Saturday, 21 July 2018 13:00

የታክሲ ጥበቃ ወግ!

Written by  አብይ ተስፋዬ አሳልፍ - (አተአ)
Rate this item
(9 votes)

ድብደባው ቢከብድም፣ ስቃይ ቢኖረውም - ምቾት
ባይኖር እንኳ
መከፈቱ አይቀርም፣  ጠብቆ የተንኳኳ!
***
ከጓደኞቼ ጋር ቀጠሮ ስለነበረኝ ከስራ በጊዜ ወጣሁ። ያነገትኩትን ቦርሳ እንደ ካንጋሮ የልጆች ማዘያ ከፊት ለፊቴ ደግኜ የተለመደውንና የማይቀረውን የታክሲ ግፊያ ተቀላቀልኩ ፡፡
የምነሳው ከቦሌ ነው፡፡ (ቦሌ፣ ደምበል፣ እስጢፋኖስ፣ አምባሳደር፣ ጥቁር አንበሳ እሄድና ቴዎድሮስ አደባባይን ከፍ ስል እወርዳለሁ!) እናም የቶሞካን ቡና እየጠጣሁ፣ የቢኒያምን ስልክ እጠብቃለሁ፡፡ ስለዚህ ቀድሜ ለመድረስ ግፊያውን መቀላቀል ግድ ነው፡፡
የእኔ ብቸኛው ችግር ይህ ነው፡፡ ታክሲ ግፊያ መጋፋት አልችልም፡፡ የሆነ ታክሲ መጥቶ ሮጬ ከሄድኩ በኋላ ለመጋፋት አይቻለኝም፡፡ ለምን እንደሆነ ባላውቅም መጨረሻ ላይ ቦታ ኖሮ ካልተሳፈርኩ በቀር ሰው ገፍቼ መግባት አይሳካልኝም፡፡ አብዛኛው ጊዜዬን የማሳልፈው ወደ መጣው ታክሲ ሁሉ በመሮጥና ሳይሳፈሩ በመመለስ ነው፡፡
(ነገር ሳላምጥና የራሴን የታክሲ ፍለጋ ሩጫ ሳስተውለው፣ የኢትዮጵያን ህዝብና የመንግስት አቀባበል ይመስለኛል፡፡ ወደ መጣው መሮጥ፤  የጓጉለትን ሳያገኙ መመለስ፤ ደግሞ በመረጋጋትና በተስፋ ከእንደገና መሞከር፡፡ በየመሃሉ ደግሞ መረጋገጥ፣ መድማት፣  መቁስል፣ ማጣት፡፡ ሃሳቤን ለራሴ እያምሰለሰልኩ ፈገግ ብዬ ወደ ሌላው ታክሲ በተስፋ እሮጣለሁ፣ እሞክራለሁ፡፡)
ከፊት ለፊቴ ድንገት አንዱ ታክሲ፤ በጀት ፍጥነት እየበረረ ሲመጣ፣ አየውና ገና የጫነውን ህዝብ ሳያወርድ ረዳቱን በልመና መልክ እጠይቀዋለሁ፡፡ ‹‹አባቱ የት ነው!›› (ለስሙኮ የሚሄድበትን አቅጣጫ የያዘ ምልክት (ታፔላ) ከላይ ተሸክሞ ይነበባል፤ ሆኖም በዚያ መስመር ስለመሄዱ እርግጠኛ ስለማንሆን ለመጠየቅ እንገደዳለን፡፡ እንለምናለን፡፡)
ሆኖም ጭራሽ አይሰማኝም! እንዳልሰማ ወደ ስራው ይቀጥላል! ረዳቱ የታክሲውን በር እየደበደበ ቶሎ ቶሎ እንዲወርዱ ይጠይቃል፡፡ ህዝቡ ከኋላዬ ደርሶ እንደ ጎርፍ ሳይወድቅብኝ በፊት ቶሎ ለመሳፈር በጥድፊያና በድጋሚ በሚያሳዝን ድምፅ እጠይቀዋለሁ፤ ‹‹…አባቱ የት ነው! ››
(መብታችንንና ከፍለን የምናገኘውን አገልግሎት እንደምንለምን የሚገባኝ ያን ጊዜ ቢሆንም መጨቃጨቁን እጠላዋለሁና ሌላ እጠብቃለሁ እንጂ አልጮህም፣ በርትቼ መብቴን እለምናለሁ፡፡ ‹ኧረ ስለ ባለ ኮከቡ ባንዲራ!› ወዴት ነው እላለሁ!)
