Print this page
Saturday, 28 July 2018 15:43

ከያኒው በፈጠራ ሥራዬ ድምቡሎ አላገኘሁም ይላሉ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

  - ቡናና ሻይ ባለሥልጣን አሁንም ድረስ በመዝሙሩ ይጠቀምበታል
     - በህይወት እያለሁ ሀገሪቱ ወደ ትልቅነቷ ተመልሳ ማየት እፈልጋለሁ

    በ1970ዎቹ መጨረሻ ተወልዶ ነፍስ ያወቀ ህፃን ጠዋት ከእንቅልፉ ሲነሳ እንደ ዛሬው ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያ ባልተስፋፋበት በዚያን ጊዜ አንድ ለእናቱ በነበረው ኢትዮጵያ ሬዲዮ አንድ የዘወትር ጀሮ ገብ ዜማ በጆሮው እየተንቆረቆረ ከእንቅልፉ እየኮረኮረ ያስነሳው እንደነበር ብዙዎች ያስታውሳሉ፡፡ ይህ ጆሮ ገብ መዝሙር አሁንም ድረስ በስራ ላይ ይገኛል፡፡ ‹‹የኢኮኖሚ ዋልታ ቡና ቡና የገቢ ምንጫችን ቡና ቡና››  የተሰኘው ይህ የዘወትር መዝሙር፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የአረንጓዴው ወርቃችን የቡና ዋጋ ስንት እንደሆነ ሲነገር አብሮ የሚዘመር፣ በኢትዮጰያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ባለቤትነት ስር ያለ ወርቃማ መዝሙር ነው፡፡
ለመሆኑ የዚህ መዝሙር ደራሲ ማን ናቸው? የት ነው ያሉት? እንዴት መዝሙሩን ለማዘጋጀት ተነሳሱ? ባለፉት 40 ዓመታት በጆሮ እየተንቆረቆረ ከዘለቀው ከዚህ መዝሙር የግጥምና ዜማ ደራሲው ምን ተጠቀሙ? ለሚሉትና ተያያዥ ጉዳዮች የመዝሙሩ ደራሲ መምህር ታረቀኝ ወንድሙ ለአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ በጅማ እንዲህ አውግተዋታል፡፡


    እስኪ ራስዎን በደንብ ያስተዋውቁ?  
ተወልጄ ያደኩት በአሁኑ ቤንች ማጂ ዞን አንድ ወረዳ ነው፡፡ ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍልም ትምህርቴን የተከታተልኩት በትውልድ አካባቢዬ ነው፡፡ ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ወደ ጅማ ሚያዚያ 28 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መጣሁ፡፡ የ12ኛ ክፍል ትምህርቴን እንዳጠናቀቅሁ ለመምህርነት ስልጠና ወደ ደብረብርሃን መምህራን ማሰልጠኛ ገብቼ፣ ለሁለት አመት ከሰለጠንኩ በኋላ በወቅቱ ከፋ ክፍለሃገር ይባል በነበረው ጅማ  ተመድቤ፣ በየአውራጃዎቹ እያስተማርኩና ትምህርቴንም እያሻሻልኩ ቆይቻለሁ፡፡
ከዲፕሎማ ወደ መጀመሪያ ዲግሪ ብሎም ሁለተኛ ዲግሪዬን እስከ መያዝ ደርሼ ሳስተምር ነበር፡፡ በአሁን ሰዓት በጡረታ የተገለልኩ ቢሆንም በአሁን ወቅት በጅማ ዩኒቨርሲቲ በውጭ ግንኙነትና ኮምዩኒኬሽን ቢሮ የፐብሊኬሽን ኤክስፐርት ሆኜ በመስራት ላይ እገኛለሁ፡፡
እንደሰማሁት በእንግሊዝኛ መምህርነት ከ35 ዓመት በላይ አገልግለው ነው በጡረታ የወጡት። በዚህ የአንድን ጎልማሳ ዕድሜ የሚያክል የአገልግሎት ዘመንዎ እንዴት እንዳለፈ እስኪ ያጫውቱኝ?
