Saturday, 28 July 2018 15:34

የያዝነው መፈክር በልቦናችን ላይ መታተም አለበት!

Written by  በድሉ ዋቅጅራ (ዶ/ር)
Rate this item
(2 votes)

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የኢትዮጵያ መሪ ከሆኑ አንድ መቶ ቀናት አልፈዋል፡፡ ፍቅር፣ ይቅርታና መደመር የነዚህ ቀናት አርማ ነበሩ፡፡ አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ ፍቅር፣ ይቅርታንና መደመርን ዘምሯል፡፡ ጉዳዩ ድንበር ተሻግሮ በኢትዮጵያና በኤርትራም መካከል ሰላም አውርዷል (ቢያንስ እርቅ ተካሂዷል)፡፡ ከኢህአዴግ ማህፀን ጠ/ሚ አብይ አህመድ ይወለዳል፤ በኢትዮጵያ እንዲህ አይነት ለውጥ ይካሄዳል ብሎ የጠበቀ ኢትዮጵያዊ ከኖረ ነብይ ነኝ ማለት አለበት፡፡ መንግስት በነዚህ ቀናት ‹‹አሸባሪ›› ብሎ ያሰራቸውን ዜጎች ከየእስር ቤቱ ለቋል፡፡ ‹‹አሸባሪ›› የተባሉና በስደት ላይ የነበሩ ግለሰቦችና ድርጅቶች የተለጠፈባቸው ስም ተነስቶ፣ በሰላማዊ መንገድ ሀገራቸውን ለማገልገል፣ ለዲሞክራሲያዊ አስተዳደር መጎልበት ለመታገል ወደ ሀገራቸው መግባት ጀምረዋል። ሌላው ቀርቶ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ራዲዮ ኢሳትን፣ የአሜሪካና የጀርመን ድምጾችን ተገዳድረው የሚናፈቁ የመረጃ ምንጮች ሆነዋል፤ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ህዝቡ በራሱ ተነሳሽነት፣ አስተባባሪ ኮሚቴ እያቋቋመ ጠ/ሚኒስትሩንና ያመጧቸውን ለውጦች ለመደገፍ ወደ አደባባይ እየወጣ ነው፡፡ ቴሌቪዥን የሚያዘጋው የመሪዎች ንግግርና የፓርላማ ፕሮግራም ተናፋቂና ተጠባቂ ሆኗል፤ … ሌሎችንም በጎ ለውጦች መጨመር ይቻላል፡፡
የዚህ መጣጥፍ ዋና አላማ ግን ይህ አይደለም፡፡ የዚህ ጽኁፍ ዋና አላማ እነዚህ ለውጦች ወደ መሬት ወርደው ህዝባዊ መሠረት እንዲጥሉ፣ ሌሎች በጎ ለውጦችም እነዚህን መሰረት አድርገው እንዲከተሉ መደረግ ያለበትን (ተጨባጭ ወቅታዊ ሁኔታዎችን መሠረት ያደረገ፣ ግላዊ ሀሳብ) ለመሰንዘር ነው፡፡
ባለፉት አንድ መቶ ቀናት ለሃያ ሰባት ዓመት ኢህአዴግ ‹‹ሀኪም ይንቀለኝ›› ብሎ የተጣበቀባቸው ሀሳቦች የተነቀሉ እስኪመስል ድረስ በጎ ለውጦች ታይተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ለህይወት መጥፋት፣ ለአካል መጉደልና ለመቶ ሺዎች መፈናቀል ምክንያት የሆኑ ጎሳዊ ግጭቶች አልቆሙም፤ እንዲያውም እየበረከቱ፣ እዚህም እዚያም እየተከሰቱ ነው፡፡ በጉጂ ኦሮሞና የጌድዮ ግጭት ጌድዮዎች፣ በቤንሻንጉል አማሮች፣ በሲዳማ ወላይታዎች … ወዘተ. ተፈናቅለዋል፡፡ የሱማሌና የኦሮሞ ግጭትም እየተባባሰ ነው፡፡ የሰው ህይወት፣ የጠፋባቸው፣ አካል የጎደለባቸው፣ ንብረት የወደመባቸውና ዜጎች የተፈናቀሉባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ህዝቦች፤ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን የፍቅር፣ የይቅርታና የመደመር ጥሪ ተቀብለው ለድጋፍ አደባባይ አጨናንቀዋል፡፡ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊት ሃያ ሰባት ዓመት ያጠላበትን ጥላ አሽቀንጥሮ ጎልቷል። የኢትዮጵያ ባንዲራ ከክልል ባንዲራዎች ከፍ ብሎ ተውለብልቧል፤ እስከ አንድ ኪሎ ሜትር በሚደርሱ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማዎች ከተሞች ደምቀዋል፡፡ ኢትዮጵያዊነት ተዘምሯል፡፡
የዚህ ጽኁፍ ዋና አነሳሽ፣ የዚህ የኢትዮጵያዊነት ደምቆ መዘመር፣ የባንዲራችንን መውለብለብና ጎሳን መሰረት ያደረገ ግጭት በአንድነት መከሰት ነው፡፡ ደቡብ ስለ ኢትዮጵያዊነት እየዘመረ፣ ሲዳማና ወላይታ ይጋጫል፤ ወልቂጤ ላይ ጉራጌና ቀቤና የኢትዮጵያን ሰንደቅ እያውለበለቡ እርስ በርስ ይጋጫሉ፤ ኦሮሞና ጌዲዮ፣ ሱማሌና ኦሮሞ. . .  ወዘተ.፡፡ ጥያቄው ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? ይችላል? ‹‹ፍቅር ያሸንፋል›› ብሎ የሚዘምር ሰው እንዴት የጎረቤቱን ቤት ያቃጥላል? …
መልሱ ከባድ አይደለም፤እንዲህ የሚሆነው በጨርቅ ላይ ጽፈን በየአደባባዩ የምንሸከመው፣ በአንደበታችን የምንዘምረው ‹‹ይቅርታ፣ ፍቅርና መደመር›› በልቦናችን ባለመታተሙ ነው፡፡ ቁምነገሩ አንድን ጉዳይ ከልብ ደግፈን፣ ለድጋፍ መውጣታችን አይደለም፡፡ ቁምነገሩ የደገፍንበትን ምክንያት እስከነ ምክንያቱና ውጤቱ በአስተውሎት እናውቀዋለን ወይ? ነው፡፡ ብናውቀው እንኳን፣ ማወቁ ብቻ አሁንም በቂ አይደለም፡፡ በህሊናችን ያወቅነውን ጉዳይ በልቦናችን አትመን፣ የእለት ተእለት ኑሯችን መመሪያ ማድረጉ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ሲፈተሽ፣ ከጊዜውም አጭርነትና ከለውጡ አለመስከን የተነሳ የምንዘምረው ‹‹ይቅርታ፣ ፍቅርና መደመር›› ከተፃፈበት ጨርቅ ወርዶ እውቀትና የልቦና ማህተም አልሆነንም፡፡
አብዛኛው ዜጋ ሀያ ሰባት አመት ሲጋት ከነበረው የጎሳ አልኮል ስካር አልተላቀቀም፤ ስካሩ ጨርሶ ቢለቀው እንኳን ገና አንጎበሩ አለ፡፡ በመሆኑም የጎሳ ክፍፍልና ጥላቻ በልቦናው እንደታተመ ነው። አብዛኛው ሰው የሌሎች ብሔር-ብሔረሰብ አባላት ለእሱ በተከለለው ክልል የመገኘት/የመኖር መብት እንደሌላቸው፤ ከኖሩም በእርሱ ልግስናና ፈቃድ እንደሆነ ነው እውቀቱ፡፡ አብዛኛው ህዝብ ይህን የጎሰኝነትና የክልላዊነት ስሜት ከህሊናውና ከልቦናው ሳይፍቅ ነው ረዣዥም ባንዲራዎችን እያውለበለበ፣ ኢትዮጵያዊነትን እየዘመረ አደባባይ የሚያጣብበው። በነዚህ አይነት ሰልፎችና በአንድ የሙዚቃ ኮንሰርት መካከል እምብዛም ልዩነት የለም፡፡ የምሽቱ የሙዚቃ ኮንሰርት አልቆ ሲነጋ ታዳሚው ወደተለመደው እለታዊ ኑሮው እንደሚመለስ፣ መሽቶ አደባባይ ሰልፉ ሲበተን ታዳሚው ‹‹ይቅርታ፣ ፍቅርና መደመርን››፣ የኢትዮጵያን ባንዲራ አሽቀንጥሮ ወደ ጎሳ ጎጆው ይገባል፡፡
