Saturday, 21 July 2018 12:42

የመደመር ፍልስፍና! (ከሥነ ፍጥረት እስከ ዘረ-መል ምህንድስና)

Written by  ጥላሁን ተስፋዬ (ዶ/ር) (አ.አ.ዩ ፊዚክስ ዲፓርትመንት)
Rate this item
(15 votes)

 “--ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዘመናት አብሮነታቸው አንዱ ከሌላው ጋር ባብዛኛው በጎ መስተጋብር ነበራቸው፡፡ በበጎ ስራዎች ተደምረው የትየለሌ የሆነ ቁሳዊና መንፈሳዊ ሃብት ፈጥረዋል፡፡ ከሁሉም በላይ በደም የተደመሩ ናቸው፡፡--”
      
     ባለፉት ሦስት ወራት፣ በየሰው አንደበት በመዘውተር ላይ ከሚገኙትና በሃገራችን እየታየ ያለውን በጎ መንፈስና ሀገራችንን ወደ ቀደመው ታላቅነቷ የማሸጋገር ተስፋ ገላጭ ከሆኑት ቃላት መካከል መደመር (ደ ይጠብቃል) የሚለው ቃል ይገኝበታል፡፡ ይህ አዎንታዊ ሁነት ስንሰማውና ስንጠቀምበት የኖርነውን ቃል እንደገና ለመመርመርና በተለያዩ አገባቦቹ ያሉትን በርካታ ትርጉሞች ለመረዳት የሚገፋፉ ሁኔታዎችን ፈጥሯል፤ እንዲሁም ስለ መደመር ጽንሰ ሀሳብ ለማወቅ እድል የሰጠ ከመሆኑም በተጨማሪ ለዚህ አነስተኛ መጣጥፍም መነሻ ሆኗል፡፡
መደመር፤ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናት ምርምር ማዕከል በ1993 ዓ.ም ባዘጋጀው መዝገበ ቃላት ውስጥ ደመረ ከሚለው ግስ የሚገኝ ሲሆን ደመረ፤ ሰበሰበ፣ አካበ፣ አከማቸ፣ አንድ ላይ አጠቃለለ በሚሉ ትርጉሞች ይገልጸዋል፡፡ በሒሳብ (አልጀብራ) ውስጥ ደግሞ ከአራቱ የሒሳብ መደቦች አንዱ የሆነና ልዩ ልዩ መጠን ያላቸውን አሃዞች በአንድ ላይ አጠቃሎ የመቀመር ዘዴ የሚል ተጨማሪም ፍቺ በመስጠት ያብራራዋል፡፡
በአልጀብራው የመደመር ፍቺ፤ተደማሪዎች ሁለትና ከሁለት በላይ ተመሳሳይ ነገሮች ወይም መጠኖች መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ ለምሳሌ 3 ብርቱካኖች ላይ 4 ብርቱካኖች ሲደመሩ ተመሳሳይ ነገሮችን መደመር ነው። ይህ የመደመር ፍቺ ጠባብ በመሆኑ 3 ብርቱካኖች ላይ 4 ሙዞችን መደመርን አይፈቅድም፡፡ ሆኖም ይህ ጠባብ የመደመር ትርጓሜም ቢሆን ብርቱካኖችና ሙዞችን የጋራ በሆኑ መጠኖች ወይም መጠሪያዎች በኩል መደመርን ይፈቅዳል፡፡ ለምሳ 3 ብርቱካኖችና 4 ሙዞች የያዘ ከረጢት በድምሩ 7 ፍራፍሬዎች ይዟል ብለን፣ ለብርቱካንም ለሙዝም የጋራ በሆነው የፍራፍሬነት ባህርይ ልንደምራቸው የመደመር ሒሳባዊ ፍቺ ይፈቅዳል፡፡ ብርቱካንና ሙዝ የሚጋሯቸው ሌሎች በርካታ ባህርያት አሉ፡፡ ከነዚህ የጋራ ባሕርያት መካከል ክብደት አንዱ ነው፡፡ በዚህ የጋራ ባህርይ አማካይነት የ3 ኪሎ ግራም ብርቱካንና የ4 ኪሎ ግራም ሙዝ ድምር ክብደት 7 ኪሎ ግራም ይሆናል በማለት ልንደምራቸው እንችላለን፡፡
