Saturday, 21 July 2018 13:05

ወንዶችና የጡት ካንሰር…

Written by 
Rate this item
(2 votes)

  ….አንድ ስራ ልቀጠር አስቤ በቅድሚያ የጤና ምርመራ ማቅረብ ስለነበረብኝ ወደ ሕክምና ባለሙያ ዘንድ ቀረብኩ። እሱም …የሚሻለው ወደ ግል ሐኪምህ ሄደህ ብትታይ ጥሩ ነው …አለኝ፡፡ ወደሁዋላ መለስ ብዬ ሳስበው…ላለፉት ሁለት አመታት አንድ ችግር ገጥሞኝ ነበር፡፡ በሰውነቴ ላይ በተለይም በጡቴ አካባቢ አንድ ትክክል ያልሆነ ተፈጥሮአዊ ቅርጽ ማየት ጀመርኩ፡፡ ለካስ የጡት ካንሰር የሚባል በሽታ ቀስ በቀስ እየተስፋፋ ኖሮአል፡፡ እኔ የነበረኝን ስሜት ችላ ብዬ ነበር የቆየሁት። አሁን ግን ሕይወቴ አደጋ ላይ ነው፡፡
አንድ ምክር አለኝ፡፡ እባካችሁ ማንኛችሁም ብትሆኑ ትንሽ ነገር ነው ብላችሁ ችላ አትበሉ፡፡ ምንም አዲስ ነገር ቢሰማችሁ በፍጥነት ወደባለሙያዎች በመቅረብ ምንነቱን ተረዱ፡፡
ጽሁፉን ያገኘንበት ምንጭ ያሰፈረው የግለሰብ ታሪክ ነው፡፡
የጡትን ተፈጥሮ ስንመለከት ወንዶችም ሴቶችም ከተፈጥሮ የሰውነት አካላቸው መካከል ጡት የሚባል ነገር መኖሩ እሙን ነው፡፡ የሴቶች ጡት በተፈጥሮአቸው ባላቸው ሆርሞን ሳቢያ እንዲያድግና የተለያዩ ተፈጥሮአዊ ግዴታዎችን እንዲወጣ የሚያስችል ይሆናል፡፡ የወንዶች ጡት ግን በደረት ላይ ተፈጥሮውን ለማመላከት ያህል ይታያል እንጂ ወደየትም የማያድግ እና ምንም የተለየ አገልግሎት ማለትም ለልጆች እንደወተት መስጠት የመሳሰሉትን ግዴታዎች እንዲወጣ የማይጠበቅ ነው። በእርግጥ ሴቶች ጡታቸው ወተት የሚያመርተው ከእርግዝና ጋር በተያያዘ በሚኖር ተፈጥሮአዊ ሂደት ነው፡፡
የጡት ካንሰር ለወንዶች አልፎ አልፎ የሚከሰት ሕመም እንጂ እንደሴቶቹ በስፋት የሚስ ተዋል አይደለም። ምናልባትም ከሚከሰቱት የጡት ካንሰር ሕመሞች ከ1% በታች የሚሆነው በወንዶች ላይ የሚከሰት ይሆናል፡፡ ወንዶች በሕይወት ዘመናቸው በጡት ካንሰር ሕመም የሚ ጠቁት ከ1000/ከአንድ ሺህዎቹ አንድ ሰው ቢሆን ነው፡፡ ይሄ ሲታይ ምናልባትም ወንዶች የጡት ካንሰር ሕመም አይይዛቸውም ለማለት ሊያስደፍር ይችል ይሆናል፡፡ ነገር ግን እውነታው በመጠኑም ቢሆን ወንዶች ጡታቸውን ሊታመሙ ይችላሉ፡፡
ወንዶች የጡት ካንሰር ይዞአቸዋል የሚያሰኙ አንዳንድ ምልክቶች አሉ፡፡
በጡት ላይ የመጠጠር ወይንም የማበጥ ምልክት ይታያል፡፡ በእርግጥ ካልነኩት በስተቀር ሕመም ላይሰማ ይችላል፡፡
የጡት መደደር መኖሩ የማይታወቅ እና በራሱ ጊዜ በጡት ውስጥ ወዲያ ወዲህ የማይንቀሳቀስ ነው፡፡
የጡት ጫፍ አቅጣጫ ጠመም የማለት ነገር ሊታይበት ይችላል፡፡
