Saturday, 21 July 2018 12:47

የጅማ ዩኒቨርሲቲ ከየት ወዴት?

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

 በአገራችን ስመ-ጥር ከሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ የሆነው ጂማ ዩኒቨርሲቲ፤ በምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚ ከሆኑ 10 ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ እንደሆነም ይነገርለታል፡፡ ዩኒቨርሲቲ ከመሆኑ በፊት በግብርና ኮሌጅነት፣ በጥቂት አቅምና በውስን የትምህርት ፕሮግራሞች ሥራውን የጀመረው ተቋሙ፤ እ.ኤ.አ በ1999 ዓ.ም ነው ወደ ዩኒቨርሲቲነት ያደገው፡፡
በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች እምብዛም ያልተሞከሩ አሰራሮችን በመጠቀምና ጥናትና ምርምር ላይ በማተኮር ውጤት ማስመዝገቡ ይነገርለታል፡፡
በተለይም ማህበረሰብ አቀፍ የትምህርት መርሃ ግብሩና የፓርትነርሺፕ አሰራሩ ተጠቃሽ ናቸው፡፡
የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ ከጂማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ፍቅሬ ለሜሳ ጋር ባደረገችው ቃለ ምልልስ፣ የዩኒቨርሲቲውን አጠቃላይ እንቅስቃሴ ታስቃኘናለች፡፡

    ጂማ ዩኒቨርስቲን የተቀላቀሉት መቼ ነው?
በዚህ ዩኒቨርሲቲ ማገልገል የጀመርኩት በ1983 ዓ.ም ከለውጡ ትንሽ ወራት ቀደም ብሎ ነው፡፡ ከሀረማያ ዩኒቨርሲቲ በዕፅዋት ሳይንስ የመጀመሪያ ዲግሪዬን ካገኘሁ በኋላ በዛን ወቅት ጂማ ግብርና እና እንስሳት ህክምና ኮሌጅ ነበር፡፡ ዩኒቨርሲቲ ሳይሆን ጀምሮ በመምህርነት ተቀጥሬ እስካሁን እያገለገልኩ እገኛለሁ፡፡
አሁን  ጂማ ዩኒቨርሲቲ ያለው አቅምና አጠቃላይ እንቅስቃሴው  ምን ይመስላል?
ዛሬ በዩኒቨርሲቲው የመምህራን ቁጥር ሁለት ሺህ ሲሆን የአስተዳደር ሰራተኛው ብዛት ከ5 ሺህ 600 መቶ በላይ ደርሷል፡፡ የተማሪዎች ቁጥር ወደ 43 ሺህ አድጓል፡፡ በመደበኛው 20 ሺህ ሲሆኑ ቀሪዎቹ በርቀት፣ በማታና በክረምት መርሃ ግብር የሚማሩ ናቸው፡፡ በተጨማሪም ለአገር ጠቃሚ የሆኑ የተለያዩ ሥራዎችን በመስራትም ትልቅ አቅም ያለው ግዙፍ ተቋም ሆኗል፡፡
ኮሌጅ በነበረበትና ለዲፕሎማ በሚያስተምርበት ጊዜ ስለ ጥናትና ምርምር፣ ስለ ማህበረሰብ አገልግሎትም ሆነ ስለ ሌሎች ሥራዎች አይታሰብም ነበር፡፡ ያኔ ማስተማርና ማስመረቅ ላይ ብቻ ነበር ትኩረቱ፡፡ ዩኒቨርሲቲ ከሆነ በኋላ ግን ጥናትና ምርምር ማካሄድና የማህበረሰብ አገልግሎት ዋና ሥራው ሆነ፡፡ እናም በዚህ ሂደት ነው ጅማ ዩኒቨርሲቲ “We are In the community” በሚል መርህ ሰፊ ሥራ መስራት የጀመረው፡፡ ከዚያ ውጭ በጤና ሳይንስ ተቋሙ ብቻ ሳይሆን ማህበረሰብ አቀፍ ትምህርትም (Community Based Education) የዩኒቨርሲቲው ፍልስፍና ሆኖ ቀጥሏል፡፡
ማህበረሰብ አቀፍ ትምህርት (CBE) ሲባል ምን ማለት ነው?
