Saturday, 21 July 2018 13:02

“ንፋስ ያነሳው ጥላ” - የግብዝነታችን ወረንጦ!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(1 Vote)

 በየዓመቱ ከሚታተሙ የግጥም መጻሕፍት ውስጥ ጥቂቱ፣ እጅግ ጥቂቱ የዘውጉን መስፈርት አሟልተው፣ የጥበቡን ውበት ይዘው ብቅ ይላሉ፡፡ ሙሉ ለሙሉ ምሉዕነት ተጎናፅፈዋል ባይባልም በቋንቋ ገለፃ፣ በሃሳብና በምት፣ ወዘተ አንዱ ከአንዱ ይለያያሉ፡፡ በልዩነታቸው ውስጥ ያለው ምትሀትና ሙዚቃ፣ የሃሳብ ጡዘትና ትዕይንት በየፈርጁ፣ ሊማርኩን ይችላሉ፡፡
እንደ ተርታው አንባቢ፣ በመጀመሪያ ንባብ የምንስማማባቸው የራሳችን ምርጦች ቢኖሩም መሰላል ዘርግተን ወደ መመዘኛዎቹ ስንሄድ የምንሰጠው አስተያየት ይለያያል፡፡ ግጥም የሁሉም፣ በሁሉም ደረጃ የሚነበብና የሚዳኝ ስለሆነ፣ ሰው ለራሱ፣ የራሱንም መምረጥ መብት አለው፡፡ ውበትና ቅርፅ የሚያዩ እንዳሉ ሁሉ፣ የሀሳቡን ስብከት ብቻ የሚያደምጡ (message hunters) ጥቂት አይደሉም፡፡
ወዲህ መለስ ስንል ግን ለምርጫ የተወሰኑ አላባውያንን ማየት ግድ ይለናል፡፡ በተለይ ማዕከላዊ ሀሳቡን ለማጎልበት ከግራና ከቀኝ ገጣሚው የሚጠቀማቸውን ስልቶችና ሌሎች ፈርጦች፡፡  
ዛሬ የገጣሚ ብርሃነሥላሴ ከበደ፤  “ንፋስ ያነሳው ጥላ” የግጥም መድበልን ይዤው ብቅ ያልኩትም፣ ከአላባውያኑ የተወሰኑትን ተጠቅሞ፣ በሀሳብና በቅርፅ የተሻለ ቀለም አለው ብዬ ስላመንኩ ነው፡፡ ምናልባትም ይህ ወጣት ገጣሚ ይበልጥ ካነበበና የሕይወት ልምዱን መልዕክቶች ካደመጠ፣ የተሻለና ሀገር የሚያጣፍጥ ሰው ይወጣዋል ብዬ በመገመትም ነው፡፡
እስቲ ከሰሞነኛ ሀሳቦቻችን ጋር የምትጣጣመውን ግጥም አጥቅሼ ልጀምር፡-
“ለ‘ኛ”
መቻቻል ትርጉሙ፡-
አበው ሲተርቱ
“ከአጋም የተጠጋ ቁልቋል..”
እንደሚሉ፣
ሰርክ እየተናጩ
እየተቋሰሉ፣
ተዛዝሎ መኖር ነው
ሳይነጣጠሉ፡፡
የሚያምም ነገር ነው፡፡ አጋም አጠገብ ያለ ቁልቋል ሁሌ እንዳለቀሰ ነው፡፡ እንደተነጨ፣ ነጭ ደም እንደደማ ነው፡፡ ግን “አብሮ መኖር አይታክተውም” የሚል ሀሳብ ያንጸባርቃል፡፡ ወደ መሬት ስናወርደው፤ አንዱ ብቻ ሁሌ አልቃሽ ከሆነ ግፍ ስለሚሆን አብሮ መዝለቁ ከባድ ነው፡፡ ግን ቦታ እየተለዋወጡ፣ አንዱ አንዱን እየታገሰ ከኖረ መልዕክቱ ጥሩ ነው፡፡ ንቡር ጠቃሽ ዘይቤ ተጠቅሞ፣ “ከአጋም የተጠጋ ቁልቋል” የሚለውን አባባል ማምጣቱ የግጥሙን ኃይል ከፍ ያደርገዋል፡፡
ለሁለቱ ተክሎች አጥር ማበጀት አይቻልም፤ አይጠቅምም፣ አያድንም፤ ፍቅር ግን ሊያስተዛዝላቸው አቅም አያጣም፡፡
ገጣሚው ሁለንተናዊነት ላይ ያተኮሩ ግጥሞችም አሉት፡፡ ለመላው የሰው ልጆች ልዕልና የሚሞግቱ፣ ሥዕሉን የሚያስቀምጡ፣ በሂስ የሚሸነቁጡ፣ የሰብዕናን ልክ፣ የክብርን መለኪያ፣ የማንነትን ቁመና ሊያሳዩ የተደረደሩ ስንኞች በጌጥ ተቀምጠዋል፡-
“በነጋዴው ዓለም”
ሸቀጥ ዋጋው ንሮ
ከላይ መቀመጡ፣
የሰውነት ተመን
እያደር መዝቀጡ፣
በገበያ ሕግነት
ይኖራል ያለ እክል፣
ሰው የራሱን ዋጋ
እስከሚያስተካክል፡፡