በዚህ አነስተኛ ጽሑፍ ለመመልከት የተፈለገው ሰፋ ያለውን የመደመር ጽንሰ ሀሳብ ነው፡፡ ሰፋ ያለው የመደመር ጽንሰ ሀሳብ ከላይ እንደተጠቀሰው ሒሳባዊ የመደመር ፍቺ፣ በአሃዞች በሚገለጹ ባህርያት ብቻ የተገደበ አይደለም፡፡ በዚህ ፍቺው መደመር የሚያስገኛቸው፣ በተደማሪዎች ውስጥ የማይገኙ ነገር ግን በተደማሪዎቹ መስተጋብር በድምሩ ውስጥ የሚፈጠሩ አዳዲስ ባህርያትንና ሁነቶችን ሁሉ ያካትታል፡፡ ይህ ማለት አንድ ሲደመር አንድ ከሁለት በላይ እንደማለት ያህል ነው፤ በዚህ ፍቺ፣ የመደመር ፍቺ፣ ጠቅላላው ከተደማሪዎቹ ድምር ይልቃል (The whole is more than the sum of its parts) ከሚለው የአሪስቶትል አባባል ጋር የሚገጥም ነው፡፡
መደመር በአገራችን በአሁኑ ጊዜ የሚነገርበት አግባብ፣ ይህንኑ ሰፋ ያለውን የመደመር ጽንሰ ሀሳብ መሰረት ያደረገ ስለሆነ፤ ከስነ ፍጥረት እስከ ማህበረሰብ ያሉ አንዳንድ ምሳሌዎችና ይህንኑ ሰፊ የመደመር ጽንሰ ሀሳብ አስረጂ የሆኑ ምልከታዎች ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡  
ውኃ ያለውን ሀይድሮጅንና ኦክስጅን የላቸውም፤ እነሱ ግን ውኃ ውስጥ አሉ፡፡
በሁለንተና (ዩኒቨርስ) ውስጥ ህይወት እንዲኖር ያስቻለው ውሃ፤ ከሁለት አይነት የጋዝ እኑሶች (ሀይድሮጅንና ኦክስጅን አቶሞች) ድምር የተገኘ ነው፡፡ የኬሚስትሪ ባለሙያዎች የውሃን አፈጣጠር በሚከተለው ቀመር ይገልጹታል፡፡
H2+0 = H2O
ሁለት ሃይድሮጅን አቶሞችና አንድ የኦክስጅን አቶም ሲደመሩ አንድ የውሃ ሞለኪዩል ይሆናሉ። የሃይድሮጅንና የኦክስጅን ድምር የሆነው ውሃ፤ ሃይድሮጅንና ኦክስጅን በተናጠል የሌሏቸው በርካታ ባህርያት አሉት፡፡
ሀይድሮጅን ለብቻው ነዳጅ ነው፡፡ ኦክስጅንም የሚነዱ ነገሮች ሁሉ እንዲቀጣጠሉ የሚያደርግ ነው፡፡ የሁለቱ ድምር የሆነው ውሃ ግን እሳት ማጥፊያ ነው፡፡
ውሃ ከብዙ ልዩ ቁሶች የተለየ ባህሪ ያለው ነው። ከ4 ዲግሪ በታች ሲቀዘቅዝ የመስፋፋት ልዩ ባህርይ አለው፡፡ ይህ ባህርይ ባይኖረው ኖሮ ውሃ የውስጥ ፍጥረታት ህልውና ሊኖራቸው አይችልም ነበር፡፡
ውሃ ያለው ሙቀትን የማቀብ ችሎታ ነው መሬትን እንደነ ማርስና ከማርስ ማዶ እንዳሉ ፕላኔቶች ግዙፍ ቀዝቃዛ አካል ከመሆን የታደጋት፡፡ ይህ ባህርይ ነው በሞተሮችና ሃይል ማመንጫዎች ውስጥ ውሃን ለማቀዝቀዝ እንድንጠቀምበት ያስቻለው፡፡