ማህበረሰብ አቀፍ ትምህርት እንግዲህ በሁሉም የትምህርት ፕሮግራሞች በቅድመ ምረቃም ሆነ በድህረ ምረቃ ፕሮግራም ላይ ተግባራዊ ተደርጎ እስካሁን እየሰራንበት ነው፡፡ ይሄ ማህበረሰብ አቀፍ ትምህርት፤ ተማሪዎች በትምህርት ላይ እያሉ የሚማሩትን ትምህርት ወደ ህብረተሰቡ እየገቡ፣ በተግባር የሚለማመዱበት ነው፡፡ ወደ ማህበረሰቡ ወርደው፣ የማህበረሰቡን ህይወት፣ ልምድ፣ ባህልም ሆነ ሌሎች እሴቶችን ከሚማሩት ትምህርት አንፃር ያጠናሉ፡፡ ችግሮችን በጥናትና ምርምራ ይለያሉ፡፡ ለችግሩ መፍትሔ እስከ መስጠት ይዘልቃሉ፡፡ ይሄ ነገ ተመርቀው ሲወጡና ወደ ማህበረሰቡ ሲገቡ ምን መስራት እንዳለባቸው እንዲያውቁ፣ ባህልና ልምዱ አዲስ እንዳይሆንባቸው፣ የማህበረሰቡን ችግር ለይተው ወደ መፍትሄ እንዲሄዱ ሥንቅ ይሆናቸዋል። ምክንያቱም ገና በትምህርት ላይ እያሉ የሚማሩትን ፅንሰ ሀሳብ፣ ከተግባር ጋር እያዋሃዱ በመስራት ቀድመው አውቀውታል፡፡ በዚህ ዩኒቨርሲቲያችን ትልቅ ሥራ በመስራት  ተመስጋኝ ነው። በተለይ በማህበረሰብ አገልግሎት ትልቅ ዝና አለው፡፡
ዩኒቨርሲቲው ከአገር ውስጥ ዩኒቨርሲቲዎች አንጋፋና ስመ-ጥር ነው፡፡ በምስራቅ አፍሪካ  ከሚገኙ ቀዳሚ 10 ዩኒቨርሲቲዎችም አንዱ መሆኑ ይነገራል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ለዚህ የላቀ ደረጃ የበቃው እንዴት ነው?
ጅማ ዩኒቨርሲቲን በተለይ ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ለየት የሚያደርገው በትኩረት እየሰራበት ያለው ማህበረሰብ አቀፍ የትምህርት አሰጣጥ ዘዴው ነው። ቀደም ሲልም እንደገለፅኩልሽ በእኛ አመለካከትና ፍልስፍና፤ ተማሪዎች ጥሩ እውቀት ሊጨብጡ የሚችሉት በካምፓስ ምሁራን፣ ፕሮፌሰሮችና ክፍል ውስጥ በተገደበ ንድፈ ሀሳብ ብቻ አይደለም። በመምህራን የሚያገኙት እውቀት እንዳለ ሆኖ፣ በማህበረሰቡም ውስጥ እውቀትና ክህሎት አለ፤ ሁለቱን አቀናጅተው እንዲማሩ ማድረጋችን ነው። ይህን ለማድረግ ተማሪዎቹ ወደ ማህበረሰቡ ይወርዳሉ፤ ችግር ይለያሉ፤ ለችግሩ መፍትሄ ይሰጣሉ፡፡ ይሄ በአብዛኞቹ ዩኒቨርሲቲዎች እምብዛም የተለመደ አይደለም፡፡ በ3 ዓመት የሚመረቅ ተማሪ፣ በትንሹ ሁለት ጊዜ ወደ ማህበረሰቡ ይወርዳል፡፡ ታዲያ ሲሄዱ ኮርስ ነው፣ ክሬዲት አወር አለው፤ ይገመገማሉ፤ ውጤታቸው በስራቸው ይለካል፡፡