በድጋሚና ተስፋ ባለመቁረጥ ለሦስተኛ ጊዜ ‹‹አባቱ የት ነህ!…››
ሳተኩርበት፣ አይኑ እንደ ዶቃ የተድቦሎቦለ መሆኑን ለመጀመሪያ ጊዜ አስተውላለሁ፣ መርቅኖ የእስስት አይን የተተከለለት መስሏል፡፡ እርሱ ግን በሩን እየደበደበና ጫቱን እያላመጠ … ‹‹…አይሄድም፣ አይሄድም…›› ይለኛል፡፡ መለስ ብሎ ደግሞ ወደ ውስጥ አንገቱን አስግጎ ‹‹ቶሎ ቶሎ ውረዱ…›› ይላቸዋል፡፡ ሰዎች ለመውረድ ይዋከባሉ፡፡ አጎንብሰውና ተቀጣጥለው፣ መቀመጫቸውንና ግንባራቸውን አገጣጥመው ሹልክ እያሉ ይወርዳሉ፡፡
(‹ምነው ስልጣን እንዲህ በሆነ› እላለሁ፤ ቦርሳዬን ታቅፌ ቀጠሮዬን እያሰብኩ፡፡ (ይህ ሀሳብ ካነበብኩት ማስታወሻ የመጣ ነው!) ‹ምነው እነዚህ ፖለቲከኞች ወደ ስልጣን ሲንጦለጦሉ አይጭንም በተባሉ፤ ሞልቷል አይሔድም በተባሉ፡፡ ደግሞ ስልጣኑ ላይ የተጫኑቱ፣ ውረዱ ደርሳችኋል ሲባሉ ተቃጣጥለው ዱብ ዱብ ቢሉ ምናለበት!›)
ትንሽ እንደቆዬ በአካባቢው የሞላው ታክሲና ተሽከርካሪ አልባ ጠባቂ ሁላ የቆመችውን ብቸኛ ታክሲ ዙሪያዋን ይከባታል፡፡ ረዳቱም የታክሲውን በር በኩራት ተደግፎና መድረሻውን አሳጥሮ መጥራት ይጀምራል፡፡
‹‹…ሸዋ ዳቦ … ሸዋ ዳቦ …… ሸዋ ዳቦ …›› ይላል፡፡ እኔ በንዴት ጨጓራዬ ቅጥል ይላል፡፡ (ይድፋህ አቦ!)
