Saturday, 28 July 2018 15:52

ነገሩ እንደ ማሰብ ቀላል አይደለም!

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(2 votes)

አጣጥሜ የማስብባቸው ቅፅበቶች አሉ፡፡ ሀሳቡን የቀሰቀሰብኝ የማነበው መፅሐፍ ሊሆን ይችላልም ብዬ እያወራሁልህ “አንተ ደግሞ ዝም ብለህ እያዳመጥከኝ ተቀመጥ” የሚለኝን መፅሐፍ ብዙም አልወድም። በመፅሐፉ መነሻ የራሴን ሀሳብ በመሀል እያስገባሁ ሳጣጥም ነው ደስ የሚለኝ፡፡ … የሰው ሀሳብ ፈረስ እስከ መጨረሻው እንዲጋልበኝ አልፈልግም፡፡ መፅሐፉን አጠፍ አድርጌ እኔም መፅሐፉ ካስፈነጠረኝ አቅጣጫ ባሻገር በራሴ ምናብ ወደ ሌላ መዳረሻ መፈርጠጥ እሻለሁ፡፡
የሪሶርስ ሽሚያ ነው፡፡ ሽሚያው የሚደረገው በእኔ አእምሮ ላይ ነው፡፡ “እኔን ብቻ አድምጠኝ” ይላል መፅሐፉ … እኔ ደግሞ “ቆይ ራሴንም ማድመጥ እፈልጋለሁ” እለዋለሁ፤ አጥፌ አስቀምጬው አጣጥሜ ማሰብ እቀጥላለሁ፡፡
የሪሶርስ ሽሚያ ነው፡፡ … የእኔ አእምሮ በህልውና የመቆያ ሪሶርስ ነው፡፡ ለእኔ ህልውና የሚጠቅመኝን ሁሉ አዳምጣለሁ፡፡ የሰው ማዳመጫ ሆኜ መቅረት ግን አልፈልግም፡፡ መርሳት የለብኝም፤ሪሶርሱ የራሴ መሆኑን፡፡ አእምሮዬ በር እና መስኮት አለው፡፡ … ቅፅር እና ግቢ አለው፡፡ … የሚያንኳኳ እንግዳን ሁሉ አልቀበልም፡፡ ከራሴ ህልውና እና ምርጫ አንፃር መዝኜ የማስገባውን አስገባለሁ፤ የምመልሰውን እመልሳለሁ፡፡ ያስገባሁት እንግዳ በእኔ ሪሶርስ ላይ አዛዥ ሆኖ ካጨናነቀኝ ጓዙን ጠቅልሎ እንዲሰናበት አደርገዋለሁኝ፡፡ ዋናው ነገር ሪሶርሱ የማን እንደሆነ በመዘናጋት አለመዘንጋት ነው፡፡
አእምሮዬ የእኔ አንጡራ ሀብት ነው፡፡ አካሌም የእኔው “Survival machine” ነው፡፡ እኔ አካል ብዬ የምጠራውን ሪሶርስ የገነቡት ዘረ - መሎቼ እንደሆኑ ሪቻርድ ዳውኪንስ ነግሮኛል፡፡ … የነገረኝ በጣም ምክኒያታዊ ሀሳብ ሆኖ ስለተሰማኝ ተቀብዬዋለሁ። ሪሶርሴ እንዴት እንደሚሰራ ነው የነገረኝ፡፡ በጣም ጠቃሚ እውቀት ነው ስለ ራሴ ያሳወቀኝ፡፡ ግን ይሄንን ስላሳወቀኝ ወይንም ዘረ - መሎቼ አካሌንና አእምሮዬን ለራሳቸው ጥቅም ሁሉ እንደገነቡ ስለነገረኝ የሪቻርድ ዳውኪንስ ሀሳብ ባሪያ መሆን አልሻም፡፡ መፅሐፉን አጥፌ የማስቀመጥ ምርጫ አለኝ፡፡ … አእምሮዬ ማንበብ ቢፈልግ እንኳን እኔ የመከልከል ስልጣን አለኝ። አእምሮዬ የእኔ እንጂ የዳውኪንስ ሪሶርስ አይደለም፡፡ አእምሮዬንም ማዘዝ እችላለሁኝ፡፡ “free will can be absolutly free”