ችግር ወደ መፍታት ሲሄዱ፣ ከማህበረሰቡ ጋር ተወያይተው፣ ማህበረሰቡን አንቀሳቅሰው እዛው ሃብት አሰባስበው፣ ችግሩን ይፈታሉ፤ በዚህ መልኩ የመጠጥ ውሃ ችግር ፈትተዋል፤ መፀዳጃ ቤቶች ሰርተዋል፤ ሌሎች ተግባራትንም ከውነው ተመልሰዋል፡፡ በዚህ ሥራቸው መምህራን ውጤት ይሰጧቸዋል፡፡ ይሄ በግብርናውም በጤናውም በቱሪዝም ዘርፍ የሚማሩትም የሚከውኑት ነው፡፡ ማህበረሰቡም ተጠቃሚ ይሆናል፡፡
ሌላው ጂማ ዩኒቨርሲቲ የሚታወቅበትና የሚለይበት ኢኖቬቲቭ የሆኑ ፕሮግራሞችን በመጀመር ነው፡፡ ይሄ ምን ማለት ነው … በአገሪቱ የሌሉ ነገር ግን ለአገሪቱ በጣም አንገብጋቢና አስፈላጊ የሆኑ ፕሮግራሞችን በመጀመር ይታወቃል፡፡
እስቲ ዩኒቨርሲቲው ከጀመራቸው ፕሮግራሞች  ጥቂቶቹን ይጥቀሱልን?
በጣም ጥሩ! ለምሳሌ “ባዮሜዲካል ኢንጂነር”ን እንውሰድ፡፡ ይሄ በአገሪቱ የሌለ ነገር ግን በእኛ ዩኒቨርሲቲ ቀደም ብሎ የተጀመረ የትምህርት ፕሮግራም ነው፡፡ እንደሚታወቀው በየሆስፒሎቻችን ለላብራቶሪ የሚሆኑ እቃዎች ይገዛሉ፤ የሚገዙት በውድ ዋጋና በውጭ ምንዛሬ ነው፤ ጥገና ሥለሌለ እቃዎቹ ሲበላሹ ይጣላሉ፡፡ እኛ ችግሩን ለየን፡፡ ምንም ሳይኖረን በአገሪቱ በዘርፉ መምህራን እንኳን ሳይኖር፣ ስርዓተ-ትምህርቱን ቀርፀን ጀመርነው፡፡
የመምህራንን ችግር እንዴት ተወጣችሁት?
አንድም ከውጭ በማስመጣት፣ በአብዛኛው ግን ቀጥታ ከትምህርቱ ጋር ባይገናኙም ቀረብ ከሚሉ ሳይንሶች መምህራንን በማሳተፍ፣ ዩኒቨርሲቲው ባለው ፓርትነርሺፕ (ሽርክና) እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርቱ ድጋፍ እንዲያገኝ በማድረግ ጀምረነው፣ አሁን ላይ በአመርቂ ሁኔታ አገሪቱን ተጠቃሚ ማድረግ ችለናል፡፡ በዚህ ዘርፍ እነዚህ ተመራቂዎችን ለማግኘት ከባድ ሆኖብን ነበር፡፡ አሁን ድረስ የሚመረቁት በቁጥር በጣም ጥቂት ነገር ግን በጣም ተፈላጊ ናቸው፡፡
ሌላው በአገሪቱ የሌለ እኛ የጀመርነው “ማቴሪያል ሳይንስ ኢንጂነር” ነው፡፡ ለምሳሌ በዘንድሮ አንቺ በተገኘሽበት የምርቃት ሥነ ሥርዓት ላይ በፒኤችዲ በሜታሎጂ ያስመረቅነውና የፈጠርነው ዘርፍ ነው። በአገራችን የብረታ ብረት ሀብት አለ፡፡ ሀብት ካለ ባለሙያ መኖር አለበት፡፡ በእኛ አገር ግን በዘርፉ የባለሙያ ክፍተት አለ፡፡ ዩኒቨርሲቲያችን በዚህ ዘርፍ በመጀመሪያ፣ በሁለተኛና በሶስተኛ ዲግሪ እያስተማረ ያስመርቃል፡፡ ይህ ያለው ሀብት በባለሙያ ተጠንቶ፣ በዘፈቀደ ከሚሰራበት አሰራር ወጥቶ፣ ፕሮፌሽናል በሆነ መንገድ ጥቅም ላይ እንዲውል ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረክታል፡፡ ማቴሪያል ሳይንስ ስንል ብዙ ነገሮችን ያካትታል፡፡ ከአፈር ሸክላ መስራት፣ ብርጭቆና ብረታ ብረትን አካትቶ የያዘ ነው፡፡ ይሄ እንግዲህ ከሁሉም የሚለየን ነው፡፡ በሌለ ሪሶርስ በድፍረት በመጀመር ውጤት ያስመዘገብንበት ነው፡፡
