Saturday, 21 July 2018 12:50

ዶ/ር ዐቢይ እኮ ሰው ናቸው!

Written by  አስናቀ ሥነስብሐት
Rate this item
(1 Vote)


    ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአገራችን እየተለመዱ ከመጡ አባባሎች መካከል አንዱ ነው፤ በተለይ በአሽከርካሪዎች ዘንድ፡፡ አንድ አሽከርካሪ ከፊቱ ያሉ ሌሎች ተሽከርካሪዎችን ቀድሞ ለማለፍ በሚያደርገው ሩጫና ችኮላ ያለመጠን ሲንቀዠቀዥና ጥሩምባ በጣም እያሰማ ሽብር ሲፈጥር፣ በግርግሩ የሚረበሸው ከፊት ያለው መኪና አሽከርካሪ “ልትሞት ነው?” ይለዋል፡፡ አሪፍ አባባል አይደል? በተለይ ለሁሉ ነገር ጥድፊያና ችኮላ ያበዛ በአብዛኛው ከፊቱ ምን እንዳለ የማያስተውል ስለሆነ፣ በጥድፊያ መሃል ሞትም እንዳለ ማስታወሱ የተገባ ነው፡፡
በኢትዮጵያችን በየዘመናቱ የሆነውንና እየሆነ ያለውን ነገር ስንመለከት፣ ለአብዛኛዎቹ ነገሮቻችን መበላሸት ወይም አለመሳካት ምክንያት ከሆኑት ችግሮቻችን መካከል አንደኛው ችኮላ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ የምንፈልገው ነገር ዛሬውኑ ካልተደረገልን ኩርፊያችን፣ ቁጣችን፣ ስድባችንና እርግማናችን “እግዚኦ!” የሚያሰኝ ነው፡፡ አዲስ ነገር፣ አዲስ ሀሳብ፣ አዲስ መሪ፣ አዲስ ክስተት፣… ሲመጣ አካሄዱን በጥሞና ከመመልከት ይልቅ ውጤቱን “ዛሬና አሁኑኑ ካላየሁ” ባዮች ብዙ ነን። ይህ ክፉ አመላችን፣ በእውነትም “ልትሞት ነው?” የሚያሰኝ ነው፡፡
የትናንት፣ የትናንት-በስቲያውን ትተን፣ የዛሬውን ሁኔታችንን እንኳን ብናይ፣ ትናንት በችኮላችን ካመለጡን ወርቃማ ዕድሎችና አጋጣሚዎች ምንም አለመማራችንን መረዳት ይቻላል፡፡ ይህንን የሚያሳዩ ብዙ አስረጂዎች ቢኖሩም፣ በዚህ ጽሑፍ እኔ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ ብቻ በመውሰድ ሐሳቤን ለማብራራት እሞክራለሁ፡፡
ዛሬ በአገራችን አዲስ የለውጥ ምዕራፍ ተጀምሯል። ባለፉት ዓመታት በተጓዝንበት መንገድ፣ ካገኘነው ይልቅ ያጣነው፣ ካለማነው ይልቅ ያጠፋነው እንደበዛ በተጨባጭ የታየበት ወቅት ላይ ደርሰናል፡፡ በዚህም ምክንያት የሕዝቡ ምሬት ጫፍ ደርሶና የግፉ ጽዋ ሞልቶ “በቃኝ!” ወደሚልበት ደረጃ ተሸጋግሯል፡፡ የዚህ ምሬት ውጤትም ሕዝቡን ወደ አደባባይ ወጥቶ ድምጹን እንዲያሰማ ከማድረግ ባለፈ፣ ግጭትና የኃይል አማራጭን አክሎ በቅርብ ዓመታት ውስጥ ይታያል ተብሎ እምብዛም ያልተጠበቀ ለውጥ እንዲመጣ አስችሏል፡፡