እውነት ነው፤ ረጅም ጊዜ ነው በመምህርነት ያገለገልኩት፡፡ መምህርነት እንደሚታወቀው ትውልድን መቅረፅ ነው፤ ተተኪ ትውልድ ማፍራት ነው፡፡ በዚህ ስራዬ ብዙ ፈተናዎችን በፅናት በማለፍ፣ ብዙ ትውልድ እንደቀረፅኩ ይሰማኛል፡፡ በሙያዬም እጅግ ደስተኛ ነኝ፤ እጅግ የማከብረው ሙያ ነው፡፡ አሁን ላይ እኔ ሳስተምራቸው የነበሩ በርካታ ሀኪሞች ፣ኢንጂነሮች ፣ጋዜጠኞች ወዘተ… ሆነው ለቁም ነገር ደርሰው ሳይ ከፍተኛ እርካታ ይሰማኛል፡፡
አየሽ የለፋሽበት ትውልድ በተለይ አንቺ በህይወት ቆመሽ እያለሽ ፍሬ አፍርቶ ለቁም ነገር ሲበቃ ማየት ራሱን የቻለ በረከት ነው። የመምህርነት የረጅም ርቀት ጉዞዬ ውጤታማ ነው ብዬ አፌን ሞልቼ መናገር እችላለሁ፡፡
መምህር ታረቀኝ መምህር ብቻ ሳይሆኑ የኪነ- ጥበብና የስነ-ፅሁፍ ባለሙያም ናቸው ሲባል ሰምቼ አለሁ፡፡  ከሥነ-ፅሁፍ ጋር ያለዎት ቁርኝት እንዴት ይገለፃል?
በእርግጥ የስነ-ፅሁፍና የኪነ-ጥበብ ፍቅር ከልጅነት ጀምሮ ነበረን ገና ከአንደኛ ደረጃ ጀምሮ በሃይስኩልም ሆነ በመምህራን ማሰልጠኛ የኪነት ቡድን ውስጥ እሳተፍ ነበር፣ ሙዚቃ እወዳለሁ፣ ድራማም እሰራ ነበር፡፡ ስለዚህ ኪነ-ጥበብ ከልጅነቴ ጀምሮ አብሮኝ ያደገ ነው፡፡ እኔም ልዩ ፍላጎትና ስሜት አለኝ፡፡ ያ ስሜት እያደገ መጥቶ በመምህርነቴም ስነ-ግጥም ሁሉ እፅፍ ነበር፡፡
በመምህርነት ዘመንዎ በርከት ያሉ የአብዮት ግጥሞችንና ሌሎችንም ግጥሞች ይፅፉ እንደነበር ይነገራል፡፡ ስለገጣሚነት ዘመንዎ ያውጉኝ…?
እንግዲህ ከፃፍኳቸው ግጥሞች መካከል አንዱና ዋነኛው የነበረው
 መምህር ብርቁ
መምህር ድንቁ
መምህር የአገር አድባር አውጋር፡፡
…የሚል ግጥም ፅፌ ነበር፡፡ ይህ ግጥም፤ ትኩረትና እንክብካቤ ሲገባው ብዙ ትኩረት የተነፈገውን የመምህርን ድንቅነት እንቁነት አጉልቶ የሚያሳይ ስለነበር በ2000 ዓ.ም የጅማ መምህራን በዚሁ ዛሬ ተማሪ ባስመረቅንበት ሚኒ ስታዲየም ቀርቦ በጣም አድናቆት ተችሮኝ ነበር፡፡