 ሌላው ውጤት ለማስመዝገብ በራሳችን ሳንታጠር በፓርትነርሺፕ ከተለያዩ ዓለማትና ከአገር ውስጥ ተቋማት ጋር በመስራትም እንለያለን፡፡ በአገር ውስጥም በሌላው ዓለምም ብዙ ፓርትነሮች ሥላሉን፣ በጥናትና ምርምር የሰው ሃይል በመንገባት፣ ፋሲሊቲዎችን ምቹ በማድረግና በብዙ ጉዳዮች ዘርፈ-ብዙ የፓርትነርሺፕ እንቅስቃሴዎችና ትግበራዎች አሉን፡፡ በዚህ አግባብ ባለሙያዎቻችን ከተለያዩ አለማት አጋሮች ጋር ሰፊ ተሳትፎ ያደርጋሉ፡፡ በዚህም ዩኒቨርሲቲው በእጅጉ ተጠቃሚ ሆኗል፡፡ በአሁኑ ወቅት የሰው ሀይላችን ሲኒየሮች ናቸው፤ ፕሮፌሰሮች ፒኤችዲ ያላቸው ናቸው፡፡ በዚህ ረገድ አቅማችን የተገነባ በመሆኑ የተለያዩ የምርምር ተቋማትን ማቋቋም ችለናል፡፡
እስቲ ስለ ምርምር ተቋማቱ በጥቂቱ ያብራሩልን?
ለምሳሌ ባዮ-ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አቋቁመናል። የሞሎኪዮላር ባዮሎጂ ማዕከል አለን፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና የተቸረውና እነ ዩኤስአይዲ እንዲሁም ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ባለሙያዎች የሚያሰለጥኑበት የወባ ምርምር ማዕከል መስርተናል፡፡ አካባቢው ቡና በስፋት የሚመረትበት እንደመሆኑ የቡና ምርምር ማዕከል አለን፡፡ በፋርማሲ ላይም አሁን እንደ ልዕቀት ማዕከል (center of excellence) ሆኖ  የሚያገለግልና በዘርፉ ከሚሰሩ ተቋማት ጋር የምንሰራበት ትልቅ ማዕከል ባለቤት ነን፡፡ ይሄ ቀላል አይደለም፡፡ ይህ ሁሉ አቅም የተገነባው እንደ አንድ ምሰሶ አድርገን በምንሰራው የፓርትነርሺፕ ሥራ ነው፡፡ በስትራቴጂክ እቅዳችን ውስጥ “ኢንተርናላይዜሽንና ፓርትነርሺፕ” ዋናውን ቦታ ይይዛል፡፡ በጋራ መስራት በየትኛውም መልኩ ውጤታማ ማድረጉን በተግባር አምኖበት ነው። አጋሮቻችንን የምንይዝበትን መንገድ ሲስተማቲክና አዎንታዊ በሆነ መልኩ ማድረግ የምንችልበት ልምድም አካብተናል፡፡ ሌሎችንም ጠቅመን እኛም የምንጠቀምበትን አሰራር በመዘርጋታችን፣ በአጋሮቻችን ተወዳጅነትንም አትርፈናል፡፡
ከሌሎች ጋር በአጋርነት ከሰራችኋቸው ሥራዎች ውስጥ  ጥቂቶቹን ለአብነት ሊጠቅሱልን ይችላሉ?
