Print this page
Saturday, 21 July 2018 12:45

“የእነ ቶሎ ቶሎ ቤት ግድግዳው ሰንበሌጥ”

Written by 
Rate this item
(15 votes)

  ከዕለታት አንድ ቀን፤
አያ አንበሶ ለዱር እንስሳት ሁሉ አንድ መልዕክት አስተላለፈ፡-
“እስከ ዛሬ መኖሪያ ደናችን ላይ ጥፋት ያላደረሰ እንስሳ፣ እኔ ቤት መጥቶ ፀበል ይቅመስ!” አለ፡፡
የዱር እንስሳት ሁሉ እየተጋፉ መጡ፡፡ እራሳቸውን የተጠራጠሩ ግን ቀርተዋል፡፡
“አሁንስ አያ አንበሶ አበዛው! እንዳለፈው ጊዜ ቤቱ አስገብቶ ያለ የሌለ ሥራ ሊያሰራን ይሆናልኮ!” ብለው ጉልበታቸውን የሰሰቱና መልፋት አንፈልግም ያሉ ተሰወሩ፡፡
“ከዚህ ቀደም አያ አንበሶ በደል አድርሶብናል - የአስተዳደር ግፍ ፈፅሞብናል” ያሉና ያቄሙ ደግሞ አድራሻቸውን አጥፍተው ተቀመጡ፡፡
አያ አንበሶ ግን በየሰበብ አስባቡ ከድግሱ የቀሩትን ከምንም ሳይቆጥር፤ ከመጡት ጋር ያለውን ምግብ ለመቋደስ ተዘጋጀና ተበላ፣ ተጠጣ፡፡
በመጨረሻ ላይ፤
“ጎበዝ፤ እንግዲህ የሥራ ዘመን ነውና ቀበቶን ጠበቅ ማድረግ ያስፈልጋል! እስቲ ለመጪው ጊዜ ምን ማድረግ እንዳለብን ሀሳብ አምጡ” አለ፡፡
ጦጢት፤
“አያ አንበሶ፤ የተሰባሰብነው እንስሳት አንድ ዓይነት አይደለንም፡፡ አንዳንዶቹ ጨርሰው ከዚህ ቀደም መጥተው የማያውቁ ናቸው! መጥተው የነበሩና አሁን ግን በስንት ጊዜያቸው የመጡ አሉ፡፡ በረባ ባልረባው ከእኔና ከእርሶ ጋር ተቀያይመው ቀርተው የነበሩ አሁን ሀሳባቸውን ቀይረው ድግስ ለመብላት የመጡ አሉ፡፡ ድግሱን ሳይፈልጉት አያ አንበሶን ፈርተው የመጡም ይታያሉ፡፡ ከአያ አንበሶ ጋር አዲስ ፍቅር ያመናቅር ዓይነት ሆነው የመጡ አዲስ ግልብጦችም አሉ፡፡ ድንገት ደራሾች ናቸው፡፡ ብዙ ይበሉ ይጠጡ ይሆናል እንጂ ደህና ሀሳብ አያመጡም፡፡ እንዴት ብለን ተስማምተን አንድ የጋራ ሀሳብ እናመጣለን?” ብላ ተቀመጠች፡፡
“አጨብጭቤም ቢሆን እመለሳለሁ፣ ከድግስ አልቀርም ብሎ የመጣ አለ!” አለ አያ ዝንጀሮ፡፡
አያ ዝሆንም፤
“ሁልጊዜ በሞቀበት የሚዘፍንም ፀበል ሊቀምስ የመጣ አለ፡፡ በቀላሉ አንግባባም!” አለ፡፡
ሁሉም ተራ በተራ እንዲህ ያለ ሀሳብ ሰጡ፡፡ ውጤቱ የማይታወቅ ሁሉም እንስሳ የሚናገርበት ስብሰባ እየሆነ መጣ። የሚዘባርቀው፣ ሙግት የሚወደው፣ አንደበት አለኝ ከኔ በላይ ተናጋሪ ላሳር የሚለው … ሁሉም ልፍለፋ ቀጠለ፡፡ የጨረባ ተዝካር መሰለ፡፡
ጥቂት ቆይቶ ወደ ጠብ አመራ! ዝም በሉ ቢባል ማን ሊሰማ? “ሀሳብ ሥጡኮ ነው ያልኩት” ቢል አያ አንበሶ፣ ማን አደብ ሊገዛ? ሁሉም የኔን ሀሳብ የሚያክል የለም እያለ ጭራሽ ይዋጣልን እስከ መባባል ደረሰ!
ይሄኔ አያ አንበሶ ትዕግሥቱ አለቀ፡፡