ቲቲ አይም እያለሁ ግጥም እፅፍ ነበር፡፡ በደርግ ሰዓትም እንዲሁ “ተናገር ወንበሩ” የተሰኘ ግጥም ፅፌ ነበር፡፡ ይህ ግጥም በዚያን ግዜ ሙስናን የሚቆጣጠርና በስልጣን መባለግን የሚያቆም የሰርቶ አድር ቁጥጥር ኮሚሽን የተሰኘ ቡድን ነበር፡፡ እስኪ እባክህ ይህንን ሙስናና በስልጣን መባለግን ለማስቀረት የሚያግዝን ግጥም ጻፍልን ብለውኝ ነው የጻፍኩት፡፡ የዚህ ግጥም አጠቃላይ ይዘት፤ “ሙሰኞችና ባለስልጣኖች ያልተገባ ስራ የሚሰሩት ከሰው ተደብቀው ቢሆንም ከአንተ ግን አይደበቁምና አንተ ወንበር እስኪ የሚሰራውን ሙስናና ብልግና ተናገር!፡፡ እንዴት ዝም ትላለህ? የሚዶልቱት የሚሸምቁት አንተ ላይ ቁጭ ብለው አይደለም ወይ?!” እያልኩ ወንበሩን ሰውኛ ባህሪ አላብሸ ድራማታይዝ አድርጌ ነበር የጻፍኩት፡፡ ይህ ግጥም በዚያን ወቅት የቀረበው ከታች ከወረዳ እስከ ጅማ ዋና ዋናዎቹ ባለስልጣናት ከፍተኛ አመራሮች በተሰበሰቡበት እዚሁ ጅማ ግቢ አዳራሽ ውስጥ ነበር፡፡ ግጥሙንም ያቀረብኩት እኔው ራሴ ነበርኩ፡፡
ግጥሙን ካቀረቡ በኋላ ከባለስልጣናት ዛቻና ማስፈራሪያ አልደረስዎትም?
እንግዲህ ጊዜው ረጂም ነው፡፡ ያው በደርግ ጊዜ ነበር፡፡ በትክል ቀኑንና አመቱን አላስታውሰውም። ነገር ግን ያ ሁሉ ባለስልጣን እዚህ ቁጭ ባልንበት እንዴት ታሰድቡናላችሁ፤ ገመናችን ይወጣል፤ በሚል በግቢ አዳራሽ ጉርምርምታ ሰፊ ሆኖ ባለስልጣኑ ኩርፊያ በኩርፊያ ሆኖ ነበር፡፡ እኔ እንድጽፍ ያደረገኝ ሰርቶ አደር ቁጥጥር ኮሚሽን ላይ ሲጮሁ ነበር፡፡ እንደውም አንዳንድ የቅርብ ጓደኞቼ “አንተ ግን አልታሰርክም፣ ችግር አልደረሰብህም?” እያሉ ይጠይቁኝ ነበር፡፡
በእለቱ በስብሰባው ላይ የተገኙት የክፍለ ሀገር ዋና አስተዳዳሪ፤ ይህን ትዝብት የጻፈው እኛ ከጊዜ ጊዜ ጥፋታችንን ከማረም ይልቅ ጥፋት እያሳደግን በመምጣታችን ነው፡፡ ግጥሙ አስተማሪና ማንቂያ ደወል ነው ብለው አስተያየት ሰጡና እኔን ደገፉኝ። ሰርቶ አደር ቁጥጥር ኮሚሽንም ግጥሙን ካጻፈኝ በኋላ ግምገማና ሳንሱር አድርጎ አሳልፎት ነው በስብሰባው ላይ የቀረበው፡፡
ስለ ተዋቂው መዝሙር ከማውራታችን በፊት … የባሶ 4 ቀበሌ ህጻናት ኪነት ቡድንን እንዴት እንዳቋቋሙና እንዳሰለጠኑ ይንገሩኝ?
