Saturday, 28 July 2018 15:53

የአሜሪካ ዲያስፖራነትና የግል ምልከታዬ

Written by  ከዳግላስ ጴጥሮስ
Rate this item
(0 votes)

የኢትዮጵያ የወቅቱ አየር በነውጥና በለውጥ ደመና እየከበደ እንደሚሄድ የዕለት ተዕለቱ የኑሯችን ሜትሮሎጂ በትንበያ ሳይሆን በተግባር እያረጋገጠልን ነው፡፡ ከደመናው ሰማይ ሥር ብሩህ ተስፋ የሚፈነጥቁ ጨረሮች ሲያሞቁን ሃሌሉያ የምንለውን ያህል በአንፃሩም በሌላው የደመና ክፍል የከበደው አየር ምን አይነት ውሽንፍር ሊያዘንብ ይችል ይሆን እያልን በአትኩሮት አንጋጠን እየተመለከትን በኤሎሄ የለሆሳስ ቋንቋ ማማተባችንና እርስ በርሳችን ማጉተምተማችን አልቀረም፡፡
የሀገራችን የወቅቱ የፖለቲካ ነፋስ የሚያሳየው የነውጥና የለውጥ መንታ ባህርይም በሃሌሉያና በኤሎሄ ተቃርኗዊ ስሜት ውስጥ እያንቦጫረቀን ነው የምንለውም ስለዚሁ ነው፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) የለውጥ ባቡር ከፊሉን እያራገፈ፣ ከፊሉን እያንጠባጠበ፣ ከፊሉን ለምሽግ እየዳረገ፣ ከፊሉን እያስደነበረ፣ ከፊሉን ግራ እያጋባ፣ብዙኃኑን እያስፈነጠዘና እያፍነከነከ በሃዲዱ ላይ በፍጥነት መገስገሱን ቀጥሏል፡፡
የለውጡ ባቡር የፍጥነት በረራ ከሀገር ልጆችም ግርምት አልፎ በመላው ዓለም የሚገኙ ባዕዳን ዜጎችን፣ የመንግሥታት መሪዎችንና የሚዲያ ተቋማትን ሳይቀር  በአድናቆት እጃቸውን በአፋቸው ላይ ጭነው “ደግሞ ከሰዓታት በኋላ በኢትዮጵያ ምድር ምን ሊፈጠር ይችል ይሆን?” እያሉ የለውጡን ፍጥነት ልብ ተቀልብ ሆነው እየተከታተሉ ይገኛሉ፡፡ (በቀናት ሳይሆን በሰዓታት ልዩነት ማለቴን ልብ ይሏል፡፡)
በዛሬው ዕለት ሰኔ ሃያ ስድስት ቀንም ጠቅላይ ሚኒስትራችን በሽምጥ ግልቢያ ውቂያኖሶችን አቆራርጠው ምድረ አሜሪካ በመግባት በሦስት ዓሠርት ሺህዎች ለሚገመቱ የሀገሬ ልጆች  በታላቋ አሜሪካ የመንግሥት መቀመጫ በዋሽንግቶን ዲሲ እጅ እንደሚነሱ እየተጠበቀ ነው፡፡ የእርሳቸውን የፍጥነት ሩጫ እየተከተለ የሚከንፈው የለውጥ ደመና በተቀሩት ሁለት “የኢትዮጵያዊያን” ከተሞች፤ በሎስ አንጀለስ እና በግሌ በምወዳትና ጥቂት አመታት በኖርኩባት የሴንት ፖል መንትያ በሆነችው በሚኒያፖሊስ መዲና፤ በውይይቱም መካከል ምን ዓይነት ውሽንፍር እንደሚዘንብ ለማወቅ ዓይናችንንም ጆሮአችንንም ቀስረን እየተከታተልን ነው፡፡
በግፍ ለተሰደዱ፣ እንጀራ ፍለጋ ወጥተው ለቀሩ፣ ሎተሪ በከፈተላቸው በር ለነጎዱ፣ በፅንስ ውስጥ እንዳሉ ተሰደው በአሜሪካ ሆስፒታሎች ተወለደው የዜግነት ክብር ላገኙ፣ ለትምህርት ፍለጋ ወጥተው በዚያው የውሃ ሽታ ሆነው ለቀሩ፣ መንግሥታዊ ሹመቴ ይቅርብኝ በማለት ከድተው ለኮበለሉ፣ የፖለቲካ አጀንዳዬ ሰሚ አጣ በማለት ላኮረፉ (አቤት የዓይነቱ ብዛት) ለእነዚህ ሁሉ ዝንጉርጉር ተሰዳጅ ወገኖቼ አሜሪካ የተስፋ ምድር፣ የማረፊያ ጎጆ ሆናለችና አንቺ ታላቅ ምድር ሆይ ባለሽበት ምስጋናዬን ተቀበይ፡፡