ከአገር ውስጥ ብንጀምር አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የግል ተቋማት፣ ባንኮችና ከኢስት አፍሪካ ሀይ ካፒታል ጋር በቅርበት እንሰራለን፡፡ ለምሳሌ የእኛ ዩኒቨርሲቲ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ከግል የባንክ ተቋማት ጋር በመሆን “ኢስት አፍሪካ ፋይናንስ ሰሚት” አዲስ አበባ ላይ በኢኮኖሚክ ኮሚሽን ፎር አፍሪካ (ኢሲኤ) አዳራሽ አዘጋጅተናል። ይሄ እንግዲህ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የአገሪቱ ችግሮች ጎላ ብለው እንዲወጡና በችግሮቹ ላይ መፍትሄ እንዲመጣ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በተሳትፎ መስራት አለባቸው፡፡ የፋይናንስ ስርዓታችን ያለበትን ችግር የሰው ሃይልና ተያያዥ ችግራችን ላይ ሰፊ ውይይትን በማድረግ መፍትሄ ማፈላለግ የግድ ነው፡፡ ሌላው የመንገድ ደህንነት በአገራችን ከፍተኛ ችግር ነው፡፡ ይህን ችግር ለመቅረፍ ከሉሲ አካዳሚና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በየዓመቱ ብሄራዊ ጉባኤ በማዘጋጀት በዘርፉ ያሉ ችግሮች ጎልተው እንዲወጡ በኢሲኤ ውይይት እናካሂዳለን። በሌላ በኩል፤ ሁለተኛ ሦስተኛና አራተኛ ትውልድ ለሚባሉ ዩኒቨርሲቲዎች ድጋፍ እናደርጋለን፡፡ እነዚህ ዩኒቨርሲቲዎች በጅምር ላይ በመሆናቸው ካለባቸው ክፍተት ተነስተን እንደግፋቸዋለን፡፡ ያልነገርኩሽ ግን ጅማ ዩኒቨርሲቲ በስፋት ከሚታወቅባቸው መካከል የአይቲ ማዕከላችን ነው፡፡ ይህ ማዕከላችን በስራችንም እንድንልቅና ወደፊት እንድንራመድ ያደረገን፣ትልቅ የጀርባ አጥንታችን ነው፡፡ ስለሆነም ለእነዚህ ጀማሪ ዩኒቨርሲቲዎች ኔትወርክ በመዘርጋት፣ ስቱደንት ሪሰርች ሲስተም እና ማኔጅመንት ኢንፎርሜሽን በመዘርጋት ትልቅ ድጋፍ እናደርጋለን፡፡
በሌላ በኩል ከሌሎች ዓለም አቀፍ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በፕሮጀክት የምንሰራቸው ትልልቅ ሥራዎች አሉን፡፡ ለምሳሌ በካናዳ፣ ቤልጂየም፣ ኖርዌይ፣ ኮሪያና ከሌሎችም ዩኒቨርሲቲዎች የምርምር ተቋማት ጋር በጋራ እንሰራለን፡፡ ለምሳሌ ከኮሪያ ድርጅቶች ጋር በጂማ ዞን የገጠር ክሊኒኮች ላይ ውሃና መብራት በሌለበት ሶላር ፓኔሎችን በመግጠም፣ የጉድጓድ ውሃ በማውጣትና ሌሎች ፋሲሊቲዎችን በመገንባት ብዙ ሥራዎችን እየሰራን ነው፡፡ በግብርናውም በኩል