Saturday, 21 July 2018 12:44

የጭፍንነት፣ የምቀኝነትና የዘረኝነት (የነባር ውሸቶች) ምርኮኛ አንሁን!

Written by  ዮሃንስ. ሰ
Rate this item
(8 votes)

• “Enlightenment Now” የሚል መፍትሄ ያቀርቡት Steven Pinker፣ ዋናዎቹን የዘመናችን በሽታዎች ይዘረዝራሉ!
  1. እውነትን የሚያጣጥልና እውቀትን የሚጥላላ የፖስትሞደርኒዝም ፈሊጥም ሆነ ሃይማኖት ነክ ጭፍንነት...!
  2. ሰዎች፣... እንደማገዶ የሚቆጠሩበት የመስዋዕትነት አስተሳሰብም ሆነ የአካባቢ ጥበቃ ቡድኖች መፈክር...!
  3. በዘር፣ በቋንቋ፣ በትውልድ ቦታም ሆነ በሌላ ሰበብ፣ የግል ህልውናና የግል ማንነትን ጨፍልቆ የማቧደን በሽታ...!
• መፍትሄዎቹስ? Reason, Capitalism, Individualism ናቸው መፍትሄዎቹ ትላለች Ayn Rand። ማለትም ስልጣኔ
 

     የዘረኝነት አስተሳሰብና መዘዞቹ፣ በእጅጉ ከመባባሳቸው የተነሳ፣... የዘረኝነትን አደገኛነት፣ አስፀያፊነትና አጥፊነት፣... በተደጋጋሚና በየቦታው፣ በግላጭና በአካል እያየነው ነው። በጅምላ የመፈረጅ ብሽሽቅ፣ በጅምላ የመወነጃጀል ጥላቻ፣ በጅምላ የመቧደን ዘረኝነት፣... ምንኛ ጨለማ፣ አጥፊና አስቀያሚ እንደሆነ፣ በየጊዜው በግላጭ ስናይ፣... በየጊዜው ዘረኝነትን ማውገዝ፣ አደገኛነቱን መናገር፣ አንድ ቁም ነገር ነው። ነገር ግን፣ የምንመኘው ያህል፣ ብዙም ውጤት እያስገኘልን አይደለም። ለምን? መፍትሄውስ?

“ሁለገብ ሚስጥር፣ ሁለገብ ውስጥ-አዋቂ” - እውነትንና እውቀትን የሚያዋርድ፣ የአሉባልታ ፉክክር!
አንዳንዱ “ሁለገብ ውስጣዋቂ”፣... የዚሁ የአገራችንን ጓዳ ብቻ ሳይሆን፣ የሲአይኤና የኤፍቢአይ ሚስጥሮችን ሁሉ በእጁ ያስገባ ይመስላል - ሲፅፍ። በራሺያ የስለላ ድርጅቶችም ሳይቀር፣  በድሮው ኬጂቢና  በዛሬውም ውስጥ ዋና ቤተኛ፣... የሞሳድና የኤምአይ6 ጭምር ዋና ተጠሪ ሆኖ፣ ጓዳ ጎድጓዳቸውን ሁሉ ሲፈትሽ የሚውል፣ ሚሊዮን የሚስጥር መዛግብቶችን ሲያገላብጥ የሚያድር ይመስላል -  ሲያወራ። ሌላ ተፎካካሪ “ሁለገብ ውስጣዋቂ”ም በበኩሉ፣ በልጦ ለመታየት ይወዳደራል። ከኬጂቢ በላይ ስለሲአይኤ አብጠርጥሮ የሚያውቅ፣ ሲአይኤ ገና ያልደረሰበት የሞሳድ ሚስጥር ሳይቀር ለሱ በቀላሉ የሚገለጥለት “ተዓምረኛ ውስጣዋቂ” ሆኖ ይፅፋል፣ ያወራል። የመንግስት ካቢኔ ውስጥ የተቀመጡ የሚስጥር ሰነዶችን፣ የመከላከያ ወይም የፖሊስ የሚስጥር መዝገቦችን ብቻ ሳይሆን፣... ለሚቀጥለው ዓመት የሚፈጠሩ ሚስጥሮችን ሁሉ ከፖሊስና ከመንግስት ቀድሞ የማወቅ ልዩ ሃይልና “ማስተር ኪ” የተሰጠው ያስመስላል።
የሚስጥር ውሳኔዎችን፣ ድብቅ እቅዶችን፣ ማንም የማያውቃቸው በስውር የተካሄዱ ዘመቻዎችንና ድርጊቶችን ሁሉ፣ በእጁ ውስጥ የገቡለት ይመስል፣... በትረካ ወይም በሕልም ስታይል፣ በምሬተኛ ወይም በአዝማሪ ስታይ፣ በምስራች ወይም በትንቢተምፅአት ስታይል ያወራል። ሌላኛው “ሁለገብ ውስጣዋቂ”ስ? በስም የሚታወቁ ሰዎችን እንደ ተዋናዮች እያነሳ ትንግርተኛውን ታሪክ ዘርግፎ ይተርካል - እንደ ድራማ። የማጋነንና የማምታታት ፉክክር፣ የውሸትና የአሉባልታ እሽቅድምድም፣ የመበላላት ቁማር መስሎ ይታያቸዋል። እውነትን መናገር፣ በየዋህነት መበለጥ ሆኖ ይሰማቸዋል። ለምን?
