Saturday, 21 July 2018 12:52

ሸረሪት ያደራበት የመንግሥት አጀንዳ

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(4 votes)

እራሱን፣ ደጃዝማቹን፤ ግራዝማቹን፤ ጭቃ ሹሙን፤ አቶውን ሳይቀር ነቅሎ፣ ባለባትነትን ገድሎ፣ ባላባታዊ ሥርዓት አጥፍቶ መንግሥት ባላባት ከሆነ፣ በመሬት ጉዳይ ፈላጭ ቆራጭ፣ ሁሉ በእጄ ሁሉ በደጄ ካለ አርባ ሶስት አመት ሆነ፡፡
የከተማ ቦታንና ትርፍ ቤትን የመንግሥት ያደረገው አዋጅ 47/67 ከታወጀ፣ መንግሥት ባልሠራው ቤት፣ ባልገነባው ግቢ የቤት ባለቤት ሆኖ፣ የቤት አከራይነት ሥልጣን ከተቀዳጀ መጪው ሐምሌ 19 ድፍን አርባ ሶስት አመቱ፡፡
መሬት በግል ባለቤትነት መያዝ፣ መሸጥ መለወጥ አለበት ሲባል፣ የእጅ ጣቶቹን አንድ ሁለት እያለ እየቆጠረ “መሬት ማለት የፓርላማ ወንበር ነው፤ ድምፅ ነው፤ በግል አይያዝም” የሚል መንግሥት ከተተከለም ሃያ ሰባት አመት አለፈ፡፡
ደርግ የመቀሌ ከተማን ለቆ ሲወጣ፣ ከተማውን ተቆጣጥሮ ጠቅላይ ግዛቱን ማስተዳደር የጀመረው ሕወሓት፤ ደርግ የወረሰውን ቤት ለባለ ቤቶቹ መለሰ፡፡ እሱ እና ኢሕአዴግ መሐል አገር ከመግባታቸው በፊት ወሬው በመላ አገሪቱ ተናኘ፡፡
የሕወሓት ሠራዊት ከአልውኃ ማዶ ያለ አገር እኔን አይመለከተኝም በማለቱ፣ አመራሩና ሠራዊቱ አንድ አመት ቆመው መከሩ፡፡ ጠቅላላው ኢትዮጵያ “ነፃ ካልወጣ” የትግራይ ነፃነት ዋጋ የለውም ተብሎ ተደመደመ፡፡
ሕወሓት ኢሕአዴግ በተከታታይ ባደረገው ውጊያ ከወልድያ ጀምሮ ደብረ ታቦርን፣ ጎንደርን፣ ባህርዳርን  ደሴን፣ ነቀምትን ወዘተ እየያዘ አዲስ አበባ ደረሰ፡፡ ግንቦት 20 ቀን 1983 አዲስ አበባን ተቆጣጠረ፡፡ የደርግ መንግሥት ወርዶ (ወድቆ) የኢሕአዴግ መንግሥት ወጣ ወይም ተመሠረተ፡፡ በሁሉም አቅጣጫ ኢሕአዴግ ስልጣን ዘረጋ፡፡
በዚያን ወቅት ሕወሓት ማለት ኢሕአዴግ፣ ኢሕዴግ ማለት ሕወሓት መሆኑን የተገነዘበው ሕዝብ፤ ሕወሐት ትግራይ ውስጥ እንዳደረገው ሁሉ በደርግ የተወረሰበት ቤቱ እንደሚመለስለት ወይም ካሣ እንዲከፈለው ጠየቀ፡፡ የሌላውን አካባቢ አላስታውስም፡፡ በተለይ አዲስ አበባዎች ሠላማዊ ሰልፍ ውጥተው የአዲስ አበባን መንገዶች አጥለቅልቀውም ነበር፡፡ ኮሚቴ አቋቁመው፣ ሽቅብ ቁልቁል ተሯሩጠውም ነበር፡፡ ያስገኙት ውጤት ግን አልነበረውም፡፡ እነሱ ወ/ሮ እንቶኔ እና አቶ አንቶኔ ስለሆኑ በመንግሥት ፊት ዋጋ አልነበራቸውም፡፡ ቦታ የሚሰጣቸውም አልነበሩም፤ ስለዚህም ድምፃቸው አቤቱታቸው እንደ ጉም ተኖ እንዲጠፋ ሆነ፡፡ ይህም ከሆነ ሃያ ሰባት አመት ሞላው፡፡
