Print this page
Saturday, 28 July 2018 15:38

“ፖለቲካ በአዲስ መልክ ጀምረናል”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(9 votes)

  እንዴት ሰነበታችሁሳ! 
ስሙኝማ… መአት ‘ቦተሊካ’ ፓርቲዎች ሊመሰረቱ ህዝቤ ሰብሰብ፣ ሰብሰብ እያለ ምክር ይዟል አሉ። እናማ…በፖለቲካ ፓርቲዎች ብዛት “ከአፍሪካ አንደኛ፣ ከዓለም ሁለተኛ” ምናምን የምንሆንበት ጊዜ ሩቅ አይደለም ማለት ነው። እኔ የምለው…ለምንድነው በመፈንቅለ ፓርቲ ከአፍሪካና ከዓለም ያለንበት ደረጃ የማይነገረን! ልክ ነዋ…“ምናምነኛ ክፍለ ጦር፣ ምናምነኛ ብርጌድ አመጸ” ምናምን ብሎ ነገር ሳይኖር፣ የቢሮ በር ቆልፎ ጥበቃዎቹን… “እነ እንትና ሲመጡ አታስገቧቸው” ማለት ነው፡፡ ወይንም “ፉርሽ ባትሉኝ” ብሎ…ማህተሙን መያዝ ነው፡፡ የምር እኮ… ለስታንድ አፕ ኮሜዲ የሚሆን መአት ነገር አለን እኮ!
ስሙኝማ…በአንድ ወይም በሌላ ጊዜ ያልተተራመሰ ‘ቦተሊካ ፓርቲ’ አለ እንዴ! እንደው እቁብም፣ የግል ሽርክናውም፣ እድሩም ጣጣ የማያጣት አገር! (“የተፎካካሪ ፓርቲዎች ‘አጄንዳ’ ሁሉ ተወሰደባቸው፣ ምን አዲስ አጄንዳ ይዘው ሊመጡ ነው!” የምትሉ ሰዎች አብራሩልንማ!)
እናማ…አዳዲስ የምትቋቋሙት ይሄ “ሊበራል ነን፣” “ሶሻል ምናምን ነን…” የምትሉትን ተዉንና ለየት ብላችሁ ኑልንማ፡፡ አለ አይደል… ለምሳሌ ‘ጸረ-ምቀኝነት አገር አቀፍ ግንባር’ ምናምን የሚል መስርቱልን፡፡ ‘ሊበራሊዝም’ን ‘ሶሻል ምናምኒዝም’ን የመሳሰሉትን ከማብራራት ይልቅ ምቀኝነትን ማብራራት ይቀላል ብለን ነው፤ ቂ…ቂ…ቂ…፡፡ ምቀኝነት አገራችንን እግር ተወርች ካሰሯት ‘እርግማኖች’ አንዱ ነውና፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…የሸሚዝ ኮሌታ አጥቦ መልበስ እንኳን አስቸጋሪ የሚሆንበት ጊዜ አለ፡፡ ይሄን ጊዜ አንዱ ውራጁን ወርውሮለት ይሆናል፤ ኮሌታዋ ጠየም ያለች ጊዜ እኮ አሁን የአንድ ብር ሳሙና ጠፍቶ ነው ሲባል ተከርሟል፤ ያቺው ኮሌታ ፏ ብላ ስትመጣ ግን ከሊበራሊዝም ወደ ኒኦ-ሊበራሊዝም ትሸጋገራለች፡ ቂ…ቂ…ቂ… (የምር ግን ይሄ ነገር ግርም ነው የሚለው…እስካሁን እኮ እነኚህን ነገሮች እንዲገባን አድርጎ ያብራራልን የለም፡፡) ድሮ “እነሱ አምስተኛ ረድፈኞች ናቸው!” የሚባል ነገር ነበር፡፡
‘አምስተኛ ረድፈኛ’ ማለት ምን ይሁን ምን ማንም አያውቅም… ‘የሚታወቀው’ ነገር ቢኖር “አምስተኛ ረድፈኛ” መባል ‘መጠቆር’ና…አለ አይደል… ጸረ—ምናምን መሆኑን ነው፡፡ ዘንድሮ ደግሞ “ይሄ የኒኦ ሊበራሎች ተንኮል ነው፣” ምናምን ሲባል ልክ “የአምስተኛ ረድፈኞች ሴራ ነው” ምናምን ከሚለው ጋር ቢመሳሰልብን ምን ይገርማል፡፡ መንደር ውስጥ ጎረቤታሞቹ ተጣልተው አንዷ…“የማናውቅሽ መሰለሽ፣ አንቺ ኒኦ ሊበራል!” ብትል በኮፒራይት ትጠየቃለች? ወይንም “ምድረ ኪራይ ሰብሳቢ በሌሊት መንገድ ላይ ቆሻሻ እየደፋ በበሽታ ሊጨርሱን እኮ ነው!” ቢባል ምን ክፋት አለው… “ኪራይ ሰብሳቢ” የሚለውን ትክክለኛ ትርጉሙን ልባችን እስኪደርስ ያስረዳን ባይኖርም፣ ያው የሆነ ሰውን ‘ልክ ልኩን’ እንደ መንገር መሆኑ ገብቶናላ!