ስለዚህ እነዚህና ሌሎችም ያልዘረዘርኳቸው የውሃ ባህርያት ሃይድሮጅንና ኦክስጅን ለብቻ ሲሆኑ የሌሏቸው በመደመራቸው ግን ካለመኖር ወደ መኖር የሚመጡና ድምር በሆነው ውሃ ውስጥ ብቻ የሚገኙ ናቸው፡፡ በኬሚካላዊ መንገድ ውሃ ወደ መሰረታዊ አቶሞቹ ሲለይ፣ ሀይድሮጅንና ኦክስጅን የየራሳቸው ባህርያትን እንደያዙ መገኘታቸው በመደመር ህልውናቸው አለመጥፋቱን አመልካች ሲሆን መለያየቱ ግን የመደመር ውጤት የሆኑትን የውሃ ባህርያት ያጠፋል፡፡
ነጭ ብርሃን የቀለማት ድምር ነው፡፡ ቀለማት በትክክል የሚታዩት በነጭ ብርሃን ነው፡፡
መደመር ሰፋ ባለው ትርጉሙ የሚታይበት ሌላው ተፈጥሮአዊ ክንውን የተፈጥሮ ብርሃን የሚባለው ነጭ ብርሃን ህልውና ነው፡፡ ከፀሐይ የሚመጣው ተፈጥሯዊ ነጭ ብርሃን፣ ብዙ ቀለም ያላቸው ብርሃናት ድምር እንጂ በራሱ ህልውና የለውም፡፡ ቀለማቱ ሲደመሩ ነጭ ቀለምን ያስገኛሉ፤ ካልተደመሩ ግን ነጭ የሚባል ብርሃን በራሱ ህልው አይደለም፡፡
ተፈጥሮና የሰው ልጅ እነዚህን ቀለማት በተለያዩ ሁኔታዎችና መጠን በመቀላቀል በህብረ ቀለማት ውበትን ይገልጻሉ፡፡ ለምሳሌ ቀስተደመና ብለን የምንጠራው ውብ የተፈጥሮ ክስተት የሚፈጠረው፣ ነጭ ብርሃንን ያስገኙት ባለ ቀለም ብርሃናት በአየር ውስጥ በሚገኙ የውሃ ጠብታዎች አማካይነት ራሳቸውን ሲገልጹ ነው፡፡ በተጨማሪም በፀሐይ መግቢያና መውጫ አድማስ ላይ የምናያቸው ቀለማት፣ የሰማይ ሰማያዊ ቀለም፣ በሰሜንና ደቡብ ዋልታዎች የሚታዩ የቀለማት ተፈጥሮአዊ ትእይንቶች የሚነግሩን፣ በነጭ ቀለም ውስጥ ተደምረው የሚገኙት ቀለማት ድምር በሆነው ነጭ ቀለም ውስጥ ህልውናቸው እንደተጠበቀ መቆየቱን ነው፡፡ የሰው ልጅም ቀለማት እየደመረ በማዋሃድ፣ የተዋሃዱትን እየለያየና በተለያየ መንገድ እንደገና እየሰበሰበ፣ በስዕል ጥበብ አማካይነት ራሱንና አካባቢውን ይገልጻል፣ ያሸበርቃል፣ መንፈሱን ያረካል፡፡
የብዙ ቀለሞች ብርሃኖች ድምር የሆነው ነጭ ብርሃን፣ በተደማሪዎቹ ውስጥ የማይገኙ የራሱ የሆኑ ልዩ ባህርያት አሉት፡፡ ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል፡-
ዐይናችን የሚያያቸው ነገሮች በትክክለኛ ቀለማቸው የሚታዩን የቀለማት ሁሉ ድምር በሆነው ነጭ ብርሃን (የተፈጥሮ ብርሃን) ስንመለከታቸው ብቻ ነው፡፡ ቀለም ባላቸው የብርሃን ምንጮች ተጠቅመን ስንመለከት የምናያቸው ነገሮች በትክክለኛ ቀለማቸው ሊያሳዩን አይችሉም፡፡ ለምሳሌ አረንጓዴ ቀለምን በቀይ ብርሃን ውስጥ ብናየው፣ የሚታየን ጥቁር ሆኖ ነው፡፡ ይህ እንግዲህ አባላቱ የሌላቸው ድምራቸው ግን አለው ማለት ነው፡፡
አረንጓዴ ተክሎች ፎቶ ሲንተሲስ በሚባል ሂደት ምግብ የሚፈጥሩት ነጭ ብርሃንን ተጠቅመው ነው፡፡
ሥርዓት (ሲስተም) ተብሎ የሚጠራ ቅንብር ሁሉ ከመደመር የሚገኝ ነው፡፡