ከላይ በዘረዘርኳቸው ምክንያቶችና ባልጠቃቀስኳቸው በርካታ ሰበቦች መንስዔነት ተሰደውና ስደት መርጠው በአሜሪካ ምድር ለሰፈሩት የሀገሬ ልጆች እስከ ትናንትናዋ ጀንበር ድረስ ፖለቲካችንና መሪዎቻችን በጅምላ የፈረጇቸው በመልካም ምሳሌነት አልነበረም፡፡ ዲያስፖራ ዜጎቹን በአብዛኛው በጥቅል ምደባ “ወንጀለኞች” እያለ ቀይ መስመር አስምሮ ግማሽ ክፍለ ዘመን ያስቆጠረ ፖለቲካ በሌሎች ሀገሮች ስለመከሰቱ እርግጠኛ አይደለሁም። የእኔዋ ሀገር ግን ከዘመነ ደርግ እስከ ዘመነ ኢህአዴግ በራሷ ልጆች ላይ ይህንን የከፋ የአግላይነት በደል በዲያስፖራ ማህበረሰቡ ላይ እያደረሰችና በአሳደደቻቸው ልጆቿም እየባነነች ስለመኖሯ ምስክር አያሻውም፡፡ መሪዎቻችንና ሹማምንቶቻችን በአሜሪካ ከተሞች ብቅ ባሉ ቁጥር የሚወርደባቸው ስድብና ውርደት፣ የሚወረወርባቸው ቲማቲምና ዕንቁላል በሀገራችን የወቅቱ የሬሽን ዋጋ ተመን ይውጣለት ቢባል ምን ያህል ሰው ሊቀልብ እንደሚችል ኢኮኖሚስቶቹ ይረዱን ይመስለኛል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድወደ አሜሪካ ያቀኑት ይህንን መሰሉን ዘመን ያስቆጠረ የጠብ ግድግዳ አፍረሰውና የተሰባበረውን የሀገርና የልጆቿን የግንኙነት ድልድይ በመጠገን “ተዘግቶባችሁ የኖረው የእናታችሁ በር ወለል ተደርጎ ተከፍቶላችኋልና ወደ ምድራችሁ ኑ!” የሚለውን ጥሪ በመሪ አንደበት ለማድረስ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመንግሥት መሪ፣ “አስታራቂ ካህን”፣ አሸማጋይ አዛውንት፣ ቀስቃሽ ምሁርን ወዘተ. ባህርዮችን በመላበስ የማስታረቅ፣ የፍቅርና የሰላም አዋጅ አብሳሪ ሆነው መጨከናቸው የሚገርምም የሚደንቅም ክስተት ነው፡፡ ልባቸውን አስፍተውና ራሳቸውን ዝቅ አድርገው በታሪካችን  ውስጥ ያልተሞከረውንና ያልታሰበውን ድርጊት ለመፈፀም ሲወስኑም ምን ያህል ተግዳሮቶችን ተቋቁመው እንደሆን ለመገመት አይከብድም፡፡ ለጠቅላይ ሚኒስትራችን አርአያነት ያለው ተግባር ኮፍያዬን አውልቄና ዝቅ ብዬ አክብሮቴን እገልፃለሁ፡፡
በሌላው አንፃር ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአሜሪካ ምድር በሚኖራቸው ቆይታ ከዲያስፖራ ማኅበረሰቡ ይጠየቃሉ ወይንም ይሞገቱባቸዋል ብዬ የምገምታቸውን የጥያቄዎች ናዳ ሳስብ “ፅናቱን ይስጣቸው” ከማለት ውጭ የምላቸው የለኝም፡፡ እንደምገምተው ከሆነ ግን በግማሽ ክፍለ ዘመን ውስጥ በዲያስፖራው ማኅበረሰብ ውስጥ ታምቆ የኖረው የብሶት ወላፈን ልክ እንደ አፋሩ የኤርታኢሌ እሳተ ጎመራ ምንጭ በተለያየ ቀለማት ውህደት እየተፍለቀለቀና እየተንተከተከ የሚለበልብ ይመስለኛል፡፡ ደግሜ እላለሁ ፅናቱን ይስጣቸው፡፡