አንዱ የተናደደ ጮክ ብሎ እንዲህ ይለዋል፤ ‹‹ ታፔላህ የሚያወራው ሌላ፣ አንተ ሸዋ ዳቦ ትላለህ! ምን ታደርጉ ጠገባችሁ!››
‹‹…መንገድ ዝግ ነው አባቱ! መንገዱን እኔ አልዘጋሁት፣ በየት ልሔድልህ ነው! … ሸዋ ዳቦ … ሸዋ ዳቦ … ከቻልክ መንገዱን አስከፍትልንና እንጭናለን፡፡››
*‹ምናባቴ ላድርግ!› ስል አስባለሁ፡፡ ደግሞ ወደ ሌላው ታክሲ እሮጣለሁ፡፡ ሌሎች ምስኪን ህዝቦች ከኋላዬ የእግራቸውን ዳና እንደ ፈጥኖ ደራሽ ሰልፈኛ እየተመተሙ ሲከተሉኝ ይሰማኛል፡፡ ቢሆንም ቀድሞ ለመድረስ ጥቂት ሩጫ አክልበታለሁ፡፡ እናም እንደ ጀት ሲበር የነበረ ሌላ ታክሲ አጠገቤ ሲጢጥ! … አደርጎ ሲቆም መሳፈሩን እተወውና ወደ ኋላዬ እሸሻለሁ፡፡ እነዚህ ባለታክሲዎች እኛን እንደ ሰውም አይቆጥሩንም ስል አስባለሁ፡፡ በተለይ ሰው በሚበዛበት በዚህ አይነት ሰዓት ይጨክኑብናል፡፡ እኔ ሳፈገፍግ ሌሎች እንደ ወታደር ለነፍሳቸው የማይሳሱ የሚመስሉቱ ግን በአንድ ጊዜ እንደ ንብ ይወሩታል፡፡ እናም በሰከንድ ልዩነት በግፊያ ይንጡት ይጀምራሉ፡፡ (አዲዎስ! የአዲስ አበባ ታክሲዎች ‹ፈጣን ነው ባቡሩ!› እያሉ የሚዘምሩ ይመስለኛል፡፡ ቆራጦች ካልሆኑ ሌሎች ፈሪዎችና አቅመ ደካሞች አይሳፈሩምና!)
ረዳቱ ግን በልበ ሙሉነትና በድል አድራጊነት ብቅ ይልና ፀጉሩን እየቆጣጠረ፡፡
‹‹…ሸዋ ዳቦ … ሸዋ ዳቦ …… ሸዋ ዳቦ…›› ( ራቅ ብዬ ቆሜ በንዴትና በፈገግታ መሃል ሆኜ … ‹ጨጨባ!› የሚል ቃል አልጎመጉማለሁ፡፡)
በመሃል እግሬ ሲዝል፣ ተስፋ እቆርጥና ከግርግሩ ወጥቼ የሆነ ነገር ተደግፌ እቆምና በሩቁ መታዘብ እጀምራለሁ፡፡ አቤት ሰው ግን እንዴት ነው አቅሉን ስቶ የሚሯሯጠው! የሚገርመኝ ነገር ግን ሁሉም ሰው የሚያድረው ቤቱ ገብቶ መሆኑ ነው! (ስልጣንም እንዲሁ ነው ስል አስባለሁ(የተሰረቀ ሀሳብ!)፣ ወራጆች በስቃይና በትግል ከወረዱ በኋላ ወጪዎች አጥብቀው ይሻማሉ። ይናጠቃሉ፣ ይጫረሳሉ ፣ ደም ይቃባሉ፣ ይደባደባሉ። ነገር ግን ቦታው ውሱን ነው! የሚገቡበትም ጥቂቶች ናቸው፡፡)
*ሌላ ታክሲ …
ሌላ ታክሲ …
ሌላ ታክሲ …
ይመጣል ይሄዳል፣  ይቆማል ያራግፋል፣ ጥቂቶች ይወርዳሉ፤  ጥቂቶች ይሳፈራሉ፡፡ ሁሉም በየአቅጣጫው ይነጉዳል፡፡ አቅመ ደካሞችና የሰለቻቸው ወደ ኋላ ይቀራሉ፡፡ ካሰቡበት ሳይደርሱ ስልቹዎች ይደክማሉ፡፡