“እንግዲህ ሁልሺም አርፈሽ ተቀመጪ፡፡ ትዕግስት ፍርሃት አይደለም፡፡ አዳሜ ትምህርት እንዲሆንሽ፣ ብጥበጣውን በጣም ያበዛውን አያ ነብሮን ምን እንደማደርገው ተመልከቺ” ብሎ ነብሮ ሳያስበው ክፉኛ ደቆሰው፡፡ ነብሮ ተብረክርኮ ወደቀ!
ይሄኔ ጦጢት፤
“ትላንትና ሞቼ በቀረሁ ሳልቀበር
 እኔም የፈራሁት ይሄንኑ ነበር” አለችና “አያ አንበሶ፤ ከእንግዲህ እርሶ ባሉት እስማማለሁ!” ብላ ውልቅ አለች፡፡
ሁሉም “ዓመት ዓመት ያድርሰን! የዓመት እንስሳ ይበለን!”
እያሉ ጦጢት በቀደደችው ወጡ፡፡ አንዳንዶቹ ግን “እሱ ነው! እሱ ነው!” እያሉ ለአያ አንበሶ፤ በጥባጩን እየወነጀሉ፣ አስመዝግበው ተመስግነው ወጡ፡፡
አያ አንበሶም፤ “ለአህያ ማር አይጥማት”፤ ያሉት አባቶቻችን ዕውነታቸውን ነው!” ብሎ አሰናበታቸውና “በሚቀጥለው ዓመት አሳያቸዋለሁ!” አለ በሆዱ፡፡
*   *   *
አለመግባባት ክፉ አባዜያችን ነው! ዘይትና ውሃ አይቀላቀሉም፡፡ ብዙዎች የሚመሳሰሉ ይመስላቸዋል እንጂ ፈታኝ ወቅት ሲመጣ ሀሳባቸውም ይበታተናል፡፡ ዋንኛው ችግር በአካልም በሥነ ልቦናም አለመዘጋጀት ነው፡፡ ለመዘጋጀት የጊዜ ዕቅድ ያስፈልጋል፡፡ በጊዜ፣ በተገቢ ጉዳይ ላይ አስቦ፣ ወጥኖ መነሳትን ይጠይቃል፡፡ ድንገት ተሰብስቦ፤ ድንገት አዲስ ሀሳብ አፍልቆ፣ መልካም ነገር እሰራለሁ ብሎ ማሰብ ከቀናነት አያልፍም፡፡ ቢረፍድም እንኳን ተመሳሳይ ሀሳብ ያለው መሰባሰብ ይኖርበታል፡፡ ልባችን ምንም ያህል ንፁህ ቢሆን ወይ አስቀድመን ስናስብበት የቆየን ያልተዳሰሰ ሀሳብ ከሌለን፣ ወይ አሮጌ ሀሳባችንን በአዲስ አቀራረብ ካላመጣን፣ እንደው በአንድ ጀምበር ሁኔታው አመቺ ስለሆነ በፍጥነት እንለወጣን ብንልም ምኞታችን ይበዛና ተግባሩ ላይ እንሰንፋለን፡፡ ቆይተንም እንወድቃለን፡፡ ስለዚህ ምን ምን ጉዳዮች ያስማሙናልና ወደ ተግባር ያሸጋግሩናል ብሎ ከትንሹ ዕቅድ መነሳት ተገቢ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ያልተመለሱ ጥያቄዎችን በጥሞና መመርመር ዋና ጉዳይ ነው፡፡ እነሱ ላይ አተኩሮ ከስር ከስር በዕቅድ መመለስና እንዲጨበጡ ማድረግ፣ የማይታለፍ እርምጃ ነው፡፡ የተመለሱ የሚመስሉንን ጥያቄዎችም ደግመን መፈተሽ ያስፈልጋል፡፡ ለብ ለብ እንዳይሆኑ፡፡ ለዚህ እንቅፋት የሆኑብንን ጉዳዮች አበጥሮ ማውጣት ተገቢ ይሆናል፡፡ በእኛ አገር “አለባብሰው ቢያርሱ፣ በአረም ይመለሱ” የሚለው ተረት የሁልጊዜ ዕውነት ነው፡፡ አንድም ደግሞ “እርስ በርሱ ሥጋ በኩበት ጠበሱ” የሚለው እውነታ የሚሻል ወይም አመለካከቱ የተለየ ሰው ሳይኖር እንመሳሰላለን በሚል ብቻ አብሮ መዝመት ኋላ ሁኔታው ሲጠራ፣ ከተሰራው ሥራ ውሽልሽልነት ውጤቱ ይታያልና ከወዲሁ ጠንቀቅ ማለት የአባት ነው፡፡
