፅሔትን በማሳተም ይታወቃል፡፡

Read 676 times