እውነት ነው የሚቀድመው ያንን የዘመሩት የኪነት ቡድን እንዴትና ለምን ተመሰረተ የሚለው ነገር ነው፡፡ በደርግ ጊዜ መስከረም 2 ቀን የአብዮት በዓል በየአመቱ ይከበር ስለነበር፤ ለዚያ አብዮት በግል ሰው ሁሉ በየቀበሌው ይለማመዳል፡፡ በወቅቱ የኩባ ሰልፍ አንድ የሰልፍ አይነት ነበር። እጅ ደረት ላይ ተደርጎ የሚኬድ ነው፡፡ መቼስ ለዚህ ሰልፍ በየቀበሌው የሚደረገው ዝግጅትና ልምምድ ሌላ ነበር፡፡ እናም በየቀበሌው ባለው አዳራሽ ሴቱም ወንዱም፣ አዋቂውም ህጻኑም ነበር የሚዘጋጀው፡፡ እኔ በዛን ቀን ከትምህርት ቤት ከ11 ሰዓት በኋላ ወጥቼ እዚሁ ጅማ ኪቶ ኳስ ሜዳ የሚባል  እሄዳለሁ፡፡ የሰልፉንና ዝግጅቱን ጉዳይ ለማየት ስሄድ የሰልፉ ስልጠና በተለይ በህጻናቱ ላይ ማራኪ ሆኖ ስመለከት፣ አንድ ሃሳብ ወደ አዕምዬ መጣ፡፡
ምን አይነት ሃሳብ ነበር
እነዚህ ህጻናት እንደዚህ አምረው ሰልፉን ብቻ ከሚያካሂዱ ለምን የሆነ መዝሙር አጥንተው እየዘመሩ አይሄዱም የሚል ሃሳብ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ሰልፉን የሚያሰለጥነው ሰውዬ፤ “እነዚህ ልጆች መዝሙር እየዘመሩ ቢሄዱ አይሻልም ወይ?” አልኩት፡፡ “ተገኝቶ ነው ጥሩ ነው” ሲለኝ 15 ወንድ፣ 15 ሴት ህጻናትን መለመልኩና አንድ ወቅቱንና አብዮቱን የሚመለከት መዝሙር ጽፌ አሰለጠንኳቸው፡፡ ያችን መዝሙር ከአማረው ሰልፋቸው ጋር እየዘመሩ ሄዱ፡፡ እዚህ ጅማ እስታዲየም ነበር ሰልፉ የሚከበረው፡፡ በጥሩ ሁኔታ አሳለፉ፡፡ በቃ ተለያየን፡፡
ከዚያስ?
ከዚያማ እነዚህ ህጻናት በየጊዜው ሲያገኝ “ኸረ ቲቸር ሌላም መዝሙር ይጻፊልን እንዘምር” እያሉ ጥያቄ ማቅረብ ጀመሩ፡፡ የመጀመሪያውን መዝሙር የሰራሁላቸው በ1969 ዓ.ም መጨረሻ ክረምት ላይ ነበር፡፡ በዓሉ መስከረም 2 ስለነበር ማለት ነው፡፡ ጥያቄያቸው እየበዛ ሲሄድ በዚያን ጊዜ ነው የባሶ 4 ቀበሌ ህጻናት ኪነት ቡድን የተመሰረተው፡፡ እኔም ለካ ሳስበው  እንዲህ አይነት ስራ የመስራትና የመፍጠር ፍላጎት በውስጤ አድሮ ነበር፡፡ በኋላ ነው የተገነዘብኩት እናም መዝሙር እየጻፍኩ እያለማመድኳቸው እሳት የሆነ የኪነት ቡድን ወጣቸው፡፡ ህጻናቱ ያምራሉ፤ ቶሎ ጭንቅላታቸው ይቀበላል፡፡ ድምጻቸው ቆንጆ ነበር፡፡ የመድረክ ላይ ስራቸው ሁሉ በጣም አስገራሚ እየሆነ ሄደ። በሬዲዮ ቴሌቪዥን ድምጻቸው እየተቀረጸ መተላለፍ ሲጀምር በጣም ዝነኛ ሆኑ፡፡ እዚህ ጅማ ላይ የትኛውም አይነት ዝግጅትና በዓል ሲኖር እየተጠሩ መስራት ጀመሩ፡፡ በየቦታው ሾው ማቅረብ ሆነ ስራችን፡፡ ዝነኛ ተወዳጅ እየሆነ ቀጠለ፡፡ በአንድ ወቅት ታዲያ የዛን ወቅት የቡናና ሻይ ሚኒስቴር ሚኒስትሩ እዚህ ጅማ ስብሰባ መጡ፡፡ ስብሰባው በግቢ አዳራሽ የተካሄደ ትልልቅ የስራ ሃላፊዎች የተገኙበት ነበር፡፡
እናም እንደተለመደው ተጠርተን ለታዳሚው ስራችንን አቀረብን፡፡ ሚኒስትሩ ታዲያ በጣም ነበር ተደነቁት፡፡ “እነዚህ ልጆች ለምን ቡናችንን የሚያሞግስ ስራ አይሰሩልንም?” ብለው አጠገባቸው ተቀምጠው ለነበሩት የክፍለ ሀገሩ አስተዳዳሪ ይነግሯቸዋል፡፡ እናም አስተዳዳሪው የሚኒስትሩን ጥያቄ ተቀብለው በነጋታው ደውለው አስጠርተው “እንዲህ አይነት ስራ ሚኒስትሩ ጠይቀዋልና ቆንጆ ስራ ይሰራ” ብለው አዘዙን። ይህን የቤት ስራ ሳወጣ፣ ሳወርድ ስጽፍ ስቀድ ቆይቼ፣ በ45 ቀናት መዝሙሩ ተሰራ እልሻለሁ፡፡ ልጆቹም አጥንተው ዘመሩት፡፡ በሬዲዮና በቴሌቪዥን ተቀርጾ ይኸው ከ1971 ዓ.ም ጀምሮ ላለፉት 40 አመታት በስራ ላይ ይገኛል፡፡ ቡናና ሻይ ሚኒስቴር ከጠበቀው በላይ ሆነና በተከታታይ ላለፉት 25 እና 26 አመታት ጠዋት ጠዋት መዝሙሩ እየሄደ የቡና ዋጋ በአለም ገበያ ምን ያህል እንዳወጣ ይነገር ነበር፤ አሁንም ይሰራበታል፡፡
እውነት ነው ጠዋት ጠዋት ትምህርት ቤት ከመሄዳችን በፊትም መዝሙሩ ይለቀቅ ነበር። በሁሉም ሰው አዕምሮ ውስጥ የታተመ ነው። አዎ! ሰው መዝሙሩን ይሰማው ያውቀው ነበር እንጂ ማን ግጥምና ዜማውን እንደሰራው አያውቅም ነበር፡፡ በኋላ ነው  ሚዲያዎች አነጋግረውኝ በመጠኑም ቢሆን የታወቅሁት፡፡ እንዳልሽው በሁሉም ሰው አዕምሮ ውስጥ ተቀርጾ የተቀመጠው ቡናና ሻይ ባለስልጣን ግን አሁንም ይጠቀምበታል፡፡
ከዚህ መዝሙር የስራው ፈጣሪ እርስዎ አልተጠቀሙም በድምጻቸው ያቀነቀኑት የቀድሞዎቹ ህፃናትስ ምን ጥቅም አገኙ?