ለዚህ ሀሳብ ማጉያ አንድ ምሳሌ እንጥቀስ፡፡ በማህበራዊ ሚዲያ (በተለይ በፌስቡክ) ላይ አብዛኞቹ የማህበራዊ ዲያሎግ አመንጪ የሆኑ ልሂቃን፣ በጠ/ሚ አብይ አመራር የመጣውን የመደመር ለውጥ ደግፈው፣ ኢትዮጵያዊነትን ያቀነቅናሉ፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ልሂቃን በጠ/ሚኒስትሩ የሹመት አሰጣጥ ላይ ተቃውሞ መሰንዘር ጀምረዋል፡፡ ከዚህም አልፎ የለውጡን ጉዞ ከወዲሁ በጥርጣሬ መመልከት እንደጀመሩ መጠርጠር አይከብድም፡፡ በተለይ የአዲስ አበባ ከንቲባ ከኦሮሞ ብሔረሰብ በመሾማቸው፣ የሹመኞችን ዝርዝር እያሰፈሩ ባለፈው የትግራይ ተወላጆች ተጠቅልሎ የነበረው ስልጣን፣ ለኦሮሞ እየተሰጠ ነው የሚሉ በዝተዋል፡፡ በርግጥ ጎሳን መሠረት ባደረገ የፌደራሊዝም ስርዓት በምትተዳደር ሀገር ውስጥ የብሔረሰብ ስብጥር በስልጣን ላይ ዋጋ የለውም ማለት አይቻልም፡፡ የአስተዳደሩ አደረጃጀት መሰረት ጎሳ በመሆኑ፣ እያንዳንዱ ጎሳ በየደረጃው ራሱን በማስተዳደር ውስጥ ውክልና/ተሳትፎ ያሻዋል። ጽንሰ ሀሳቡ ይህ ቢሆንም፣ በየአስተዳደር እርከኑ ያለው የስልጣን ውክልና በበርካታ ዝርዝር ጉዳዮች ይወሰናል።
ዋናው ነጥብ ‹ሃያ ሰባት ዓመት ሙሉ በቀዳማዊ ኢህአዴግ አገዛዝ ሀገሪቱን በብሔር ሸንሽኖ ሲያስተዳድር፣ የክልል ባንዲራ እየተውለበለበ፣ የብሔር ብሔረሰብ መብት የመብቶችና የማንነት ቁንጮ ሆኖ፣ የግለሰብ መብትንና ብሔራዊ ማንነትን ድጦ በነበረበት ዘመን የትግሬ ባለስልጣናትን ሲቆጥር የነበረ ሰው፣ ዛሬ የኢትዮጵያን ሰንደቅ እያውለበለበ፣ ጎሰኝነትን በመደመር ደፍጥጦ፣ ኢትዮጵያዊነትን እየዘመረ (ቢያንስ በአደባባይ) አሁንም የኦሮሞ ባለስልጣናትን የሚቆጥር ከሆነ፣ ለውጡ የያዝነው ባንዲራና የምንዘምረው መዝሙር እንጂ፣ የልቦናችን ማህተምና ተግባራችን እንደነበረ እየቀጠለ ነው፡፡
በዚህ የተነሳ ነው ወደ ይቅርታ፣ ፍቅርና መደመር የምናደርገው የለውጥ ጉዞ ለፍሬ ይበቃ ዘንድ መፈክርና መዝሙራችን በልቦናችን ላይ መፃፍ ያለበት፡፡ ፍቅር  ያለ ምርጫ ወገኑን ማፍቀር አለበት፡፡ ይቅርታ ያለ ምርጫ የበደለውን (በድሎኛል ያለውን) ሁሉ ይቅር ማለት አለበት፡፡ መደመር ያለ -- በዚህ የኢትዮጵያ የለውጥ ሂደት የእርሱም አስተዋፅኦ ይኖር ዘንድ ከለውጥ ሀይሉ ጋር መቀላቀል አለበት፡፡ ከለውጥ ሀይሉ ጋር የተደመረ ዜጋ የሚያስጨንቀው ሀገሪቱ ከገባችበት የኢኮኖሚ ችግር፣ በጎሳ ግጭት የተነሳ የሚታየው ሞት፣ የአካል ጉዳትና መፈናቀል፣ ሀገሪቱን ግጦ የጨረሳት ሙስና፣ የፍትህ አለመከበር… ወዘተ. እንጂ የተሿሚዎች ጎሳዊ ማንነት መሆን የለበትም፡፡ ‹‹የጠ/ሚኒስትሩ የለውጥ ንቅናቄ የእኛ ነው›› ብሎ ከዳር እስከ ዳር የተነቃነቀ ህዝብ፣ የእሳቸውን ‹‹ፍቅር፣ ይቅርታና መደመር›› የለውጥ መንገድ ተቀብሎ ‹‹ወደፊት›› ያለ ህዝብ፣ እሳቸው ‹‹ለውጡን ከግብ ያደርሳል›› ብለው በመሪነት የሚያመጧቸውን ባለስልጣናት ካልተቀበለ ውገናው ምክንያታዊ አይደለም፡፡ ትክክለኛው አካሄድ ተሿሚዎች እውን የለውጥ አካል መሆን ያለመሆናቸውን በትኩረት መከታተል ነው፡፡
የጠ/ሚኒስትሩ የመደመር የለውጥ ንቅናቄ ህዝባዊ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ ይህም የሆነው ጠ/ሚኒስትሩ ካፈራቸው ዛፍ በተለየ ታማኝነትና ተቀባይነትን በማግኘታቸው ነው፡፡ ‹‹ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን አስቀድሞ በተነሳ ለውጥ፣ በእያንዳንዱ ሹመት የጎሳ ተዋጽኦን መጠበቅ ወደ ኋላ ተመልሰን፣ በምንሸሸው አዘቅት ውስጥ መዘፈቅ ነው፡፡ አሁን ዋናው ጉዳይ ሃያ ሰባት ዓመት በብሔር ተደራጅተን፣ በጎሳ ተከፋፍለን ከቆፈርነው አዘቅት ውስጥ መውጣታችን ነው። ከአዘቅቱ ለመውጣታችን እርግጠኞች ስንሆን - ስንርቀው፣ ያኔ ረጋ ብለን ፌደራሊዝሙ እንደምን መሻሻል - መቀጠል እንደሚገባው ማጥናት - መነጋገር - መስማማትና መወሰን እንችላለን፡፡
እስከዚያ ድረስ አሁን ዋናው ጉዳይ በአደባባይ ለውጡን ለመደገፍ የገባነውን ቃል፣ በተዘጋ ቤት ለየራሳችን መድገም ነው፡፡ ለዚያ ደግሞ የአደባባዩን ድጋፍ በየደረጃው እስከ ቤተሰብ ድረስ ማውረድ ያሻል። የአንድ ብሔረሰብ አባላት፣ የአንድ ቀበሌ ነዋሪዎች፣ የአንድ እድር ሰዎች፣ የአንድ ቤተሰብ አባላት. . . ኢትዮጵያ የኢትዮጵያውያን መሆኗን፣ የትኛውም ብሔረሰብ በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል መኖር እንደሚችል መቀበል አለባቸው፡፡ ከሁሉም በላይ እያንዳንዱ ዜጋ በምንም ምክንያት የሌላውን ጎሳ አባላት ላለማጥቃት ከልቦናው ጋር መነጋገርና እንደ ሀይማኖት በልቦናው ሊጽፈው ይገባል፡፡ ያ ከሆነ ድርጊቱን ይፀየፈዋል፡፡ ይህ እንዲሆን ደግሞ መንግስትም ከአደባባይ ወደ ት/ቤት፣ ቀበሌ፣ ቤተሰብ … ወዘተ. መውረድ አለበት፡፡
ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት በየፖሊሲያችን፣ በየስርዓተ ትምህርቱ፣ በየብዙሃን መገናኛው፣ በየደረጃው ባሉ ባለስልጣኖቻችን አንደበት በየቤተሰቡ፣ በየስታዲየሙ ሲንፀባረቅ የነበረው፣ በአንድ ወይም በሌላ መልኩ ብሔርን መሰረት ያደረገ ከፋፋይ ሀሳብ ትኩረት ሊሰጠውና በፍጥነት ሊሻሻል ይገባል፡፡ ይህ ደግሞ በዋናነት የመንግስት ተግባር ነው፤ ለአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትርም ትልቁ ፈተናም ይኸው ነው፡፡

Read 742 times