Saturday, 21 July 2018 12:48

ብህትውናና ዘመናዊነት ክፍል-5 ተአምራዊነት (Mysticism)

Written by  ብሩህ ዓለምነህ (በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር)
Rate this item
(5 votes)

 ጥንታዊ የኢትዮጵያ ስልጣኔ የቆመበትን መሰረት እየፈተሽን እዚህ ደርሰናል፡፡ ለዚህ ፍተሻ መሰረት የሚሆነንም በታሪክ ምሁራኖቻችን ዘንድ ብዙም ትኩረት ያላገኘው፣ ከፍልስፍና አንፃር ግን በጣም ጠቃሚ የሆነው 6ኛው ክ/ዘ ላይ የተከሰተው የኢትዮጵያ ታሪክ ነው፡፡ ይህ ዘመን በነባሩ አክሱማዊ ባህልና በአዲሱ የብህትውና አስተሳሰብ መካከል የባህል ምስቅልቅል (cultural turmoil) የተፈጠረበት ወቅትና በስተመጨረሻም ያሬዳዊውን ስልጣኔ ያስገኘው ብህትውናዊው ባህል አሸናፊ ሆኖ የወጣበት ዘመን ነው፡፡
ከፍልስፍና አንፃር ስንመለከተው 6ኛው ክ/ዘ ላይ ጥንታዊውን የአክሱም ስልጣኔን በመተካት የመጣው ያሬዳዊው ስልጣኔ ሦስት አምዶች ላይ የተገነባ ነው - ስነ ምግባራዊ (Ethical)፣ ኪነ ጥበባዊ (Aesthetic) እና ዲበ አካላዊ ወይም ስነ መለኮታዊ (Metaphysical) አምዶች፡፡ ስነ ምግባራዊው አምድ ብህትውና ሲሆን፣ ይሄንንም በክፍል አንድና ሁለት ፅሁፎቼ ላይ ተመልክተነዋል፡፡ ኪነ ጥበባዊው አምድ ደግሞ ከሰሞነ ሕማማት እንደሚቀዳ በክፍል ሦስትና አራት ላይ ተመልክተነዋል፡፡ በዛሬው በክፍል-5 ፅሁፌ ላይ ደግሞ፣ ያሬዳዊው ስልጣኔ የቆመበትን ዲበ አካላዊ (ስነ መለኮታዊ) መሰረት እንመለከታለን፤ ዲበ አካላዊው መሰረትም ‹‹ተአምራዊነት (Mysticism)›› ነው፡፡
ዲበ አካላዊው አምድ ስንል ‹‹የሰው ልጅ የዩኒቨርሱን አመጣጥ፣ አሰራርና ከራሱ ህይወት ጋር ስላለው ግንኙነት፣ እንዲሁም ተፈጥሯዊ ክስተቶችን በተመለከተ ምን ያስባል?›› የሚለውን ጥያቄ የሚመልስ ነው፡፡
የኢትዮጵያን ማህበረሰብ ባህሉንና አስተሳሰቡን የወሰኑ ሁለት ጥንታዊ ፅንሰ ሐሳቦች ጥቀስ ብትሉኝ ‹‹ተአምራዊነት›› እና ‹‹ብህትውና›› መሆናቸውን አስረግጬ እነግራችኋለሁ፡፡ እነዚህ ሁለት ፅንሰ ሐሳቦች የኢትዮጵያውያንን ስነ ልቦና፣ ታሪክ፣ ኪነ ጥበብና የዘመናዊነት ክሽፈቶችን ለመተንተን በጣም ጠቃሚ የሆኑ የማስተንተኛ ሐሳቦች ናቸው፡፡ እኔም በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ በተከታታይ በማወጣቸው ፅሁፎች ላይ የእነዚህን ሁለት ፅንሰ ሐሳቦች ጠቃሚነት ለማሳየት እየሞከርኩ ነው፡፡
