Saturday, 28 July 2018 15:50

የኢሕአፓ ነበልባል ልቦች ትዝታ!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(1 Vote)

በታሪክ ሁነቶች ፍም ብቻ ሳይሆን ዐመዱ ውስጥ ተደብቀው ብቅ የሚሉ ብርቆች እንዳሉ የዘመን ብራናዎች ላይ የተከተቡ ሀቆች፣ በታሪክ ሸራ ላይ የተሳሉ ውብ ሥዕሎች ያወሩናል!
በኢትዮጵያ ታሪክ በደም የጨቀየው የደርግ ዘመን፣ ከሁሉ ይልቅ የኢሕአፓና የደርግ- መኢሶን ፍልሚያዎች ዕብደት፣ ዛሬም ድረስ ቆይቶ፣ ሀገሪቱ አብዳ የጣለችውን ጨርቅ መልሳ ልትሰበስበው ቀርቶ ልታሸርጠው እንኳ ያዳገታት መስሏል፡፡ ይሁንና ከዚያ የፋመ የታሪክ ቋያ መሃል በተአምር ያመለጡ ትንታግ ሰዎች ግን በእጅጉ የሚያስደምም የማስታወሻ ዝክሮችን ለትውልድ አስቀምጠዋል፡፡
በተለይ በኢሕአፓ ወገን ሆነው የፃፉት ሕይወት ተፈራ (“ማማ በሰማይ”) እና ሀብታሙ አለባቸው (“የሱፍ አበባ”) የዘመኑን ትርዒት፣ የማርክሲስት ሌኒንስት ጥሬ ፍልስፍናን ዕብደትና የኢትዮጵያውያንን የባቢሎን ቋንቋ ቁልጭ አድርገው ያሳዩናል፡፡ ሕይወት ተፈራ በዋነኛነት ይዛው የተነሳችው ፀፀት ባንዲራዋ፣ በፍቅር ዓለም ያጠመቃትን ጌታቸው ማሩን ይሁን እንጂ ሌሎች ጓደኞችዋን፣ የፓርቲውን ዋነኛ ሰዎችና ለፓርቲያቸው ቁርጠኝነት የነበራቸውን የዘመኑን ችቦዎች ድምቀት ነው፡፡  
ከቅድመ አብዮት ጀምሮ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የነበረውን የለውጥ ኃይል፤የአውሮፓ ተማሪዎችን ትግልና ስዕል፣ የንጉሠ ነገሥቱንና የደርግን መንግሥት ጥላ በእንባ በተነከረ ብዕር፣ ግን ደግሞ ሳንሞቀው የቀረውን የነፃነት ፍም እሳት እንዴት ውኃ እንደተደፋበት አስቃኝታናለች፡፡ ሕይወት ተፈራ የነበረባትን ያን ሁሉ የጤና እክል  ተቋቁማ፣ ከሕመሟ ይልቅ ዓላማዋን አስቀድማ መኖሯ በዘመኑ የነበሩ ወጣቶች ለራሳቸው ሕይወት ሳይሳሱ፣ ለሌሎች ነፃነትና ፍትህ-ናፍቆት የከፈሉትን ዋጋ ይጠቁመናል፡፡  
መነሻቸውን ማርክሲዝም ሌኒኒዝም ማድረጋቸውና የሰውን ልጅ በኃይል በማስወገድ በማመናቸው ጠመንጃ ነካሽ ቢሆኑም፣ ለሕዝብ ያላቸው ቅርበትና በተለይ ለአርሶ አደሩ የነበራቸው ህልም የሚያስደንቅ ነው፡፡ የታሪኩን ሂደትና መቼቱን እንደ ሥዕል ቁጭ ያደረጉት እነዚህ ደራስያንም፣ አዲስ አበባ ከተማን የናጣትን የጥፋት ጩኸትና በሰው ልጆች ደም የተጨማለቀችውን ሀገር ከፊልም ባልተናነሰ አሳይተውናል፡፡  
የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ስብሰባ፣ የከተማው እንቅስቃሴና ሕይወት ዑደት ሁሉ በሚገርም ሁኔታ ይተረካል፡፡ “የሱፍ አበባ” ላይ ያሉት ሰመረ፣ የዐድዋው ልጅ ኢሳይያስ፣ ምግብ አብሳይዋ ሸዋዬ፣ የሰመረ ፍቅረኛ ቢታንያ፣ የገዳይ ስኳዱ፣ ደጀኔ፣ ጋራዣቸው፣ ስብሰባቸው ሁሉ ይናፍቃል፡፡ ሕይወታቸው ይደንቃል። ለዓላማ ያን ያህል መዛመድና መጋመድ ተአምር ነው፡፡ አሁን በሃይማኖቱ ተርታ የሌላ የፓርቲ ታማኝነት በውስጣቸው ሲነድድ ማየት የሚያስገርም  ነው፡፡
የፍቅር ሕይወትን በሚመለከት የጌታቸው ማሩና የሕይወት ተፈራ ፍቅር ልብ ይነካል፤ነፍስ ያሳምማል። ያንን ሁሉ ፖለቲካ የሚተነትንና ታላቅ ሕልም ያለው ጌታቸው፤ የአንዲት ወጣት ሴት ፊት እንደ እሳት እየፈራ የሚያጎነብሰውና ፊቱን የሚያሸሸው ነገር የተፈጥሮን ኃያል መስመር እንድናደንቅ ያደርገናል፡፡ የፍቅር ጥያቄ በዘመኑ አውድ ምን ያህል ከባድ እንደነበር፣ እንደ ዋዛ ዘው እንደማይባልበት፣ መልሱም በምጥ የሚገኝና “እምቢታም” ያፈጠጠበት በመሆኑ ፈተናው ያስፈራ ነበር፡፡
የማኦን ሳይንስ ያስተምራት የነበረው ጌታቸው፤ፍቅር የፓርቲውን ደንብና ዲሲፕሊን ሳያልፍ ራስን በመግዛት መከወኑ ለማመን የሚያስቸግር ነበር፡፡ ከራስ በላይና ከፍቅረኛ በላይ የፓርቲን ትዕዛዛት ማክበር ከየት የተገኘ ተአምራዊ ውሳኔ እንደነበር ማመን ያዳግታል፡፡
እስቲ ጥቅሉን ትቼ ለዛሬ የሀብታሙ አለባቸውን “የሱፍ አበባ” ሕይወት በጥቂቱ እንቃኝና እንደ ሁኔታው ደግሞ የሕይወት ተፈራን ሁለት መጻሕፍት በሌላ ጊዜ እንፈትሻቸዋለን፡፡
እውነት ለመናገር “የሱፍ አበባ” የሚለው ርዕስ መጀመሪያ ሳየው ፈፅሞ ለኔ ማራኪ አልነበረም፡፡ ባልጠፋ ርዕስ ለምን ይህንን መረጠ? ብያለሁ፡፡ በኋላ ግን ውስጡን ገብቼ ሳነብበው፣ ርዕስ አመራረጡና የርዕሱ መነሻና የቆነጠጣቸው ሀዲዶችን ሳይ በእጥፍ ተገርሜያለሁ፡፡ ኢሕአፓን ሰመረ የሚያየው ፀሐይን ትቶ አምፖል እንደተከተለ የሱፍ አበባ ነው፡፡ የሱፍ አበባ ፍሬዎችም እነዚያ በየተራ የረገፉት አበቦች ናቸው፡፡ የኤክስፕሬሽኒስቱን ፈር ቀዳጅ ሠዐሊና ቫን ጎግን መነሻ ያደረገው የሱፍ አበባ ከኢሕአፓ ጋር የተዛመደበት መንገድ እጅግ ግሩም ነው፡፡
