Saturday, 28 July 2018 16:04

ፍቅር ጠርዝ የለውም፤ ማጣትም መሙላትም አይደለም

Written by  ደረጀ ኅብስቱ
Rate this item
(2 votes)

 ጀብደኛው ደራሲ በዓሉ ግርማ ከአቀረበልን ምርጥ ሥራዎቹ ውስጥ ‹ኦሮማይ› አንዱ ተጠቃሽ ነው፤ ሰሞኑን ፍቅር ፍቅር የሚሸቱ ወሬዎች በዝተዋልና በበዓሉ ገጸባህሪያት በኩል አጮልቀን፣ ጀብደኛ ፍቅሮችን እንኮምኩም (ጋሼ ስብሐት በህይወት ቢኖር ኖሮ ‹እነሆ ጀግና› ይለን ነበር)፡፡ ፍቅር ጠርዝ የለውም፤ እንደ መኪና በተጠረገለት መንገድ ብቻ ሳይሆን እንደ ቡልዶዘር ጋራውን፣ ቋጥኙን፣ ሸንተረሩን፣ ገደሉን፣ ጢሻውን ሁሉንም እየጠረማመሰ መጓዙን ይችልበታል፤ ያለመው ያሻው ግቡ ሳይደርስ የሚበግረው የለም፡፡ ‹‹ፍቅር መሐል ዳር፣ ሰሜን ደቡብ አይልም›› ይለናል፤ በዓሉ በፊያሜታ በኩል አጮልቆ፡፡ ሽማግሌው ፈላስፋ ሶቅራጥስ፤ ‹Love desires that of which love is› የሚለው ነገር አለው፡፡
ፍቅር የሚፈልገው እራሱ ፍቅርን ብቻ ነው፤ ምክንያቱም ፍቅር በርቀት በኩል ሳይሆን በአቅጣጫ በኩል ካየነው ሁሌም የመካከለኛ መንገድ ተጓዠ ነው፤ ጠርዝ ብሎ ነገር አያውቅምና፤  ማናችንም ብንሆን ሁሌም የምንፈልገው  የሌለንን ነገር ማሟላት ነው። ፍቅር ግን የአንድ አቅጣጫ መንገደኛ ስላልሆነ መሃል ሰፋሪ ነው፤ ግን መሃል ሰፋሪነቱ በየአቅጣጫው እንዲወጠር ያደርገዋል፤ ሽሚያ፣ ድካም፣ ፍትጊያ፣ ግፊያ፣ ጉንተላ፣ ውጥረት የተሞላበት መሃል ሰፋሪነት። ‹‹በይበልጥ ማነሳሳትና ማስቆጣት--- አርፎ እንዳይተኛ በአእምሮው ውስጥ ዘላቂና ቋሚ ሽብር መፍጠር---ማንም ያለ ስጋት መኖር የለበትም። ሠላም የለም›› በማለት በዓሉ ውጥረት ይፈጥራል፤ እፍፍ ባለ ፍቅር ለሚጦዙት ቀበጥባጣዋና አፍቃሪዋ ፊያሜታና ጋዜጠኛው ጸጋዬ፡፡ ‹…then he and every one who desires, desires that which he has not already, and which is future and not present and which he has not, and is not, and of which he is want, these are the sort of things which love and desire seek?› ይለናል ሽማግሌው ሶቅራጥስ የፍቅርንና የመፈለግን ነገር ውስብሰብ ሲያደርገው፡፡