“እርግጠኛውን እውነት ለመካድም ሆነ ሃሰትን ተፈናጥጦ ለመጋለብ አለመፍቀድ”፣ “እውነትን መያዝና ለእውነት ታማኝ መሆን”፣ “እውነትን በሚገነዘብ የራስ አእምሮና በእውቀት ብርሃን መመራት”፣ “ለእውነት የመቆምና ለእውቀት የመትጋት ፅናት”፣... ስራህን በሃቅ፣ ኑሮህን በእውነት መንገድ ማከናወን፣ ለዚህም ጠንካራ ሰብዕና ማነፅ... ይሄ ይሄ ሁሉ፣ ለይስሙላ ብቻ የካልሆነ በቀር ፍሬ የሌለው፣ የማያዋጣ አላዋቂነት መስሎ ይታያቸዋል - ለብሽሽቅ ተፎካካሪዎች፣ ለ”ሁለገብ ውስጣዋቂዎች”።
ራስን “በእውነት መንገድ” መምራት፣... “የውሸት የውሸት” ሆኖ ይሰማቸዋል። እናም፣ ውሸትን የመፈልፈልና አሉባልታን የማሰራጨት እሽቅድምድም ውስጥ ይገባሉ - እውነትን እያሰመሰሉ።
ራስን በራስ ለመምራት “በተረጋገጠ እውቀት ላይ መተማመን”፣... “አላዋቂነት” ይሆንባቸዋል። ጭፍን ፍረጃና የጅምላ ውንጀላ እንደ ስራ ይያያዙታል - “እውቀትን የሚያዋርዱ፣ ሁለገብ ውስጣዋቂዎች”።
አንዱ “ሁለገብ ውስጣዋቂ”፣ እንደ ቀለድ ጀማምሮት፣ ወደ ብሽሽቅ ይዘቅጥና ይብስበታል። “ሰው አያውቅም እንጂ፣ ፀሐይ የጠለቀችውኮ፣ በመንግስት ድብቅ ተንኮል ነው”... የሚል የውንጀላ መዓት ያወርዳል። “የነሱ ተንኮል፣ እኛ ላይ...” በማለት ጭፍን ውንጀላውን፣... ወደ ጭፍን የጅምላ ውንጀላ ያሳድገዋል። በጅምላ፣... “የጠላትና የወዳጅ ጎራ” ለማቧደን ይዘምታል።
ይኸኔ፣ ሌላኛው ተቀናቃኝ “ሁለገብ ውስጣዋቂ”፣ አፀፋ ለመመለስ አመቺ የብሽሽቅ ሰበብ አገኘ ማለት ነው። “መንግስት፣ ሙያ በልብ ብሎ በሚስጥር ባይሰራ ኖሮ ፀሐይ እንዲህ ደምቃ አታበራም ነበር”... የሚል አይነት አድናቆት ያጎርፋል። “መንግስት፣ ሰው አያውቅለትም እንጂ፣ ያለ እረፍት ለኛ ሲሰራ፣... እነዚያ ለተንኮል የማይተኙልን ግን”... እያለ፣ ጠላትና ወዳጅ በመንጋ የማቧደን ዘመቻውን ያጋግለዋል።        
የስልጣኔ መሰረቶች፣... “እውነት፣ አገናዛቢ አእምሮና እውቀት”፣... እንደ የዋህነትና እንደ ድክመት ወደሚቆጠሩበት፣ ወደባሰበት ኋላቀርነት በተንሸራተትን ቁጥር፣ ውሸትና አሉቧልታ፣ ብሽሽቅና ስድብ፣ ጭፍን ውንጀላና የጅምላ ፍረጃ፣... በመንጋ የማቧደንና የማንጋጋት ፉክክር ይቀጣጠላል። በመንጋ የማቧደኛ ሰበቦች ደግሞ እልፍ ናቸው። ብዙውን ጊዜ ግን፣ ከነእልፍ ቅርንጫፎቻቸው ጋር፣ ዋናዎቹ የጭፍን ጥላቻ ሰበቦች፣ ሦስት ናቸው።

ሦስቱ የጭፍን ጥላቻ አጥፊ ሰበቦች!