ታዲያላችሁ ጸረ-ምቀኝነት ቡድኑ “ዓላማችን ምቀኝነትን ከአገራችን ሙሉ ለመሉ ማጥፋት ብቻ ሳይሆን በግሎባላይዜሽን መርህ ከአፍሪካ ብሎም ከዓለም ማጥፋት ነው፣” ምናምን ብሎ በካሜራ ፊት ይንገረን፡፡ (ምንም ሳይኖረን ሁሉ ‘ከአፍሪካ፣’ ‘ከዓለም’ የምንላት ነገር አለች አይደል!) እናማ… ያው ፖለቲካው የእኛው አገር ‘ቦተሊካ’ ስለሆነ በሰባተኛው ወር… “ሊቀመንበሩን እኮ ፈነገሉት…” ምናምን ይባላል፡፡
“ገና ዓመት እንኳን ሳይሆናቸው! ምነው ምን ሆኑ?”
“ስሙ በሚዲያ እየታወቀ ሲሄድ ተመቀኙት!”
እናማ…የአንኮበር ቅጠል ብቻ ሳትሆን የእኛም ነገር ጉድ የሚያሰኝ ነው፡፡ የጸረ-ምቀኝነት ፓርቲው በ‘ምቀኝነት’ የተነሳ ሊታመስ የሚችለው በእኛይቱ አገር ብቻ ሳይሆን አይቀርም፡፡ (በበፊት ጊዜ ውሸት መናገር የሚያበዛ ሰው…“አትቦትልክብኝ” ይባል ነበር፡፡ ምንም ለማለት ሳይሆን ለጠቅላላ እውቀት ያህል ነው፡፡)
የምር ግን ሀሳብ እናቅርብ…የሁሉም ቦተሊካ ቡድኖች መሪዎች ኤግዚብሽን  ማእከል ይሰብሰቡልንና የፖለቲካ ጠቅላላ እውቀት ፈተና ይሰጥልን፡፡ አሀ…“እንትን አዋጅን ደገፉ፣” “እንትን አዋጅን ተቃወሙ፣” የሚል ማናችንም ማለት የምንችለው ነው እኮ! እናማ…በህዝባዊ ዓላማ ፖለቲካ ውስጥ የገባውንና በግላዊ ዓላማ ፖለቲካ ውስጥ የገባውን መለየት አቃተና! የአሜሪካ ቪዛ የተከለከለ አንድ ወዳጃችን … “ይሄኔ አንዱ ፓርቲ ገብቼ አመራር ብሆን ኖሮ አሜሪካን እመላለስባት ነበር…” ሲል ነበር፡፡
‘የጸረ- እብሪት አገር አቀፍ ዴሞክራሲያዊ ቅንጅት’ (በምህጻረ ቃል ‘ዴድ’ እንዲል… የእንግሊዘኛ ትርጉሙን አይደለም!) ይቋቋምልንማ! እብሪት ቁም ስቀላችንን ከሚያሳዩን ችግሮቻችን አንዱ ሆኗል፡፡ ግርም እኮ የሚል ነው…በአንድ በኩል እንደ ቅንጦት አልጋ ሊያገለግል የሚችል ቆዳ ወንበር ላይ ስለተቀመጠ ብቻ፣ በሌላ በኩል የአንድ አነስተኛ አገር ዓመታዊ በጀት መሆን የሚችል ፈራንክ ስላለው ብቻ፣  ደግሞ በሌላ በኩል በአንድ የስልክ ጥሪ ብቻ ‘መኖራችንን እንድንጠላ ማድረግ የሚችሉ ዘመዶች ስላሉ ብቻ…“እኔ ስመጣ እያንዳንድሽ መሬት ተደፍተሽ አሳልፊኝ፣” ሊል የማይቀረው መአት ነው፡፡
እብሪት እዛ ላይ ብቻ ሳይሆን ‘እዚህ ታችም’ ሞልቷል፡፡ (ለዚህም ነው ሰዋችን…“ላይ አካባቢ እየተሞከሩ ያሉ ለውጦች በፍጥነት ወደ ታች ይውረዱ” የሚለው፡፡ ምክንያቱም ከህብረተሰቡ የእለት ተእለት ኑሮ ጋር በቀጥታ የተሳሰረው ክፍል እዛ ታች ያለው ነውና፡፡ (ከቤተ መንግሥት ቤተ ቀበሌ ይቀድምበታልና!)