ፍቅር የተራበ ሰው ዛሬ ላይ ፍቅርን አንሶታል ማለት ነው፤ ለወደፊቱ ለነገ ግን ማግኘትን ይሻል፤ በመሻት ውስጥ ደግሞ ውጥረት አለ፤ ሙሉም አይደለም ባዶም አይደለም፤ በሙላትና በባዶነት መካከል ሆኖ የሁለቱም ስበት ወጥሮ ይዞታል፤ በባዶነትና በሙሉነት መካከል መሐል ሰፋሪ ነው፡፡ ሙሉ ቢሆን ኖሮ ምንም አይፈልግም ነበር፤ ባዶም ከሆነ ባዶ ነው፤ የፍቅር ባዶነት በምንም አይጠገንምና፡፡ ፍቅር ግን ባዶም ሳይሆን ሙሉም ሳይሆን መካከለኛ ነው፡፡ ፍቅር ውስጥ ብቸኝነት የለም ብዙነትም የለም፤ የመሃል ቤት ሆኖ የራሱን አዲስ ዓለም እንደ መተዋወቅ ይሆናል፤ ሰው ባጠገባችን ባይኖርም እንኳን በፍቅር ውስጥ ያለ ሰው ተፈጥሮ አብራው ትሆንለታለች፡፡ ይህንን ለማሳየት ይመስላል በዓሉ፤ ፊያሜታን በሌሊት የቀይ ባሕር ዳርቻ ብቻዋን ወስዶ ጸጋዬ እንዲያገኛት ያደረገው፡፡ ‹‹ከባሕር ጋር ሆኖ ማንም ብቻዬን ነኝ ማለት አይችልም›› ትላለች ፊያሜታ፣ ጊላይ ጸጋዬ፤ ‹‹ምነው ብቻሽን›› ሲላት፡፡
ፍቅር በውስጧ ያረገዘችው ፊያሜታ ከባሕሩ ሞገድ፣ ከንፋሱ ወጀብ፣ ከብርሃናት ብርቅርቅታ ሙዚቃ እየቀመረች ትጫወታለች፤ አንዳች የማታውቀው የባሕር ውስጥ አቀናባሪ የሚያሰማውን ከበሮ፣ ጊታር፣ ዋሽንት፣ ጡሩንባ …. ከምሽት ጨረቃዋ ጋር ደምቃ የፍቅር አማልክት መስላ ከባሕሩ ጋር ቆማለች፡፡ ‹‹…he [Love] interprets … between gods and men, conveying and taking across to the gods the prayers and sacrifices of men, and to men the commands and replies of the gods, he [Love] is the mediator…›› ይለዋል ፍቅርን ሶቅራጥስ ከአሮጊቷ ዲያቴማ የተማርኩት ነው በሚለው ንግግሩ፡፡ ፍቅር መለኮትም ሰውም አይደለም፣ ሟችም ዘላለማዊም አይደለም፤ መካከል ላይ ያለ መንፈስ ነው ትለዋለች - አሮጊቷ ዲያቴማ ለሶቅራጥስ፡፡ ሰውም መለኮትም ስላልሆነ ነብይ መንፈስ ነገር ነው፤ የሰዎችን ጸሎትና መስዋዕት ለአማልክት ያደርሳል፤ ከአማልክቱ ደግሞ ትዕዛዛትንና መልሶችን ይዞ ወደ ሰዎች ያደርሳል፤ በቃ ይሄው ነው ፍቅር ማለት፡፡
‹‹ጣፋጭ ደደብ›› ‹‹ጣፋጭ ውሸታም›› የሚል ለየት ያለ የፍቅር መግለጫ ቋንቋ አላቸው፤ ፊያሜታና ጸጋዬ። ውሸታምነትን እያጣፈጡ፤ ደደብነትን ባህሪውን ቀይረው እያጣጣሙ መኖር የሚቻለው እንደነ ፊያሜታና ጸጋዬ ጭልጥ ባለ ፍቅር ውስጥ ሲሆኑ ብቻ ነው፡፡ ፍቅር ቋንቋውን ለቻለበት ሰው፤ ያልነበረውን እንደነበረ፣ ተፈጥሯዊ የማይመስለውን እንደ ተፈጥሮ እንድንቀበለው ያስችለናል፤ ፍቅር ነዋ ቋንቋው። የፍቅር አማልክት ከመለኮት ተልከው ሲመጡለት ሁሉም ነገር በመለኮት ይቻለዋል፤ ለአፍቃሪ ሰው። ተፈጥሮ ትታዘዘዋለች፤ ብቻውን የቆመ ቢመስልም ብቻውን አይሆንም፤ ንፋሳት ያዜሙለታል፤ ባሕር ታጫውተዋለች፤ ብርሃናት ያሸበሽቡለታል፤ ጨረቃ ቤተኛው ትሆናለች፤ ከዋክብት ያጅቡታል፤ በፍቅር ሁሉም ይቻላል። ‹‹በሥነ ሥርዓት ግን ሠላም አይሰጠኝም፡፡ ፍቅር ሠላም አይሠጠኝም፡፡›› ትላለች፤ ቀበጥባጣዋ አፍቃሪ ፊያሜታ፡፡