ከዚህ በፊት ስለ ብህትውና በተከታታይ ፅፌላችኋለሁ፡፡ ዛሬና በቀጣይነት ደግሞ ብህትውና ከ‹‹ተአምራዊነት›› ጋር ያለውን ጥልቅ የባህሪ ትስስር ለማሳየት እሞክራለሁ፡፡
‹‹ተአምራዊነት›› በባህሪው የስነ መለኮታዊ ፅንሰ ሐሳብ ቢሆንም፣ በሂደት ግን ይህ ፅንሰ ሐሳብ ሃይማኖታዊ ከሆነው ክበብ ወጥቶ ዓለማዊ በሆነው አስተሳሰብ ውስጥ ገዥ ሐሳብ ለመሆን ችሏል፡፡ እኔም በዚህ ፅሁፍ ውስጥም ሆነ ከዚህ በኋላ ስለ ‹‹ተአምራዊነት›› ፅንሰ ሐሳብ ሳነሳ ዋነኛ ትኩረቴ ሃይማኖታዊው እሳቤ ሳይሆን፣ ‹‹ተአምራዊነት›› መንፈሳዊ ከሆነው ክበብ ወጥቶ ዓለማዊ በሆነው አስተሳሰብ ውስጥ ገዥ ሐሳብ ሆኖ መቅረቡ በማህበረሰባችን ውስጥ የፈጠራቸውን ማህበራዊ አንድምታዎች ማሳየትና መተንተን ነው፡፡ ይሄንን ሳደርግ ግን መንፈሳዊውንም እሳቤ መነካካቴ አይቀርም፡፡
ሃይማኖታዊ በሆነው እሳቤ መሰረት፣ የሰው ልጅ ወደ ፍፁምና (perfection) ለመድረስ የተለየ ስነምግባር ወይም ከዓለም የተለየ የአኗኗር ዘይቤ ያስፈልገዋል፡፡ ይሄም ለፍፁምና የሚረዳ የአኗኗር ዘይቤ ‹‹ብህትውና›› (ascetic life) ነው ተብሎ ይታመናል፡፡ ሆኖም ግን፣ ‹‹ብህትውና›› በእርግጥም ወደ ፍፁምና የሚያደርስ ትክክለኛው የአኗኗር ዘይቤ መሆኑንና አለመሆኑን ማረጋገጫ የለም፡፡ ያለማረጋገጫ ደግሞ ‹‹ብህትውና›› ትክክለኛ ስነ ምግባራዊ አስተምህሮ ሆኖ፣ በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ ሊቀጥል አይችልም። ሆኖም ግን፣ መሬት ላይ ያለውን ሐቅ ስንመለከት፣ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ በርካታ የመካከለኛው ዘመን ማህበረሰቦች ውስጥ ‹‹ብህትውና›› ለረጅም ዘመናት ብቸኛው የስነ ምግባር አስተምህሮ ሆኖ ኖሯል፡፡ ይሄ እንዴት ሊሆን ቻለ? የትክክለኛነት ማረጋገጫ ሳያገኝ ‹‹ብህትውና›› እንዴት ዘመን ተሻጋሪ የስነ ምግባር አስተምህሮ ሊሆን ቻለ?