ሕግ ሁለት ሰዎችን እውቅና ይሰጣል፡፡ ለተፈጥሮ ሰውና በሕግ እውቅና ለተሰጠው ድርጅት፡፡ ሁለቱም ሀብት የማፍራት፣ የመክሰስ የመከሰስ መብት አላቸው፡፡ መንግሥት ከተፈጥሮ ሰዎች ይልቅ በሕግ እውቅና ለተሰጣቸው የህግ ሰውነት ለአላቸው ይጨነቃል፡፡ የኢትዮጵያ አርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን፣ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳይ ጽ/ ቤት፣ የኢትዮጵያ ወንጌላዊ መካነ ኢየሱስ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ወዘተ ሁሉም የሕግ ሰውነት ያላቸው ተቋሞች ናቸው፡፡ በቢሮነት ከያዙት በስተቀር ትርፍ የነበሩ ቤቶቻቸውና ሕንፃዎቻቸው የተወረሱት እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በአዋጅ ቁጥር 47/1967 መሠረት ነው፡፡ እነሱ የፖለቲካ ጥቅም ስለሚሰጡ፣ ከጀርባቸው ያለውን ሕዝብ ለአንድ አይነት አገልግሎት ማሰለፍ ስለሚችሉ፣ በአዋጁ የተወረሰ ንብረታቸው በቀላጤ ሊመለስላቸው ችሏል፡፡ ሕዝብ ግን ሕዝብ ስለሆነ መንግሥት ደግሞ ሕዝብን ስለማይፈራና ስለማያከብር እንደተወረሰ ቀረ፡፡ ንግድ ምክር ቤቱ ለአራተኛ የአብዮት በአል ኤግዚቢሽን ማሳያ በማለት በትውስት የሰጠው የአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል፤ ከአዋጁ ውጪ ተወርሶበት መቅረቱ፣ በገዛ ንብረቱም ዛሬም ኪራይ እየከፈለ እንደሚገለገል መጠቀስ ይኖርበታል፡፡
ግን ግን የውርስ ጉዳይ ዛሬም በመንግሥትና በሕዝብ መካከል መተማመን ያጠፋ ሥራ መሆኑ በአፅንኦት፣ በድርብ መስመር ተሰምሮበት ሊታወስ የሚገባው ጉዳይ መሆኑን ማሳወቅ እወዳለሁ፡፡ ጠቅላይ ሚነስትር ዐቢይም በአንድ ንግግራቸው ይህን ስጋት ጠቀስ አድርገውታል፡፡ ምን ያህሉ ባለ ሀብት ከዚህ ሥጋት ነፃ ነው? ተብሎ ቢጠየቅና ቢጠናም ለነገዋ ኢትዮጵያ መልካምነት የሚበጅ ነገር ያመጣል ብዬ አምናለሁ፡፡
ወደያዝነው ከግለሰቦች ስለተወረሱ ቤቶች ጉዳይ እንመለስ፡፡ ያልፈረሱት ስለ አልፈረሱ የሚያናግሩት ነገር የላቸውም፡፡ የአዲስ አበባ አስተዳደር አንድን አካባቢ ለመልሶ ማልማት በሚያፈርስበት ጊዜ በቀበሌ ወይም በኪራይ ቤቶች ቤት ለሚኖሩ ሰዎች የጋራ የመኖሪያ ቤት ይመድባል፡፡ በራሳቸው ይዞታ ለሚኖሩት ደግሞ ቦታና የቤት መሥሪያ ገንዘብ ይሰጣል፡፡ ይሁን እንጂ እየፈረሱ ያሉ ቤቶች የእነዚያ በአዋጅ ንብረታቸውን የተቀሙ ሰዎች ቤቶች ናቸው፡፡ ትርፍ ተብለው ባይወሰድባቸው ኖሮ ዛሬ እነሱም ተለዋጭ ቦታና ግምት የማግኘት መብት የነበራቸውም ነበሩ፡፡ ግን