የአውሮፓ ተረተኞች “ሮም በአንድ ቀን አልተገነባችም” እንዲሉ የሀገሬ ልጆችም የሚመኟት ዓይነት ኢትዮጵያ በአንድ ጀንበር ትገነባለች ብለው እንደማይገምቱ ይጠፋቸዋል ብዬ አላምንም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚጠየቋቸው ጥያቄዎችና “ቃል ግቡልን” ተብለው የሚሞገቱባቸው ሁለንተናዊ ሀገራዊ ጉዳዮቻችን በሙሉ በአንድ ጀንበር ተግባራዊ ይሁኑ ብሎ መበየን ያዳግታል፡፡ “በአጭር ጊዜ ይህንና ያንን የማያደርጉ ከሆነ ግን እንዲህና እንዲህ ከማድረግ አንቆጠብም” በማለትም የውጥር ይዘው እንደማይሰንጓቸውም እምነት አለኝ፡፡
ዘመናት ያስቆጠረውና ከንብርብር አለትጋር የሚመሳሰለው የሀገራችን ዘርፈ ብዙ ችግር በአንድ መድረክ ተስፋ ሰጭ የንግግር ድማሚት ይደረመሳል ብዬ አላምንም፡፡ ሥር ሰዶ በግፍ የታጀለውንና በጥቂት ግለሰቦች የካቴና ሰንሰለት ተቀፍድዶ የኖረውን የፖለቲካ፣ የዲሞክራሲና የኢኮኖሚ ሀገራዊ ጣጣ ከሥሩ ነቃቅሎ ምህዳሩን ለማፅዳት ጊዜ መጠየቁ አይቀርም፡፡ ከዛሬ አርባ ዓመታት በፊት አዲሱ መጤ ደርግ ሲያመሳቅላቸው “ፋታ! ፋታ! ፋታ!” በማለት የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጠቅላይ ሚኒስትር  ሕዝቡን እንደተማፀኑት የዛሬው ጠቅላይ ሚኒስትራችንም ከዲያስፖራው ማኅበረሰብ ይገጥማቸዋል ተብሎ ለሚገመተው “የሱሪ ባንገት” ተግዳሮት፤ መሰል ተማፅኖ ቢያሰሙ “ታሪክ ራሱን ደገም” ሊያሰኝ አይገባም፡፡
አንዳንድ የዲያስፖራው ማኅበረሰብ አባላት ወገኖቼም ቢሆኑ የጠቅላይ ሚኒስተሩን መልካም አርዓያነት ሊከተሉ እንደሚገባቸው ሳላነሳ ማለፉን አልወደድኩትም፡፡ መቼም በመሃከላቸው ኖሬ እውነታውን በሚገባ ተገንዝቤ ነበርና በትሁት መንፈስ ማስታወሱ አግባብ ይሆናል፡፡ ጥቂት የማይባሉ ወገኖቻችን በንጹሐን ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ላይ አእምሮአቸውን ያጠለሹበትን የጥላቻ ጥቀርሻ ለማስወገድ ይደር ማለት ያለባቸው አይመስለኝም፡፡ ይህንን ጉዳይ ለማንሳት በቂና ከበቂ በላይ ምክንያት ስላለኝ ነው፡፡
የሀገራችን የለውጥ ነፋስ መንፈስ ከመጀመሩ እስከ ጥቂት ወራት ድረስ ለቤተሰብ ጥየቃም ሆነ ለጉበኝትና ለዕረፍት ወደ ሀገር ቤት ይመጡ የነበሩት ወገኖቻችን “ወደ አሜሪካ ስመለስ ምን ስም ያወጡልኝ ይሆን?” በሚል ስጋት በምን ዓይነት መሳቀቅ ሀገራቸው ገብተው እንደሚወጡ ብዙዎቻችን ሳንረዳ አንቀርም፡፡ ስለ ሀገራቸውና ስለ ሕዝባቸው በጎነት አንዳችም መልካም ነገር እንዳይመሰክሩ ማዕቀብና መገለል ይደርስባቸው እንደነበር ብዙ ሰምተናል፡፡
