Saturday, 28 July 2018 15:21

ጠ/ሚኒስትሩ ከ“ግንቦት 7” ሊቀመንበር ፕ/ር ብርሃኑ ጋር ተወያዩ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

  ሌሎች የተቃዋሚ አመራሮችንም ያነጋግራሉ

     ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ዛሬ እና ነገ በአሜሪካ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር ከሚያደርጉት የጋራ ውይይት በተጨማሪ ዋነኛ የተቃዋሚ ድርጅት አመራሮችን እንደሚያነጋግሩ ምንጮች የጠቆሙ ሲሆን ከትናንት በስቲያና ትናንትና ከ “አርበኞች ግንቦት 7” ሊቀ መንበር ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ጋር በዝግ መምከራቸው ታውቋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ጋር የተገናኙት በዋሽንግተን ዲሲ ዋተርጌት ሆቴል ሲሆን የዝግ ስብሠባ ማካሄዳቸውም ታውቋል፡፡
ከትላንት በስቲያ ሃሙስ አሜሪካ የገቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ፤ ምሽት ላይ በአሜሪካ ከሚገኙት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የሲኖዶስ አባላትና ከፓትርያርክ አቡነ መርቆሬዎስ ጋርም ተገናኝተው፣ በቤተክርስቲያኒቱ በተፈፀመው እርቅ ጉዳይ ላይ ተነጋግረዋል፡፡ ትናንት አርብ ደግሞ ዋሽንግተን በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ፅ/ቤት ውስጥ በሠጡት መግለጫ፤ “ኢትዮጵያ የፈረሰች ሃገር ሆናለች፤ አፍሪካ በኛ የተነሣ ተዋርዳለች፤ ኑ እንደገና እንገንባት፤ ከመፍረስ እንታደጋት” ሲሉ ለኢትዮጵያውያን ጥሪ አቅርበዋል፡፡
አክቲቪስቶችና ፖለቲከኞችንም “ድምፃችሁን ስታሠሙ ነበር፤ አሁን እንኳን ደስ አላችሁ ወደ ዲሞክራሲ እየተሸጋገርን ነው” ብለዋል- ጠ/ሚኒስትሩ፡፡ በሎስ አንጀለስ እና በዋሽንግተን ዲሲ በሚኖራቸው ቆይታም ከ25 ሺህ በላይ ከሚሆኑ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር በመሠብሠቢያ አዳራሾች የሚወያዩት ጠ/ሚኒስትሩ፤ በተጨማሪም በዋሽንግተን ዲሲ ከ1500 ያህል የዳያስፖራው ማህበረሠብ ተወካዮች ጋር ሰፋ ያለ ውይይት ያደርጋሉ ተብሏል፡፡ የኦሮሞ ተወላጆች በስፋት ወደ ሚገኙባት ሚኒሶታም በመሻገር ከክልሉ ተወላጆች ጋር የሚመክሩ ሲሆን በዚህ መድረክ ላይም የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሣ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡
 “ግንቡን እናፍርስ ድልድዩን እንገንባ” በሚል መሪ ቃል፤ ዛሬ ሐምሌ 21 ቀን በዋሽንግተን ዲሲ እንዲሁም ነገ ሐምሌ 22 በሎስ አንጀለስ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዳያስፖራ ኢትዮጵያውያን ጋር ውይይት እንደሚያካሂዱ የተገለፀ ሲሆን ቆይታቸውም እስከ ሐምሌ 24 ቀን 2010 ዓ.ም ይሆናል ተብሏል፡፡
በአሜሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ለሚያደርጉት ውይይት ከኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር ጥምረት በመፍጠር ሠፊ ዝግጅት ሲያደርጉ የሠነበቱ ሲሆን ለዶ/ር ዐቢይ ከፍተኛ አቀባበል እንዳደረጉላቸውም ለማወቅ ተችሏል፡፡ ብዙዎች በጉጉት ሲጠብቁት በቆዩት በዚህ የጠ/ሚኒስትሩና የኢትዮጵያውያን የውይይት ፕሮግራም ኢትዮጵያውያን ደስታቸውን ለመግለፅ ነፃ የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡

Read 3347 times