ከጡት ጫፍ ፈሳሽ የመውጣት ነገር ይስተዋላል፡፡አንዳዴም የደም ምልክት ሊታይበት ይችላል፡፡
በጡት ጫፍ ዙሪያ ምቾት የማይሰጥ የህመም ስሜት ሊኖር ይችላል፡፡
የጡት ጫፍ ወይም በዚያ አካባቢ ባለው ቆዳ ላይ የመቅላት የመደደር ወይንም የማበጥ ሁኔታ ይስተዋላል፡፡
ወንዶች ብዙ ጊዜ ይህ ህመም ይደርስብኛል ብሎ ካለማሰብ ነገሩን ችላ የማለት ነገር ይስተዋ ልባቸዋል። በእርግጥ ሁኔታው እንደሴቶቹ በተስፋፋ መልኩ የሚያጋጥም ባይሆንም እንደችግር ግን መስተዋሉ አይቀርም፡፡  
ለጡት ካንሰር ወንዶች ሊጋለጡ የሚችሉባቸው የተለያዩ ምክንያቶች አሉ፡፡
እድሜ፤ ይህ በምክንያትነት ከሚጠቀሱት ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው ነው፡፡ ልክ ሴቶች   በእድሜ ምክንያት ለጡት ካንሰር እንደሚጋለጡት ሁሉ ወንዶችም ይጋለጣሉ። ወንዶች በእድ ሜያቸው ወደ 68/አመት ሲሆናቸው ለጡት ካንሰር የመጋለጥ እድል ሊያጋጥማቸው ይችላል፡፡ ከፍተኛ የኢስትሮጂን መጠን፤ በጡት አካባቢ ያሉ ሴሎች እድገት በትክክለኛውም ወይንም ትክክል ባልሆነው መንገድ የሚከሰት ሲሆን ኢስትሮጂን እንዲኖር ያደርጋል፡፡ ወንዶች በከፍተኛ ደረጃ ይህ ኢስትሮጂን ሊያጋጥማቸው የሚችለው፤ የሆርሞን መድሀኒቶችን ከመውሰድ፤ ከልክ ያለፈ ክብደት ሲኖር፤ እና የኢስትሮጂን መመረትን የሚጨምር ሲሆን ነው፡፡
በአኑዋኑዋር ምክንያት ለኢስትሮጂን መጋለጥ ፤ የአልኮሆል መጠጦች ሱሰኛ መሆን፤ እና በዚህም የተነሳ ጉበት በደም ውስጥ ሊኖር የሚገባውን ኢስትሮጂን መመጠን ሲያቅተው፤ የጉበት በሽታ ሲኖር እና በዚህም ሳቢያ አንድሮጂን(የወን ዶችን ሆርሞን) ዝቅ ሲያደርገው እንዲሁም ኢስትሮጂንን ማለትም (የሴቶችን ሆርሞን )ከፍ ሲያደርገው ችግሩ ሊከሰት ይችላል፡፡:
ከቤተሰብ ጋር በተያያዘ ፤ ይህ የጡት ካንሰር ሕመም የነበረና ያለ ሲሆን በዘር ሊተላለፍ ይችላል፡፡
ለጨረር የመጋለጥ ሁኔታ ፤አንድ ወንድ በደረቱ አካባቢ በጨረር ሕክምና ከተረዳ ምናልባትም በዚያ ሳቢያ የጡት ካንሰር ሊይዘው ይችላል፡፡  
ከላይ የተጠቀሱትና ሌሎችም ለጡት ካንሰር ለመጋለጥ በተለይም ለወንዶች ምክንያት ይሆናሉ ተብለው ተጠቅሰዋል፡፡ የጡት ካንሰር ከምን ደረጃ ላይ ይገኛል የሚለውን ለመለየት የህክምና ባለሙያዎች እንደሚከተለው አስቀምጠዋቸዋል፡፡
ደረጃ 0፤ የጡት ካንሰሩ ምርመራ ሲደረግ በ0/ደረጃ ላይ ያለ ከሆነ የካንሰር ሴሉ ወደሌላ ሰውነት ሊሰራጭ ከማይችልበት ደረጃ ላይ ይገኛል ማለት ነው፡፡
ደረጃ 1፤ በደረጃ አንድ ላይ የሚገኝ የካንሰር ሴል በጊዜው የህክምና እርዳታ ካልተደረገለት ወደሌላ ሰውነት ሊሰራጭ እንደሚችል አመላካች ነው፡፡