እንዲያውም ሀገራችን እንዲህና እንዲያ ደረጃ ላይ ደርሳለች፣ በማለት በዓይናቸው ያዩትንና በጆሯቸው የሰሙትን የእውነት ምስክርነት በቅንነት የሰጡ ሰዎች በአንዳንድ የራሳቸው ወገኖች ከማኅበረሰቡ እንዲገለሉ መደረጋቸው፣ በንግድ ስራቸው እንዳይቀጥሉ በሴራ መወገዳቸው፣ መሳቂያና መሳለቂያ እንዲሆኑ የመዳረጋቸውን ዜና ደጋግምን ሳንሰማ አልቀረንም፡፡ በርካቶችም ለከፋ የሥነ ልቦና ቀውስ ተዳርገው ችግር እንደደረሰባቸው ተወርቶላቸዋል፡፡ ይህንን ያልተገባ የማግለል ተፅእኖና ተግባር ይከውኑ የነበሩ ወገኖችም ወደ አእምሮአቸው ተመልሰው ሊፀፀቱና በንሰሃ ሊታደሱ ይገባል፡፡
የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ይህንን መሰል ጉዳይ በድፍረት የሚጽፈው ዛሬ ቀኑ ብራ ስለሆነ ብቻ ሳይሆን በዚያው በአሜሪካ ምድር በነበረባቸው ዓመታት ያስተዋላቸውን መሰል ጉዳዮች  በቋንቋችን ይታተም በነበረ ጋዜጣ ላይ ሳያሰልስ ይጽፍ እንደነበረ የሚያስታውሱ አይጠፉም። አልፎም ተርፎ ትምህርታቸውን አጠናቀው ወይንም የተላኩበትን ተልዕኮ ፈፅመው “የሀገሬን አደራ አከብራለሁ!” በማለት ወደ ሀገር ቤት የሚመለሱና ከምንም ውስጥ የሌሉ ንፁሃን ዜጎች ይደርስባቸው የነበረው የማጥላላትና የጥላቻ ዘመቻም አይዘነጋም፡፡
በአንፃሩም በስመ ልማትምይሁን ወይንም በሌላ የግል ጉዳይ ወደ ሀገር ቤት እየተመላለሱ የዲያስፖራ መብቴ ከሁሉም በፊት ቅድሚያ ተሰጥቶ ሊከበርልኝ ይገባል፣ የመጀመሪያ የጥቅም ተጋሪ ካልሆንኩኝ ሞቼ እገኛለሁ በማለት ራሳቸውን እንደ በኩር ኢትዮጵያዊ በመቁጠር “ሆቸ ጉድ!” በማሰኘትም በይሉኝታ ቢስነት ያሸማቀቁን ጥቂት የማይባሉ የዲያስፖራ አባላትንም አስተውለን በግርምትና በትዝብት አልፈናል፡፡
ለልማት የወሰዱትን መሬት ወይንም ቤት ለመሥራት የተመሩትን ርስት በጠፍ ጨረቃ ወደ ገንዘብ ለውጠው እብስ ያሉ ጥቂት የዲያስፖራ ወገኖች ጉዳይም ሲያስፈግገንና ሲያስገርመን መባጀታችን አይዘነጋም፡፡
በአንፃሩም ከጀርባቸው በመሠረተ ቢስ የሀሜት ልምጭ እየተገረፉም ቢሆን እንዳልሰሙ መስለው በስማቸውና በክብራቸው በመወራረድ በዋሽንግቶን አደባባዮች ላይ መሰደባቸው ሳያንሳቸውና በሀገር ውስጥ የቢሮክራሲው ጥልፍልፍ አቀበትና ሙስና ሰቅዞ ቢይዛቸውም ሀብታቸውንና ዕውቀታቸውን በሀገራቸው ላይ ለማፍሰስ የጨከኑ የዲያስፖራ ጀግኖች ቁጥራቸው እልፍ ጊዜ እልፍ ነውና ለእነርሱም አክብሮት መስጠት ግድ ይሏል፡፡
መቼም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በመድረክ ላይ የሚያሰሙት ንግግር እያንዳንዱ ዐረፍተ ነገር በጥቅስነት የሚመዘገብ እንደሆነ መስካሪው ብዙ ነው፡፡ በተለይም ኢትዮጵያዊነትን ከክቡር አፈር ጋር ያመሳሰሉበት፣ ኢትዮጵያዊ ወገን ከሀገር ቢርቅም ሀገሩን በልቡ እንደተሸከመ መኖሩን ለመግለፅ የተጠቀሙባቸው አባባሎች ልብ ጠለቅ ናቸው። በአሜሪካ ከሚገኘው የዲያስፖራ ማኅበረሰብ ጋር ሲገናኙ ከሚናገሯቸው ንግግሮች ውስጥም ምን ያህል ለጥቅስ የሚበቁ አባባሎች ሊመዘዙ እንደሚችሉ ነግ ተነገወዲያሲደርስ የምንሰማው ይሆናል፡፡