አካሌ የእኔ ሪሶርስ ነው ብያለሁኝ፡፡ የእኔ የሆነው ከ18 ዓመት ልደቴ በኋላ ነው፡፡ ከዛ በፊት የቤተሰቦቼ ነበር፡፡ እነሱ ነበር የሚያዙበት፡፡ ምናልባት ያኔ በእኔ ሪሶርስ ላይ ከቤተሰቦቼ ባሻገር በአካልና አእምሮዬ ላይ በእኩል ስልጣን ይወስኑ የነበሩት የትምህርት ቤት አስተማሪዎቼ ነበሩ፡፡ … ግን የወሰኑ ይመስላቸዋል እንጂ በእውነት በእኔ ላይ ይወስኑ የነበሩት የማነባቸው መፅሐፍት ነበሩ፡፡ መፅሐፍቱ በወሰኑልኝ ግን እስከ መጨረሻው አልመራም፡፡ አንዱን መፅሐፍ በሌላኛው አጣፍቼ፣ ነፅሮ የወጣውን መፅሐፍም አጥፌ የማስቀመጥ ብቃት ላይ ደርሻለሁኝ፡፡ ሪሶርሴን የራሴ የማድረግ ትግል ነው፡፡
ከቤተሰቤ፣ ከአስተማሪዎቼና ከመፅሐፍት ተፅዕኖ አእምሮዬን ነፃ ሳወጣ፣ የትዳር ጓደኛ የማገኝበት እድሜ ላይ ደረስኩኝ፡፡ … አካሌ በመሰረቱ የኔ ነው፡፡ ግን ሚስቴ፤ የእኔን አካል ነው “ባል” ብላ የምትጠራው፡፡ … ትዳር ደግሞ አካልን በመጋራት የሚመሰረት ተቋም ነው፡፡ … አንዳንድ ጊዜ ለትዳር ሲባል የግል ምርጫን እንደ መፅሐፍ አጥፎ ማስቀመጥ ግድ ይሆናል፡፡ … ባለትዳሮች በማዕድ ቀርበው ሲመገቡ የሚጎራረሱት፣ የአንዱ ሪሶርስ ግዛትና የሌላው አንድ መሆኑን ለመጠቆም ነው፡፡ … ተጎራርሰው ሲጨርሱ ከሁለቱም ሪሶርስ አዋጥተው፣ አንድ ራሱን የቻለ ልጅ ይወልዳሉ። … ሪሶርሳቸው ላይ ኢንቨስት ማድረግ ይጀምራሉ፡፡ እነሱ መጉረሳቸውን እየቀነሱ ለታዳጊው ማጉረስ ላይ ያተኩራሉ፡፡
… እና አሁን እያጣጣምኩ እያሰብኩ ነው፡፡ … ማሰቤን በቀጠልኩ ቁጥር “ነፃ ምርጫ” ወይም “የብቻ ሪሶርስ” የሚባል ነገር እንደሌለ ይታየኝ መጣ፡፡ የእኔ አካልና አእምሮ … የእኔ ቅጽር፣ በርና መስኮት የእኔ ብቻ የመሆኑ ነገር ተንሳፋፊ ምኞት እንጂ እውነታ አይደለም። … እኔ፤ የእኔ አይደለሁም … “እኔ፤ የእኔ ከመሆኔ በላይ የሌሎች መሆኔ” የተለያዩ ንፅፅሮች ውስጥ እውነት ሆኖ ታየኝ፡፡
