Saturday, 28 July 2018 15:41

ካዎ ጦና (ወይም አባ ጅፋር) ሚኒልክን ቢያሸንፉ እና ሌሎች ብሄር ተኮር ሃሳቦች ለኢትዮጵያ

Written by  ተመስገን ማርቆስ (ዶ/ር)
Rate this item
(4 votes)

ቅድመ አያቶቼ የሚኒልክን ጦር ለስንት ጊዜ ገትረው ይዘው ሲያበቁ፣ በመጨረሻ ሚኒልክ ጠንከር ያለ ዘመቻ አካሂደው የወላይታን ጦር አሸነፉ፡፡ ከዛ መልስ የሆነው ሁላችንም ከታሪክ የምናውቀው ነው። ግን ታሪክ ተገልብጦ ካዎ ጦና አሸንፈው ቢሆንስ ወላይታዎች ምን እናደርግ ነበር?
የመጀመሪያ እርምጃ የሚሆነው እያንዳንድሽ ታላቁን የወላይታ ግዛት መቀላቀልሽን ለማሳየት የዜግነት ጭንቅላትሽ ላይ ከቀኝና ከግራ ምልክት (ባቄ) እናደርግልሽ ነበር፤ ባዮሜትሪክ ፓስፖርት! ከዛ ባህሉን፣ ቋንቋውን ትለምጃታለሽ፡፡ ሲቆይም አመጋገብሽን ትቀይሪያለሽ፡፡ እንጀራ፣ ዶሮ ወጥ ምናምን ቤት ውስጥ ነው የሚበላው፡፡ ሆቴል ተገብቶ የሚታዘዘው ቦዬ፣ ቦይና፣ በአዋዜ ቦታ ዳታ ወዘተ ይሆናል፡፡ ሲቆይ ደግሞ የልጆችሽን ስም አወጣጥ ታስተካክያለሽ፡፡ አይ ብለሽ ሰጥአርጋቸው፣ ለጥይበሉ፣ ትርሃስ ምናምን አይነት ስም ያወጣሽ፤ ትምህርት ቤት እነ በርገና በልጅሽ ስም በሳቅ ፍርፍር አዘው ይበላሉ፡፡ ተሳስቼ ነው ፍርፍር የለም፤ ቆጭቆጮ ነው በሳቅ አዘው የሚበሉት!
ይሄ እንደማይሆን፣ ይባስ ብሎም የወላይታ ገዢ በሌላው ህዝብ ላይ በደል እንደማያደርስ ምን ማረጋገጫ አለን? ምንም የለንም፡፡ ሊያደርስም ይችላል፤ ላያደርስም ይችላል፡፡ ግን አንድ ህዝብ ከአብራኩ የወጡ በሌላው ላይ ጉልበት ስላልነበራቸው፣ ያ ህዝብ ጥሩ ይሆን ነበር ማለት አይቻልም፡፡ ከታሪክ ካየን ሁሉም ብሄርና ሃገር በውስጡ ለክፋትም ለደግነትም የሚሆን ሰው አለው፡፡ እንደ ሚኒልክ ልማትም የጦና አገዛዝ ወይ የአባ ጅፋር አገዛዝ ተመሳሳይ ወይም ሌላ አይነት ልማት ያመጣ ይሆናል፡፡
ዴሞክራሲያዊ ያልሆነ ገዥ መደብ ለስልጣኑ መሰረት የሚያደርገው ዘር ወይ ሃይማኖት ወይ ሌላ የህዝብ ክፍል ይይዛል። ያ ብሄር ወይ ሀይማኖት ግን የገዥው አካል ሳይሆን ሲደላ መነገጃ ሲከፋ መደበቂያ ነው። በኢትዮጵያ ታሪክ ከአማራ ከዛም ከትግራይ ብሄሮች የወጡ ሰዎች ስልጣን ተቆጣጥረው ስለነበር፣ በዛ ምክንያት የጠፋውን የነዛ ግለሰቦች ጥፋት ሳይሆን የአማራ ጥፋት ወይም የትግሬ ጥፋት አድርገን መቁጠር እስክንተው ድረስ የትም አንደርስም፤ ልማቱንም እንደዛው፡፡ ልጆቻችንንም ስናስተምር፣ ስለ እገሌ ልማት ወይም ጥፋት በግለሰብ ወይም በቡድን እንጂ ስለ አማራ ወይ ኦሮሞ ወይ ትግሬ ወይ ወላይታ ክፋት ወይ ደግነት ካስተማርን መርዝ እየጋትናቸው ነው።