  የሰው አካል ክፍሎችን በቅርበት ስንመለከት ስርአተ ትንፈሳ፣ የደም ዝውውር ስርአት፣ የነርቭ ስርአት ወዘተ የሚባሉ ንኡስ ስርዓቶች ድምር ነው፡፡ እነዚህን ስርአቶች የሚያስገኙት የአካል ክፍሎቻችን እያንዳንዳቸው በየራሳቸው የስራ ድርሻ እጅጉን የተራቀቁ፣ የበለፀጉና ውስብስብ ስራዎችን የሚከውኑ ናቸው፡፡ የሰው ልጅ አእምሮ ከፍተኛው የመዳበር (የማደግ) ከፍታ የተቀዳጀ የቁስአካል አይነት ነው፡፡ ጉበትን የሚወዳደር ውስብስብ የኬሚካል ላቦራቶሪ እንደሌለ ይታወቃል፤ ዘመናዊ ተደርገው የሚታሰቡ መቅረጸ ምስሎች ከሰው ዐይን ጋር ሲነፃፀሩ በብዙ መመዘኛዎች በርቀት አንሰው ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን እነዚህ ድንቅና ምጡቅ ችሎታ ያላቸው የአካል ክፍሎች ካልተደመሩና በመደመራቸው የሚመጣው መስተጋብርና መቀናበር ከሌለ በስተቀር ለየብቻቸው የሰው አካልን የመሰለ አስደናቂ ሲስተም ሊያስገኙ አይችሉም፡፡ በዚህ ምሳሌ ደግሞ የአካል ክፍሎች የመደመራቸው ውጤት ከሆነው ሰው፣ ህልውና ውጭ በራሳቸው ህልውና እንደሌላቸው እንረዳለን፡፡
ስርዓተ ፀሐይ (ሶላር ሲስተም) የሚባለው ትልቁ መኖሪያችን፤ መሬታችን ህይወትን ለማኖር የሚያስችሉ ባህርያት እንዲኖራት ማድረጉ መሬት ብቻዋን ወይም ጸሐይ ብቻዋን ያስገኙት አይደለም፡፡ ይህ የመሬት ህይወትን የማኖር ባህርይ ሁሉም የጠፈር አካላት ተደምረው ያስገኙት ነው፡፡ ሁለንተና በስርዓት የሚመራ የበርካታ ነገሮች ህብር መሆኑንና ይህን ህብር የሚያስገኙት አካላትም በመደመር በሚፈጥሩት ስርዓት ውስጥ ይኖራሉ፡፡ ይህ ስርዓት በመኖሩ ምክንያት ተፈጥሮን መረዳት የምንችል መሆኑን ለመግለጽ አንስታይን የሚከተለውን ብሏል፡፡
“ስለ ተፈጥሮ የማልረዳው (የማይገባኝ) ነገር፤ ልንረዳት (ልትገባን) የምትችል የመሆኗ ነገር ነው፡፡”
ተፈጥሮን የምንረዳው በተፈጥሮ አካባቢ ያሉ ነገሮች ሁሉ ተደምረው፤ ከመደመራቸው የሚመነጨው መስተጋብር ስርዓት የሚፈጥርና በስርዓትም የሚመራ በመሆኑ ነው፡፡ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ይህንን ስርዓት ተገንዝቦ፣ ለሰው ልጅ ጥቅም ስራ ላይ የማዋል ክንውን ነው፡፡
የጉልበት (ኢነርጂ) መታቀብና መለቀቅ ስረ- መሰረቱ የአቶሞች መደመርና መደመሩን የሚከተለው መስተጋብር ነው፡፡
ከምግብ ዓይነቶች ጀምሮ በአሁኑ ጊዜ የምንጠቀምባቸው ነዳጅ ዘይት፣ ሃይድሮ ኤሌክትሪክ፣ ማገዶ፣ የነፋስ ጉልበት የመሳሰሉት የኢነርጂ ምንጮች ሁሉ ስረ መሰረታቸው የፀሐይ ጉልበት ነው፡፡ ፀሐይ ባትኖር ውሃ በመትነን ደመና አይፈጥርም፤ ደመና ከሌለ ዝናም የለም፤ ዝናም ባይኖር የምንገድባቸው ወንዞች የሉም፤ ስለዚህ ሃይድሮ ኤሌክትሪክ ኢነርጂ ብሎ ነገር የለም፡፡ ነዳጅና ነፋስም ማገዶን ጨምሮ መሰረተ አመጣጣቸው ከፀሐይ ጉልበት እንደሆነ መሰረታዊ ሳይንስ ይነግረናል፡፡