ይህ ለውጥ አብዛኛውን ኢትዮጵያዊ ያስደሰተና ለነገም የተስፋ ስንቅ ያስቋጠረ ታሪካዊ ክስተት፣ ብሎም ዕድል ነው፡፡ “ለውጥ ያስፈልጋል!” የሚለውን የሕዝብ ድምጽ ሰምተው “አዎን፣ ለውጥ ያስፈልጋል” ያሉና ለዚህም የተጉ ተራማጆች፣ ከገዢው ድርጅት ውስጥ ብቅ ብለው ወደ መሪነቱ አድገዋል፡፡ በእነዚህ መሪዎች በየዕለቱ እየተነገሩና እየተተገበሩ ያሉ የለውጥ እርምጃዎች ሚዲያዎቻችንን በ“ሰበር ዜናዎች” ከማጨናነቅም አልፈው፣ ሰዎቹንም “እስከዛሬ ድረስ የት ነበራችሁ?” ብለን እንድንጠይቅ ያደረጉን ሆነዋል፡፡
ባለፉት ሦስት ወራት ያየነው የለውጥ ጉዞ የአብዛኛውን ሕዝብ ይሁንታ የማግኘቱን ያህል አልጋ-በአልጋም አልነበረም፡፡ ብዙ ባይባልም ጉርምርምታ፣ ቅሬታ፣ ተቃውሞ፣… አላጣውም፡፡  ይህ በራሱ ችግር ነው ብዬ አላስብም፡፡ ምክንያቱም፣ በለውጥ ሂደት ውስጥ ሁሉንም ማስደሰት የማይቻል በመሆኑ ነው፡፡ ስለዚህም፣ በዓለም ታሪክ ተደጋግሞ እንዳየነው፣ አዲስ ነገር ሁሉንም አያስደስትም፣ በዚህም ተግዳሮት መኖሩ አይቀርም፡፡ ነገር ግን፣ እነዚህ ተግዳሮቶች ከየት፣ ለምን፣ እና እንዴት እንደመጡ መመርመር ለጉዞው መቃናት ያለው አስተዋጽኦ ቀላል አይደለም፡፡
የተግዳሮቶቹን የት-መጣ’ነት ስንመረምር፣ የዚህ የለውጥ ጉዞ ፈተናዎች “ውጫዊ ብቻ ናቸው” ብሎ ማሰብ ስህተት ይመስለኛል፡፡ እንዴት? ቢባል፣ ውስጣዊ ተግዳሮቶችም አብረው ስላሉ እነሱንም ማየት የግድ ይላል፡፡ በእኔ ትዝብት፣ ውስጣዊዎቹ የዚህ የለውጥ ጉዞ ተግዳሮቶች፤ ስሜታዊነት፣ ችኩልነት፣ በተቀደደው ቦይ ያለ ጥያቄ መፍሰስ፣ ለውጡን በተግባር ከማገዝ ይልቅ ከትናንቱ ያልተለየና ወደ ውድቀት የሚመራ የውዳሴና የመፈክር ጋጋታ፣ ለዚህ ለውጥ ዕውን መሆን የተከፈለውን መስዋዕትነት መዘንጋት፣ ወዘተ ናቸው፡፡
ከእነዚህ ከላይ ከተዘረዘሩት ውስጣዊ ተግዳሮቶች መካከል የዚህ ጽሑፍ ዋነኛ ትኩረት “ችኩልነት” ነው። በመግቢያዬ ላይ እንደጠቀስኩት፣ “የምንፈልገው ነገር አሁኑኑ…” የሚለው ጥያቄያችን፣ በዚህ ተስፋ በሰነቅንበት ወቅት በተለያየ መልክ ሲንጸባረቅ ይታያል። ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነቱ ከመጡበት ዕለት አንስቶ በተቆጠሩት ሦስት ወራት ውስጥ በርካታ “ይሆናሉ” ብለን ያልጠበቅናቸውን ሥራዎች ሠርተው አስደምመውናል፡፡ አብዛኛዎቻችን ለእነዚህ ስኬቶቻቸው እርሳቸውንና ባልደረቦቻቸውን እያመሰገንን፣ “ቀጥሎስ ምን ይሠሩ ይሆን?” እያልን በጉጉት፣ ቀድሞ የማንከታተላቸውን የመንግሥት ሚዲያዎች መከታተል ጀምረናል፡፡ አንዳንዶቻችን ግን፣ ከጉጉትም አልፈን እየተቻኮልን ጠቅላይ ሚኒስትሩን እያቻኮልናቸው ነው፡፡ ጉጉት እና ችኮላ ይለያያሉ፡፡ ስንጓጓ፣ የጓጓንለት ነገር የሚሆንበትን ጊዜ በናፍቆት እንጠብቃለን፡፡ ስንቸኩል ግን፣ የጊዜን ዑደት፣ የሁኔታዎችን ባሕርይ፣ የሰዎችን አቅምና ሌሎች መሥፈርቶችን ለማየት ዐይንም፣ ጊዜም የለንም፡፡ ሂደቱን ዘልለን ውጤቱ ላይ ማረፍ ነው የምንፈልገው፡፡ ሲዘሉ ደግሞ መሰበርም አለ፡፡ “በሬ ሆይ፣ ሣሩን አየህና ገደሉን ሳታይ” እንደሚባለው፡፡