እንግዲህ የኔም ዋናው ጥያቄ ይህ ነው፤ የኔ ልጅ፣ የኔ መዝሙር ለረዥም አመት አገልግሏል። ቡናና ሻይ ባለስልጣን፣ ፋና ሬዲዮ ላይ የሬዲዮ ፕሮግራም ስላለው አሁንም መዝሙሩን ይጠቀምበታል፡፡ ግን አንድም ክፍያ የለም፡፡ እርግጥ በዚያ ወቅት ለአብዮቱ ነው የምንሰራው፤ ክፍያም አንጠብቅም፤ ወቅቱም አይፈቅድም ነበር፡፡ አሁንም ቡናና ሻይን የሚያህል ተቋም እስከተጠቀመበት ድረስ ክፍያ ሊከፍል ይገባል። ብታይ ዘመድ፣ ጓደኛ ቤተሰብ እየመጣ “ምን የመሰለ ወርቅ ስራ ሰርተህ አንድ ሽራፊ ጥቅም እንዴት አታገኝም፡፡ ሌላው በፈጠራ ስራው እየጠቀመ አይደለም ወይ?” ይላሉ፡፡ እንዳልኩሽ ያኔ ለአብዮት ለአገር ስለሆነ ባንጠይቅም የሰራሁት ስራ ለአንድ ተቋም እያገለገለ እስካለ ድረስ የፈጠራ መብቴ ተከብሮ ሊከፈለኝ ይገባል። ግጥሙም ዜማዉም የራሴ ፈጠራ ነው። አንዳንዶች ጊዜው ስለረዘመ ግጥምና ዜማው የኔ ነው ሊሉ የሚዳዳቸው አሉ፡፡ ግን ሚዲያውም ህዝቡም እውነቱን ያውቃል፡፡ በወቅቱ ቡናና ሻይ ሚኒስቴር፤ ለዘመሩ 35 ወጣቶች ቡኒ ከለር ያለው ጣቃ ጨርቅ ገዝቶ ሰጠን፡፡ ያንን ጣቃ ጨርቅ  ደግሞ እዚሁ ጅማ የነበሩ ቡና ነጋዴዎችና ሌሎች ሰዎች አዋጥተው በትብብር አሰፉልን፡፡ ከዚያ ውጭ ሌላ ያገኘነው ነገር የለም፡፡ የኪነት ቡድኑም ሆነ የግጥምና ዜማው ደራሲ እኔ ያገኘሁት ጥቅም የለም፡፡
ለመሆኑ ክፍያ እንዲከፈልዎ ለቡናና ሻይ ባለስልጣን ጥያቄ አቅርበው ነበር?
በተደጋጋሚ ጥያቄ አቅርቤ ምላሽ አላገኘሁም። እነርሱም “እሽ የሚሆነውን ነገር እናደርጋለን” እያሉ ጉዳዩን ትተውታል ማለት ይቻላል፡፡ እኔ በአሁኑ ወቅት ጡረታ ወጥቼ በቀበሌ ቤት ውስጥ ነው የምኖረው፡፡ በአሁኑ ወቅት እንደኔ አንጋፋዎቹ ቀርቶ ሌላው ሁሉ ባለቤት ሆኗል፡፡ ይህ ሁሉ የአገልግሎት ዘመኔ የራሴን ቤት እንድሰራ እንኳ አላስቻለኝም፡፡ ጉዳዩ ይህን ይመስላል፡፡ እንግዲህ እናንተም ተጨማሪ ድምጽ ሆናችሁ ጥያቄዬን ለሚመለከው አካል ብታቀርቡልኝ፣ ለልጆቼ እንኳ አንድ ነገር ጥዬ ባልፍ ደስ ይለኛል፡፡ ካልሆነ ከማዘን ውጭ ሌላ ነገር የለም፡፡
አሁን የመዝሙሩን ሙሉ ግጥም ያስታውሳሉ?
አይጠፋኝም እሞክራለሁ፡፡
የኢኮኖሚ ዋልታ ቡና ቡና
የገቢ ምንጫችን ቡና ቡና
የእድገታችን ገንቢ ቡና ቡና
አውታር ነው ቡናችን ቡና ቡና
በዓለም ገበያ የውጭ ምንዛሪን ለሀገር
የሚያስገኘው ቡና ቡና
በጥራት በጣዕሙ በጣሙን ተወድዶ
በጣም የታወቀው ቡና ቡና
ከምርታችን ሁሉ ተፈላጊነቱ እጅጉን
የላቀው ቡና ቡና
የምንመካበት የገቢ ምንጫችን ቡና
ቡና
ግጥሙ ይህን ይመስላል፡፡
ግጥሙን ብቻ ሳይሆን ዜማውን በደንብ ነው የተጫወቱት እንደው እነዚያ 35 የኪነት ቡድን አባላት የት ደረሱ?