የየትኛውም ብሄረሰብ ሰዎች ስልጣን ቢቆጣጠሩ ጥሩ ይሆናሉ ብሎ ማሰብም ዝርክርክ አስተሳሰብ ይመስለኛል፡፡ እስቲ የየራሳችንን ብሄረሰብ እንይ፡፡ በጎሳ ክፍፍል አንዱ አንዱን እዛው ብሄረሰብ ውስጥ አይንቅም? እኔ ብሄረሰብ ውስጥ ልክ እንደ ህንድ untouchables በአሳዛኝ ሁኔታ ሌላው ጎሳ የሚንቃቸው ጎሳዎች አሉ፡፡ የየራሳችሁ ውስጥ የለም ካላችሁ አሪፍ ፎጋሪ ናችሁ፡፡ ሂዱና አያታችሁን “ከብሄረሰቤ ውስጥ የፈለግኩትን ማግባት እችላለሁ?” በሉ፡፡ “ከዚህኛው ብቻ እንዳታገባ እንጂ ሌላው ችግር የለም” የሚባልለት ጎሳ አለ በየብሄሩ፡፡ ያ ነው እንግዲህ ስልጣን ቢኖር የመበደል፣ የማሸማቀቅ እምቅ ሃይል (potential) ማለት፡፡
የተጎዳ ሁሉ ነገ ሰላማዊ ይሆናል ቢባል፣ እንደ አይሁዶች በዚህ አለም የተጎዳ አለ? ስንት ሚልየን በመርዝ ጋዝ ተጨፍጭፈው እንደምንም የተረፉት ከሁለተኛው አለም ጦርነት መልስ ዘመናዊዋን እስራኤል መሰረቱ፡፡ የእስራኤል መንግስት ዛሬ ላይ በፍልስጤማዊያን ላይ ስንት በደል እያደረሰ አይደል? ለመጀመሪያው ጥፋት የናዚ ፓርቲን እንጂ ጀርመናዊያንን በሙሉ በተለይም የአሁኑን ትውልድ ተጠያቂ እንደማናደርገው ለእስራኤል መንግስት ጥፋት ደግሞ አክራሪ እስራኤላዊያንን እንጂ ሁሉንም እንደ ህዝብ አንጠይቅም፡፡ ለፍልስጤማዊያን ኑሮ መርጃ ገንዘብ የምትሰጥ ስዊዘርላንዳዊት ይሁዲ አውቃለሁ እኔ እንኩዋን።
ሃዋሳ በወላይታ ብሄር ተወላጆች ላይ የደረሰውን አይነት ጥቃት የወላይታ ብሄር ተወላጆች ሶዶ ላይ መቼም አያደርሱም ብለን እርግጠኛ መሆን እንችላለን? አንችልም! እንደዛ አይነት ጥፋት ለማድረስ የሚያስፈልገው የዚህ ወይም የዚያን ብሄር ደም ወርሶ መወለድ ሳይሆን በኑሮዉ ተስፋ የቆረጠ ወጣትና ያንን ወጣት ለጥፋት ለመቀስቀስ ዝግጁ የሆነ ስግብግብ ፖለቲከኛ ነው፡፡ በትምህርቱ ያልገፋና፣ በኢኮኖሚ የተደቆሰ በዛ ያለ ወጣት ሶዶ ላይ አስተባብሮ “የችግርህ ሁሉ ምንጭ እዚህ ከተማ የሚነግዱት ጉራጌዎች ናቸው” ቢል ጥፋት እንደማይከሰት ምን ያህል እርግጠኛ ነን?