ፀሐይ ራሷ እጅግ ግዙፍ የጉልበት (የኢነርጂ) ምንጭ የሆነችበት ምስጢር በውስጧ የሚገኙ ሀይድሮጅንና ሂሊየም የተሰኙ አቶሞች መደመር (ፊዩዥን ሪአክሽን) ምክንያት የሚመጣው ጉልበት ነው፡፡ የሰው ልጅ በመሬት ላይ ይህን ጉልበት በሙከራ ደረጃ መፍጠር የቻለ ቢሆንም ከግማሽ ምዕተ አመታት ጥናትና ምርምር በኋላም አቶሞችን በመደመር ለሰላማዊ ጥቅም ጉልበት የማመንጨት ክንውን ፍሬ ያፈራ ዘንድ ብዙ የቴክኖሎጂ ጉዞ ይቀረዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ሳይንስና ቴክኖሎጂ አለም ውስጥ የየሃገሩ ሳይንቲስቶች ሁሉ ተደምረው ከሚያካሂዷቸው ጥናትና ምርምሮች መካከል አቶሞችን በመደመር ሀይል ማመንጨት የሚቻልባቸውን አስቻይ ሁኔታዎች የሚፈትሸው ጥናትና ምርምር በተሰማራበት የሰው ኃይልና በሚፈስበት መዋዕለ ንዋይ ብዛት በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ነው፡፡
እዚህ ላይ አስገራሚው ነገር አቶሞችን በማፈራረስ ኃይል ማመንጨት፤ በተነፃፃሪ ቀላል መሆኑ ነው። አቶሞችን በማፈራረስ ኃይል ማመንጨት በብዙ ሀገሮች ተግባራዊ በመሆኑ በዚህ ዘዴ የሚመነጨው የኤሌክትሪክ ጉልበት በዓለም ውስጥ ከሚመነጨው ጠቅላላ የኤሌክትሪክ ጉልበት 20 በመቶ ገደማ ይሆናል። ቀላሉ አቶሞችን የማፈራረስና ጉልበት የማመንጨት ዘዴ ግን ጎጂ ጨረሮችን የመልቀቅና አካባቢን የመበከል ተጋላጭነት አደጋ ያዘለ ሲሆን በተፈጥሮ እንደ ፀሐይ ባሉ አካላት ውስጥ የሚካሄደው አቶሞችን በመደመር ጉልበት የማውጣት ክንውን ግን እነዚህ አደጋዎች የሉትም፡፡
ተፈጥሮ ያበረከተችልን ብዝሃነት ለፍላጎታችን በቂ አልሆነም፡፡ የጎደለውን የምንሞላው በመደመር ነው፡፡
እስከ አለንበት ክፍለ ዘመን መባቻ ድረስ በተፈጥሮ የሚገኙ ቁሳቁሶችና ያሏቸው ባህርያት የሰውን ፍላጎት ለማሟላት በቂ ነበሩ፡፡ ለምሳሌ አውሮፕላን መሰራት ያለበት ቀላል ግን ጠንካራ ከሆነ አካል ነው። ይህ ባህርይ አሉሚኒየም የሚባል የብረት አይነት ይሰጠናል። ለቴርሞሜትር መስሪያ የምንጠቀምበት ፈሳሽ በአነስተኛ የሙቀት ልዩነት የሚስፋፋና የመኮማተር ባህርይ ያለው መሆን ይኖርበታል፡፡ ይህን ባህርይ ሜርኩሪ ውስጥ እናገኘዋለን፡፡ ቀደም ብለው የነበሩትን የመብራት አምፑሎች ለማምረት በብዙ መቶ ዲግሪ ሙቀት የማይቀልጥና የኤሌክትሪክ ፍሰትን የመቋቋም ባህርይ ያለው ብረት ያስፈልግ ነበር። ተንግስተን የተሰኘው የብረት አይነት ይህን ባህርይ አሟልቶ ስለተገኘ ለዘመናት አምፖሎቹን ለመስራት ሲያገለግል ኖሯል፡፡