እናማ… ዓመት ከሁለት ወር ከርሞ ‘ሰበር ዜና’…“የጸረ-እብሪት አገር አቀፍ ዴሞክራሲያዊ ቅንጅት አባላት ሊቀመንበሩና ጸሀፊው እንዲወርዱ እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ተናገሩ፣” ይባላል፡፡ ምክንያቱ ሁለቱ ሰዎች…“በእብሪተኝነት የአባላቱን ሰብአዊ መብት እየጣሱ ነው፣” የሚል ነው፡፡
“ትናንት ዜና ሰማህ?”
“ምኑን? ይሄ ጸረ-እብሪት ነው ምናምን የሚሉት ፓርቲ…”
“ፓርቲ ነው ቡድን?”
“የፈለግኸውን በለው፣ እነሱ ሊቀመንበሩንና ጸሃፊውን ሊያወርዷቸው ነው አሉ”
“ምነው፣ ካዝናውን ገለበጡት እንዴ?”
“እንደሱ ሳይሆን እብሪተኞች ናቸው ተብሎ ነው”
“እና ወዳጄ ከዚህ የበለጠ ኮሜዲ የት ይገኛል። ትሬቨር ኖህ እዚህ ቢመጣ ሁለት ቀን ቆይቶ የአስራ ሁለት ዓመት ግብአት ያገኝ ነበር፡፡” እናላችሁ… የጸረ-እብሪት ስብስቡ በእብሪት የተነሳ ሊፈርስ የሚችልባት ብቸኛዋ አገር የእኛዋ ሳትሆን አትቀርም፡፡ እንዲህ የምንለው…ስናይ ከኖርነው ልምድ ተነስተን ነዋ!
የምር የሆነ ኮሚክ…አለ አይደል…መታበዮች አሉ፡፡ በባዶ ሜዳ ጉራ ነስነስው የሚደሰቱ ሰዎች አይገርሟችሁም! “እኔ ኪስ ያለው ሱሪ አልወድም፣ አድርጌም አላውቅ፣” ሲል የነበረው ሰው “ዋሌቴን ሱሪ ኪሴ ውስጥ ረስቼው ስለመጣሁ መቶ ብር ታበድረኛለህ!” ሲል ቅሽምና ነው፡፡
የብድር ነገር ካነሳን አይቀር ይቺን ስሙኝማ…ሰውየው ጓደኛውን፤ “ተበዳሪ ማለት ምን ማለት ነው?” ይለዋል፡፡ ጓደኝዬውም…
“ተበዳሪ ማለትማ የሰው እዳ ያለበት ማለት ነው” ሲል ይመልስለታል፡፡
“እሺ አበዳሪ ምን ማለት ነው?” ሲል ይጠይቃል።
“አበዳሪ ደግሞ ያበደርኩት ገንዘብ ይመለስልኛል ብሎ የሚያስብ ሞኝ ሰው ነው” ብሎት አረፈ፡፡ አበድሮ አጨብጭቦ የቀረውን ቤቱ ይቁጠረው፡፡
እናማ…አሁን በየቦታው የፖለቲካ ፓርቲ ምስረታ ምክክር እየተደረገ ነው ለሚባለው ሀሳባችን ይደመጥልን፡፡ ድስት ብቻ እየለወጣችሁ አትምጡብን፡፡ ድስቱን አንበላው! ይልቁንም አስሬ ከፍሪጅ እየወጣ የሞቀ ሳይሆን ያልሰለቸን ምግብ አቅርቡልን፡፡ ወይንም በከተማው ሁሉ “ምግብ በአዲስ መልክ ጀምረናል” እንደሚባለው… “ፖለቲካ በአዲስ መልክ ይዘን መጥተናል” ምናምን በሉን። (አሀ… “እነኚህ ደግሞ ምን የሚሏቸው ናቸው! ምንም አዲስ ነገር ሳይኖራቸው… ለምን አሁን ካሉት ጋር አይቀላቀሉም!) ምናምን ማለት የለብንማ!  
የምር ግን አሁን ነገሮች አስበን በማናውቀው መንገድ እየሄዱ ባለበት ሰዓት ትኩረቱ ወደ ላይ ብቻ ሳይሆን ወደ ጎንም መሆን አለበት፡፡ አሀ…ስናንጋጥጥ ጎናችንን ለማን ትተን!  እናማ…ከሁሉም በላይ ደግሞ ‘በፖለቲካ ስም ህዝብ ላይ መቀለድ ይቁም ብሔራዊ ጥምረት’ ምናምን የሚባል ፖለቲካ ፓርቲ ይቋቋምልን፡፡  እንግዲህ በአምስተኛ ወሩ “የፓርቲው መሪዎች ሥራቸውን በትጋት ከመሥራት ይልቅ ቀልድ ስላደረጉት እነሱን ለመተካት ጉባኤ ተጠርቷል” ምናምን መባሉ ባይቀርም…ማምሻም እድሜ ነው፡፡ ‘በህይወት መኖራቸውን’ በየአራት ዓመቱ የሚያሳውቁ ‘ቦተሊካ ፓርቲዎች’ በሽ ያሉባት አገር እኮ ነች!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 7144 times