በተለይ ከሆላንድ መንግስት ጋር የተለያዩ ምርጥ ተሞክሮዎችን በመሰብሰብ፣ በገበሬዎች ማሳ ላይ በመሞከር ውጤታማዎቹን በማሳደግ፣ ግብርና ሚኒስቴርም ስኬልአፕ እንዲያደርግ ብዙ ሥራዎችን እንከውናለን፡፡ ስንዴና በቆሎ ላይ ውጤታማ የሆነ ዘር በምርምር ተገኝተዋል፡፡ በጤናና በቴክኖሎጂም ላይ የምንሰራ ሲሆን በተለይ በእኛ ሆስፒታል ምርመራ ተደርጎላቸው ከፍተኛ የልብ ችግር ያለባቸውን፣ በየዓመቱ 12 ያህል ህፃናት ወደ እስራኤል በመላክ፣ የቀዶ ህክምና ተደርጎላቸው ድነው እንዲመጡ በማድረግ በኩል ስኬታማ ነን፡፡ ይህ ሁሉ በአጋርነት የመስራት ውጤት ነው፡፡
ከምታከናውኗቸው ዘርፈ ብዙ ሥራዎች አንጻር ከመንግስት የሚመደብላችሁ በጀት በቂ እንደማይሆን መገመት ይቻላል፡፡ የገቢ ማስገኛ ሥራዎችን ትሰራላችሁ?
ትክክል ነው! ምክንያቱም ዩኒቨርሲቲን የሚያክል ትልቅ ተቋም በመንግስት በጀት ላይ ጥገኛ ሆኖ ትልቅ ስራ ሊሰራ አይችልም፡፡ በተለይ ደግሞ መንግስት በሂደት ዩኒቨርሲቲዎች ራሳቸውን እንዲችሉ የሚፈቅድበት አሰራር ስላለና ዓለም አቀፍ ተመክሮዎችም የሚያሳዩት ይህንኑ በመሆኑ፣ እኛም የገቢ ማስገኛ ሥራዎችን መስራት ከጀመርን ቆይተናል፡፡ የራሳችንን የውስጥ ገቢ ለማመንጨት፣ የራሳችንን ኢንተርፕራይዞች አቋቁመናል፡፡ በግብርና ኢንተርፕራይዛችን አትክልትና ፍራፍሬ፣ የወተት ላሞችና ዶሮዎችን እናመርታለን። በተጨማሪም የብረታ ብረትና የእንጨት ስራ ኢንተርፕራይዛችን፣ የተለያዩ የብረታ ብረትና የእንጨት ቁሳቁሶችን ይሰራል። በቅርቡ ደግሞ የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ሥላሉን፣ የራሳቸውን ኢንተርፕራይዝ ፈጥረው የሚሰሩበት፣ ወደ ግንባታ የሚገቡበት ሁኔታ ተመቻችቷል፡፡ ጠንካራው ማዕከላችን አይሲቲ ስለሆነ በዚህም በኢንተርፕራይዝ ተሰማርቶ ገቢ እንዲያመነጭ በዝግጅት ላይ ነን፡፡ በመማር ማስተማር ሂደቱም፣ ፐብሊክ ፕራይቬት ፓርትነርሽፕ አዲስ አበባ ላይ የከፈትነው ካምፓስ የግል ዊንግ አለን፡፡ ይህ ካምፓስ በድህረ ምረቃ ተማሪዎችን ተቀብሎ ያስተምራል። ዘንድሮ በሜዲስንም ጀምረናል፡፡ በቅርቡም ሱማሌላንድ ሀርጌሳ ላይ በቅርቡ የጀመርነው ፕሮጀክት ስላለ እያሳደግነው፣ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት የሚያስችል አቅም ለመፍጠር አቅደናል፡፡ በዚህ መልኩ የውስጥ ገቢን እያመነጨን እንገኛለን፡፡
በዩኒቨርሲቲያችሁ አማካኝነት በተለይ ለከተማው ነዋሪ ምን የተለየ ጥቅም አስገኝተናል ይላሉ?
