Saturday, 28 July 2018 16:01

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(1 Vote)


     “ሚሊዮን ወገኖች በረሃብ፣ በስደት፣ በህመምና መጠለያ በማጣት በሚማቅቁበት ሃገር ገንዘብ ባንክ እንዳይቀመጥና ጥቅም
እንዳያስገኝ፣ በልማት ስራ እንዳይውልና የስራ ዕድል እንዳይፈጠርበት፣ በማዳበሪያና በፌስታል አጉሮ ማስቀመጥ ያሳዝናል፡፡…
የመደመርን “ፍልስፍና”ም ይፈታተናል፡፡--”
      

     ይቺን ቀልድ ሰምተሃል ወዳጄ?... ለዛሬው የሀሳብ መንገዳችን “ውሃ ልክ” ትመስላለች፡፡… ሁለቱ ጓደኛሞች ናቸው አሉ፡፡… ሁለቱም መሃንዲሶች ናቸው። አንደኛው አውሮፓ፣ ሌላኛው እኛ ጎረቤት ይኖራሉ፡፡ ከረዥም ጊዜ በሁዋላ አውሮፓ የሚኖረው መሃንዲስ ጓደኛው መጥቶ እንዲጎበኘው ጋበዘውና ሄደ፡፡… በጨዋታቸው መሃከል አፍሪካዊው፡-
“አንድ ዓይነት ትምህርት ነው የተማርነው፤ ኑሮህ እንዲህ የተሟላው እንዴት ነው?” ብሎ ይጠይቀዋል…ጓደኛውን፡፡
ጓደኛውም…. “ይሄ እኮ ያደገ አገር ነው፣ በስራህ መጠን ታገኛለህ” አለውና ትንሽ አሰብ አድርጎ…”ና…ላሳይህ” ብሎት ወደ ላይኛው ክፍል ወሰደው፡፡ በመስኮት በኩል እያመላከተው…
“ያ ድልድይ ይታይሃል?” በማለት ጠየቀው፡፡
“አዎን” አለ፤አፍሪካዊው፡፡
“እኔ ነኝ የሰራሁት፤ከሱ ላይ 5% ሰርቄአለሁ”… አለ እየሳቀ፡፡… ከሁለት ዓመታት በሁዋላ አፍሪካዊው መሃንዲስ በተራው ጓደኛው እረፍቱን ከሱ ጋር እንዲያሳልፍ ጋበዘው፡፡ እንደመጣም በጠበቀው ተዓምር እየተገረመ…
“ይኽን ሁሉ ሃብት በአጭር ጊዜ እንዴት አገኘህ?... ኑሮ ከባድ መሆኑን አጫውተኸኝ ነበር” አለው…
ጓደኛውም፤ “ና… አንድ ነገር ላሳይህ” አለውና እጁን ይዞት፣ ወደ ሁለተኛው ፎቅ ወጡ፡፡ ምን ሊያሳየው ይሆን?
* * *
“ድህነት፡- የመጥፎ መንግሥት አስተዳደር እንዲሁም ስልጣኔ የሚያደናቅፉ ሁዋላ ቀር ልማዶች ውጤት ነው (Poverty is the result of corrupt leadership and retrograde cultures that impade modern development”) የሚለን ፕሮፌሰር ጄፈሪ ሳሽ ነው፡፡ ፕሮፌሰሩ የብዙ አገሮች የዕድገት ማነቆ የሆኑትን ምክንያቶች በማጥናትና መፍትሄ በመጠቆም የሚታወቅ የምጣኔ ሃብት ሊቅ ሲሆን ከሁለት ዓመት በፊት ወደ ሃገራችንም መጥቶ ነበር፡፡ ሳሽ ዋነኛ ከሚላቸው የዕድገት ማነቆዎች ውስጥ…
አንደኛ፡- ድህነት (Poverty trap) የሚለው ሲሆን… ስር የሰደደ ድህነት ለረሃብና ለስደት ምክንያት መሆኑን፣ ለዚህም የመሰረተ ልማት አለመሟላት (ውሃ፤ መብራት፣ ስልክ፣ ትራንስፖርት፣ የትምህርትና የጤና ተቋማት የመሳሰሉትን) እንደ ምሳሌ ይጠቅሳል፡፡ የደን መመንጠር፤ የመስኖ ውሃ አለመጠቀምና ቁጠባን አለመልመድም ችግሩን እንደሚያባብሱት `The End of Poverty` በሚለው መጽሐፉ አስፍሯል፡፡
ሁለተኛው፡- ሃገሪቱ የምትገኝበት ክልል ወይም መልክዐ ምድራዊ አቀማመጥ (Physical geography) ሲሆን…. የተፈጥሮ ሃብት (natural resource) ማነስ ወይም አለመኖር፤ ድርቅና ጎርፍ ለመሳሰሉ የተፈጥሮ አደጋዎች መጋለጥ፣ የኮንትሮባንድ ንግድ አመቺነት፣ የወደብ አለመኖር ወይም የወደብ ኪራይ ንረት እንዲሁም የእርሻ መሬትና የዝናብ ሁኔታንም ይዳስሳል።