በዚህ ሁኔታ ባለፉት ሦስት ወራት ውስጥ ከችኮላ የመነጩ በርካታ ድምፆችን ሰምተናል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ብቻ ሳይሆን፣ በዚህ የለውጥ ጉዞ ውስጥ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ዜጎችን ጨምሮ የፈለግነውን ነገር ዛሬ ላይ አሟልተው ስላልሰጡን የተቸናቸው፣ አለፍ ሲልም የሰደብንና የዘለፍናቸው አልታጣንም፡፡ እስቲ እኔ የታዘብኳቸውን በጥቂቱ ላስቀምጥ፡፡
“ዐቢይ ለምን የኦሮሚያና የሶማሌን ችግር አልፈታም”፣ “ዐቢይ ለምን ለሙስሊሙ ችግር መፍትሄ አልሰጠም”፣ “የሰብዓዊ መብት ጥሰት የፈጸሙ ለምን አልታሠሩም”፣ “የታሠሩ ሰዎች በሙሉ ለምን አልተፈቱም”፣ “ስንት መስዋዕትነት የተከፈለባት ባድመን እንዴት ለኤርትራ እንሰጣለን”፣ “አየር መንገድ እና ቴሌን መሸጥ ለምን ያስፈልጋል”፣ “የእኛ ዞን ለምን ክልል አይሆንም”፣ “ለኢሳይያስ ለምን የደመቀ አቀባበል ይደረግለታል”፣ “ቴዲ አፍሮ ለምን በዐቢይና በኢሳይያስ ፊት አላስጨፈረንም፣” …፡፡
እነዚህ ሁሉ ቅሬታዎች መነሻቸው ችኮላ ነው፡፡ እነ ዶ/ር ዐቢይን ሰው መሆናቸውን ረስተው እንደ አምላክ ሁሉን ነገር “ይሁን” በሚል ቃል ብቻ የሚፈጽሙ የሚመስላቸው አሉ፡፡ ሁኔታው ያልገባቸው ሰዎች መኖራቸውን ታዝበው ነው፣ ዶ/ር ዐቢይም ሀዋሳ ላይ ከኅብረተሰቡ ተወካዮች ጋር ሲወያዩ “ለእኔስ ጊዜ አያስፈልገኝም?” ብለው በሀዘኔታ የጠየቁት፡፡ አነዚህ ሰዎች፣ ባይታያቸው ነው እንጂ በሦስት ወራት ውስጥ የተሠራው ሥራ፣ በዓመታት ውስጥ ያልተሠራ ነው፡፡ ደግሞስ፣ አስተውለን ከሆነ፣ አንዳንዶቹ ጥያቄዎች እኮ በሂደት መልስ አግኝተዋል፡፡ ሌሎቹ ደግሞ በሂደት ላይ ናቸው፡፡ የተወሰኑትን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማ ተገኝተው የተብራራ መልስ ሲሰጡባቸው “ለካ ይኼም አለ” አሰኝተውናል፡፡ ካልቸኮልን ለሌሎቹም መልስ ማግኘታችን አይቀርም፡፡ የሚያሳዝነው ግን፣ ይህንን ሁሉ አይተንም ዛሬም ያልተማርንና አንደበታችን ለዘለፋና ለስድብ የሰላ ሰዎች መኖራችን ነው፡፡ ልንሞት ነው እንዴ?
ጎበዝ! አንቸኩል፡፡ በሐምሌ የተዘራ ዘር ፍሬ ለመስጠት እስከ ታህሳስ ድረስ ያስጠብቃል እኮ! አብሲት እንኳን ተጥሎ የጥሩ እንጀራ ግብዓት ለመሆን ሦስት ቀን መቀመጥ አለበት እኮ! ዛሬ የተፀነሰ ጽንስ ሕፃን ሆኖ ምድርን ለመቀላቀል ዘጠኝ ወር ይፈልጋል እኮ! ተፈጥሮ መታገስን ካላስተማረችን ማን ሊያስተምረን ነው? “ልትሞቱ ነው?!” ከሚል ትችት ይሰውረን፡፡
እንታገስ! እግር እንጂ ክንፍ እንዳልተሰጠን አውቀን፣ መራመድና መሮጥ እንጂ መብረር እንደማንችል ተገንዝበን ረጋ እንበል! በችኮላችን መውደቅ እንዳለም አንዘንጋ፤ እንኳን ተሩጦ፣ ተራምዶም መደናቀፍ አለ፡፡


Read 2762 times