እውነት ለመናገር ጅማ ከተማ አሁን ላለችበት ደረጃ እንኳን የደረሰችው፣ ይሄ ዩኒቨርሲቲ በመኖሩ ነው፡፡ ምክንያቱም ከተማው ላይ ዋናው ሰራተኛ ቀጣሪ ጅማ ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ ኢንዱስትሪ የለም፤ ምንም የለም፤ ወደ ስምንት ሺህ ከሚጠጉ ሰራተኞች መካከል አብዛኛው የአስተዳደር ሰራተኛ ነው፡፡ አብዛኛውም የከተማው ተወላጅና ነዋሪ ነው፡፡ ስለዚህ የጅማ ከተማ እምብርት (ነርቭስ ሲስተም) ጂማ ዩኒቨርሲቲ ለመሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡
እንደውም የጅማ ዋና ከተማ፣ ጅማ ዩኒቨርሲቲ ነው ሲባል ሰምቻለሁ…
ልትይው ትችያለሽ፡፡ ምንም እንኳን የከተማዋ እድገት ፈጣን ባይሆንም እንዳልኩሽ አሁን ላለችበትም ያደረሳት ዩኒቨርሲቲው ነው፡፡ ለምሳሌ ቴክኖሎጂ ኢንስትቲዩት የተቋቋመበት አካባቢ፣ የበፊቱንና የአሁኑን ብታይው፣ ብዙ ልዩነት አለው፡፡ አሁን የአካባቢው ነዋሪዎች በተቋሙ አካባቢ የተለያዩ ቢዝነሶችን መስርተው እንቅስቃሴ ጀምረዋል። ሻይ ቡና፣ ፍራፍሬና ሌሎች ንግዶች በመክፈት ማለት ነው፡፡ በምርምር የምንደግፈው እንዳለ ሆኖ፡፡ ለመማር ፍላጎት ላላቸውም ብዙ ጥቅም ነው ያለው። በአብዛኛው የከተማው የመንግስት ሰራተኞች ራሳቸውን ያበቁት በዩኒቨርሲቲው ነው፡፡ በወባ ምርምር ስራችን አካባቢን ስናጠና፣ ለወባ የሚሰጠው መድሃኒት ከወባ የተላመደ መሆኑ ተደርሶበት፣ ለፖሊሲ አውጭዎችና አስፈፃሚዎች ሪፖርት ተደርጎ፣ አዲስ መድሃኒት እንዲቀየር አድርገናል፡፡ ይሄ ቀላል አይደለም። ማህበረሰቡን ከወባ እልቂት ጠብቀናል ማለት ነው፡፡ በሌላ በኩል ጅማን የኮንፈረንስ ማዕከል ለማድረግ ትልቅ አቅም ያለው አዳራሽ፣ ከ60 ሺህ በላይ ሰው የሚይዝ ስታዲየምና ሌሎች በመንግስት አቅም ያልተሰሩ መሰረተ ልማቶችን ጅማ ዩኒቨርሲቲ አሰርቷል። በቀጣይ የሆስፒታሊቲ ዘርፉ ላይ በመሰማራት ባለ 5 ኮከብ ሆቴልና ደቡብ ምዕራብ ያለው 20 ሚ. ብር የሚፈጅ ትልቅ ሆስፒታል ለመገንባት በዝግጅት ላይ ነን፡፡ በዚህ በሌሎች ክልሎች ካሉ ትልልቅ ከተሞች ማለትም ከባህርዳር፣ አዳማ፣ ሀዋሳና መሰል ከተሞች እኩል ሆና የቱሪስት መዳረሻም እንድትሆን ጅማ ዩኒቨርሲቲ በትጋት እየሰራ ነው፡፡ ሰሞኑን በከተማዋ የተካሄደው “የከተሞች ሳምንት”፤ ጅማ በትክክል የኮንፈረንስ ከተማ መሆን እንደምትችል ያመላከተ ነው፡፡

Read 1841 times