ሦስተኛ፡- የገንዘብ አጠቃቀም ውሱንነት (Fiscal trap) አስፈላጊ ዕቃዎችንና አላቂ ሸቀጦችን በተገቢው ጊዜና ቦታ ማቅረብ አለመቻል፤ የገንዘብ ግሽበትና የመግዛት ዓቅም ማነስ፤ የውጭ ምንዛሪ ማጣት፤ ታክስ በጊዜና በአግባብ አለመሰብሰብ፤ የተሰበሰበውን ታክስ ለሌሎች ጉዳዮች (ለዕዳ ክፍያ፣ ለጦርነት ወዘተ) ማዋል፣ ኢንቨስትመንት መፍጠር ወይም መሳብ አለመቻልና የመሳሰሉትን ይመለከታል፡፡
አራተኛ፡- መንግሥት መሆንን አለመቻል (Government failure)… በዚህም ውስጥ ብሔራዊ ማንነትን፤ ብሔራዊ አንድነትን፤ ብሔራዊ ግዛትና ሉዓላዊነትን አለማስከበር፤ የግል ንግድን አለማበረታታት፣ የተረጋጋ ሰላም አለመኖር፣ ለባለ ሃብቶች ንብረት ጥበቃ አለማድረግ፤ ከባለ ሃብቶች ጋር የሚደረገው የልማት ስምምነት በሃቅና በጥናት ላይ የተመረኮዘ አለመሆን፣ ከአድሏዊነት፣ ከጉቦኝነትና ከሌብነት የፀዳ መንግስታዊ አገልግሎት መስጠት አለመቻልና ሌሎች የመንግሥትን ሚና ዝቅተኛነት የሚያጎሉ ጉዳዮች ይገኙበታል… (Poverty+bad governance= instability)
አምስተኛው፡- የአጓጉል ልምዶችና ሁዋላ ቀር ወጎች ማነቆነት (Cultural barriers)… በተለያዩ እምነቶችና ሃይማኖታዊ ልማዶች ሰበብ ሥራ መፍታትና ጊዜ ማባከን፣ በሴቶች ጭቆና የሚመጣ የምርት መቀነስ፣ በጎላ ንቀትና መገለል ምክንያት የሚፈጠር የሥራ በደልን (ሸክላ ሰሪ፤ ፋቂ ወዘተ) ይጨምራል፡፡
ስድስተኛ፡- ጂኦ-ፖለቲክስ (geopolitics)… አገሪቱ የምትገኝበት ክልል ጠቀሜታ፣ የምትከተለው የፖለቲካ አቅጣጫና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የሚያስገኙላት ጥቅሞችና ጉዳቶችን (የገንዘብና የቴክኒክ ዕርዳታ፣ ማዕቀብና ኢኮኖሚያዊ ጫና ወዘተ) ይመለከታል፡፡
ሰባተኛ፡- ለአዳዲስ ቴክኖሎጂዎችና ፈጠራዎች አለመትጋት (Lack of innovation)… ለሳይንስ ምርምር፤ ለዕውቀት ዕድገትና ለጥበብ መንገዶች ስራ ቦታ አለመስጠት፣ ሁኔታዎችን አለማመቻቸትና አጋዥ መሳሪያዎችን ማቅረብ አለመቻልና የመሳሰሉትን ያጠቃልላል፡፡
ስምንተኛ፡- የህዝብ ቁጥር እየጨመረ መምጣትና የሰው ሃይልን በአግባቡ አለመጠቀም (The demographic trap)… የቤተሰብ ምጣኔና የወሊድ ቁጥጥር ስርዓት አለመኖር፤ የወላጅ አልባ ህፃናትና ዓቅመ ደካማ አረጋውያን ጉዳይ፣ ሥራ አጥነትና የሥራ መስክ ማነስ፣ ከሥራ መፈናቀል፣ የጤና፣ የምግብና የመጠለያ አሳሳቢነት፣ በግጭትና በተለያዩ ሰው ሰራሽ ምክንያቶች አካባቢን መልቀቅ፤ ከቦታ ቦታ በነፃነት እየተዘዋወሩ መሥራትና እድልን መሞከር አለመቻልና የመሳሰሉት ይካተታሉ፡፡… ፕሮፌሰሩ የጠቀሳቸው የድሃና ታዳጊ አገራት ችግሮች ከሞላ ጎደል እንዳሉ ሆነው፣ ራሳችን በራሳችን ወገኖች ላይ የምናደርሰው በደል ሲታከልበት ብሶታችን መረን ይለቃል፡፡… በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ!!
