Saturday, 28 July 2018 15:56

ብህትውናና ዘመናዊነት

Written by  ብሩህ ዓለምነህ (በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር)
Rate this item
(7 votes)

  ክፍል- 6 ጠ /ሚ ዐቢይ አህመድን በተአምራዊነት ተረክ
              ብሩህ ዓለምነህ (በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር)


    የተአምራዊነት እሳቤ በዋነኛነት የመንስኤ-ውጤት ግንዛቤ ላይ የሚያተኩር ፅንሰ ሐሳብ ነው፡፡ በዚህ ትኩረቱም ‹‹ተአምራዊነት›› በአብዛኛው መንስኤውን በመተው ውጤት ላይ ብቻ ያተኩራል፡፡ ውጤት ላይ ብቻ የሚያተኩረው ደግሞ መንስኤው ‹‹መለኮታዊ›› ነው የሚል የ‹‹ተአምራዊነት›› ተረክ ስላለው ነው። ይሄም ትርክቱ ተአምራዊነትን ስለ መንስኤ እንዳይጨነቅና መንስኤንም ለማወቅ ፍላጎትና አቅም እንዳይኖረው አድርጎታል፡፡ በእኛ ማህበረሰብ ውስጥ የአንድ ነገር መንስኤው ሁልጊዜ ‹‹መለኮታዊ ነው›› ተብሎ ነው የሚታሰበው፡፡
‹‹መንስኤ›› ሳይታወቅ ዕውቀትን ማመንጨት አይቻልም፡፡ የአንድ ህዝብ ቀጣይ ዕድገቱ ከሚወሰንባቸው ነገሮች አንዱና ዋነኛው ‹‹መንስኤ›› ላይ ያለው መረዳት (Concept of Cause) ነው፡፡ ሳይንስ የተወለደው የሰው ልጅ መንስኤን መረዳት ሲጀምር ነው፡፡ በመሆኑም፣ ሳይንሳዊ ዕውቀት የተመሰረተው ተፈጥሮ እንዴት እንደሚሰራ በሚኖረን የመንስኤ ፅንሰ ሐሳብ ላይ ነው፡፡ ባጭሩ ዕውቀት የሚባለው ውጤትን ማየት ሳይሆን መንስኤን መረዳት ነው፡፡
መንስኤን በ‹‹ተአምራት›› የሚሸፍን ማህበረሰብ ግን ምንም ዓይነት ዕውቀትና ሳይንስ ሳያመነጭ በድንቁርናና በድህነት ዘመኑን ይበላል፤ ንጉሳቸውንም በዓለም መድረክ ፊት ያዋርዱታል፡፡ አፄ ቴዎድሮስ ይሄ ነበር የገጠማቸው፡፡ ‹‹በርካታ ሊቃውንቶች አሉን›› እያልን በምንኮፈስበት ወቅት ነበር አፄ ቴዎድሮስ ራሳቸውን አዋርደው ‹‹እኛ እውርና ደንቆሮ ነንና ባለሙያ ልከው አይናችንን ያብሩልን›› እያሉ እንግሊዞችን ሲማፀኑ የኖሩት፡፡ አፄ ቴዎድሮስን እንዲህ ለውርደት አሳልፈን ሰጥተናቸው ሳለ ከጀርባቸው ግን ‹‹በፍካሬ እየሱስ ይነሳል የተባለው ንጉስ እኚህ ናቸው!!›› እያልን ከንቱ ውዳሴ እናስወራላቸው ነበር፡፡ የአፄ ቴዎድሮስን ወታደራዊ ጀግንነት ከማድነቅና የአመጣጣቸውን መንስኤዎች ከመረዳት ይልቅ ንጉሱን ‹‹ተአምራዊ›› ክስተት አድርገን ለትውልድ አስተላለፍናቸው። የሥነ መንግስት እሳቤያችን በእንደዚህ ዓይነት ‹‹ተአምራዊነት›› ላይ የተንጠለጠለ ነው፡፡