አሁን አሁን በተፈጥሮ የሚገኙ ቁሳቁሶችና ያላቸው ባህርያት ለሰው ፍላጎት በቂ ሆነው አልተገኙም። ለምሳሌ ሞባይል ቻርጅ በምናደርግባቸው ቁሶች ውስጥ ወደ አንድ አቅጣጫ ኤሌክትሪክ የማስተላለፍ፣ በተቃራኒ አቅጣጫ ደግሞ ኤሌክትሪክ ያለማስተላለፍ ባህርይ ያለው ቁስ ያስፈልጋል፡፡ እንዲህ ዓይነት ባህርይ ያለው ቁስ በተፈጥሮ አይገኝም፡፡ ስለዚህ የሰው ልጅ አቶም አይነቶችን በሚታወቅ መጠን ቀምሮና ደምሮ (ሲንተሳይዝ) አድርጎ፣ ይህ ባህሪ ያለውን ቁስ ከ150ዎቹ ጀምሮ መስራት ችሏል፡፡ ይህ እመርታ ለትራንዚስተር ቴክኖሎጂ ከዚያም የተለያዩ ደረጃዎችን አልፎ ለምንገኝበት የአይቲ ዘመን እውን መሆን የመሰረት ድንጋይ ሆኗል፡፡ በጠፈር ምርምር ለሚያስፈልጉ ልዩ ባህርያት ያላቸው ቁሳቁሶች መልሱ የሚገኘው አቶሞችን በተለያየ መጠን ቅንብራቸውን እየለወጠ ተፈላጊው ባህርይ እንዲኖራቸው አድርጎ ደምሮ የሚጋግራቸው የማቴሪያል ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘንድ ነው፡፡
የዘረ-መል ምህንድስናን አስፈላጊ ካደረጉት ነገሮች አንዱ ይኸው ተፈጥሮ የቸረችን ብዝኃነት ከፍላጎታችን አንፃር ውስን መሆን ነው፡፡ የዘረ-መል መሀንዲሶች በአንዱ ዝርያ የሌለን ባህርይ ከሚገኝበት በማምጣት ይደመራሉ፤ ያልነበረ ባህርይ ይፈጥራሉ፡፡
ሰውን ከእንስሳት ሁሉ የበላይ እንዲሆን ያስቻሉት ነገሮች የመደመር ውጤቶች ናቸው፡፡
ቋንቋ የሰው ልጅ ልዩ ችሎታ ነው፡፡ ድምፆች ተደምረው ቃላትን፣ ቃላት ተደምረው ዐረፍተ ነገሮችን፣ ዐረፍተ ነገሮች ተደምረው አንቀፆችን ሲፈጥሩ እያንዳንዳቸው ካላቸው ትርጉምና መልዕክት በላይ ድምሩ ይኖረዋል፡፡ ይህም ከፍተኛ የሆነ የመግባባት ችሎታን አጎናጽፎታል፡፡ በቀላል ምሳሌ ብናይ፤ ፀጉር እና ልውጥ ተደምረው ፀጉረ ልውጥ የሚል ቃል ሲፈጥሩ ድምሩ የተለየ ትርጉም አለው፡፡ በተመሳሳይ ጨርቁን-ጣለ የሚለው ቃል ትክክለኛ ትርጉም የሚገኘው፣ ቃሉ ጥቅም ላይ በዋለበት አውድ መሆኑን ስናስብ፣ የቃላትና ሀረጎች ትርጉም በድምሩ እንጂ በነጠላ ውስጥ እምብዛም መሆኑን እናያለን፡፡
የሰው ልጅ ከእንስሳት በተለየ ያካበተውና በፈጣን ሁኔታ እያካበተ ያለው የእውቀት ክምችትና የቴክኖሎጂ ግስጋሴ ያለ ጥርጥር የግለሰቦችና ተቋማት ድምር ውጤት ብቻ ሳይሆን በሀገራትና በአህጉራት ደረጃም ጥረትን የመደመር ውጤት መሆናቸውን መሳት አይቻልም፡፡