ይህ ግጥም መላውን የሰው ልጅ ያቀፈ ነው፡፡ በተለይ በዚህ ዘመን፤ ገንዘብና ሀብት ዘውድ ደፍቶ፣ የሰው ልጅ ማቅ ለብሶ፣ ዐመድ ነስንሶ እያለቀሰና እያላዘነ ሊኖር የተገደደበት ደረጃ ደርሷል፡፡ የመኪና አደጋ ሲደርስ እንኳ “ሰው ተረፈ?” ከማለት ይልቅ ውዱን ዕቃ መትረፉን የምንጠይቅበት ደረጃ ላይ ደርሰናል፡፡
ግና የዚህ ሁሉ ምንጭ፣ የጥበብ ሁሉ ምንጭ ራሱ ሰው ነው፡፡ በራሱ እምነት ከፈጣሪ አገኘሁ ይበልም አይበልም፣ መሳሪያው ግን ራሱ ሰው ነው፡፡ ይሁንና ዋጋው ዘቅጧል፡፡ ገጣሚው ይህንን ሀሳብ ነው በሙዚቃ ጣዕም፣ በቃላትና ፍቺ አበልፅጎ፣ ለአንባቢው እርካታን ለማምጣት የፃፈው፡፡ የሙግቱን ጡንቻ፣ የሰቀቀኑን ዜማና ትኩሳት ሊያወርሰን አቅም ፈጥሮ መጥቷል፡፡
የገጣሚው ጭብጦች፤ ታሪክን ትውልድንና ማኅበራዊ ህይወትን ያጣቀሱ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ከጥቅሉ የሰው ልጅ አጥር ወጣ ብሎ ሀገራዊ የታሪክ እርሻዎቻችንና ፍሬያቸውን እየጎበኘ፣ ከታሪክ ድርሳናት መነሻ ዛሬ የቆምንበትን መሬትና ሀቅ ያሳያል። የነገም አድማስ ወለል ብሎ እንዲታየን መቆሚያ ቦታ ሰጥቶናል፡፡ “ቅብብል” የምትለው ግጥሙ፣ ያለፍናቸውን መቆሚያ ቦታ ሰጥቶናል፡፡  ያለፍናቸውን ዘመናት ፎቶግራፎች ከፊታችን አምጥታ ታቆማለች፡፡ ዐይኖቻችንን ከፍተን እንድናይ፡-
ከባዕድ ሰማይ ስር
ጉም እንደጨለፈ፣
የነሌኒን ምርኮ  
ያ ትውልድ አለፈ፡፡
አወይ ምስኪን ቧጋች
ሕልሙን የተቀማ፣
ራዕይ መሳይ ቅዠት
ደጋግሞ እየሰማ፤
መልስ አልባ ጥያቄ
ከንቱ እየጠየቀ፣
ይኼኛውም ያልፋል
ከራሱ እንደራቀ፡፡
ይህ ትርክት ዛሬ እንደ ጎርፍ በፈሰሱት መጽሐፍት የተነበበ ሀቅ ነው፡፡ ከባዕድ ምድር የመጣው የሶሻሊስት ርዕዮተ ዓለም አምልኮ፣ የዚህን ትውልድ ልብ ነጥቀው፣ ደሙን እንዲሰጥ፣ በፍቅር አክንፈውት እንደነበር ሁሉም በየራሱ ማዕዘን ፅፎታል፡፡ የራሱ ህልም የበቀለበት ምድር ራዕዩን ሙሉ ለሙሉ አስቀምጦ፣ ሲባትት፣ ሲመኝና ሲፋለም ባክኖ የቀረ ትውልድ አለ፡፡ የዚያ ትውልድ ጥያቄ ደግሞ በዛሬው ትውልድ ላይ የወደቀ ጥላ ሆኖ፣ ወደ ኋላ እያየ፣ ወደፊት ማየትና መራመድ  ሲሳነው፣ ራሱን ሳያይ፣ እርሱም በሀገሩ ሰዎች ህልም ውስጥ ሰምጦ ይቀራል እያለን ነው፡፡
እውነትም አልባነንንም ይሆን? ብለን ውስጣችንን መበርበር፣ ራሳችንን መፈለግና ጀንበራችን ሳትጠልቅ ከህልማችን ጋር መግጠም የኛ ፈንታ ነው፡፡ ገጣሚው ግን እንደ ጣፋጭ ሽሮፕ መድኃኒቱን ሰጥቶናል። እየጣፈጠ ሊፈውሰን፡፡ ከዚሁ ሀሳብ ጋር የተያያዘ የዘመናችንን ሥዕል ያሳየበት ግጥም አለ፡፡
“ውጭና ውስጣችን”
በየቤተ እምነቱ ያሞቅነው እልልታ፣
በየኳሱ ሜዳ ያቀለጥነው ሆታ፤
በየመሥሪያ ቤቱ የካድሬ ስብሰባ፣
በስሜት ተውጠን ያሞቅን ጭብጨባ፣
ወደየቤታችን አብሮን ስላልገባ፣
በደስታ ናፍቆት ጎጇችን ኮሰሰ፣
ውጭና ውስጣችን እንደተለያየ፣
ወደምንም ጅረት ዕድሜያችን ፈሰሰ፡፡
“እምነት” ብለን የያዝነው የውሸትና የግብዝነት ሜዳ ነው፡፡ በየኳሱ ሜዳ፣ የጨፈርነው የውስጥ ጩኸታችንን ለመሸሽ ነው፡፡ በየካድሬው ስብሰባ እጃችን እስኪቃጠል ያጨበጨብነው ልባችን ሞቆት አይደለም፤ ውስጣችን በርዶታል፤ ስለዚህ ቤታችን ስንገባ እንደሚንሿሿ ፀናፅል ነን፡፡ ባዶ ሙዚቃ፣ ኦና ቃላት! … ልብ የማይነካ ቃል!