በተደጋጋሚ እንዳወሳነው መንገዶች ሁሉ አልጋ በአልጋ አይደሉም፡፡ እንዲያውም እንደኛ ባለው የፖለቲካ አካሄድ፤ ኮረኮንቹና እሾኻማው ክፍል ሳይበዛ አይቀርም፡፡ አዲስ ሀሳብ የማይጥመው ወገን ይኖራል፡፡ በዱሮው ቋንቋ ወግ - አጥባቂ የሚባለው መሆኑ ነው፡፡ ወንበሩን የተነጠቀው፤ ጥቅሙ የተነካበትና የከመርኩት ሁሉ ተናደብኝ የሚለው ውሎ አድሮ ለሰራው ሁሉ ተጠያቂ እንደሚሆን ስለሚገነዘብ ወይም ስጋት ስለሚኖረው፤ ለህልውናው መታገሉና መፍጨርጨሩ አይቀሬ ነው፡፡ ሆኖም ሶስት ነገሮች ካልተስተካከሉ ሞተሩን ወደ ኋላ መመለስ አዳጋች ነው፡፡ እነዚህም የኃይል ሚዛን፣ የጊዜ ሚዛን እና የነባራዊ ሁኔታ ሚዛን ናቸው፡፡ የኃይል ሚዛን ላዕላይ መዋቅሩ ላይ ካሉት ተዋንያን ወደፊት ልራመድ የሚለውና ወደ ኋላ የሚጎትተው (ያለንበት ሁኔታ ምን አጠፋ? የሚለው) ከሚያደርጉት ፍጭት የሚከሰት ነው፡፡ ይህም ከሂደት እንጂ ከድንገቴ ክስተት የመጣ አይደለም፡፡ የጊዜ ሚዛን ደግሞ ክፉን ከደግ አነፃፅሮ፣ ወቅትን ለክቶ ከሚወሰድ አቋም የሚመነጭ ነው፡፡ “ጊዜው ገና ነው” ወይም “ጊዜው አሁን ነው!” ብሎ የመንቀሳቀስን ዕቅጩነት (Precision) የሚጠይቅ የጥንቃቄ ስሌት ነው። የነባራዊ ሁኔታ ሚዛን ደግሞ ከሁለቱ ከቀደሙቱ ጋር የተሳሰረ ሲሆን፤ ህብረተሰብ በዚህም በዚያም ምክንያት የተጠራቀመ ምሬትና ጥያቄ ሲኖረው፣ ያንን ለማፈንዳት ባመቸው መንገድ ሁሉ ተጠቅሞ ሲያስተነፍሰው የሚመጣ እንቅስቃሴ ውጤት ነው፡፡ ሰለስቱ ሚዛናትን መርምሮ መጓዝ ለብዙ ችግሮች መፍትሔ ይሆናልና አንዘንጋቸው፡፡
“አያሌ አደራዎችን መቀበል ትከሻን ያጎብጣል” ይላሉ አረቦች፡፡ ለብዙኃኑ ደስታ ብለን እሰራለሁ የምንላቸው፣ ቃል የምንገባቸው ሁኔታዎች መልሰው እንዳይጠልፉን ቆም ብለን ማሰብ፣ ውስብስቦቹን ከቀላሎቹ መለየት ያሻናል፡፡ ይሄንን ለመተግበር የሚኖረን ፍጥነት ራሱ ጥንቃቄን ይጠይቃል፡፡ በሰራነው ልንረካ እንችላለን፡፡ ሆኖም ምን ያህል ውሃ የቋጠረና ሥር የሰደደ ስራ ሰርቻለሁ? መሰረቱን በአግባቡ ደልድያለሁ ወይ? ምን ያህል የውጪ ኃይሎች ጣልጋ ገብነት አለብኝ? በቤት ውስጥ ጉዳይ ስጣደፍ፣ የጎረቤቶቼን ነገር እንደምን ይዤዋለሁ? ማህበራዊ መስህብን የመፍጠር አካሄድ ብቻ ላይ ካተኮርኩ ፖፑሊስት (Populist) ያደርገኛል አያደርገኝም? ፍጥነቴን ለመቆጣጠር በተለይ ምን ኃይል መፍጠር አለብኝ? እዚህ ጋ ቁም፣ እዚህ ጋ ሩጥ የሚል አካል አለኝ ወይ? ከስሜታዊነት ከሞቅ ሞቅና ከለብ ለብ ፍጥነት፣ ስክነትን ለመውለድ፤ አቅምንም ላለመጨረስ በብስለት መጓዝ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ “የእነ ቶሎ ቶሎ ቤት ግድግዳው ሰምበሌጥ”ን ልብ ማለት ይበጃል!


--------------

Read 8501 times
Administrator

Latest from Administrator