Saturday, 21 July 2018 13:14

የ“አዲስ ሚዩዚክ አዋርድ” እጩዎች ይፋ ሆኑ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(5 votes)

 የዘጠነኛው ዙር “አዲስ ሚዩዚክ አዋርድ” ተወዳዳሪ እጩዎች ይፋ መሆናቸውን አዘጋጆቹ ገለፁ፡፡ አዲስ ሚዩዚክ አዋርድ ላለፉት 8 ዓመታት በስምንት የውድድር  ዘርፎች የተመረጡ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችን ሲሸልም የቆየ ሲሆን ዘንድሮም ለ9ኛ ጊዜ ሽልማቱን ለማካሄድ ከፍተኛ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን የሽልማት ድርጅቱ ረቡዕ ዕለት ቦሌ በሚገኘው ሽራር አዲስ ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል፡፡
ዘንድሮ የዓመቱ ምርጥ አልበም፣ ምርጥ ነጠላ ዜማ፣ ምርጥ አዲስ ድምፃዊ፣ ምርጥ የሙዚቃ ቪዲዮ፣ የዓመቱ ምርጥ አቀናባሪ፣ ምርጥ ፊልም፣ ምርጥ ተዋናይና ተዋናይት እንዲሁም በአዘጋጁ የሚመረጥ ምርጥ የኪነ-ጥበብ ባለውለታ በሚሉ የሽልማት ዘርፎች ውድድሩ እንደሚካሄድ ተገልጿል፡፡ በአሁኑ ሰዓት የየዘርፉ ተወዳዳሪዎች፣ ሰው እንዲመርጣቸው ራሳቸውን የሚያስተዋውቁበት ኮድ የተሰጣቸው መሆኑም ተጠቁሟል፡፡ ከ40 ቀናት በኋላ የዘርፉ ምርጥ አምስቶች ይፋ የሚደረጉ ሲሆን ጳጉሜ 1 ቀን 2010 የሽልማት ሥነ ስርዓቱ እንደሚካሄድና የእንቁጣጣሽ ዕለት በፋና ቴሌቪዥን ለእይታ እንደሚበቃ የአዲስ ሚዩዚክ አዋርድ መስራችና ባለቤት ይግረም ስንታየሁ (ዲጄ ቤቢ) በመግለጫው ላይ ተናግሯል፡፡
አሸናፊዎችና ምርጥ አምስት ውስጥ የገቡት ተወዳዳሪዎች ጳጉሜ 3 ቀን 2010 ቢሾፍቱ ፒራሚድ ሪዞርት የምሳ ግብዣ እንደሚደረግላቸው፣ የኪነ ጥበብ ባለውለታው የገንዘብ ሽልማት እንደሚሰጠውና በምርጥ አዲስ ድምፃዊነት የሚያሸንፈው ለአልበም ማሳተሚያ 15ሺ ነፃ የሲዲ ሽልማት እንደሚያገኝ የገለፀው ዲጄ ቤቢ፤ አድማጭ ተመልካቾች የሚፈልጓቸውን ምርጦች ለመምረጥ www.addismusic.net በመግባት በተሰጣቸው ኮድ ድምፅ መስጠት እንደሚችሉ አስታውቋል፡፡

Read 3112 times