ሳይንስና ቴክኖሎጂ የሰው ልጆች ሁሉ የጋራ ፕሮጀክት ነው፡፡ በሀገራችን ከሚገኝ እንዶድ፣ ቀንድ አውጣን የሚያጠፋ ጠቃሚ ውህድ በማግኘት፣የሰው ልጅ የሳይንስ እውቀት ላይ አንድ ተደማሪ ያበረከቱት ኢትዮጵያዊ ሳይንቲስት፤ ምልከታቸውን ለመፈተሽና ለማረጋገጥ በዓለማችን ሁሉም ጥጎችና በየዘመኑ የዳበሩ ዘዴዎችን፣ መሳሪያዎችን፣ ኬሚካሎችን ጨምሮ በነባሩ የእውቀት ክምችት ድምር እገዛ ነው፡፡ ለዚህ ነው ባለፉት ጥቂት መቶ አመታት የሰው ዘሮች ሁሉ በጋራ ጥረትና እርዳ ተራዳ ያዳበሩት አንድና ዋና ነገር ቢኖር፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ነው የሚባለው፡፡ ሳይንስና ቴክኖሎጂ የሰው ዘር ሁሉ የጋራ ውርስም በመሆናቸው የሰውን አኗኗርና አሰራር ከመሰረቱ ቀይረው ህይወትን ቀላልና ምቹ ያደረጉ ናቸው፡፡ ተጽእኖአቸውም ድንበርና ወሰን፣ ዘርና ቀለምን ተሻጋሪ ነው፡፡
መደመርን በተለይ ከሀገራችን ማህበራዊ ሁነቶች ጋር አዛምደን ለማሰብ የሚያስችሉንን ጥቂት ምሳሌዎችን እንመልከት፡፡
የ1960ዎቹ ተከታታይ የማራቶን ኢትዮጵያዊ ድሎች፣ የሻምበል አበበ ቢቂላና የሻምበል ማሞ ወልዴ ድምር ጥረት ውጤቶች ናቸው፡፡ የዚህ መደመር አርዓያነት ከ1970ዎቹ አረንጓዴ ጎርፍ እስከ ሲድኒ ዘልቆ፣ በአትሌቲክስ ዘርፍ ሀገራችንን ከአለም አውራዎች አንዷ አድርጓታል፡፡ በአትሌቶቻችን መካከል እርስ በርሳቸውና በአትሌቶቻችንና በአሰልጣኞቻቸው መካከል እንዲሁም አትሌቲክሱን በሚመሩ አካላት መካከል መደመር ሳስቶ፣ መፋተግ  ራሱን ቀና አድርጎ በነበረባቸው ጊዜያት፤ እንኳን የዓለም የበላይ መሆን በአፍሪካም የነበረ የአትሌቲክስ የበላይነት እንደምን ተፈትኖ እንደነበር ሁላችን ያየነው ነገር ነው፡፡
አገራችንን ከወራሪዎች የታደግንባቸው የአድዋና የካራማራ ድሎችን የመሳሰሉት አኩሪ ክንውኖች ሁሉ ተደምረን ያስገኘናቸውና ተደምረን አንድ ከመሆን ውጭ ሊገኙ የማይችሉ ውጤቶች ሲሆኑ እንደ ቀይሽብርና በቅርቡ የምናየው የውስጥ መፈናቀልና መናቆር የመሳሰሉት አንገት የሚያስደፉ ክንውኖቻችን ደግሞ ከመደመር በተቃራኒ ጉልበት ጨርሰን ያገኘናቸው አሉታዊ ውጤቶች ናቸው፡፡
ከመደመር በተቃራኒ ስንጓዝ የምንሰበስበው ውጤት ምን ሊሆን እንደሚችል ለማየት፤ “ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያለው በሀገር ውስጥ የተፈናቀሉ ሰዎች ካሉባቸው ሀገራት አንዷ ሆናለች” በማለት የሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ በቅርቡ የሰጠው መግለጫ፤ አሁን በምንኖርበት ዘመን ያለ ሁነኛ አስረጂ ነው፡፡ በኮሎኔል መንግስቱ አስተዳደር ምክትል ፕሬዚደንት የነበሩት ኮሎኔል ፍስሃ ደስታ ባሳተሙት መፅሐፍ፤ በዚያ ዘመን ኢትዮጵያውን ከመደመር በተቃራኒ፣ ተቧድነውና ተከፋፍለው እንደምን ሁሉንም ያሳነሰ ክስተት እንደፈጠሩ እንዲህ ሲሉ ገልጸውታል፡-