የመጽሐፉ ደራሲ ታሪክ ማዋቀር፣ መቸት መምረጥ፣ ልብ ሰቀላ፣ ሳቢያ/መንስኤና ውጤት የመሳል ችሎታው  ብቻ ሳይሆን ፖለቲካዊ ዕውቀቱም ታሪኩ ከፍታ እንዲኖረው በጣም እረድቶታል፡፡ የቋንቋ አጠቃቀሙና የገለፃው ልዕቀት እጅግ የተመረጡ ከሚባሉት ደራሲያን መካከል የሚያስደምረው ነው፡፡
የመጽሐፉ ታሪክ የሚጀምረው ዋና ገፀ ባሕሪው፣ ከእናቱ ጋር ባደረገው የአየር በረራ ቀን ከነበረው ወከባ ነው፡፡ በምልሰት ጀምሮ አጠገቡ የነበሩትን ገፀ ባህርያት አስተዋውቆ ያሟሸዋል፡፡ በመጽሐፉ ሙሉ ታሪክ ውስጥ እንዳየሁት፣ ዋና ገፀ ባህሪው ሰመረ፣ ለኢሕአፓው መስራች ብርሃነ መስቀል ረዳ ልዩ ፍቅርና አክብሮት አለው፡፡ እየተሳሳተ እንኳ ይሳሳለታል። የሚያደንቅበትን ምክንያቶችም ይዘረዝራል፡፡ ገና በመግቢያው አካባቢ ገፅ 12 ላይ ስለ ብርሃነ መስቀል የሚነግረን ነገር በውስጡ የተሳለበትን ቀለም ውበትና የፍቅር ነፀብራቅ ነው፡፡  
“ከብርሃነ መስቀል ረዳ ጋር የተዋወቅንበት ዕለት ልክ እንደ ሰርግ ቀን ልዩ ስሜት ይሰጠኛል፡፡ ከሁለት ወራት በፊት ሰባ ደረጃ አካባቢ በሚኖርበት ቤት አግኝቼው ነበር፡፡ ከሦስት ሰዓት በላይ ተጫወትን--” ይልና የታሪኩን መነሻ ቀን የቱን  ያህል እንደማይረሳው በምልልሱ ይጠቁማል፡፡
“ረዘነ፤ ብታምንም ባታምንም ከሰባት አመታት በፊት ሐምሌ 10 ቀን ሰኞ ዕለት ነው ለመጀመሪያ ጊዜ ያየሁህ” ስለው ሁሌም ግርም ይለዋል፡፡ ረዘነ ነው የትግል ስሙ፡፡ ሁለቱንም ስሞች እወዳቸዋለሁ። እጅግ አድርጌ የማከብረው መሪዬ ነው፡፡ ብርሃነ መስቀል ሌላም ባህሪ አለው፡፡ ቶሎ ስሜታዊ ይሆናል። ገፀ ባህሪው ሲነግረን ጥርጣሬው ስራ ስለሚበዛበት ይሆናል፡፡
ሌላው መጽሐፉ ውስጥ ትልቅ ቦታ ያለው ገፀ ባህሪይ ኢሳያስ ነው፡፡ ኢሳያስና ሰመረ፣ የሚተዋወቁት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ የንጉሡን መንግሥት ተቃውመው ሰልፍ ሲወጡ በጥይት ተመትተው ቆስለው፣ የካቲት አስራ ሁለት ሆስፒታል መግባታቸው ግን በእጅጉ የማይለያዩ ጓደኞች አድርጎ አስተሳስራቸው፡፡ ከዚያም ኢሳያስ ሰመረን ኢሕአፓ አድርጎ መለመለው፡፡ ሕይወታቸው በሙሉ አንድ ላይ ተቋጠረ፣ ኑሯቸውና እንጀራቸው በአንድ ማዕድ ሆነ፡፡
ሰመረ የኢሕአፓ ተልዕኮውን የሚከውንበትን ጋራዥ ወስዶ አንድ ባንድ ያስረከበውም ኢሳያስ ነው፡፡