የሀገራችን ጉዳይ በጠቅላይ ሚኒስትራችን የንግግር ውበትና ማራኪ አንደበት ብቻ ተደንቆ የሚታለፍ ሊሆን አይገባውም፡፡ እየተጋፈጥነው ያለነው የለውጥና የነውጥ አብዮት በተባበረ አቅምና ጥበብ እየተመራ ወደምንመኘው ግብ እንዲደርስ ካልተረዳዳን በስተቀር አደጋውን ለመቀነስ ዋጋው ይከብድ ይመስለኛል፡፡
በሀገር ውስጥ የሚገኘው ዜጋና በመላው ዓለም የተበተነው ወገን ከምን ጊዜውም በተሻለ መልኩ በመተባበር የለውጡ ባቡር ሀዲዱን እንዳይስት ሊጠብቀው ይገባል፡፡ የለውጡ ሂደት ከተሰነካከለ በሀገር ላይ የሚያመጣው የህልውና አደጋ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ለትውልድ ጥቅምም ሆነ ለታሪክ ገፆች አንዳችም የሚፈይደው ቁምነገር አይኖርም፡፡
ፖለቲካችን ለራሱም ችግር ላይ ወድቆ ሕዝቡንም አረንቋ ወስጥ ዘፍቆት የኖረው “በመቃብሬ ላይ” የሚሉትን መሃላ ማለዘብ ተስኖት ነው፡፡ “ተቃዋሚ ተብዬ የፖለቲካ ድርጅቶችም” ቢሆኑ ለመደማመጥና ለውጥ ለማምጣት ተስኗቸው ልምሻ እንዳጠቃው ህፃን በመፍገምግም ላይ ነበሩ፡፡
የሀገሬ ምሁራንም ቢሆኑ “ውሻን ምን አገባው ከእርሻ” በሚል ፈሊጥ በራቸውን ከርችመው “አንሰማም፣ አናይም” በማለት በተዝረከረከው ብዙ ሀገራዊ ጉዳዮቻችን ዙሪያ መፍትሔ ከመጠቆም አኳያ አካዳሚያዊ ሥልጣናቸውንና የሞራል ልዕልናቸውን በተገቢው ሰዓትና ጊዜ ተግባራዊ ለማድረግ መቸገራቸውን ደጋግመን ሰልቀነዋል፡፡ የሃይማኖት አበውና ቤተሰቦችም ቢሆኑ የየግላቸውን ቅጥር አጠነካክረው ቸል በማለታቸው ፍትህ በአደባባዮች ሲያለቅስ፣ እውነት ከመንበሯ ስትገፋ፣ የጥቂቶች ስግብግብነት የሀገር ባህል ሲሆን እየተመለከቱ መንፈሳዊ ስልጣናቸውን ከመጠቀም ታቅበው ኖረዋል።
ጊዜው ሲደርስ ግን የሕዝብ ቁጣ ገንፍሎ የብረት አጥሩ ተነቅሎና ጥቁሩ መጋረጃ ተቀዶ አዲስ የተስፋ ወጋጋን መፈንጠቅ ጀማመረ፡፡ ይህ የተስፋ ብርሃን እየፈካ እንዲሄድ ዛሬ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ውሎ ማድረግ የሚጀምረው የአሜሪካው ዲያስፖራ ማኅበረሰብ ሰከን ብሎና ትረፋሹን ዋጥ አድርጎ ውይይቱን በሰላምና በስኬት ሊያጠናቅቅ ይገባል፡፡ ሀገር ቤት የሚስተዋሉት ችግሮች በሙሉ እንዲወገዱ በአንድ የመድረክ ቆይታ ዋስትናው ይረጋገጥልን ብሎ ሙግት መግጠም ብልህነት አይመስለንም፡፡ እንደማይሆንም እርግጠኛ ነኝ፡፡
ዲያስፖራው  ጥያቄ ማንሳትና ውጤት መጠበቅ ያለበት ሀገር ውስጥ ላሉ ጉዳዮቻችን ብቻም ሳይሆን በዚያው በራሱ መካከል የተገነባውን የልዩነት ግንብ አፍርሶ የእርስ በእርስ መሸጋገሪያ ድልድዩን ሊገነባ ይገባል፡፡ የጎሪጥ የሚተያዩ የዲያስፖራው ማኅበረሰብ አባላትና ቡድኖችም በፍቅር፣ በይቅርታና በምህረት በጠቅላይ ሚኒስትራቸው ፊት ሊተቃቀፉ ይገባል ባይ ነኝ፡፡ “ከመምህሩ ደቀ መዝሙሩ አንዲሉ፡፡”
ቸር እንሰንብት! 

Read 1399 times