አንደኛው ሰበብ፣ በአስተሳሰብ ዙሪያ፣ ውሸትን እንደአስተማማኝ መሳሪያ የመቁጠር ሱስ ነው። “እውነትና እውቀት... ጊዜ አልፎባቸዋል” የሚል ፈሊጥ የሚራገብበት የፖስትሞደርኒዝምና የፖስትትሩዝ ዘመን ተጨምሮበት፣ የአሉባልታና የፕሮፓጋንዳ ሱስ፣ እንዲሁም፣ ሃይማኖት ነክ ጭፍን እምነትን ያካትታል - የመጀመሪያው የማቧደኛ ሰበብ! (ይሄ፣ “አእምሮንና ሃሳብን፣ ከእውነታ የማፋታት ጭፍንነት ነው”)።
ሁለተኛው ደግሞ፣ በአኗኗር ዙሪያ፣ “የሃብት ክፍፍል” ወይም “የሃብት እኩልነት” የሚል ነባር የማቧደኛ ሰበብ ነው። ላለፉት 40 ዓመታት እንዳየነው፣ በዩኒቨርስቲ ኮሙኒስት አብዮተኞችና በደርግ ዘመን፣ “በዝባዥ ቡርዡዋ” የሚል ጅምላ ውንጀላ፣... ከዚያም በኢህአዴግ ዘመን “ኪራይ ሰብሳቢ” የሚል ድፍን ማጣጣያ፣ የዚህ ሰበብ ምሳሌዎች ናቸው። የእነዚህ ሁሉ ስረመሰረት ግን፣ አንድ ነው። ከጥንት እስከዛሬ ጨርሶ ያልተዳፈነውና ያልበረደው፣ ለምዕተዓመታት የዘለቀው፣ “ራስ ወዳድ” የሚል የውንጀላና የምቀኝነት መፈክር ነው ስረመሰረታቸው። እያንዳንዱ ሰው እንደማገዶ እየተቆጠረ፣ ራሱን ንብረቱን፣ ለመስዋዕትነት እንዲያቀርብ የሚያስገድድ ነው - መፈክሩ። ንብረቱን ይዞ ለመቀጠል የፈለገ ሰው ግን፣... ንብረቱን ያገኘው በዝርፊያ ይሁን አይሁን፣ ሰርቶ ያፈራው ይሁን አይሁን ልዩነት የለውም - ሃብት ማፍራትም እንደ ጥፋት የሚቆጥር የማቧደኛ ሰበብ ስለሆነ።
ሦስተኛውና በዘመናችን እጅጉን የገነነው የማቧደኛ ሰበብስ?
በየእለቱ ለዓመታት ያየነውና እየተባባሰ የመጣው በሽታ፣ በዘር የመቧደን የጅምላ ቅስቀሳ አይደል? በዘር የመቧደን በሽታ... ከነትብታቡ (በቋንቋ፣በ ጥንታዊ ልማድ፣ በትውልድ ሃረግ ወይም በትውልድ ቀበሌ፣ ወዘተ...) ነው ሦስተኛው የጥፋት ጎዳና።

አለምን የሚያተራመሱና የሚያቃወሱ 3 በሽታዎች!