ከእንደገና የማይቀረውን ጉዞዬን ሳስብ ተመልሼ በተስፋ ወደ ህዝቡ እቀላቀላለሁ፡፡ ቦርሳዬን ታቅፌ እንደቆምኩ፣ እንደ እድል ሌላው ታክሲ መጥቶ በአጋጣሚ ከአጠገቤ ቆመ፡፡ ገና ዘልዬ ሳልገባ በፊት ብዙሃኑ ግርር ብለው መጥተው እንዳለ ጥርቅም አድርገው ሲሞሉት ስባሪ ሰከንድ አልፈጅም፡፡ የት እንደሚሔድ እንኳ ሳይናገር በፊት ሞልቷል፡፡ በሃዘኔታ ረዳቱን እጠይቀዋለሁ (ቁጭቴን ለመቀስቀስ ይመስል)፤
‹‹…ወንድሜ የት ነው!››
‹‹…ሞልቷል!››
‹‹አይ ለማወቅ ያህል ነበር፡፡››
‹‹…ሞልቷል አልኩህኮ፡፡ ዛሬ ደግሞ ሰው ሁሉ ምነው ሬዲዮ ሆነብኝ፡፡ ማውራት ብቻ የሚሰማ የለም። የሞላ ብነግርህ ምን ይጠቅምሃል!…›› ወደ ታክሲው ገባ ብሎ ደግሞ ለተሳፋሪዎች እንዲህ ይላል … ‹‹…‹ሁሉም ሰው ፒያሳ ነው አይደል፣ በአቋራጭ ነው የምሔደው፡፡ መንገድ ላይ ወራጅ ምናምን አልጭንም። ሰምታችኋል።›… ››
(ጠጋ ብዬ በተስፋ ወደ ውስጥ አስተውላለሁ፡፡ ምናልባት መንገድ ወራጅ ነኝ የሚል ቦታ ቢለቅ ብዬ ነበር፡፡ ሆኖም ሁሉም ወንበሩን ከያዘ በኋላ የመጣው ይምጣ ብሎ ሙጭጭ ይላል፡፡ ሲያናድድ፡፡ ቦታ አይለቀቅም፣ ወንበር አይነጠቅም፡፡)
እናም ይነጉዳል፡፡ (እኔስ መጠየቁ ምን ይሰራልኛል፣ እርሱስ ቀጥታ ቢመልስልኝ ምን ይጎድልበታል! እያልኩ እያሰብኩ እቆማለሁ፡፡ ሰው ግን ትዕግስት የለውም ወይም ቀናነት ትቷል፡፡ አሁን ያንን ሁሉ ከሚዘላብድ እዚህ ነኝ ቢለኝ ምን ይጎዳዋል! ኤጭ እኔ ራሴ ነኝ እንጂ!…)
እንደ እጣ ፈንታና እንደ የግል ድርሻዬ የመጣችው ይህቺ ታክሲ አልፋኝ ስትሔድ ከማየት ውጪ ምንም ማድረግ አልቻልኩም፡፡ በታክሲው መስኮት ወደ ውስጥ ስቀላውጥ፣ ወጠምሾች ብቻ ሳይሆኑ ወጣት ሴቶችና አንዳንድ ጎልማሶችንም አስተውላለሁ፡፡ (እናም በቅናትና በመገረም አይኔን ጎልጉዬ አፈጣለሁ።) በመስኮቱ አጠገብ የተቀመጠች ጉብልም በፈገግታና አይኖቿን በማስለምለም ቃኘት አድርጋኝ፣ የጆሮ ማዳመጫዋን ትሰካለች፡፡ እኔ ግን እዚያው እንደ ሃውልት ቆሜ ነገሮች ይፈጥናሉ፣ ወደ መድረሻቸው … ወደ ጉዳያቸው … ወደ ቀጠሯቸው ይነጉዳሉ፡፡
እናም የቀጠሮዬ ሰዓት ትዝ ሲለኝ የእጅ ሰዓቴን አውጥቼ አስተውላለሁ … 12.20 …. ኡ! … በመገረም እሞላለሁ፡፡ ምን አይነት ቀን ነው ዛሬ ደግሞ፡፡ ሌላው አማራጭ ወደ ኋላ አንድ ታክሲ ያህል መመለስ፤ ከዚያ እዚህ ድረስ መሳፈርና ዞሮ አንድ ላይ መሄድ ነው። እርሱም ሰዓት ሲኖር አይደል፤ ጥድፊያው የሽንት ፊኛዬን ያላላዋል፡፡ ሽንቴ የመጣ ይመስለኛል፣ አማራጭ የለኝም፡፡ በተስፋ ትንሽ እጠብቃለሁ፡፡ ምናልባት ሰው ቀነስ ሊያደርግ ይችላል፡፡ (…አንዳንዴ ወደ ኋላ መመለስ መፍትሔ እንደሚሆን እገምታለሁ!)
