Saturday, 28 July 2018 15:24

አንጋፋው አሜሪካዊ ዲፕሎማት ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ ሰላም የኖቤል ሽልማት እንዲታጩ ጠየቁ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(10 votes)

 ዶክተር ዐቢይ ለሁለተኛ ጊዜ አለማቀፍ ሽልማት አግኝተዋል

    በ3 ወራት የስልጣን ጊዜያቸው ያስመዘገቡት አስደማሚ ስኬት ከአገር ውስጥ ባሻገር የውጭ መንግስታትን ቀልብ የሳቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ከፍተኛ የሠላም ሽልማት ከዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ መንግስት ያገኙ ሲሆን የአሜሪካው ታዋቂ ዲፕሎማት ኼርማን ኮኸን በበኩላቸው፤ ጠ/ሚኒስትሩ ለታላቁ የሰላም ኖቤል ሽልማት እንዲታጩ ጠይቀዋል፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ ከወር በፊት በኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ላመጡት ፖለቲካዊ መሻሻልና ላሳዩት በሳል አመራር ከኡጋንዳ መንግስት የሃገሪቱን የአርበኝነት ታላቅ ኒሻን መሸለማቸው የሚታወስ ሲሆን ከሠሞኑም በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ለ20 ዓመታት የዘለቀውን ወደ እርቅና ሰላም በመቀየራቸው ከዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ መንግስት የሃገሪቱን ከፍተኛ የሠላም ሜዳሊያ ሽልማት አግኝተዋል፡፡
የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሣያስ አፈወርቂም ከዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ መንግስት ተመሳሳይ የሰላም ሜዳሊያ ሽልማት ተቀብለዋል፡፡
የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሥሪት ጠንቅቀው እንደሚያውቁ የሚነገርላቸውና በ1983 የሽግግር መንግስት ምስረታ ወቅት የአሸማጋይነት ሚና የነበራቸው አሜሪካዊው ዲፕሎማት ኸርማን ኮኸን በበኩላቸው በትዊትር ገፃቸው ባሠፈሩት ማስታወሻ፤ ዶ/ር ዐቢይ ለታላቁ ኖቤል ሽልማት እንዲታጩ አመለክታለሁ ብለዋል፡፡
“በሥራ ዘመኔ ለመጀመሪያ ጊዜ አንድ ሰው ለኖቤል የሰላም ሽልማት እንዲታጭ በይፋ እጠይቃለሁ፤ እሱም የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ነው” ያሉት ኸርማን ኮኸን፤ “በኢትዮጵያ የመድበለ ፓርቲ ስርአት በቀጣይ የሚፈጠር ከሆነ መላው ምስራቅ አፍሪካ ወደ ተሻለ ፖለቲካዊ ሁኔታ መሻገሩ እርግጥ ይሆናል፡፡” ብለዋል፡፡
አንድ ታዋቂ የስዊድን ዲፕሎማትም በተመሳሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ለታላቁ የሠላም የኖቤል ሽልማት እንዲታጩ የሚጠይቅ ቅስቀሣ እያደረጉ መሆኑ ይታወቃል፡፡

Read 9670 times