ይሄም የሚያሳየን፣ ‹‹ብህትውና›› ወደ ፍፁምና የሚያደርስ ትክክለኛው የአኗኗር መንገድ መሆኑን ማረጋገጫ አግኝቷል ማለት ነው፡፡ ያለዚህ ማረጋገጫ ‹‹ብህትውና›› ይሄንን ያህል ዘመናት ሊቆይ አይችልም። ምንድነው ታዲያ ይህ ማረጋገጫ? ‹‹ተአምራዊነት››!! ‹‹ብህትውና ወደ ፍፁምና ያደርሳል›› የሚለው አስተሳሰብ ብቸኛው ማረጋገጫ አመክንዮ ሳይሆን ‹‹ተአምራዊነት›› ነው- ተአምራዊ መገለጥ!! በዚህ መልኩ፣ ‹‹ተአምራዊነት›› ብህትውናን ያፀናዋል። ብህትውናም በተራው ‹‹ተአምራዊ›› ተረኮችን ይሸከምለታል፡፡
‹‹ተአምራዊነት›› የሚለው ቃል ‹‹ተአምር›› ከሚለው ቃል የመጣ ሲሆን፤ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ‹ተአምር›› የሚለውን ቃል ሲተረጉሙ፡- ‹‹አስገራሚ››፣ ‹‹አስደናቂ››፣ ‹‹ልዩ የሆነ›› ይሉታል፡፡ የአንድ ክስተት ‹‹አስገራሚነት›› የሚመነጨው ደግሞ ከምናቀው የመንስኤ - ውጤት (cause and effect) መስተጋብር ውጭ ሆኖ ሲከሰት ነው፡፡ ይሄንን የ‹‹ተአምራዊነት›› ልዩ ባህሪ በማካተት የተሟላ ትርጉም የሚሰጠን ደግሞ የማርክሲዝም- ሌኒኒዝም መዝገበ ቃላት ነው፡፡
ማርክሲዝም- ሌኒኒዝም መዝገበ ቃላት ‹‹Mysticism›› የሚለውን ቃል ‹‹ተማለለ፣ ተማልሎአዊነት›› ብሎ ሲተረጉመው፣ መገለጫ ባህሪውንም ‹‹በፀሎት ወቅት ከአመክንዮአዊነት በላይ በሆነ መንገድ ከእግዚአብሔር ጋር ወይም ከሁሉም በላይ ከሆነ ኃይል ጋር መገናኘት ነው›› ይለዋል፡፡ የዚህ መለኮታዊ ግንኙነት ዋነኛ መገለጫዎቹ ደግሞ ተአምራት ማድረግ፣ እርገት (ከንቃተ ህሊና መውጣት)፣ ርዕይ ማየትና ትንቢት መናገር ናቸው፡፡ በመሆኑም፣ ከእነዚህ የ‹‹ተአምራዊነት›› መገለጫዎች በመነሳት እኔ ‹‹Mysticism›› የሚለውን ቃል ‹‹ተማልሎአዊነት›› ከማለት ይልቅ ‹‹ተአምራዊነት›› ብሎ መተርጎሙ ይበልጥ ገላጭ ሆኖ ስላገኘሁት በዚሁ ቃል እቀጥላለሁ።
ይሄ ‹‹ተአምራዊነት›› ወይም ‹‹ከመለኮታዊ ኃይል ጋር መገናኘት›› የሚለው ሐሳብ የማንኛውም ሃይማኖት ዋነኛና ቀዳሚ እሳቤ ነው፡፡ ሃይማኖትን ከዚህ እሳቤ ውጭ መመስረትም ሆነ ማስኬድ አይቻልም፡፡ ይሄ አስተሳሰብ በሃይማኖት ውስጥ ብቻ ሳይሆን ‹‹ሁሉ አምላክነት›› (Pantheism) በሚባለው የፍልስፍና አስተሳሰብ ላይ ሳይቀር ሰርፆ የምናገኘው ሲሆን፤ ክስተቱም ንቃተ ህሊና ከአካል ወጥቶ ከመላው ተፈጥሮ ጋር የሚዋኻድበትን ቅፅበት የሚገልፅ ነው፡፡
ሁለቱ የ‹‹ተአምራዊነት›› መገለጫ ባህርያት
የ‹‹ተአምራዊነት›› ዋነኛ እሳቤ፤ ‹‹የሰው ልጅ አእምሮ ወይም አመክንዮ መለኮታዊውን ነገር ለመረዳት የአቅም ውስንነት አለበት›› የሚል ነው፡፡ ምክንያቱም፣ በተአምራዊነት እሳቤ መሰረት አመክንዮ የሚሰራው ምድራዊ የሆኑ ክስተቶችን ብቻ ለመግለፅ ነው፤ ምድራዊ ከሆነው ነገር በላይ ያሉትን መንፈሳዊና መለኮታዊ ክስተቶችንና ግንኙነቶችን አመክንዮ የመግለፅ አቅም የለውም፡፡ በመሆኑም፣ በዚህ መንፈሳዊ ትርጉም ውስጥ ተአምራዊ መገለጥ (Mystical experience) ‹‹የስውርነት›› እና ‹‹የሚስጥራዊነት›› ባህሪ አለው፡፡
ከዚህም በመነሳት፣ ሁለቱ ‹‹የተአምራዊነት›› መገለጫ ባህሪያት ‹‹ስውርነት›› እና ‹‹ሚስጥራዊነት›› ናቸው ማለት እንችላለን፡፡ እነዚህም ባህርያት ሁለት ነገሮችን ያመላክቱናል፡፡ የመጀመሪያው፣ ተአምራዊ ክስተት ‹‹ስውር›› እና ‹‹ሚስጥራዊ›› ከሆነ፣ ለማንኛውም ሰው የሚከሰት ነገር አይደለም ማለት ነው፡፡ ‹‹ተአምራዊነት›› ለማንኛውም ሰው የሚከሰት ከሆነ፣ የስውርነትና የሚስጥራዊነት ባህሪውን ያጣል። ሁለተኛው ደግሞ፣ ተአምራዊነት ከአመክንዮአዊነት ጋር በተቃርኖ የሚቆም መሆኑን ነው፡፡ ምክንያቱም፣ ተአምራዊነትን ‹‹ስውር›› እና ‹‹ሚስጥራዊ›› የሚያደርገው ክስተቱ የሰው ልጅ መረዳት ከሚችለው የመንስኤ - ውጤት ህግ በላይ ሆኖ መከሰቱ ነው፡፡ እስቲ እነዚህን ሁለት ባህሪያት በየተራ እንመልከታቸው፡፡
‹‹ተአምራዊ መገለጥ›› ማንኛውም ሰው የሚያጋጥመው ነገር አይደለም፤ የመንፈሳዊ ህይወት ከፍታን ይፈልጋል፡፡ ‹‹ተአምራዊ መገለጥ›› ላይ የሚደርሱ ሰዎች በመንፈሳዊ ህይወት የበቁ በጣም ጥቂት ሰዎች ሲሆኑ፣ እነሱም በአብዛኛው የብህትውና ህይወትን የሚመሩ ናቸው፡፡ ይሄም በብህትውናና በተአምራዊነት መካከል ያለውን የባህሪ ትስስር የሚያሳይ ነው፡፡
‹‹ተአምራዊነት›› በአብዛኛው የብህትውና ህይወት ላይ መገለጡ፣ ‹‹ብህትውና ወደ ፍፁምና የሚያደርስ ትክክለኛው የአኗኗር መንገድ ነው›› ለሚለው አስተሳሰብ ማረጋገጫ ከማቅረቡም በላይ፣ አስተሳሰቡ በእኛ ማህበረሰብ ውስጥ አሸናፊ ሆኖ እንዲወጣ አድርጎታል፡፡ ይሄም አሸናፊነት፣ ‹‹ተአምራዊነት›› መንፈሳዊ ከሆነው ክበብ ወጥቶ፣ ዓለማዊ በሆነው አስተሳሰብ ውስጥ ሳይቀር ገዥ ሐሳብ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ምክንያቱም፣ በመንፈሳዊና በዓለማዊ ህይወት መካከል ድንበር ማስመር አይቻልምና፡፡
የ‹‹ተአምራዊነት›› አስተሳሰብ በዚህ መልኩ በመንፈሳዊም ሆነ በዓለማዊ ህይወት ውስጥ አሸናፊ ሆኖ ከወጣ በኋላ ህዝቡ መንፈሳዊ ክስተቶችን ብቻ ሳይሆን ዩኒቨርሱንና በውስጡ ያሉትን ተፈጥሯዊ ክስተቶችን ጭምር የሚመለከትበት መነፅር ለመሆን ችሏል፡፡