… ሪሶርስ ያስፈለገው ለአእምሮዬ ነው፡፡ … የእኔን ህልውና ከሚያሳድጉ ጋር አብራለሁ፡፡ የራሳቸውን ህልውና ለማሳደግ ሲሉ የእኔን ሪሶርስ ከሚበዘብዙ ጋር ግን እጣላለሁ፡፡ ይኼ የተፈጥሮ ህግ ነው፡፡ … እኔ የራሴ ብቻ ላለመሆን የሚፈቅድ ህልውናዬን ለማቆየት ወይ ለማስቀጠል ስል ነው፡፡ … የወላጆቼ፣ የአስተማሪዎቼ፣ የሚስቴ ወይም የመንግስትም ልሆን እችላለሁ፡፡ ህልውናዬ የተሻለ አማራጭ መስሎ ከታየው ፡፡ ህጎች ሁሉ፣ ባህሎች ሁሉ፣ እውቀቶች ሁሉ በዚህ መሰረት እስከሆኑ ድረስ ቅፅሬን ክፍት አድርጌ አስገባቸዋለሁኝ። … አከብራቸዋለሁኝ …እተባበራለሁኝ፡፡ … ከዚህ በተቃራኒ የሆኑ ስብከቶችን እንደ መፅሐፍ አጥፌ አስቀምጣቸዋለሁኝ፡፡
አንበሳና ሚዳቋ አይተባበሩም፡፡ ሊተባበሩ አይችሉም፡፡ ሚዳቋዋ በተፈጥሮ የተሰጣትን አካል ለራሷ ህይወት ልትገለገልበት ትፈልጋለች። ሳር እንድትግጥ፣ እሷን የመሰሉ የሚዳቋ ግልገሎች እንድታፈራበት በተፈጥሮ የተሰጣት አካል አላት፡፡ ሪሶርሷ ነው፡፡ … ችግሩ ሚዳቋ በራሷ የአካል ጥቅም ላይ የሚታያትን ግብ አንበሳው በተመሳሳይ መንገድ አያይም፡፡ እንዲያይም አይጠበቅም፡፡ አንበሳውም የራሱን አካል (ሪሶርስ) ህልውና የማቆት የተፈጥሮ ተልዕኮ አለው፡፡ … የሚዳቋዋን ስጋ መብላት አለበት። ሚዳቋዋም የራሷን ላለማስበላት መሮጥ አለባት። … የራሷን የአካል ህልውና ለማቆየት ትሮጣለች፡፡ … የወለደቻቸውን ግልገሎች ለመብላት የመጣን ግን በቀንዷ ለመግጠም ልትወስን ትችላለች፡፡ .. ይኼንን ያደረገችው “አመዛዝና አይደለም” ወይም “በደመነፍስ” ነው ልንል እንችላለን፡፡ … ያም ሆነ ይህ ከራሷ አካል የበለጠው ሪሶርስ ግልገሎቿ ላይ እንዳዋለችው በደመ-ነፍሷም ቢሆን አውቃለች፡፡
አንበሳ በሚዳቋ ፈንታ ለምን ሌላ አንበሳን አይበላም። “ስጋ ስጋ ነው!” ልትሉ ትችላላችሁ፡፡ አንበሳ አንበሳን ለመግደል የሚያወጣው ኢነርጂና በመግደል ፋንታ የመገደል እድሉ ከሚዳቋ አንፃር ከታየ ከፍ ያለ ነው፡፡ … አንበሳው ስጋ ማግኘት ያለበት በየዕለቱ ነው፤ በየዕለቱ አንበሳው ሌላ አንበሳ ገድሎ እየተመገበ በህልውና የመቆየቱ ነገር የሚመስል አይደለም። ስለዚህ ሚዳቋውን ይመርጣል፡፡ ግን አንበሳ ሁሉ ለተመሳሳይ ሪሶርስ (ሚዳቋ) እስከሮጠ ድረስ እርስ በራሱ መጋጨቱ አይቀርም፡፡ … የአደን ሜዳን የበላይ ሆኖ ለመቆጣጠር ከመሰሎቹ ጋር ግጭት ውስጥ ይገባል፡፡ … ህልውናውን በልጆቹ ውስጥ ማስቀጠል እንዲችል ሴት አንበሳ ለማጨት ከሚዳቋ ጋር ሳይሆን ከአንበሶች ጋር ነው የሚዋጋው፡፡ … አንበሳ በሚዳቋ ላይ ያለውን እቅድ፤ሚዳቋዋም በሣሩ ላይ ተግባራዊ ታደርጋለች፡፡