የፍቅርን ቋንቋ እስክንለምደው ድረስ የቆየ ልማዳዊ ተፈጥሯችንን ይፈታተነናል፤ ከሰውነታችን እስኪመጥን ድረስ ሠላም ያሳጣናል፣ ያቅበጠብጠናል፣ እረፍት ይነሳናል፤ ፍቅር በባዶነትና በሙሉነት መካከል ላይ የተወጠረ ነውና ቋንቋውን እስክንለምድ ይረብሸናል፤ ሠላም አይሰጠንም፡፡ ህመሜ ህመሜ እያልን ልናዜም ሁሉ እንችላለን፤ ነባራዊ ተፈጥሯችንን ሲፈታተነን የታመምን ስለሚመስለን፤ እናም በዓሉ ግርማ በፊያሜታ በኩል አጮልቆ ‹ፍቅር ሠላም አይሰጠኝም› ይለናል፡፡ የቀይባሕር ማዕበል ከጣና ሞገድ ጋር መሳሳብ ሲጀምሩ፤ ጥልቁ ዳሎል እንደ ራስ ዳሸን ተራራ ሲንጠራራ፤ የኤርታሌ የምድር እሳት ጽጌረዳ ማቆጥቆጥ ሲጀምር፤ ሠላም እናጣለን፣ ከለመድነው ውጭ ይሆንብናል፡፡ አዲስ አበባና አስመራ በፍቅር ሲከንፉም እንዲሁ ይምታታብናል፤ ‹በሥነ ሥርዓት ግን ሠላም አይሰጠኝም› ይለናል፤ በዓሉ ግርማ በፊያሜታ በኩል አጮልቆ፡፡ ፍቅር ያሸንፋል ይሉሃል ይሄም ነው፡፡
አሮጊቷ የፍቅር መምህር ዲያቴማና ሶቅራጥስ ውይይታቸውን ቀጥለዋል፤ ሶቅራጥስ ይጠይቃል፣ አሮጊቷ ትመልሳለች ‹‹is Love then evil and foul ?›› ይላል ሶቅራጥስ፡፡  ‹‹Must that be foul which is not fair … and is that which is not wise, ignorant … do you not see that there is a mean between wisedome and ignorance›› አሮጊቷ ትመልሳለች፡፡ ‹‹..and what that may be?›› ሶቅራጥስ ይጠይቃል፡፡ ‹‹right opinion›› ትለዋለች መምህሩ። ጸጋዬና ፊያሜታ ግን ምን አይነት ጅሎች ናቸው፤ እኔንጃ፤ ምናልባት እንደ ሶቅራጥስ አይነት ጅሎች ይሆኑ ይሆናል፡፡ የሶቅራጥስ የፍቅር ትምህርት ብዙ ነገሮችን የሚፈትሽ አይነት ነው፤ፍቅር ሃያል አምላክ ካልሆነ ከቶ ምን ሊሆን ይችላል፤ ሞኝና አድሏዊ፡፡ አድሏዊ የሆነ ሁሉ ግን ሞኝ ነው፤ ጠቢብ ያልሆነ ሁሉ ደደብ ነው፤ በጠቢብነትና በድድብና መካከል ምንም ስፍራ የለም፤ ፍቅር አለ፤ ትክክለኛ አመለካከት፡፡ ‹‹ዋእ እኔ! ምን መሰልኳት እባክህ? ለሽያጭ የሚቀርብ ከብት? ... አባቴ ይሙት፡፡ የሰው ልክ አያውቁም…›› ትላለች ለጸጋዬ፤ ቀበጥባጣዋ ፊያሜታ የዋህነቷን አፍቃሪነቷን አይታ ለሌላ ወንድ ልታታልላት የሞከረቻትን ጓደኛዋን እያሰበች። አፍቃሪ ሰው ደደብ ነው አይጠረጥርም ማለት አይደለም ወይም ደግሞ ፍቅር ውስጡ ስላለ ጠቢብ ነው ማለትም አይደለም፤ በደደብነትና በጠቢብነት መካከል ላይ ፍቅር አለ፤ ፍቅር ደግሞ በሰውየውና በአምላኩ መካከል ነብይ ሆኖ ይኖራል፡፡
ጋዜጠኛው ጸጋዬና አፍቃሪዋ ፊያሜታ ጨዋታቸውን እንደቀጠሉ ነው፡፡ ‹‹አባቴ ይሙት እኔ’ኮ መወሰን አልችልም፡፡ ሁሉንም ነገር እንደ ቀልድ እንደ ጨዋታ ነበር የምወስደው፡፡ አልጠፋሁ (ከሃገር ማለቷ ነው) ወይ አርፌ አልኖር፡፡