ደረጃ 2፤ የካንሰር ሴሉ በደረጃ ሁለት ላይ ከተገኝ ትናንሽ የካንሰር ሴሎች በቡድን ወደአጎራባች የሰውነት ክፍሎች የተሰራጨ መሆኑን እና በእርግጥ ወደ ቲዩመር/ወይንም ወደዋናው የካንሰር መገለጫ እንዳላደጉ ወይም ደግሞ ከ2/ሴንቲ ሜትር በላይ ያላደገ ቲዩመር መኖሩን ይናገራል፡፡ በዚሁ በደረጃ ሁለት ቀጣዩ ነገር ወደሌሎች የሰውነት ክፍሎች ሊሰራጭ የሚችል የካንሰር ሴል መኖሩን እና እርዝመቱም ከ2-5 ሴንቲሜትር የሚገመት መሆኑን እንዲሁም ወደሌላ የሰውነት ክፍል መተላለፍ አለመተላለፉን በሚመለከት እርግጠኛውን ለመናገር የማያ ስችል ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ እስከ 2/ሴንቲሜትር የሚደርስ ቲዩመር ወደሌላ የሰውነት ክፍል ተላልፎ ሊገኝ ይችላል፡፡ የካንሰሩ ደረጃ በዚህ መልክ እድገቱን እየጨመረ የመስፋፋት አቅሙ ንም እያጠናከረ እስከ 5/አምስተኛ ደረጃ ድረስ ይቀጥላል፡፡ በደረጃ አራት ላይ የሚታየው  የጡት ካንሰሩ ወደሌላ የሰውነት ክፍል ተሰራጭቶ  ለከፍተኛ ሕመም የሚዳርግበትና በሕክምናም ለማዳን አስቸጋሪ የሚሆንበት ደረጃ ሲሆን ደረጃ 5/አምስት ደግሞ የመጨረሻው ክፍል ነው፡፡
        ምንጭ፡- Breast Cancer.com
የጡት ካንሰር መከላከያ ዋና መፍትሄ የሚባለው የህክምና ክትትል ማድረግ ነው ያሉን ዶ/ር መብራቱ ጀምበር የጽንስና ማህጸን ሕክምና ባለሙያ ናቸው፡፡ ዶ/ር ከዚህም በተጨማሪ የገለጹት እራስን መመርመር እንዴት ይቻላል የሚለውን ነው፡፡ ካንሰሩ መኖር አለመኖሩን ለመለየት ራስን በራስ መመርመር  ጠቃሚ ነው፡፡ ሰውነትን ሙሉ በሙሉ ወይም ግማሽ አካልን በሚያሳይ መስታወት ፊት ለፊት ቆሞ ሁለት እጅን ከሁዋላ ማጅራት ላይ በማስቀመጥ ጡት ወደፊት እንዲፈጥ በማድረግ የጡት ቆዳ ለስለስ ያለ ወይንም የተጨማደደ ነገር እንዳለበትና እንደሌለበት ማየት አንዱ ዘዴ ነው፡፡ ጡት በተፈጥሮው አፍንጫው አካባቢ ጠቆር ያለ ነው። ከተለመደው ውጪ የተለየ ጥቁረት ወይም የነጣ የገረጣ ለማሳከክም የሚጋብዝ ነገር ካለ ቶሎ  ማየት ያስፈልጋል። እንደገናም ጡትን በሃሳብ አራት ቦታ በመክፈል አራቱን ቦታዎች በጣት በመዳሰስ እጢ ወይም እብጠት.. የጓጐለ ነገር መኖር አለመኖሩን ማረጋገጥ ይገባል፡፡ ሌላው እራስን የመመርመሪያ ዘዴ ደግሞ ገላን በሚታጠቡበት ጊዜ ገላን ሳሙና ከቀቡ በሁዋላ ሲዳሰስ በበለጠ ተፈጥሮአዊ ያልሆኑ ነገሮችን ለማግኘት ያስችላል ፡፡ የጡትን አካባቢ ብቻ ፈትሾ ማቆም ደግሞ በቂ አይደለም ፡፡ወደብብትም ገብቶ በመዳሰስ እብጠት መኖር አለመኖሩን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡

Read 2320 times