የሰውም አለም ህልውና ትግል ተመሳሳይ ነው፡፡ በተለይ ሰውን የሚያድነው ሌላ አውሬ እስከሌለ ድረስ የሰው ዋና ጠላት ሌላው የሰው ልጅ ነው፡፡ … ለአንድ ሪሶርስ የሚፎካከሩ ሁሉ እርስ በራሳቸው ጠላትነት አላቸው፡፡ እርግጥ እንደ አውሬ አለም ሰው ሰውን አይበላም፡፡ … አንበሳ አንበሳን መብላቱ ለዘላቂነት አዋጪ እንዳልሆነው ሁሉ፣ ሰው የሰውን ስጋ በቀጥታ ለመብል አለመፈለጉም እንደዛ ነው፡፡
ሰው የሚመገበው ምግብና የሚኖርበትን ቤት ማምረት የሚችል እንስሳ ነው፡፡ ማምረትም ሆነ መኖር እንዲችል የመሬት ሪሶርስ ያስፈልገዋል፡፡ … መሬት የሚመረትባት ሪሶርስ እንጂ ራሷ እየተመረተች የምትበዛ ባለመሆኗ፣ የሪሶርስ ሽሚያው በሰው እና ሰው መሀል እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ የሚሄድ አይደለም፡፡ የአካል ሪሶርስን ባልና ሚስት ከተለያየ አቅጣጫ መጥተው በትዳር መልክ እንደሚጋሩት፣ መሬትም የዛኑ አይነት የሪሶርስ ጋብቻ ትፈፅማለች፡፡ ጋብቻ ሁሉ ለህልውና ጥቅም ሲባል ነው፡፡
…. ጋብቻው መሬቱ እያነሰ ሲመጣ በመፈቃቀድ ሳይሆን በጠለፋ መልክ የሚካሄድ ሊሆን ይችላል፡፡ እናም እንደ አንበሳው ግዛት “ህገ አራዊት” ዋነኛው ማስፈፀሚያ አማራጭ ሆኖ ሊወሰድ  ይችላል። … አንበሶችም የአደን ሜዳው በጠበበ መጠንና አንበሶቹ በቁጥር እየጨመሩ በመጡ ቁጥር ድሮውኑ በህገ አራዊት ቢተዳደሩም … በጣም አሰቃቂ ወደሆነ የእርስ በእርስ ፍልሚያ ረቂቅ አራዊትነታቸውን ሊያስመነድጉት ይችላሉ፡፡
ሰውም…. ስልጣኔና የህግ መዋቅሩን ጥሶ “መሬት የሁሉ ናት፤ ባለቤት የላትም” የሚለውን የዶ/ር ከበደ ሚካኤል ግጥም ወደ መርህ ለውጦ ሊንቀሳቀስ ይችላል፡፡