ደረጃው ይለያያል እንጂ፣ እነዚህ ሦስት በሽታዎች፣ የአገራችን ብቻ ችግሮች አይደሉም። አዎ፣ ከሶሪያ እስከ የመን፣ ከዩክሬን እስከ ቬኔዝዌላ፣... በርካታ አገራትን እያፈራረሱና እያተራመሱ፣ ሚሊዮኖችን ለድህነትና ለስደት፣ በርካታ ሺዎችን ለሞት የሚዳርጉ የጥፋት መንገዶች ናቸው። ባለፈው ሳምንት ዘኢኮኖሚስት እንደዘገበው፣ በሶሪያ ትርምስ ብቻ፣ 500ሺ ሰዎች ሞተዋል። ከ24 ሚሊዮን የሶሪያ ነዋሪዎች መካከል፣ ወደ 12 ሚሊዮን ገደማ ሰዎች ከመኖሪያ ቤታቸው ተፈናቅለዋል፣ ተሰደዋል።
ነገር ግን፣ ኋላቀር አገራት ብቻ ሳይሆኑ፣ በእውቀት፣ በብልፅግናና በስልጣኔ ደህና የተራመዱት የአሜሪካና የአውሮፓ አገራትም ጭምር፣ ለቀውስ እየተዳረጉ ነው። የአውሮፓ ነባር ፓርቲዎች ግራ እስኪጋቡ ድረስ፣ በፈረንሳይ፣ በጣሊያን፣ በስፔን፣ በግሪክ፣ በአውስትሪያ በተከታታይ እንደታየው፣... አመት ሁለት ዓመት ያልሞላቸው ፓርቲዎች፣ አንዳንዶቹ ነውጠኛ ፓርቲዎች፣ አንዳንዶቹ ደንባራ ፓርቲዎች፣ አንዳንዶቹ ሃይማኖትን እንደመቀስቀሻ የሚጠቀሙ፣ አንዳንዶቹ ኮሙኒስዝምን፣ አንዳንዶቹ ዘረኝነትን የሚቆሰቁሱ ፓርቲዎች ድንገት እየገነኑ አውሮፓን በተከታታይ ሲቃውሱ እየታየ አይደል?
“Enlightenment Now” በሚል ርዕስ ታዋቂው ምሁር Steven Pinker በቅርቡ ያሳተሙት መፅሐፍ፣ በአሜሪካና በአውሮፓ ትኩረት ያገኘውም፣ ይህንን የዘመናችን ቀውስ የሚዳስስና የመፍትሄ ሃሳቦችን የሚያቀርብ ስለሆነ ነው። ዋና ዋናዎቹን የቀውስ መንስኤዎች ይዘረዝራሉ።
አንደኛ፣... ሃይማኖት ነክ ጭፍን እምነትና በዩኒቨርስቲዎች የተስፋፋ የፖስትሞደርን ፈሊጦች፣... እውነትን፣ አእምሮንና እውቀትን የሚያጣጥሉ ናቸው፤ ለጥፋትም ይዳርጉናል ብለዋል - ጸሐፊው።
ሰዎች፣... እንደማገዶ የሚቆጠሩበት የመስዋዕትነት አምልኮ ሳቢያም፣ ዘግናኝ ጥፋቶች ተፈጥረዋል።  ከመቶ ሚሊዮን በላይ ሰዎች በረሃብና በአፈና ለሞት እንደተዳረጉም ጸሐፊው ይዘረዝራሉ። የአካባቢ ጥበቃ ቡድኖች መፈክር ደግሞ፣ ሰዎችን ለእፀዋት መስዋዕት የሚያደርግ ሆኗል ሲሉ ገልፀዋል።
መፍትሄውስ? ሰዎችን እንደማገዶ መስዋዕት እያደረገ የሚያከስል አገር ሳይሆን፣ ሰዎች በነፃነት ሰርተው ኑሯቸውን የሚሻሽሉበት፣ የሚገበያዩበትና በፈቃደኝነት የሚደጋገፉበት አገር ነው - ስልጡን አገር።
በዘር አልያም በሌላ ሰበብ የግል ማንነትን ጨፍልቆ የማቧደን በሽታም ሌላኛው በሽታ እንደሆነ ጠቅሰዋል - ጸሐፊው።
Ayn Rand ራንድም ከአመታት በፊት፣ ዓለማችን የሚያቃውሱ ዋነኛዎቹ ነቀርሳዎች፣ ከነትብታባቸውና ቅርንጫፎቻቸው ብዙ ቢሆኑም፣ ከሦስት ስረመሰረቶች የሚፈለፈሉ መሆናቸውን ጠቅሳለች፤ mysticism, altruism, collectivism።
መፍትሄዎቹስ?  Reason, Capitalism, Individualism ናቸው መፍትሄዎቹ። ይህንንም በበርካታ መጻህፍቷ አስረድታለች፣ አሳይታለች።
 የSteven Pinker መጽሐፍም እንዲሁ፣ ለበርካታ አመታት እየተዘነጋና እየተንቋሸሸ ሲሸረሸር የነበረውን የስልጣኔ ጎዳና እንደገና ዛሬ ማደስና አጥብቀን መያዝ እንዳለብን ይገልፃሉ፣ ከነርዕሱ  “Enlightenment Now” በሚለው አዲስ መጽሐፋቸው።
እውነትና አእምሮ፣ እውቀትና ሳይንስ ትልቅ ክብር ባገኙበት ዘመን፣... ከፍተኛ የእውቀትና የነፃነት ግስጋሴ፣ ታይቶ የማይታወቅ የኑሮ እድገትና የብልፅግና ለውጥ፣ በታሪክ እጅግ የተሻለ የሰላምና የመከባበር ስልጡን መንፈስ ታይቷል ሲሉ የስልጣኔ ዘመንና ያስገኛቸውን በረከቶች በአስደናቂ ዝርዝር መረጃዎች ያሳያሉ (the Age of Reason፣ the Age of Enlightenment እና በረከቶቹ)።
ያለግልፅ መፍትሄ፣ ዘረኝነትንና መዘዞቹን ማሸነፍ አይቻልም!