እንደነገርኩሽ የኪነት ቡድኑ በወቅቱ ታዳጊ ህጻናት ነበሩ የተመሰረቱት በ1969 ዓ.ም ነው፡፡ እድሜያቸው እያደገ ሲሄድ በየቀበሌው የኪነት ቡድን ነበር፡፡ ይህ የኪነት ቡድን በሶቱም ከፍተኛ ይሁን ሲባል አአወማ የሚባለው የክፍለ ሀገሩ የቀጣት ኪነት ቡድን እነዚህን ወጣቶች ጨምሮ ከሌሎች ወጣት ኪነት ቡድን ጋር በማቀላቀል አንድ ትልቅ ወጣት የኪነት ቡድን ይቋቋም ተባለና እድሚያቸው ለዚያ የደረሱ በአአወማ ስር ተደራጁ፡፡ እኔና አንድ ሌላ አሰልጣኝ አብረን ነበር የምናሰለጥናቸው፡፡ እኔ በዚያን ወቅት ለንቃት ስልጠና በሚል ወደ ሶቭየት ህብረት ሞስኮ ለ10 ወራት ያህል ተልኬ ሄድኩኝ፡፡ አብሮኝ የነበረው አሰልጣኝ ቀሪዎቹን ይዞ ማሰልጠን ቀጥሎ ነበር፡፡
እኔ ተመልሼ ሳልረከበው እርሱም አዲስ አበባ ዝውውር አግኝቶ ጥሏቸው ሄደ፡፡ አሰልጣኝ አጡና ተበታተኑ፡፡ እኔም ስመለስ ወደ መምህርነቴ ተመለስኩ፡፡
አሁን ላይ አባላቱ የት እንዳሉ የሚታወቅ ነገር አለ?
ግብርና ኮሌጅ ውስጥ ስራ ላይ ይገኛል፤ ሌሎችም አሉ፡፡ በጅማ ከተማ ውስጥም አምስት ስድስት የሚሆኑ አይጠፉም፡፡ ሌሎችም እንዲሁ በተለያየ ቦታ እንደየ ዕጣፈንታቸው እየኖሩ ነው፡፡ በቅርቡ እንደሰማሁት ሁለቱ በሞት ተለይተዋል፡፡
መምህርነት ትልቅ የህይወት ልምድ የሚካበትበት ነው፡፡ እርስዎም የካበተ ልምድ አለዎት፡፡ እናም ይህን ትልቅ የህይወት ልምድዎን በመጽሐፍ የማውጣት ሃሳብ የለዎትም?
በጣም ሀሳብ አለኝ፡፡ ሌላው ቀርቶ ከዚህ የኪነት ቡድን ታሪክ አንኳን ራሱን የቻለ መጽሃፍ አይወጣውም ብለሽ ነው? እንዴው መጽሃፍም ባይሆን ልምዴንም በወቅቱ በጅማም ሆነ በመላ ሀገሪቱ የነበረውን የኪነት እንቅስቃሴ ጎላ ጎላ ያሉ ግጥሞችንም የያዘ አንድ መጽሐፍ ብጽፍና ያለኝን ባካፍል ደስ ይለኛል፡፡ ሀሳብና ፍላጎቱ አለኝ፡፡ እንዲሁም የኑሮዬ ሁኔታ አንድ ራሱን የቻለ ነገር ነው። አሁን በብቸኝነት ነው የምኖረው፤ አብሮ መኖር እንዳለ መለያየትም መኖሩ የግድ ስለሆነ፣ ልጆቼም ራሳቸውን ችለው ነው የሚኖሩት። የሆነው ሆኖ ሁሉ ነገር ከተስተካከለ መጽሀፍ የመጻፍ ፍላጎት አለኝ፡፡ አምላክ ፈቃድ ይሁን፡፡
በሦስት መንግስታት የመኖር እድል ገጥሞታልና እርስዎ ነፍስ ካወቁበትና ነገሮችን መገንዘብ ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ የሀገሪቱን የፖለቲካ ህይወትና የህዝቡን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ እንዴት ይገልጹታል?