በግብዝነት እየኖርን ስለሆነ እግራችን መሬት አልረገጠም፡፡ የነገ አቅጣጫችንን አናውቅም፤ ንፋስ እያንገላታን ነው፡፡ ስለዚህ ዕድሜያችን ውስጥ ምንም ፋይዳ ያለው ነገር አልተቀመጠም፡፡ ለታሪክ ኮረጆ ያቀበልነው ነገር የለም፡፡ ዝም ብለን ያለ አቅጣጫ ፈስሰናል፡፡ በጥቅሉ የግብዝነታችንን ኪሳራ ተንትኖ አሳይቶናል፡፡ እንደ ሀገር በየትኛውም በኩል አልተሳካልንም፡፡
ራሳችንን ዋሽተን፣ ራሳችንን ከራሳችን ውስጥ አጥተነዋል፡፡ ጩኸታችን ግን ከአድማስ ያስተጋባል። የመጽሐፍ ቅዱሱ መሊ ልጆች ልክ እንደ ጨዋ ካህን የእግዚአብሔርን ታቦት ይዘው እንደተዋረዱት፣ በውሸታችን ዕድሜያችንን ገድለናል! ሕይወታችን ሳይሆን ሞታችን እያለቀሰ ነው፡፡ እንባችንን- ቃላችንን- ቀድሟል!!
ገጣሚው ብርሃነሥላሴ ከበደ፤ ብዙ ግጥሞቹ ማኅበራዊ ሂስ ናቸው፡፡ አፍረን ወይም እንዳናፍር፣ በየኮረጆዋችን ደብቀን በግብዝነት የተውናቸውን ሀቆች ፈንቅሎ እያወጣ ከደጃችን ደርድሯቸዋል፡፡ ብንወድ ልንቀበለው፣ ባንወድ የውስጣችንን ሀፍረት ቅመን ባደባባይ ያንኑ ሻሽ የመሰለ ንጣታችንን አጣፍተን፣ ዕድፍ ጉድፋችንን መልሰን ሳጥን ልንቆልፍበት እንችላለን፡፡ ሕሊናችን ግን ያላምጠው ዘንድ አጣፍጦ አስቀምጦታል፡፡
“ለምዶበት”ን እንያት፡-
የስጋ አምሮት ያዋለለው
በተሰጠው ያልጠገበ፣
የሰው ዳቦ ሰረቀና
ሊበላ ሲል አማተበ፡፡
አያዎን ተመልክተን፣ የራሳችንን ገፆች ሥናነብብ፣ ሳቃችን ይሁን እንባችን ማፈትለኩ አይቀርም- እንደየ ትርጓሜያችን፡፡ “ንፋስ ያነሳው ጥላ” የተሰኘው መጽሐፍ አዳዲስና የተለዩ አተያዮችን ይዟል፡፡ ጣዕም ባለው ዜማ፣ በጥሩ አሰነኛኘት፣ አንባቢን የሚማርኩ ግጥሞችን አካትቷል፡፡ ችግሮቹ ብዙ አይደሉም፡፡ አልፎ አልፎ የተለመዱ ነገሮችን በተለመደ መንገድ አቅርቧል። እንደ “መጽሐፍና ሰው” እንደ”ማንዴላ” ዐይነቶች፡፡
በተረፈ፣ ወጣቱ ገጣሚ፣ በተለይ አተያዩና አሰነኛኘቱ ሸጋ ነው፡፡ የኖርንበትን ሕይወት አሳይቶናል፡፡ “The meaning of a poem is the experience which it expresses nothingless” እንዲል የስነ ግጥም ፕሮፌሰሩ፡፡ ይሁንና የመጽሐፉ ሽፋን የግጥሙን ውበት የሚያዩ አንባቢዎችን እንደሚገፋበት እገምታለሁ፡፡ ጥንቃቄ የጎደለው፣ ወይም የገጣሚው ስዕል የማጣጣም አቅም ያነሰ ይመስለኛል፡፡

Read 1368 times