አዎ፣ ከላይ እንደገለፅኩት፣ ዘረኝነት (በጅምላ የመፈረጅ ብሽሽቅ፣ በጅምላ የመወንጀል ጥላቻ፣ በጅምላ የመቧደን ዘረኝነት) ምንኛ ጨለማ፣ አጥፊና አስቀያሚ እንደሆነ፣ በየጊዜው በግላጭ ስናይ፣... በየጊዜው ዘረኝነትን ማውገዝ፣ አደገኛነቱን መናገር፣ አንድ ቁም ነገር ነው።
ነገር ግን፣ ዘረኝነትና መዘዙ፣ ለተወሰነ ጊዜ ረገብ ረጋ ሲል፣ በዚያው መጠን አደገኛነቱ ይዘነጋል። ዛሬ ዛሬማ፣ በጥቂት ቀናት፣ ሳምንት ሳይሞላ፣ ነገሩን ሁሉ መዘንጋት ተለምዷል።
በዚያ ላይ፣ ትንሽ ትንሽ፣ መጠኑ ሳያልፍ፣ ዳር ዳሩን፣ እና እያሰለሱ ዘረኝነትን ማስተጋባትና መቀስቀስ፣ እንደ “ኖርማል” ቢቆጠር ችግር የለውም ብለው ራሳቸውን የሚያታልሉ ወይም ብልጣብልጥነት የሚመስላቸውና ራሳቸውን እንደ “ምርጥ ቁማርተኛ” የሚያዩም አሉ። በትንሹ ተመጥኖ፣ በትንሽ አካባቢ ብቻ ታጥሮ፣ ለአፍታ ብቅ ጥልቅ እንዲል በጊዜ ተገድቦ ሊቆይ አይችልም። ዘረኝነት፣ የአስተሳሰብ ቅኝት ነውና፣ ተመጥኖ፣ ታጥሮ፣ ተገድቦ አይዘልቅም። ምርጥ ቁማርተኞች እየበረከቱ፣ መበላላት እየጦፈ ይሄዳል። ዘረኝነትን እያስተጋቡ፣ ዘረኝነትን መቆጣጠር አያዛልቅም። ለዚህም ነው፣ አንዳንዶቹ፣ ወደ ለየለት ዘረኝነት የሚገቡት - “የመጣው ይምጣ” ወደሚል ክፋት ይዘቅጣሉ።
አንደኛው ችግር፣ የየዋህነት ዝንጋታ ነው። ሁለተኛው ችግር፣ እንደ ብልጥ ቁማርተኛ “የተመጠነ ዘረኝነት” በሚል ስሜት ጀምረው፣ ብዙም ሳይቆይ በለየለት ዘረኝነት ወደ መጠፋፋት እንደሚያደርስ አለመገንዘብ ነው።
ሦስተኛው ደግሞ፣ ዘረኝነትን መቃወም፣ ለመከላከልም መሞከር ብቻውን፣ ትንሽ ፋታ ለማግኘት ይረዳል እንጂ፣ ለዘለቄታው ሁነኛ ፍቱን መፍትሄ አይደለም።
የዘረኝነትን የአስተሳሰብ ቅኝት የሚተካ እውነተኛና ትክክለኛ፣ ውጤታማና አስተማማኝ የአስተሳሰብ ቅኝት በግልፅ ታውቆ፣ በቅጡ ተይዞ ጎልቶ ሲወጣ አይታይም። ለዚህም ነው፣ የዘረኝነት መዘዝ በአፍታ እየተዘነጋ፣... በነጋታው እየቀሰቀሰ፣... ግራ የሚያጋባን።
ከእለት ተእለት ባሻገር ለማየት አለመቻል፣ ከአንድ ከሁለት ጉዳይ በተጨማሪ ለማገናዘብ አለመቻልና አለመፍቀድ፣... በተለይ በተለይ ደግሞ፣... ከዘረኝነት የሚያላቅቅ እውነተኛ አስተሳሰብን ከምር ለመያዝ እንደሚቻል አለማወቅና አለመፈለግ።

Read 5600 times