“ኢሳያስ በጣም ብጭጭ ያለ ቀይ፣ ረጂምና በጣም ቀጭን ነው፡፡” በማለት በገፀ ባህሪው አንደበት ደራሲው ሲያስተዋውቀን፣ አረማመዱን፣ ሁሉ በዓይነ ህሊናችን እንስላለን፡፡
ጋራዡን ሲያስረክበውና ቤቱን ሲያስተዋውቀው፣ የአከራይዋን የወይዘሮ ማስተዋልን ቤት ሲጎበኙ፣ ሳሎን ውስጥ የነበረው የአንዲት ቆንጂዬ ልጅ ውበት ማርኮት ነበር፡፡
“ኢሱ፣ እንዲህ ዓይነት ቁንጅና አጋጥሞህ ያውቃል? ምናቸው ናት ባክህ?” በሹክሹክታ ጠየኩት ይለናል ሰመረ፡፡
“ልጃቸው ናት፡፡ ቢታንያ ትባላለች…”
እንዲህ በፎቶግራፍ የተዋወቃት ቢታኒያ፤ የታሪኩ እንዝርት ሆና በውበት ቀለም የምታሾር ሆና እናገኛታለን፡፡ ቢታኒያ በመጽሐፉ ውስጥ የዘመኑን ወጣት ሴቶች የአላማና የፅናት ኃይል የምታሳይ የታሪክ ማማ ናት፡፡ በአንድ ክንፏ ፍቅር፣ በሌላ ክንፏ የፍትህና የነፃነት ትግልዋን ይዛ ስትበር ላንደነቅባት አንችልም፡፡ ላንዘምርላት የሚያስችለን በድን ልብ አይኖረንም፡፡    
ቢታኒያ እንደ በዐሉ ግርማ ሉሊት፣ እንደ ሀዲስ አለማየሁ ሰብለ ወንጌል፣ እንደ ዳኛቸው ወርቁ ፂዮኔ የላቀ ሰብዕናና ልዕልና እናይባታለን፡፡ የቀድሞ የሰመረ ፍቅረኛ ብርክቲም አንድዋ ተወርዋሪ ገፀ ባህሪ ናት፡፡ የቀድሞ የሕይወቱ ጣፋጭ ከረሜላ፣ በኋላ ግን የሽሽቱ ጥላ ሆና የምታስደነግጠው ምትሀት! ኢሕአፓ እንደ እግዜር ቀናተኛ ይመስላል፡፡ እኔን ካፈቀርክ ከኔ በላይ ሌላ ፍቅር የለም የሚል ዓይነት! ግን ብርክቲ ጥላ ናት። ፍለጋውን የምትከተል የሱፍ አበባ፡፡ ለርሷ ሰመረ ፀሐይ ነው፡፡ መኢሶን ምናልባት አምፖል ይሆናል፡፡ በስተመጨረሻ አሟሟቷ ከመኢሶን ጋር ቢሆንም ልቧ ግን ከሰመረ ጋር እንደነበር በመልዕክቷ እንገነዘባለን፡፡  
በመፅሐፉ ውስጥ ሸዋና ኢሳያስም ደማቅ ናቸው። እዚያች ጨለማ ክፍል ወይም ድብቅ ምዕራፍ፡፡ እነርሱና የቅርቦቻቸው ብቻ የሚፈነድቁባት፣ በሐሳብ የሚቀጣጠሉባት፣ በህልም የሚንሳፈፉባት ቤት፡፡ የሸዋዬ የምግብ አቅርቦት የኢሳያስ ሲራ ጢስ፣ የደጀኔ ስፖርትና ፍልሚያ ልምምድ መልስ -የላቡ ጠብታዎች አይረሱም፡፡
የኢሕአፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ የሀሳብ ፍልሚያ፣ ዲስፕሊን፣ በኋላ ደግሞ መናቆርና ጥላቻ፣ ጥርጣሬና መሳደድ ሁሉ ቁልጭ ብለው የሚታዩበት መጽሐፍ ነው፡፡ በተለይ ጌታቸው ማሩ፤ ሕይወት ተፈራ በፍቅር ዓይንዋ እንደሳለችው ብቻ ሳይሆን ደርግንና ሊቀመንበሩን ያየበት የየዋህነት መንገድ በእጅጉ አሳዛኝ ሆኖ ታይቶኛል፡፡ ደርግ ጥርሱን ስሎ እየጠበቃቸው ሳለ፣ የጋራ ሕብረት መፍጠር የሚለውን ያልተፀነሰ ሀሳብ ዙሪያውን እየዞሩ መሀረቦሽ ሲጫወቱ ያሳዝናል። እውነት ለመናገር ሰመረም ያው የማኦን መርህ ተከትሎ፣ ርዕዮተ አለማቸው አዝሎ ስለኖረ ሀሳቡ በጦርነት ደርግን ማንበርከክ፣ የሰፊውን ህዝብ አብዮት ከተቀለበሰበት መመለስ ነው፡፡ ግን ከተማ ውስጥ ተደብቆ አይደለም። ወይም የገጠሩን ኑሮ ሸሽቶና ምቾትን የሙጢኝ ብሎ አይደለም፡፡ ይልቅስ አሲንባ ሄዶ፣ ገበሬው መሃል ገብቶ፣ የጋራ መዝሙር እየዘመሩ በማንበርከክ ነው፡፡ የሰማው ግን አልነበረም፡፡ ምናልባት ያ ቢሆን በጅምላ የተጨፈጨፈው ወጣት፣ ከሞት የማምለጥ ቀዳዳ ይኖረው ነበር፡፡
ወይዘሮ ማስተዋል በታሪኩ ማምሻ “ግንበኞች የናቁት ድንጋይ የማዕዘን ራስ ይሆናል!” ሲሉ የመሰከሩለት ሙሴ ባልዲ፤ በታሪኩ ውስጥ ትልቅ ሚና ነበረው፡፡ ሙሴ ቀድሞ የሰፈር አውደልዳይ ዱርዬ፣ ሱሰኛና ቀማኛ የነበረ፣ በኋላ ግን የእነ መንግሥቱ አብዮት በሰጠው ዕድል አብዮት ጥበቃ ጓድ የሆነና ባለጊዜው ስለነበር፣ ለቢታንያና ለሰመረ ሕይወት መትረፍ ምክንያት ሆኗል፡፡
በመጽሐፉ ውስጥ ጣፋጭ ትረካ፣ ልዩ የሕይወት ጣዕም፣ በእሳት ላይ የበቀለ አበባ ሆኖ የምናየው የቢታኒያና የሰመረ ፍቅር በእጅጉ መሳጭ ነው፡፡ በኋላም ከሁለቱ የተሰፋ-ሰው፣ ፅንስ፣ ሴት ሆና ተወልዳ ስሟ “እርምት” መሆኑ፣ ሩቅ ዘመን ተሻግሮ፣ በትውልዱ ጆሮ እየጮኸና እያስተጋባ የሚኖር ይመስለኛል!
ዘርዑ ክህሽን የደረሰው የከተማ ውጊያ ድርሰት ስህተት በጊዜው እርምት ባለማግኘቱ፣ የአንድ ትውልድ ደም በከንቱ ፈሷል፡፡ ታላላቅና ብሩህ አእምሮ የነበራቸው ወጣቶችን ሀገሪቷ አጥታለች፡፡ ጠመንጃ በመምዘዝ፣ ትልቅ ስህተት ተፈፅሟል! ምናልባት በመጽሐፉ ውስጥ የተጠቀሰው ቀዩ በር፣ የመኖሪያ ቤቱ የጀርባ መግቢያ ምስጢር ይኖረው ይሆን? ስለዚህ “እርምት” የሚለው መዝሙር ያለማቋረጥ መዘመር አለበት፡፡ በሀገራችን አድማሳት ሊስተጋባ ይገባል፡፡
ሀብታሙ አለባቸው ትልቅ ስራ፣ በሚጥም መንገድ አበርክቶልናል፡፡ እንኳን ተረፍክልን እንበለው፡፡ ኢሕአፓም ከእነ ድክመቱ የዓላማን ፅናትና ለሕልም የሚከፈል ዋጋን በዘመን ገፆች ፅፎልን አልፏል፡፡ ስህተቱን ትተን ጥንካሬውን እንቅዳ! 

Read 2045 times