ወዳጄ፡- ሚሊዮን ወገኖች በረሃብ፣ በስደት፣ በህመምና መጠለያ በማጣት በሚማቅቁበት ሃገር ገንዘብ ባንክ እንዳይቀመጥና ጥቅም እንዳያስገኝ፣ በልማት ስራ እንዳይውልና የስራ ዕድል እንዳይፈጠርበት፣ በማዳበሪያና በፌስታል አጉሮ ማስቀመጥ ያሳዝናል።… የመደመርን “ፍልስፍና”ም ይፈታተናል፡፡ ገንዘብ ከየባንኩ ያለ ኮላተራል እየተበደሩ፣ በውጭ ምንዛሪ እየቀየሩ ማሸሽና ከዝውውር ውጭ ማድረግ ጨካኝነት ነው፡፡ በባለስልጣናት ትዕዛዝ ስለሚሰጡ ብድሮችና እንዲሰረዙ ስለሚደረጉ ዕዳዎች መስማት ይዘገንናል፡፡… ከባንክ ባለስልጣናት ጋር እየተመሳጠሩ የአገር ሃብት መዝረፍ ብልግና ነው፡፡ በሌለና ባልተጀመረ ፕሮጀክት ዲዛይንና ፎቶግራፍ እየላኩ እርዳታ ሰጪዎችን ማታለል፣ ለኛ ለኢትዮጵያውያኖች ውርደት ነው፡፡
ወዳጄ፡- የመንግስት የህዝብ ፕሮጀክቶች በተመደበላቸው ጊዜ እንዳይጠናቀቁ በማድረግ፣ ጠቃሚነቱ ላልተረጋገጠ ፕሮጀከት በጀት በማስመደብ የግብር ከፋዩን ገንዘብ ለሌብነት ማመቻቸት፣ የተበላሹና ጊዜ ያለፈባቸው ሸቀጦች ሆን ተብለው ወደ አገር እንዲገቡ መፍቀድ፤ በጉቦና በምልጃ መጠላለፍ በተለመደበት አገር እንዴት ለውጥ ማምጣት ይቻላል?...በዘመድ መቀጠር፣ በፎርጅድና በግዢ ሠርተፍኬት ማደግ “ባህል” በሆነበት፣ በዘርና በጎሳ በተደራጀ ፓርቲ ምልምሎች በተዋቀረ ሲቪል ሰርቪስ አጋፋሪነት እንዴት ለውጥ ማምጣት ይቻላል?..
ወዳጄ፡- “ቂጣ ቢገላበጥ ተመልሶ ቂጣ” እንዳይሆን ነገሩ… ሙስናን ከሥሩ መንቀልና ፍትሃዊ አስተዳደር ማስፈን አማራጭ የሌለው የዕድገት መንገድ መሆኑን ሊቃውንት ይመክራሉ፡፡…ሃይድራው (Hydra) ባለ ብዙ አንገት ነውና!!
* * *
ወደ ቀልዳችን ስንመለስ… እዚህ የሚኖረው መሃንዲስ፤ ከአውሮፓ ከመጣው ጓደኛው ጋር ወደ ሁለተኛው ፎቅ ወጡ ብለን ነበር፡፡ እዛም ላይ ሆነው አፍሪካዊው መሃንዲስ ጓደኛው እንዳደረገው በእጁ እየጠቆመ፡-
“ወዲያ ማዶ ያለውን ድልድይ ታያለህ?” ሲል ጠየቀው፡፡
“አረ በፍፁም!... ምንም አይነት ድልድይ አይታየኝም” አለ ጓደኛው፡፡
አጅሬውም ከት ከት ብሎ እየሳቀ፤ “100%” አለው አሉ፡፡
ወዳጄ፡- “ስግብግብና አሳማ ሆነህ ከሚደላህ… ጨዋና ጥሩ ሰው ሆነህ ብትቸገር ይሻላል… እንደ ሶቅራጥስ!!... (Better to be a human being dissatisfied than a pig satisfied; better to be socrates dissatisfied than a food satisfied”) በማለት የሚመክረን ታላቁ ጆን ስቲዋርት ሚል ነው፡፡
ሠላም!!

Read 826 times