በዚህም የተነሳ የእኛ ህዝብ ከድሮ ጀምሮ ‹‹አካላዊ ክስተቶች ኢ-አካላዊ መንስኤ አላቸው›› በሚል ድምዳሜ ህይወቱን ሲመራ ኖሯል፡፡ ይሄም ማለት ‹‹አካላዊ ክስተቶች (ለምሳሌ - ህይወትና ሞት፣ ከበሽታ መዳን፣ ሐብትና ድህነት፣ ዝናብና ጎርፍ፣ ድርቅና ረሃብ፣ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች፣ ሹመትና ንግስና …ሁሉ) መንስኤያቸው ከመንስኤ - ውጤት ዝምድና (cause and effect relationship) ውጭ የሆነ መለኮታዊ ተአምራት ነው›› የሚል ድምዳሜ ነው። በዚህ ድምዳሜ ውስጥ ‹‹እኛ የምናቀው ውጤቱን እንጂ መንስኤውን አይደለም›› የሚል አስተሳሰብ አለ፡፡ እናም መንስኤው ሚስጥራዊ ነው፡፡
በመሆኑም፣ የ‹‹ተአምራዊነት›› አስተሳሰብ የሚያውቀው በተጨባጭ የሚያየውን ውጤት (effect) እንጂ በጊዜና በቦታ የራቀውን መንስኤ ወይም ደግሞ በረቂቅነት ያለውን መንስኤ (cause) አይደለም፡፡ በዚህም የተነሳ የእኛ ህዝብ መንስኤን የመረዳት አቅምም ሆነ ፍላጎት የለውም፡፡ በሌላ አነጋገር፣ ከድሮ ጀምሮ የተቀረፅንበት የ‹‹ተአምራዊነት›› አስተሳሰብ፣ መንስኤን የማወቅ ፍላጎትና አቅም እንዳይኖረን አድርጎናል፡፡ በዚህም፣ መንስኤን የመረዳት ስንፍናችንንም መልሰን በ‹‹ተአምራዊነት›› እንሸፍነዋለን፡፡
የእኛ ማህበረሰብ ከጥንት ጀምሮ በዚህ መልኩ ስነ ልቦናው በ‹‹ተአምራዊነት›› ፅንሰ ሐሳብ ስለተቀረፀ፣ ተፈጥሯዊና ማህበራዊ ክስተቶችን ሁሉ ‹‹ተአምራዊ›› ያደርጋቸዋል፡፡ ተረኮቻችንና የታሪክ አረዳዳችን ሁሉ በዚህ በ‹‹ተአምራዊነት›› አስተሳሰብ የተሞሉት ለዚህ ነው፡፡ የያሬድ፣ የንጉስ ላሊበላ እና የነገስታቶቻችን ታሪኮች ሁሉ በተአምራዊነት ትርክት የተሞሉ ናቸው። ይህ የተአምራዊነት አስተሳሰብ አሁን ድረስ ተከትሎን መጥቶ ዶ/ር ዐቢይ  አህመድን ‹‹ከእግዚአብሔር የተሰጡን መሪ ናቸው›› እስከማለት ደርሰናል፡፡
ይህ አስተሳሰብ ሁልጊዜ ተአምር ጠባቂ ሆነን እንድንቀርና ሌሎች ተተኪ መሪዎችን እንዳንፈጥር ቀፍድዶ የሚይዝ አስተሳሰብ ስለሆነ በጣም አደገኛ ነው፡፡ በክፍል - 6 ፅሁፌ፣ ነጋድራስ ገብረ ህይወት ባይከዳኝን እየጠቀስን፣ ‹‹ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ከእግዚአብሔር የተሰጡን መሪ ናቸው›› የሚለውን አስተሳሰብ አደገኛነት ሰፋ አድርገን እንመለከተዋለን፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊው በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር እና ‹‹የኢትዮጵያ ፍልስፍና››
መፅሐፍ ደራሲ ሲሆን  
በኢ-ሜይል አድራሻው -  
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 1980 times