Print this page
Monday, 23 July 2018 00:00

በ50 የዓለማችን አገራት የኤችአይቪ ስርጭት ጨምሯል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 በ50 የተለያዩ የዓለማችን አገራት የኤችአይቪ ኤድስ ስርጭት እየጨመረ መምጣቱንና በቫይረሱ እየተጠቁ ካሉት ሰዎች ግማሽ ያህሉ የመድሃኒትና የህክምና አገልግሎቶችን እያገኙ እንዳልሆነ ዩኤንኤድስ የተባለው አለማቀፍ ተቋም ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል፡፡
የኤችአይቪ ቫይረስን ስርጭት ለመግታት በአለማቀፍ ደረጃ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት እየተዳከሙ መሆናቸውን የጠቆመው የተቋሙ ሪፖርት፤ በ50 ያህል የአለማችን አገራት የቫይረሱ ስርጭት ጭማሪ ማሳየቱም ለጉዳዩ የሚሰጠው ትኩረት አናሳ እየሆነ መምጣቱን እንደሚያመላክት ገልጧል፡፡
የቫይረሱ ስርጭት በአንዳንድ አገራት ጥሩ በሚባል ሁኔታ መቀነስ ማሳየቱን የጠቆመው ዘገባው፤ በአለማችን በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ የቀነሰው ከዚህ በፊት በቫይረሱ ክፉኛ በተጠቁት የምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ አገራት ሲሆን፣ ለዚህ መሻሻል በምክንያትነት የጠቀሰውም የህብረተሰቡ ግንዛቤ በጥሩ ሁኔታ ማደጉና አብዛኞቹ የቫይረሱ ተጠቂዎች የኤችአይቪ ህክምና በአግባቡ ማግኘታቸው መሆኑን አስረድቷል፡፡
በምዕራብና በመካከላዊ አፍሪካ አገራት የኤችአይቪ ህክምና አገልግሎት ማግኘት የሚገባቸው በርካታ ዜጎች የአገልግሎቶች ተጠቃሚ አይደሉም ያለው ሪፖርቱ፤ በአገራቱ 75 በመቶ ህጻናት እና 60 በመቶ አዋቂዎች የሚገባቸውን የኤችአይቪ ህክምና እንዳላገኙም ጠቁሟል፡፡   
በአሁኑ ወቅት በመላው አለም በኤችአይቪ ቫይረስ የተጠቁ 37 ሚሊዮን ያህል ሰዎች መኖራቸውን የዘገበው ቢቢሲ በበኩሉ፣ በአለማችን የተለያዩ አገራት በየአመቱ አንድ ሚሊዮን ያህል ሰዎች በቫይረሱ ሳቢያ ለህልፈተ ህይወት እንደሚዳረጉም አመልክቷል፡፡

Read 2414 times
Administrator

Latest from Administrator