ቤንሻጉል ጉሙዝ ክልልም የሆነው ተመሳሳይ ነው። ወጣቱ በስራ ተጠምዶ ቢሆን ለአፍራሽ ፖለቲከኞች ስብከት ጊዜም አይኖረውም፡፡ ወጣቱ እየነገደ ቢሆን ኖሮ፣ እዛ የሰፈረውን አማራ ማጥቃት ደንበኛን  ማጥፋት እንደሆነ አውቆ አይነካም ነበር። ጀርመንም የሆነው ያው ነው፡፡ ከአንደኛው አለም ጦርነት መልስ በደረሰባት ጫና ጀርመን በኢኮኖሚ ላሽቃ እያለ “ለችግራችሁ ሁሉ ምክንያት እነዚህ ዘሮች ናቸው” የሚል ሂትለር መጣላቸውና የሆነው ሁሉ ሆነ፡፡
ትኩረታችን መሆን ያለበት በየአካባቢው ትናንሽ የሂትለር አይነት ፖለቲከኞች፣ ኢኮኖሚያዊ ተስፋው የሟጠጠ ወጣት አግኝተው፣ በእሳት ላይ ነዳጅ እንዳይጨምሩ፣ የሃገራችንን ኢኮኖሚ ከፍትሃዊነት ጋር ማሳደግና ወጣቱ አመለካከቱን እንዲያሰፋ ማስተማር ነው፡፡ አለበለዚያ ስልጣን ላይ ስላሉ ወይም ኢ-ሰብአዊ ጥቃት ያደረሱ ግለሰቦች ብሄር ላይ ካተኮርን፣ የበቀል ተራ ነው የምንይዘው፡፡ ተወያይተን የመስማማት እድል ነው የምንዘጋው፡፡ ችግሩ ከብሄር ከሆነ የደም ዝውውር ካላደረግክለት አይቀየርምና ምን አደከመህ ስትወያይ? ለዛም ነው የዘር ፖለቲካ ወደ መጠፋፋት የሚመራው፡፡
መለስ ዜናዊን እንደ መለስ ዜናዊ እንይ፡፡ አይደለም ትግሬን ሊወክል አብረውት  ጫካ የገቡትን ሁሉ አይወክልም፡፡ እነ አረጋዊ በርሄ ሳይስማሙ ቀርተው ተለያይተው፣ ይኸው ዛሬ እንደመር እያሉ አይደል? ሃይለማሪያም ደሳለኝ፣ ሃይለማሪያም ደሳለኝ ነው። አይደለም ሁሉንም ወላይታ ቅርብ ቤተሰብ ሆኜ “ሳድግ እንደሱ ሆናለሁ” ብዬ ያደግኩት ሳድግ “ከቅንጅት ላይ ድምጽ ሰርቃችኋል” ብዬው የምከራከር ነው የሆንኩትና፣ እኔን እንኳን አይወክልም፡፡ አብይ አህመድም ቢያለማም የሚመሰገነው፣ ቢያጠፋም የሚጠየቀው ራሱ መሆን አለበት እንጂ የኦሮሞ ህዝብ አይደለም፡፡ አይደለም አንድ ሰው ወይም ቡድን፣ ብሄረሰብ ሊወክል፣ አንድ ሰው ራሱ ይቀየራል፡፡ ስንቶቻችን ነን ስለ ጃዋር መሃመድ ያለን አስተሳሰብ የዛሬውና የዛሬ አምስት አመቱ አንድ የሆነ? የዛሬ አምስት አመት፣ እኔ ጃዋርን ስልጣን ቢይዝ፣ ይችን ሃገር ያቃጥላል ብዬ ሳስበው የሚሰቀጥጠኝ ነበር፡፡ ዛሬ ደግሞ አካሄዱ ስለተቀየረ “እስቲ ጃዋር ምን አለ” ብዬ ገጹ ላይ ሄጄ አንብቤ በሚሰጠው በሳልና የተረጋጋ አስተያየት ደስ የሚለኝ የምማርበት ሆኗል፡፡
ከአዙሪት ለመውጣት ማንኛውንም ህዝብ እንደ ህዝብ ጥሩ ወይም መጥፎ አድርገን በጅምላ መፈረጅ ወይም ማንቆለጳጰስ እናቁም፡፡ የምንፈርድበትም ብሄረሰብ ጥቂቶች በስሙ አጥፍተው ነው፣ የምንወደውም ብሄረሰብ ምናልባት ከአብራኩ የወጡ ለጥፋት እድል ካገኙ የሚሆነውን አናውቅም። ሰውን እናድንቅ፤ ሰውን እንውቀስ፤ እንደ ሰው መብቱን እናክብር፡፡
አንዱ ፌስቡከር (Zewdalem Tadesse ይመስለኛል) እንዳለው፤ ሰው መሆን ካቃተን ቢያንስ ከኢትዮጵያዊነት አንጥበብ፡፡

Read 1543 times