በጃንሆይ ጊዜ ገና ልጆች ነን፤ በትምህርት ላይ ነበርን፤ ነገር ግን በጥልቀት ባይሆንም ነገሮችን እናውቃለን፤ እንገነዘባለን፡፡ ኃይለስላሴ በጣም ይከበራሉ፡፡ እርሳቸውም ህዝባቸውን ይወድዳሉ፡፡ በወቅቱ ብዙ የተማረ ሰው ስላልነበረ ለትምህርት የሚሰጠው ቦታ የተለየ ነበር፡፡ በየትምህርት ቤቱ እየሄዱ ተማሪዎችን እየጎበኙ ያበረታታሉ፤ ለተማሪዎች ሳሙና ወተትና ለትምህርት የሚያገለግሉ መሳሪያዎችን ይሰጣሉ፡፡ እኛም ያንን እያገኘን ነው ያደግነው፡፡ ያን ጊዜ ለጃንሆይ አዎንታዊ አመለካከት ነው የነበረን፡፡ በደርግ ጊዜ እርግጥ በመጀመሪያው አካባቢ ሶሻሊዝም፣ ህብረተሰባዊነት እኩልነት ብሎ መጣ፡፡ እኛም ገና ወጣቶችና ወደ ስራው አለም አዲስ የገባን በመሆናችን ያንን ለውጥ በመደገፍ፣ ለሀገርና ለህዝብ አዲስ ነገር ይፈጠራል በሚል ጉጉት፣ በየፊናችን እንንሳቀስ ነበር፡፡ እኔ እንኳን በችለታዬ ብዙ የአብዮት መዝሙሮችን ሰርቻለሁ፡፡ ያውም እነ “ቡና ቡና”ን የሚያስንቁ፡፡ ኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቭዥን ውስጥ ቢፈለጉ ይገኛሉ፡፡
‹‹እንሂድ እንሂድ እንሂድ ወደፊት፣ ለአብዮቴ አለብቴ ይፍሰስ ደሜ ይርገፍ አጥንቴ፣ አለ ገና ኧረ አለ ገና…” ስራን፣ ትምህርታችን ጤናንና ኢትዮጵያን›› በሚመለከት የሀገሪቱን ውበትና ተፈጥሮ የሚያደምቁ በርካታ መዝሙሮችን ነው ያበረከትኩት፡፡
ወቅቱ የሚፈቅደው እንዲህ አይነት ርዕሶች ላይ እንጂ ስለ ፍቅር መዝፈን አይፈቅድም ነበር፡፡ ደርግም ኪነትን በሚገባ ተጠቅሟል፡፡ ጂማ ውስጥ ራሱ የኪነት አብዮት ፈንድቶበት ነበር፡፡ በ27ቱ ቀበሌ በሁሉም ውስጥ የኪነት ቡድን ነበር፡፡ ህዝቡ ይቀሰቀስ ነበር፣ ትልቅ ስራ ይሰራ ነበር፣ እና የሀገር ፍቅርና አንድነት የሚሰበክበት ነበር፡፡ በኋላ ስርዓቱ የኃይል እርምጃ በመውሰዱ ያልተገቡ ነገሮች ተፈጠሩ፡፡ በስተመጨረሻ ነገሩ አላማረም፡፡
በአሁኑ ስርዓት ብዙ ልማትና በገሃድ የሚታዩ ለውጦች አሉ፤ ችግሮችም አሉ፡፡ ዶክተር አብይ ከመጣ በኋላ ታሪኩ ሌላ ሆነ፤ የሚገርምሽ ጥልቅ ተሃድሶ ተብሎ ስልጠና ሲሰጥ፣ ዶክተር አብይ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ሆኖ በክረምት መጥቶ አሰልጥኖናል፡፡    
ኒስማኒርም ሆኖ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ቦርድ ሰብሳቢ ነበር፡፡ ጥልቅ ተሃድሶ ለሁለት ቀን ከዶክተር ምህረት ጋር መጥቶ ሲሰጠን ነበረ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ያየነው ይህ ሰው፤ ሀገሪቱን ከጥፋት ታድጓል፡፡ ክፉ እንዳይነካው እንጸልያለን፡፡ በህይወቴ ሀገሪቱ ወደ ትልቅነቷ ተመልሳ ማየት እፈልጋለሁ፡፡ በዶክተር አብይ አመራር ይህ ህልሜ እውን ይሆናል የሚል እምነት አለኝ፡፡

Read 1614 times