 የራሴ ቤት የለኝም፡፡ ትዳር አልያዝኩም፡፡ ሴንካ ካዛ ሴንካ ማሪቶ፡፡ ግን ምንድን ነኝ? መወሰን የማልችል…›› የፍቅር ውጥረትን ተሸክማ የምትንገዳገድ የምትመስለው የፍቅሯ ሴት፤ለፍቅር የተፈጠረችው ፊያሜታ የብስጭት የቁጭት ስድብ የሚመስሉ ሃሳቦችን ታዘንባለች፤ ላፍታ ያህል እንጅ ተመልሳ አፍቃሪ ልቧ ውስጥ ትሰምጣለች፡፡ ጸጋዬ በበኩሉ ተመሳሳይ ስሜት የሚንጠው ይመስላል፤ ‹‹መከረኛው አሮጌ ልቤ ሁለት ሴቶች እንዴት ብሎ እኩል ሊወድ ይችላል ብዬ ተገረምኩ፡፡ ሕይወት እንግዳ ነገር ነው፡፡ ብዙው ቀልድ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ቀልዱ ይመራል፡፡ በሁለቱ መካከል መወሰን አልቻልኩም፡፡ ለደግም ሆነ ለክፉ መወሰን አለመቻል ስቃይ ነው፡፡ ልቤ ሲደማ ተሰማኝ፡፡›› ይለናል፤ ጸጋዬም መሸከም የተሳነው እንግዳ ተፈጥሯዊ ያልሆነው ስሜት ሲታገለው፡፡
የሶቅራጥስ የፍቅር መምህሩ ዲያቴማ ትምህርቷን ቀጥላለች፤ ፍቅር ደሃም ሃብታምም አይደለም፤ አያጣምም አይሞላለትምም፤ ምንም ሳይኖረው ሁሉም አለው፤ ዝም ብሎ በድህነትና በሃብታምነት መካከል ነው፡፡ የውበት አምላክ የሆነችው አፍሮዳይት ልከቷን አባቷ ዚዎስ ዲል አርጎ ደግሶ ሰውን ሲያበላ ሲያጠጣ ይውላል፤ ጋሼ ሃብታም የሚባለው በልቶ ጠጥጦ ይሰክርና ከዛፍ ጥላ ስር ጋደም ይላል፡፡ እመት ድህነት እንደ ልማዷ አያልፍላትምና የሚበላው የሚጠጣው ካለቀ በኋላ ትደርሳለች፤ ነገሩ ይቆጫትና ዘወር ዘወር ስትል ጋሼ ሃብታም ከዛፍ ስር እንቅልፍ ወስዶታል፤ ተንኮል አሰበችና ተኛችው፤ ጸነሰች። የወለደችውም ፍቅር ሆነ፡፡ እናም ፍቅር በአባቱ ሃብታም በእናቱ ደግሞ ያጣ የነጣ ደሃ ስለሆነ እርሱ የመሃል ቤት ነው፡፡ ፍቅር ጠርዝ የለውም፤ ማጣትም መሙላትም አይደለም፤ ደደብም ጠቢብም አይደለም፤ መሃል ቤት ነው፡፡
በዓሉ ግርማ ቀጥሏል፤ የጸጋዬን ታሪክ የሚተርክልንን ደራሲውን ይጠራና በደራሲው በኩል አጮልቆ እንዲህ ይለናል፤ ‹‹ታስታውሰኛለህ? ካላስታወስከኝ ግድ የለም። በመጀመሪያ ቃል ነበር ቃልም ደራሲ ነበር፡፡ ደራሲም ቃል ነበር፡፡ ጸጋዬ ተኝቷል፡፡ ታሪኩ ግን ይቀጥላል፡፡ ህይወት አንድ ቦታ ላይ አትቆምም …ትቀጥላለች፡፡ ያንዱን ህይወት ከሌላው ጋር ድርና ማግ እያደረገች…›› ይለናል ኦሮማይን ያበረከተልን ጀብደኛው በዓሉ ግርማ። አባቶቻችን ስለ ፍቅር ብዙ ትምህርት አላቸው፤ ለዛሬው ግን ይህችን አባባላቸውን እንዋሳቸው፤ ‹‹ፍቅር ሰሐቦ ለወልድ ሐበ መንበሩ›› ከኪሩብ ዙፋኑ ላይ ተነስቶ ሰው ሆኖ አዳምን ፈጣሪ ያዳነው ስለ ፍቅር ብሎ ነውና፣ ዘላለማዊ ፍቅርና ሰላም ለኢትዮጵያና ለኤርትራ ህዝቦች እንመኛለን፡፡

Read 1620 times