… በጉልበት ማስገበሩ አዋጪ ላይሆን ይችላል በዘላቂነት፡፡ በቀጥታ በጦርነት መልክ ሪሶርስን ለመቆጣጠር ተብሎ መቆጣጠር የፈለገው አካል ህልውና አደጋ ውስጥ ሊወድቅ ይችላል፡፡ … ስለዚህ መጀመሪያ ጠጣሩን መሬት ከመቆጣጠር የአእምሮን ሪሶርስ መቆጣጠሩ ይቀላል፡፡፡ … መፅሐፍት ይፃፋል። ፕሮፓንዳ ይነዛል፡፡ የአእምሮን ሪሶርስ ለራስ ግብ ለማዋል መሞከሩ ይቀድማል፡፡ “Soft copy” የሆነው አእምሮ “Brainwash” በማድረግ የአእምሮውን ባለቤትና የመሬቱ ባለቤትን የራስ ማድረግ ቀላሉ አማራጭ መንገድ ነው፡፡ በቴሌቪዥን ጣቢያ፣ በሬዲዮ ጣቢያ .. ፕሮፓጋንዳ ይመረታል፡፡ አእምሮን ማጠብ ካልተቻለ ማደንዘዝም ይጠቅማል፡፡ በሰው መሰረታዊ ሪሶርስ (አእምሮ) ላይ የፈለግከውን መልዕክት ለዘላቂነት መፃፍ ከቻልክ የመሬት ባለቤቱን በራሱ መሬት ላይ ላንተ እንዲያመርት ወይም ለፈጣሪ ፅድቅ ሲል እያመረተ እንዲመስለው ልታደርገው ትችላለህ፡፡ ሪሶርሱ ለራሱ ማሰብ “ሀጢአት” እንደሆነ ልትነግረው ትችላለህ፡፡ ለፈጣሪና ለሀገር ማሰብ ግን ፅድቅ እንደሆነ … ይሄንን ማሰብ ለአንተ ተቋም ግብር በመስጠት እንደሚገኝ ልትነግረው ትችላለህ፡፡ ሁለትህም በአንድ ዓይነት ሪሶርስ (አእምሮና አካል) ያለህ ሆነህ ሳለ የራስህን ሪሶርስ በአግባቡና ብልጠትን ከጉልበት ቀላቅለህ በመጠቀም … ራስህን ወደ አንበሳ፣ ሌላውን ወደ ሚዳቋ መለወጥ ትችላለህ፡፡
… ምናልባት “ነፃ ምርጫ ራሱ ነፃ ላይሆን ይችላል” … ምናልባት ነፃነት ራሱ በነፃ አይገኝም፡፡ ምናልባት ነፃነት ራሱ ምን ማለት እንደሆነ ላላውቅ እችላለሁኝ። ግን አንድ ነገር የማውቀው ሪሶርሴ የራሴ መሆኑን ነው፡፡ ጭንቅላቴ የራሴ ነው፡፡ አካሌ የራሴ ነው፡፡ … የቆምኩበትን መሬት የራሴ እንዲሆን ከምለፋው ይልቅ የራሴ አእምሮ ቢያንስ … የተወሰነ የማመዛዘኛ ክፍሉ … የራሴ እንዲሆን እሻለሁኝ፡፡ … ካልሆነ የራሴ ብዬ የቆምኩበትን መሬት፣ አእምሮዬን ለተቆጣጠረው ሀሳብ ማውረሴ አይቀርምና፡፡
… የማስባቸው ሀሳቦች ምን ያህሉ በራሴ ምርጫ የታሰቡ እንደሆኑ ባላውቅም በመፅሐፍ ምክኒያት ለማሰብ የተገደድኩት እንዳልሆነ በራሴ የምናብ ፈረስ ወዲህና ወዲያ ከጋለብኩ በኋላ ተመለስኩኝ፡፡ አጥፌ ያስቀመጥኩትን መፅሐፍ በድጋሚ አንስቼ ማንበብ ጀመርኩኝ፡፡ “ነፃ ምርጫ” ምን እንደሆነ ባላውቅም፣ አሁን እያሰብኩ የመጣሁት ሁሉ የዚህ ያልታወቀው ነገር፣ “ነፃ ምርጫ” መገለጫ ተደርጎ ይወሰድልኝ፡፡  

Read 1425 times