የእኛ ማህበረሰብ ከጥንት ጀምሮ በዚህ መልኩ ስነ ልቦናው በ‹‹ተአምራዊነት›› ፅንሰ ሐሳብ ስለተቀረፀ ተፈጥሯዊና ማህበራዊ ክስተቶችን ሁሉ ‹‹ተአምራዊ›› ያደርጋቸዋል፡፡ ተረኮቻችንና የታሪክ አረዳዳችን ሁሉ በዚህ በ‹‹ተአምራዊነት›› አስተሳሰብ የተሞሉት ለዚህ ነው፡፡ የነገስታቶቻችን ታሪኮች ሁሉ በተአምራዊነት ትርክት የተሞሉ ናቸው፡፡ ይህ የተአምራዊነት አስተሳሰብ አሁን ድረስ ተከትሎን መጥቶ ዶ/ር አብይ አህመድን ‹‹ከእግዚአብሔር የተሰጡን መሪ ናቸው›› እስከማለት አድርሶናል፡፡
‹‹የእኛ›› የምንለውና እንደ ዓይናችን ብሌን የምንሳሳለትን መሪ ጠ/ሚ አብይ አህመድን በማግኘታችን በግሌ በጣም ደስተኛ ነኝ። ሆኖም ግን፣ ዶ/ር አብይ ድንገተኛ ‹‹ተአምራዊ ክስተት›› አይደሉም፤ ይልቅስ ወደ አመራር እንዲመጡ በርካታ ተያያዥ ምክንያቶች አሉ እንጂ። ምንም ዓይነት የተአምራዊነት ተረክ ውስጥ መግባት ሳያስፈልገን፣ ጠ/ሚ አብይ አህመድ ወደ አመራር የመጡበትን መንገድ ለማወቅ ወደ ኋላ ሄደን ባለፉት ሦስት አስጨናቂ ዓመታት በሀገራችን ፖለቲካ ውስጥ የተከናወኑ አበይት ክስተቶችን ብቻ ማስታወስ በቂ ነው፡፡ ፖለቲካዊ ክስተቶቹም የሚከተሉት ናቸው፡፡
በህዳር ወር 2008 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ የኦሮሚያ ልዩ ዞኖች ድረስ የሚለጠጠውን የአዲስ አበባን ማስተር ፕላን በመቃወም በአምቦ የተነሳው አመፅ በመላው ኦሮሚያ ተዛመተ፡፡ ያለ ምንም የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር የኦሮሞ ወጣቶች (ቄሮ) አመፁን መሩት፡፡ ይህ አመፅ ማስተር ፕላኑን ከማሰረዙም በላይ፣ ለ25 ዓመታት የታሪክ ቁዘማ ውስጥ እንዲኖር የተደረገው የኦሮሞ ህዝብ ከታሪክ ተብሰልሳይነት የወጣበትን አዲስ ክስተት ፈጠረ፡፡
አመፁን መቆጣጠር ያቃተው በአቶ ሙክታር ከድር የሚመራው የኦሮሚያ ካቢኔም በሙሉ ስልጣኑን በመልቀቅ በአቶ ለማ መገርሳ ካቢኔ ተተካ። የአቶ ለማ ካቢኔም ስልጣን እንደተረከበ ወዲያው ያደረገው ነገር ስር ነቀል የሆኑ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እርምጃዎችን መውሰድ ነበር፡፡ ኢኮኖሚያዊው እርምጃ ‹‹የኢኮኖሚ አብዮት››ን በማወጅ በኦሮሚያ የተዘረጋውን ‹‹የኮንትሮባንዲስቶች›› የኢኮኖሚ ኢምፓየር መበጣጠስ ሲሆን፤ ፖለቲካዊው እርምጃ ደግሞ ከታሪክ ተብሰልሳይነት የወጣውን የኦሮሞ ህዝብ በመወከል ‹‹ለወንድማማችነት›› ግንኙነት ወደ ባህር ዳር መጓዝ ነበር፡፡ በዚህም በኢህአዴግ ውስጥ ይፋዊ ያልሆነ ሆኖም ግን በግልፅ የሚታይ የለማ-ገዱ ቡድን ተፈጠረ፡፡ እንግዲህ ይህ የኦህዴድ-ብአዴን ጥምረት ነው በመጋቢት ወር 2010 ዓ.ም የተደረገው የኢህአዴግ የሊቀ መንበርነት ምርጫ ላይ ዶ/ር አብይ አህመድ እንዲመረጡ ያደረገው፡፡
ይሄ ያለፉት ሦስት ዓመታት ታሪክ ነው፡፡ ዶ/ር አብይ አህመድ ወደ አመራርነት እንዲመጡ ያደረጋቸው የመንስኤ-ውጤት ሰንሰለቶች እነዚህ ናቸው፡፡ እንግዲህ በዚህ የመንስኤ-ውጤት ሰንሰለት ውስጥ የ‹‹ተአምራዊነት›› ቦታው የቱ ጋ ነው? የሦስት ዓመታት መንስኤና ውጤት ማስተሳሰር አቅቶን ነው ዶ/ር አብይን ‹‹ከእግዚአብሔር የተሰጡን መሪ ናቸው›› እስከ ማለት ያደረሰን?
ይሄንን ‹‹የተዓምራዊነት ተረክ›› (mystical narration) እያስተጋቡ ያሉት ደግሞ ከምሁራን ጀምሮ እስከ ተራው ህዝብና ሚዲያው ድረስ ነው። ለምሳሌ፣ ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም ስለ ጠ/ሚ አብይ አህመድ አመጣጥ በፌስቡክ ገፃቸው ላይ ሲገልፁ፤ ‹‹እግዚአብሔር የኢትዮጵያን ህዝብ ስቃይና መከራ አይቶ አብይ አህመድን ፈጠረውና ወደ ኢትዮጵያ ላከው›› ሲሉ፤ ዲ/ን ዳንኤል ክብረት ደግሞ ‹‹የዶ/ር አብይ አህመድ መምጣት ኢትዮጵያ ልዩ ጥበቃ የሚደረግላት የተአምራት ሀገር መሆኗን ያሳያል›› ብሏል፡፡
የሙዚቃ ሐያሲው ሰርፀ ፍሬስብሐት በበኩሉ፤ የዶ/ር አብይ አህመድን አመጣጥ እንዲህ በማለት ነበር ተአምራዊ ተረክ ያላበሰው፤ ‹‹በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር እየሆነ ያለው ሁሉ ከቃል አቅምና ከመደነቅ ክሂል በላይ ነው፡፡ ‹‹ፀጋው›› አካሎቻችን ለሆኑት ለኤርትራውያ ሳይቀር ምን ዓይነት ስሜት እንደፈጠረባቸው ሁላችንም ያየነው ነውና ‹‹ጉድ›› እያስባለን ነው፡፡ ይሄ ሁሉ እንግዲህ ከላይ ከ‹‹መንበረ ጸባዖት›› የተፈቀደ ቢሆን እንጂ በዚህ ዓይነት ምልዓት እንዴት ሊሳካ ይችላል?››
በተለያዩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች የሚቀርቡ ሰዎችም ይሄንን የተአምራዊነት ተረክ ደጋግመው ሲናገሩ መስማት የተለመደ ሆኗል፡፡ በአዲስ አበባ በየሳምንቱ የሚታተሙ የግል መፅሄቶችም ይሄንን ህዝባዊ ስሜት በመከተል ጠ/ሚ አብይን አንድ ጊዜ ‹‹ኢትዮጵያዊው ሙሴ››፣ በሌላ ጊዜ ደግሞ ‹‹የተቀባው መሪ!!›› በማለት ተአምራዊውን ተረክ እያጠናከሩ ይገኛሉ፡፡ በጣም የሚገርመው ነገር ደግሞ ፕ/ር መስፍን በ1986 ዓ.ም ‹‹ኢትዮጵያ ከየት ወዴት?›› በሚል ርዕስ ባሳተሟት አነስተኛ መፅሀፋቸው ላይ ‹‹መንግስትን መለኮታዊ አድርጎ ማቅረብ መንግስትን የማይጠየቅና የማይከሰስ በማድረግ በሥልጣን እንዲባልግ ከማድረጉም በላይ፣ ዜጎች አመራሩ ባልተመቻቸው ጊዜ ለመቀየር እንዳይነሳሱና ጭቆናን ተሸክመው እንዲኖሩ ያደርጋቸዋል›› ብለው መፃፋቸው ነው፡፡ ፕ/ር መስፍን በ1986 ይሄንን መፃፋቸውን ዘንግተው ዛሬ ከ25 ዓመታት በኋላ የጠ/ሚ አብይን አመጣጥ ‹‹መለኮታዊ ተአምር›› አድርገው አቅርበውታል፡፡
እንግዲህ ከእነዚህ የ‹‹ተአምራዊነት›› ትረካዎች ጀርባ ‹‹የመንስኤና ውጤት›› ፅንሰ ሐሳብን የምንረዳበት መንገድ በጣም ደካማ መሆኑን ያሳያል። ኢትዮጵያዊ አእምሮ ሁለት ክስተቶች እንዴት አመክኖያዊ በሆነ ግዴታ (logical necessity) እንደሚተሳሰሩ ስለማናውቅ ብዙ ጊዜ አያያዡን ‹‹ተአምራዊ›› እናደርገዋለን።
ነጋድራስ ገብረ ህይወት ‹‹አፄ ምኒሊክና ኢትዮጵያ›› በሚለው መፅሐፉ ውስጥ ‹‹ኢትዮጵያውያን እውነቱ ሲነገራቸው አይገባቸውም›› ይላል። ምን ዓይነት እውነት? አመክኖያዊ እውነት (Rational Truth)!!! እኛ ከጥንት ዘመን ጀምሮ በ‹‹ተዓምራዊነት ተረክ›› እየተሰራን ስለመጣን ነገሮችን የምናብራራው ከአመክንዮ ይልቅ ተአምራዊ (mystical) በሆነ መንገድ ነው። እናም የእኛ ህዝብ በመንስኤና ውጤት ተሰናስሎ የሚቀርብን ‹‹አመክኖዮአዊ እውነት›› ለመረዳትም ሆነ ለመቀበል ይቸግረዋል፡፡ ለዚህም ነው ገብረ ህይወት ‹‹የእኛ ህዝብ ‹‹አንድ ንጉስ ይሄንንና ያንን አድርጎ በራሱ ጥረትና ብልሃት ነገሰ›› ከሚሏቸው ይልቅ፣ ‹‹በእንዲህ ያለ መለኮታዊ እርዳታ ነገሰ›› ተብሎ ቢነገራቸው  ይመርጣሉ›› ያለው፡፡
ይህ የተአምራዊነት አስተሳሰብ ማንነታችን ላይ በጥልቀት ስለታተመ ‹‹ማህበራዊ ውል›› (Social Contract) ላይ የተመሰረተው ዘመናዊው የሥነ መንግስት እሳቤ በአሁን ወቅት በዓለም ላይ ገዥ ሐሳብ ሆኖ በወጣበት ወቅት ላይ እንኳ አስተሳሰቡ ሊላቀቀን አልቻለም፡፡ ይቺ የሰሞኗ ‹‹ዶ/ር አብይ ተዓምራዊ ክስተት ነው›› የምትለዋ አነጋገርም የድሮው የተአምራዊነት አስተሳሰብ ቅሪቱ አሁንም ድረስ እንዳልተገፈፈልን ያሳያል።