*ቀጠሮ ማርፈድ በጣም ቢያስጠላኝም አማራጭ የለኝም፤ በምቾት ውስጥ ሆኜ አይደለምና ምን ማድረግ እችላለሁ! ሰው እየተባረረ ሲባንን፣ እኔ በህልም አለም ውስጥ ሆኜ ብዙዎች ነጉደዋል! እኔ በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ሆኜ ብዙዎች ወደ ትግሉ ገብተዋል እናም ብዙዎች ቀጠሮ ቦታቸው ደርሰዋል፡፡ ብዙዎች ትካራቸውን ፈፅመዋል፡፡ እኔ ግን መሃል ሰፋሪ ሆኜአለሁ፡፡
‹‹…የት ነህ በያ!…›› ትንሽዬ ልጅ አጠገቤ መጥቶ ይጠይቀኛል፡፡  ሰው ሁሉ ተሳፍሮ ያለቀ ይመስል ጭር እያለ ነበር፡፡ የት ነበርኩ! ደንግጬ ሰከንዶች ፈጀሁ፡፡ እ … አዎ!
‹‹….ፒያሳ...›› አልኩት እንደ መባነን፤
‹‹…ግባ፡፡ ፒያሳ በአቋራጭ! … ፒያሳ … ፒያሳ….›› እያለ መጣራት ጀመረ፡፡ ውልቅልቅ ወዳለችው ታክሲ ስገባ የቀራት ቦታ ከኋላ ወንበር ላይ ነበር፡፡ ከሁለት ዳሌ ሰፋፊ ሴቶች መሃል እንደ መርፌ ተሰክቼ ተቀረቀርኩ፡፡ እናም በልቤ ‹በመጨረሻም!› አልኩ፡፡
የእጅ ሰዓቴን ሳየው ደነገጥኩ … 12.45 … ጂሰስ! (እንዴት ግን ሳይደውሉልኝ ቀሩ!…) ወደ ኪሴ ለመግባት ስላልተቻለኝ ሂሳብ መክፈል አልቻልኩም። ግን ደውዬ መናገር ይኖርብኛል፡፡
ስልኬን ፍለጋ ከሁለቱ ሰዎች መሃል ተፋትጌ በሁለት ጣቶቼ ወደ ኪሴ ዘለቅሁ! ደነገጥኩ! ደግሞ ሌላ ኪሴ ገባሁ፤ ደግሞ ሸሚዝ ኪሴ ፣ ደግሞ ሌላ ኪሴ፣ ደግሞ በድጋሚ ሁሉም ኪሶቼን አሰስኩ፤ ስልኬ በዚያ አልነበረም፡፡ በእርግጠኝነት ከቢሮ ይዤው ወጥቼ ነበር፡፡
ኤጭ! እንዲያው ምን ይሻለናል፡፡ (እርጉም! ትውልድ! ሆነኮ!) ሰው ወደ ትካሩ ሲሯሯጥ፣ ወደ ኪስ ዘው ማለት ለመደብን! ቢሆንም ባይሆንም ታክሲው እኔን ጭኖ ወደ መድረሻው እየበረረ ነበር! መድረሻዬ ላይ የማገኘውን ሰው እንዴት እንደማገኘው ባላውቅም፣ እኔ እንደተከዝኩ ታክሲው መብረሩን አላቆመም፡፡
እናም ተስፋ በመቁረጥና በድካም ታክሲው ውስጥ እንደተወዘፍኩ በእጄ የያዝኳትን ማስታወሻ ማንበብ ጀመርኩ፡፡ መፅሃፏ … (የታክሲ ተገልጋይ ቀላል ምክሮች፤ በአለቃ ድረሴ ወ እንጦጦ፣ ደራሽ ማተሚያ ቤት፤ 1985) የምትል ናት፡፡
የተገልጋይ ምክሮች!