ማንም ትዝ ብለውት አያውቅም፡፡ ሠነዳቸው እንኳ በአግባቡ ስለ መያዙ አጠራጣራለሁ፡፡ መስተዳድሩ ያፈረሰው እና እያፈረሰ ያለው ልክ የራሱን የግል ቤት እንደሚያስፈርስ አንድ አባወራ ነው፡፡ የባለመብቶቹ ጉዳይ መታሰብ ነበረበት፤ ሊታሰብበትም ይገባል፡፡  መንግስት ግምት ለመክፈል በአዋጅ በአደባባይ የገባውን ቃል መጠበቅ አቅቶታል፣ ቃሉን ማክበር የማይችል መንግሥት፤ እዚህ አገር ላይ ከቆመ አርባ ሶስት አመት ያለፈው መሆኑን አሁንም ልብ እንዲባል እፈልጋለሁ፡፡
ምን መደረግ አለበት? እኔ በወቅቱ ከተከራዩ እንጂ ከአከራዩ ምድብ አይደለሁም፡፡ ባለመብቶቹ ምን እንደሚሉም አላውቅም፡፡ መንግሥትም ቢሆን ነገሩ ትዝ ያለው አይመስለኝም፡፡ በእኔ እምነት ግን መረሳት የለበትም፡፡ “ይህን ምክንያት አድርገው ቢወርሱኝ” በሚል ሥጋት የሚከራይ ቤት ማግኘት ፈተና እንደ ነበር ትዝ ይለኛል፡፡
ችግሩ እጅግ እየከፋ ሔዶ ሰው የሚያደርገው እየጨነቀው የመጣው በ1977 ዓ.ም ላይ ነው፡፡ በዚሁ አመት የቀበሌን ቤት ማከራየት እንደሚቻል ተፈቀደ፡፡ አብዩቱ ከፈነዳ ከአስር አመት በኋላ “ይከራያል” የሚል ማስታወቂያ ማየት ተቻለ፡፡ በዚህ ጉዳይ ቀበና አካባቢ ዛሬም ትዝ ይለኛል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዐቢይ አህመድ ይህን ዘመን፣ የይቅርታ ዘመን ብለው አውጀዋል፡፡ መንግሥት ይቅርታ መጠየቅ ያለበት ከሕግ ውጭ ያሠራቸውን፣  ልጆቻቸውን፣ ወንድሞቻቸውን፣ እህቶቻቸውን፣ ባሎቻቸውን ሚስቶቻቸውን ያሠረባቸውን፣ ያንገላታባቸውን የገደለባቸውን እንዲሁም ተበዳዮችን ብቻ አይደለም፡፡ ሃብታቸውን ወርሶ ድሃ ያደረጋቸውን ጭምር መሆን አለበት፡፡ በተወረሰ ንብረታቸው ለአመታት ሲብሰለሰሉ ኖረው፣ እሮሯቸውን ለልጆቻቸው አውርሰው ያለና በሕይወትም የሚገኙ ወገኖችንም ይቅርታ መጠየቅ ይኖርባቸዋል፡፡
ይቅርታ ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ ከፍ ከፍ ተደርገው ሊመሰገኑ ይገባል፡፡ ለዓመታት ሲወርድባቸው የቆየው እርግማንና ዘለፋ ከላያቸው ሊገፈፍም ያስፈልጋል፡፡
ዛሬ የቀበሌ ቤት ይዘው እንደ ራሳቸው የግል ቤት እየተዝናኑ እየኖሩ ያሉ ከተማ ለዚህ የበቃው እነሱ አፈር ልሰው በሠሩት ቤት ነው፡፡ እነሱ ቤት ባይሠሩ ኖሮ ከተማውና የከተማው ነዋሪዎችም ሊገጥማቸው ይችል የነበረው ችግርም ሊታወቅ ይገባል፡፡
በዚህ አጋጣሚ ለፍቶ ደክሞ ሀብት ማፍራት፣ ሃብትን በልዩ ልዩ መንገድ ማደረጃት ወንጀል አለመሆኑን፣ መንግሥት የንብረት ባለቤትነት መብትን ለመጠበቅ በቁርጥ መነሳቱን ማረጋገጥ አለበት፡፡

Read 3037 times