ይሄ ፖለቲካችንን የወረረው የ‹‹ተአምራዊነት›› ተረክ ሦስት ችግሮችን ፈጥሮብናል፡፡ የመጀመሪያው፣ የሥነ መንግስት እሳቤያችን አሁንም ድረስ ‹‹ዘመኑን የዋጀ›› እንዳይሆን አድርጎታል፡፡ ምዕራባውያን የነፃነትና የዲሞክራሲውን ጎዳና የጀመሩት የሥነ መንግስት እሳቤያቸውን ከመለኮታዊነት ወደ ማህበራዊ ውልነት (Social Contract) ከቀየሩ በኋላ ነው፡፡ እኛ ግን አሁንም ‹‹ተአምራዊ›› ተረኮችን በማምጣት መሪን የሚሾመውም ሆነ የሚሽረው መለኮታዊ ኃይል ነው የሚል እሳቤ ውስጥ እንዳክራለን፡፡
ሁለተኛ፣ እንደዚህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ለሰው ልጅ ጥረት፣ ብልሃትና ችሎታ ዕውቅና የማይሰጥና ውለታ ቢስ መሆኑ ነው። እንደዚህ ዓይነቱን ውለታ ቢስነት ገብረ ህይወት ባይከዳኝ፤ ‹‹በዓለም ላይ እንደ ኢትዮጵያ ነገስታት የመላዕክትና የሰይጣን እርዳታ የሚፈልግ መሪ ተሰምቶ አያውቅም›› በማለት ይሳለቅበታል፡፡ እኛም ጠ/ሚ አብይን ‹‹ተአምራዊ›› ክስተት አድርገን ባቀረብናቸው ቁጥር የህዝባችንን መስዋዕትነትና የአመራሮቹን ብልሃት እየዘነጋነው ነው፡፡ ለሰዎቹ ዕውቅና ስንሰጥ ለበለጠ ሥራ እንነሳሳለን፡፡
ሦስተኛው ችግር ደግሞ፣ የሰው ልጅ በረጅሙ አቅዶ እንዳይሰራና ሁልጊዜ ተአምራት ጠባቂ ሆኖ እንዲቀር ያደርገዋል። የዚህ ውጤቱ ደግሞ ገብረ ህይወት እንደሚለው፤ ‹‹ንጉስንና መንግስትን አንድ አድርጎ ማየት›› ነው፡፡ ገብረ ህይወት እንደዚህ ይላል፤ ‹‹ያልተማረ ህዝብ ንጉስና መንግስት አንድ ይመስለዋል፡፡ ከዚህም የተነሳ ንጉሳቸው ሲሞት ልክ ጌታቸው እንደሞተባቸው ባሮች እርስበርስ ለስልጣን መጣላት ይጀምራሉ፡፡ አእምሮ ባላቸው ሕዝቦች ዘንድ ግን መንግስት ማለት ማህበር ማለት ነው፤ ንጉሱም በጊዜያዊነት የሚሾም የማህበራቸው አለቃ ነው፡፡››
ኢትዮጵያውያን ሁልጊዜ የመንግስት ሽግግር ላይ የምንታመሰው ‹‹ተአምራዊው›› የሥነ መንግስት እሳቤያችን መንግስታዊ ስርዓትን ከመገንባት ይልቅ የሀገርን ህልውና ከ‹‹ተአምራዊው›› ንጉስ ህልውና ጋር ስለሚያስተሳስርብን ነው፡፡ ስለዚህ የ‹‹ተአምራዊነት›› ትረካችንን ትተን ማህበሩን እናጠናክር፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊው፤ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር እና ‹‹የኢትዮጵያ ፍልስፍና›› መፅሐፍ ደራሲ ሲሆኑ በኢ-ሜይል አድራሻቸው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 5509 times