ብዙ ጊዜ ታክሲ ማለት እንደ ታዳጊ ሃገርና እንደ ሃገሪቱ ፖለቲካ ማለት ነው ብለን ተሟግተን ነበር፡፡ ስትጠቀም እነዚህን አስታውስ፤ እንዲሁም አስተውል፡፡
ታክሲ ከተሳፈርክበት ለመውረድ ትቸኩላለህ፣ ካልተሳፈርክበት ደግሞ ልትወጣበት ትሰለፋለህ።
አሽከርካሪ ማለት የሃገሪቱ መሪ፣ ረዳት ማለት ካድሬ ናቸው፡፡ ካድሬው ሁሌም ኪስህን እንድትዳብስ ይጠይቅሃል፡፡  እናም መቀበል እንጂ መመለስ አይወድም፡፡ አሽከርካሪው ብዙ ጊዜ ተገላምጦ ነዎሪዎቹን አይቃኝም፡፡
ተሳፋሪዎቹ ጉልበተኛ፣  ኮሳሳ ወይ ደግሞ ዝምተኛና ለፍላፊ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ሞጭላፎችም ይኖራሉና ተጠንቀቅ፡፡
ታክሲዋ ሰዎችን መርጣ አትጭንም፡፡  መርጣም አትጥልም፤ ሃገርም እንዲሁ ናት፡፡ ሆኖም ከቆራጦች ጋር ብቻ ትራመዳለች፡፡
አሽከርካሪ ወንበሩ ላይ አንዳንዶች ያለ ህጋዊ መንጃ ፈቃድ (ያለ በቂ እውቀትና ልምድ፤ በትውውቅና በዘመድ ፣ በእድልና በድፍረት… ወይም በሌላ ምክንያት ይቀመጣሉ፡፡) እናማ የሆነ ሰዓት አደጋ አይቀሬ ነው፡፡ እልቂትና ጉዳት ይከሰታል! ስለዚህ አጢን፡፡
ታክሲዋን አሮጌም ትሁን አዲስ ውስጧን ለማጊያጌያጥና ለማሳመር ይሞከራል፡፡ በስድብና በወቀሳ፣ ወይም … አንዳንዶች ደግሞ በመንፈሳዊ ትምህርትና በተስፋ ይሞላሉ፡፡ የታዳጊ ሀገር ነዋሪዎችም እንዲሁ ናቸው፣ እምነትና ተስፋ ብቻ ያኖራቸዋል፡፡
መበላሸትና መቆም ፣ መጠገንና መንቀሳቀስ፣  መንገጫገጭና ፍሬን መያዝ ይከሰታል፡፡ በዚህ ሁሉ ወቅት ተሳፋሪ ሊሳቀቅና ሊጉላላ ይችላል፡፡
ታክሲዋ ምን ጊዜም አትሞላም፡፡ ነዋሪዎቿም ነገሮችን መመጠን አይሆንላቸውም፤ ካልተገደዱ በቀር ቆጥበው መቀመጥና መተዛዘን አይወዱም።
እያንዳንዱ ወንበርም ስልጣን ነው ብለን ነበር። መውጣትና መውረድ ያለ ነው፡፡ ወንበሩ ሲለቀቅና ሲያዝ ግፊያና ትርምስ፣ ዘረፋና ነጠቃ ሁሌም መታየቱ አይቀርም፡፡ በመሃል ፈዛዛ ከሆንክ ስትወዛገብ ልትነጠቅ ትችላለህ፡፡
ተሳፋሪ ከሆንክ ፈጠን ብለህ መራመድ ይጠብቅብሃል፡፡ ፈጥነህ መሳፈር ልመድ፣ አለበለዚያ እግርህን ተማመን፡፡
ወዘተ …
እነዚህን እያነበብኩ ሲመሻሽ ከመድረሻዬ ብደርስም የማገኛቸውን ሰዎች ለማየት አልታደልኩም ነበር፡፡ አገርና ታክሲን የሚያነጻጽረው ጭንቅላቴም ለሰከንድ እረፍት አላገኘም፡፡

Read 2681 times