“… የኢሕአፓ ቆራጥነት፣ የመኢሶን የርዕዮተ-ዓለም ብስለትና የደርግ ሀገር ወዳድነት ተጣምሮ አገሪቱን ወደ ላቀ ደረጃ ሊያደርስ ይችል የነበረ ኃይል፤ በአመራሮቹ ስህተት ያለአግባብ እርስ በርሱ ተጨራርሷል፡፡”
ይህ ትርምስና ቁልቁል ጉዞ የተከተለው የኢህአዴግን አዲስ አበባ መግባትና ከዛ ወዲህ የኖርንበትን ዘመን ነው፡፡ በዚህ ዘመን ኢትዮጵያን ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በገጸ ምድሯ ጎን ለጎን ተደርድረው እንደኖሩባት፣ አንዱ ከሌላው እንዳልተዛመደና እንዳልተጋደመ አድርጎ የመሳል አስተሳሰብ እየገነነ እየተለጠጠ መጥቶ ሁሉም ግንኙነት የሚታይበት መነጽር፣ የሚሰላበት ቀመር፣ እንዲያው በጥቅሉ ሁለንተናችን የተቃኘበት ዜማና ቀለም ወደመሆን አድጓል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዘመናት አብሮነታቸው አንዱ ከሌላው ጋር ባብዛኛው በጎ መስተጋብር ነበራቸው፡፡ በበጎ ስራዎች ተደምረው የትየለሌ የሆነ ቁሳዊና መንፈሳዊ ሃብት ፈጥረዋል፡፡ ከሁሉም በላይ በደም የተደመሩ ናቸው፡፡ ከሁለት እና ከዚያ በላይ ብሔር/ብሔረሰብ የሚወለዱ ኢትዮጵያውያን የዚህ መስተጋብር ውጤቶች ናቸው፡፡ ጥናት ቢደረግ ሁለትና ከዛ በላይ ከሆኑ ብሔረሰቦች/ብሔሮች የተፈጠሩ ኢትዮጵያውያን በቁጥር ከማንኛውም አንድ ብሔረሰብ የሚተካከል ወይም የላቀ ቁጥር እንደሚኖራቸው መገመት ይቻላል፡፡ እነዚህ ኢትዮጵያውያን የመደመር ውጤት ናቸውና በአንዱ ወይም በሌላው ብቻ እንዲጠሩ ወይም ራሳቸውን እንዲመድቡ መገደድ የለባቸውም፡፡ ኢትዮጵያዊነት ከነዚህ ባለ ብዙ ፈርጅና ዘመናትን የተሻገሩ መደመርና መስተጋብሮች የሚመነጭ እውነታና ተጨማሪ ትሩፋት እንጂ አየር ላይ የተንጠለጠለ ባዶ ነገር አይደለም፡፡ ከላይ በተፈጥሮ ምሳሌዎች ለመግለጽ እንደተሞከረው፤ የመደመር ትሩፋቶች የተደማሪዎችን ህልውና ጠብቆ ያበለጽጋል፣ ያዳብረዋል፣ ይጨምርበታል እንጂ የሚያጠፋው ሊሆን አይችልም፡፡
መደመርን የሚመርጡትና ደጋግመው የሚጠቀሙበት ጠቅላይ ሚኒስትራችን፤ በጥልቀት ላሰቡበት የሀገራችን ዘርፈ ብዙ ችግር፣ ዘርፈ ብዙ የሆነውን መፍትሄ በትክክል ለመግለጽ የሚመረጥ ነው፤ ግን ደግሞ ሰፊና ጥልቅ ግንዛቤዎች ያዘለ ቃል መሆኑን ለመረዳት ይቻላል፡፡
መደመር አዎንታዊ በሆኑ አስተሳሰቦች ታላላቅ ግቦች ላይ ለሚያደርሱ ክንውኖች፣ አእምሮአችን የሚቃኝበት ቅዱስ ፅንሰ ሀሳብ ነው። መደመርና ከመደመር ጽንሰ ሃሳብ ጋር አብረው የምንሰማቸው ፍቅርና ይቅር ባይነት፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ቀልብ መግዛታቸው ለዚህ አስረጂ ነው፡፡ “ከአንድ እንስራ ሃሞት ይልቅ ጠብታ ማር ብዙ ንቦችን ትስባለች” እንዲሉ!!!

Read 6567 times