Tuesday, 24 July 2018 00:00

ትዊተር በ2 ወራት 70 ሚሊዮን ተጠቃሚዎችን አባርሯል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ጎግል የ5 ቢሊዮን ዶላር ቅጣት ተጣለበት


    ታዋቂው የማህበራዊ ድረገጽ ትዊተር በግንቦትና በሰኔ ወር ብቻ ህገወጥ ድርጊት የሚፈጽሙና የተጭበረበሩ ያላቸውን የ70 ሚሊዮን ያህል ተጠቃሚዎቹን አካውንቶች በመዝጋት አገልግሎቱን እንዳያገኙ ማድረጉን ዋሽንግተን ፖስት ዘግቧል፡፡
የተጭበረበሩና ህገወጥ ድርጊቶችን በሚፈጽሙ ተጠቃሚዎቹ ላይ የሚያደርገውን ቁጥጥርና የሚወስዳቸውን እርምጃዎች እያጠናከረ የመጣው ትዊተር፤ የተጠቃሚዎቹን ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ የመቀነስ እርምጃው ገቢውንና ትርፋማነቱን አደጋ ውስጥ እንዳይከተው መሰጋቱን ዘገባው አመልክቷል፡፡
እ.ኤ.አ በ2016 ከተካሄደው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ቅስቀሳ ጋር በተያያዘ ተጠቃሚዎች ያልተገባ ድርጊት መፈጸማቸውን ተከትሎ  የተጭበረበሩ አካውንቶችን በመጠቀም የተሳሳቱ መረጃዎችንና አደገኛ መልዕክቶችን በሚያሰራጩ ተጠቃሚዎች ላይ የሚወስደውን እርምጃ ያጠበቀው ትዊተር፤ ባለፈው የፈረንጆች አመት 2017 የመጨረሻዎቹ አራት ወራት ጊዜ ውስጥ ብቻ የ58 ሚሊዮን ተጠቃሚዎቹን አካውንቶች መዝጋቱን የዘገበው ደግሞ አሶሼትድ ፕሬስ ነው፡፡
በተያያዘ ዜናም፣ የአውሮፓ ህብረት የንግድ ውድድርንና የሞባይል ተጠቃሚ ደንበኞችን ምርጫ የሚገድብ ህገወጥ ድርጊት ፈጽሟል በሚል ባለፈው ረቡዕ በታዋቂው የአሜሪካ ኩባንያ ጎግል ላይ ክብረወሰን የተመዘገበበትን የ5 ቢሊዮን ዶላር ቅጣት ማስተላለፉ ተዘግቧል፡፡
ጎግል የራሱ ምርት የሆነውን አንድሮይድ ኦፐሬቲንግ ሲስተም የሚጠቀሙ የሞባይል ስልኮችን የሚያመርቱ ኩባንያዎችን፣ የራሱ ምርት የሆኑ ሌሎች የፍለጋ አፕሊኬሽኖችን ኢንስቶል እንዲያደርጉ አስገድዷል በሚል ከአውሮፓ ህብረት የተላለፈበትን የገንዘብ ቅጣት ውሳኔ እንደማይቀበልና ይግባኝ እንደሚጠይቅ አስታውሷል፡፡
የአውሮፓ ህብረት ከሶስት አመታት ምርመራ በኋላ በጎግል ላይ ያስተላለፈው ይህ የገንዘብ ቅጣት፣ በታሪኩ ከንግድ ውድድር ህጎች ጥሰት ጋር በተያያዘ በአንድ ኩባንያ ላይ የጣለው ከፍተኛው ገንዘብ እንደሆነም አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡

Read 7230 times